በተለያዩ ርቀቶች አትሌቶች የሚያስመዘግቧቸው የዓለም ክብረወሰኖች ወዲያውኑ በዓለም አትሌቲክስ እውቅና አያገኙም። የዓለም አትሌቲክስ ሁሌም እንደሚያደርገው የተለያዩ ክብረወሰኖች ከተመዘገቡ በኋላ የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነትን ጨምሮ ክብረወሰኑ በተመዘገበበት ውድድር የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ ለተመዘገበው ክብረወሰን እውቅና ይሰጣል።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ባለፈው ኣመት በቫሌንሲያ ላስመዘገበችው የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን የዓለም አትሌቲክስ እውቅና መስጠቱን ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርጓል።
የዓለም አትሌቲክስ በሴቶች ