በ1990 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የስፖርት ፖሊሲ ፣ክለቦች ደረጃ በደረጃ በሂደት ህዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ማድረጉን ያስገነዝባል፡፡ ስፖርቱ ከመንግሥት በጀትና ድጎማ ደረጃ በደረጃ የሚላቀቅበትንና ራሱን የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርም የፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫ ነው። ይሁንና ፖሊሲው ከወጣ ሁለት አስርት ዓመታትን ቢያስቆጥርም እንደተቀመጠው አቅጣጫ እና ፍላጎት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ በግልፅ ይታያል። በአሁኑ ወቅት ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር አብዛኞቹ የአገሪቱ ክለቦች በመንግሥት ጉያ ስር የተደበቁና ህዝባዊ አደረጃጀት የሌላቸው ናቸው።
ከአገሪቱ ክለቦች 90 በመቶ የሚሆኑት የሚተዳደሩት በመንግሥት ድጎማና በልማት ድርጅቶች ወጪ ነው። ህልውናቸው መሰረቱን ያደረገው በመንግሥት ወጪ እንደመሆኑም ድጎማ ሲቀር የክለቦቹ አደረጃጀትም አብሮ ይቀራል። መዋቅር ሲስተካከልና ሲለዋወጥ ክለቦቹም አብረው ይለወጣሉ። አሊያም ይፈርሳሉ። የልማት ድርጅቶቹ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ሲወደቅ ወይም ወደ ሌላ ሲዛወሩ የክለቦቹም ህልውና ይታመማል፤ያበቃል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች በተለይም የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ራሳቸውን ችለው ባልተደራጁበት በአሁኑ ወቅት በጣም ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ወጪ ሲደረግ ይስተዋላል። ይህም የክለቦች ወጪና ገቢ እንዳይመጣጠን እያረገ ነው። የወጪ ዕድገት ጣራው ቀና ብለን መጨረሻውን ለማየት አስችጋሪ ሆኗል።
ክለቦች በዚህ መልኩ ያለቅጥ የሚያሽከረከሩት ገንዘብ ከየት ተገኘ፣ከፋዩስ ማነው?» ተብሎ ሲጠየቅ ከመንግሥትና ከህዝብ በጀት የሚለው መልስ ፈጥኖ ይመጣል። ይህን ወቅታዊ ውጤትን ፍለጋ ብቻ «ነገ ለራሱ ይወቅበት» በሚል ከመንግሥት ካዝና ተዝቆ የሚሰጥ የክለቦች ቅጥ ያጣ የገንዘብ አወጣጥን የተመለከቱ የዘርፉ ባለሙያዎችም፤ድርጊቱ ማሰሪያ ካልተበጀለት የኋላ ኋላ የከፋ አደጋ እንደሚያስከትል እየጠቆሙ ናቸው፤በዚህ ዓይነቱ ድርጊት የተነሳም ክለቦችም ሆኑ የአገሪቱ እግር ኳስ ህልውና አደጋ ላይ ስለመሆኑ እያሳሰቡ ይገኛሉ።
ይህን ሃሳብ ከሚጋሩት የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ ዋነኛው ናቸው። ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ በ1990 ዓም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ የስፖርት ፖሊሲን ካረቀቁት አንዱ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ትምህርት ክፍል በምርምርና መምህርነት እያገለገሉ ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በክለቦች ወቅታዊ ወጪ ላይ ከባለሙያዎች የሚነሱ ስጋቶችን ዋቢ በማድረግ ከረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አዘጋጅቶታል።
አዲስ ዘመን፡- የፖሊሲው አቅጣጫና የክለቦቻችን አደረጃጀት ምን ያህል ተጣጥሟል?
ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ!- ክለቦች በውድድር መድረኮች ለሚኖራቸው ውጤታማነትና ቆይታ በተለይም ለህልውናቸው ቀጣይነት የሚከተሉት የክለብ አደረጃጀት እጅግ ወሳኙን ድርሻ ይኖረዋል። አደረጃጀቱ ህዝባዊ መሰረተን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ ደግሞ ትክክለኛ አማራጭና ለውጤታማነታቸው ዋነኛ ቁልፍ ነው። የአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ ክለቦች ደረጃ በደረጃ ወደ ህዝባዊ አደረጃጀት እየተለወጡ በስፖርቱ ልማት ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው ያመለክታል። ይህ ግን እየሆነ አይደለም። ስለ ክለብ አደረጃጀትና አወቃቀር ጠንቀቆ የሚያውቅ ሰው እንዲሁም ክለቦች እንዴት መደራጀት እንዳለባቸው በጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ የ23 ዓመታትን ያስቆጠረ ሰነድ ሀገሪቱ ቢኖራትም ፣በዚህ መንገድ ተጓዙ የሚል መሪ ግን አልተገኘም። ይህን የሚከታተል ፖሊሲውን የሚያስፈፅም የለም። መንገዱ ጠፍቶናል። እናም በጭለማ እየተጓዝን ፊደል ያልቆጠረ ሰው የሚሠራውን እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የፖሊሲው አቅጣጫና የክለቦቻችን አካሄድ መግባባት እንደተሳናቸው የሚያሳዩ ማስረጃዎች ምን ይሆኑ?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ፡- በአሁኑ ወቅት ስፖርት ከመዝናኛነቱ ባለፈ ሥራ / ቢዝነስ/ ነው። ማንኛውም ክለብ ባለቤት ያስፈልገዋል። የክለብ ባለቤት ገቢ ያመነጫል። በገቢው ተጫዋች ይገዛል፤ይለውጣል፤ትርፍ ያገኛል። የክለቦች አደረጃጀት ህዝባዊ መሰረትን የተከተለ ከሆነ ደግሞ ይህን በቀላሉ ማሳካት ይቻላል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ራሱን የቻለ ህዝባዊ አደረጃጃት ያለው ክለብ የለም። ክለቦቻችን የራሳቸውን ገቢ አመንጨተው የሚተዳደሩ አይደሉም። መሰል አሠራሮችን የሚተገብሩም አይደሉም።
አብዛኞቹ የመንግሥትን ገንዘብ የሚበሉ ጥገኛና ካዝና ተቋዳሽ ናቸው። ትልቅ የገቢ ማመንጫ መዝናኛና ሜዳ ያለው ክለብ የለም ከጋራ ስታዲየም ከሚገኝ ገቢ የሚጠቀም እንጂ የራሱ ስታዲየም ገቢ ያለው ክለብም አይታይም። ሌላው ዓለም ይህን የጀመረው በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ነው። ዛሬ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን። እኛ ግን በጣም ገና ነን። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ ተቋም / ፊፋ/ እያዘነልን እንጂ አሁን የክለቦቻቸውን ቁመና ከመስፈርት በታች ነው።
አዲስ ዘመን፡- ክለቦች ራሳቸውን ችለው ባልተደራጁበት በአሁኑ ወቅት በጣም ክፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ በተለይ የውጭ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን እንዴት ይገልፁታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ፡- ምንም እንኳን አብዛኞቹ ክለቦች ራሳችውን ችለው መቆምና ገቢ መፍጠር ባይሆንላቸውም ከፍተኛ የሆነ ገንዝብ ወጪ በማድረግ ላይ ተጠምደዋል። ይህ ገንዘብ ደግሞ የመንግሥትና የህዝብ ሀብት ነው። ገንዘቡም በተለይም ታዳጊዎች ላይ በመሥራት ምርጦችን ከማፍራት ይልቅ ከውጭ ተጫዋቾችን በማምጣት ሲውል ይስተዋላል። ይሁንና በቀዳሚነት ተጫዋቾችን ከውጭ መግዛት ለምን አስፈለገ? ክለቦቻችን ፕሮፌሽናል አይደሉም።
ፕሮፌሽናል ክለቦች ከገዙት ተጫዋች ቢሊየን ዶላሮችን ያገኙበታል። እኛ የውጭ ተጫዋቾችን አምጥተን ምን አገኘን? በአሁኑ ወቅት ወርሃዊ የአንድ ተጫዋች ክፍያ ሦስት መቶ ሺ ብር ደርሷል ከተባለ ከየት መጥቶ ነው የሚከፈለው። ክለቡ የሚያመነጨው ሀብት ካለና አትርፎ ከሆነ በጣም ጥሩ ነው። ይሁንና ምንም ትርፍ የሚያመጣ የለም። ምንም ተጨባጭ ትርፍ በሌለው ገና ለገና ከማን አንሼ በሚል ለአንድ ተጫዋች ሦስት መቶ ሺ መክፈል አግባብ አይደለም። ይህ ዓይነት መካሄድም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ያስተቻል። በአጠቃላይ በጭፍን እየተጓዝን ነው። ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። ስፖርቱን የሚገድል እንጂ የሚያሳደግ አይደለም። ይህን ዓይነት ተግባር የዕድገት ደረጃ ማሳያ አይደለም። እኔ ትልቅ የአገር መሪ ባለበት መድረክ የምናገረው ይህን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ክለቦች በውጭ ተጫዋቾች የሚማረኩትና ከፍተኛ ወጪ የሚመድቡት ከአገር ባለፈ በአህጉራዊ መድረኮች ውጤታማ ለመሆን ነው የሚለውን ይስማሙበታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ፡- በርካታ ገንዘብ ከመንግሥትና ህዝብ ካዝና እየወጣ ውጤት ቢኖር መልካም ነበር። ይሁንና ክለቦቻችን በአገር ውስጥም ሆነ በአህጉራዊ መድረኮች እየተሸነፉ ከመመለስ በስተቀር ውጤታማ መሆን አልቻሉም። ከፍተኛ ወጪ እያደረጉ የውጭ ተጫዋቾች ማምጣት ለክለቦቹ ውጤት መሻሻል አስተዋጽኦ ቢኖራቸው ኖሮ አይከፋም። ይህ አሠራር እንዳውም የአገር ውስጥ ተጫዋቾች በተለይም ታዳጊዎች እንዳይጎለብቱ እያረገ ነው።
ይህ ችግር ከታች ጀምሮ በብዙ ውጣ ውረድ በየደረጃው ለሚገኙ ክለቦች ለሚበቁ የአገር ውስጥ ተጫዋቾች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማነቆ ሆኗል። ለወደፊቱ የአገሪቱ ስፖርት ምሰሶ የሆኑ ታዳጊዎችና ተተኪ ተጫዋቾች ከመንገድ እንዲቀሩ እያደረገ ነው። በእርግጥ ተጫዋቹ ምርጥ ሊሆን ይችላል። ይህ ምርጥነቱ የሚጠቅመው ግን በክለብ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊ ባለመሆኑ ብሄራዊ ቡድኑን መወከል አይችልም። ይህም አንዱ የችግሩ ማሳያ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ክለቦችን ከመደጎም የሚላቀቅበትን የጊዜ ገደብ አለማስቀመጡ ለክለቦቹ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል ይባላል፤ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ፡- በእርግጥም መንግሥት ክለቦችን ምን ያህል እየደጎሙ ማቆየት እንደሚቻል ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ላለመኖሩ ዋነኛው ተጠያቂ እንዲሆንና ለችግሩ ዘላቂነት የጎላውን ድርሻ እንዲወስድ ያደርገዋል። ይህን አለማድረጉም፤ክለቦች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ልክ ቀጣይ አደረጃጀታቸውን የሚመለከት አቅጣጫ እንዳይቀይሱና ባሉበት ደረጃ ሁሌም እንዲመላለሱ እያደረገ ይገኛል። ይህ ፈፀሞ ሊስተካከል የሚገባው ነው። መንግሥት ክለቦችን እየደጎመ መቀጠል የለበትም። እየደጎመ የሚያወዳድራቸው ክለቦች ከጥገኝነት ተላቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይገባዋል።
ክለቦች የራሳቸውን ገቢ እንዲፈጥሩ መግፋት ይገባዋል። ክለቦች ከመንግሥት ድጎማ ለመፋታት እያደረጉ ያለውን ጥረት መቃኘትና ተግባራቸውን መጠየቅም አለበት። ስፖርቱን ከእኔ እጅ ለመቀበል ምን እያደረጋችሁ ነው እያለ መጠየቅ አለበት ። ከዚያም ክለቦቹን ከመደጎም የሚርቅበትን የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ይኖርበታል። ከሞግዚትነት መውጣቱን በማሳወቅ በቃኝ ሊላቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ሲደጉም ከመኖር ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም። በአጠቃላይ ክለቦች ከመደጎም፤መንግሥትም ከመደጎም የሚላቀቁበት የመውጫ ስትራቴጂ ሊያዘጋጁም የግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- የክለቦች ወጪና የውጭ ተጫዋቾች ፍላጎትን በሚመለከት ጠንካራ ህገ ደንብ ሊኖረው ግድ ይላል የሚሉ አሉ፤ በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
ረዳት ፐሮፌሰር ወንድሙ፡- በእርግጥ የክለቦች የተጋነነ ወጪና የውጭ ተጫዋቾችን በማጋበዝ አንደኛ የመባል ፍላጎትና አቋም ሳይውል ሳያድር መታረም ይኖርበታል። ለዚህም ህግና ስርዓት ያስፈልጋል። እግር ኳሱና ክለቦች የሚተዳደሩበት፤የውጭ ተጫዋች ለምንና መቼ ይምጣሉ፤አመጣጣቸውስ እንዴት መሆን አለበት፤የሚለው በህግና ስርዓት ሊመራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ የአገሪቱን ከለቦች አደረጃጀትና የተጋነነ ወጪ ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ፡- ከሁሉ አስቀድሞ የክለቦች አደረጃጀት ህዝባዊ መሰረትን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ ለነገ የሚባል የቤት ሥራ መሆን የለበትም። ክለቦችም በራሳቸው ቆመው በትክክለኛው መንገድ መራመድ መጀመር ይኖርባቸዋል። አጋጣሚዎች መጠቀምና ደጋፊነትን በሀብትነት መጠቀም ከተቻለ አሁን መልካም ነገሮች ይታያሉ። ክለቦች ከነማ በሚል ተቋቁመዋል። ይህም ህዝብ ለማስገባትና ባለቤታቸው እንዲሆን መልካም መንገድን ይጠርጋል። የፋይናንስ ምንጭ ህዝብ እንዲሆን በማድረግም ክለቦች እየጎለበቱ እንዲሄዱ ያግዛል። ይህ ሲሆን በስፖርቱ ራሱን ለማስተዋወቅ ፍላጎት ያለው ኢንዱስትሪን መጋበዝ ይቻላቸዋል። ይህን ማሳካት ሲችሉም፤ ከመንግሥት ካዝና እጃቸውን ይሰብስባሉ። ሌላው ዓለም የደረሰበት ለመደርስ የሚያስኬደው መንገድም ይህ ብቻ ነው።
በውጭ ተጫዋች ዝውውር ረገድም አንድ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የህዝብ ፍላጎትና እርካታ ክለቡ የራሱን ምርጥ ተጫዋቾች በማብቃት ውጤታማ ሲሆን መመልከት ነው። ከክለቡ ባለፈ ለብሄራዊ ቡድን መትረፍና ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን አምርቶ ወደ ውጭ መላክ ሲችል ደስታቸው እጥፍ ይሆናል። ይህ እስከሆነም ህዝብ የሚፈልገውን እውን ለማድረግ የውጭ ተጫዋቾች ላይ መንጥልጠልና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ማድረግ መቆም አለበት። በአጠቃላይ የአገሪቱን እግር ኳስና የክለቦችን ህልውና ለማስቀጠል የክለቦቻችን ወጪ ቆም ተብሎ ሊታሳብብት ይገባል። ይህም የአገር አጀንዳ ሊሆን ግድ ይለዋል። አሁን ጥያቄው ሊሆን የሚገባው የማምጣት የመውስድና የጊዚ አይደለም። ጉዳዩ የአገር አጀንዳ ነው። የአገሪቱን ስፖርት እንዴት እናሳድግ የሚል ነው። ለዚህ ቁጭ በሎ ማሰብ፤ ማቀድና ያቀዱትንም ወደ ተግባር ለመለወጥ መሥራት ግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡- ላደረጉልን ትብብር እናመሰግናለን፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በታምራት ተስፋዬ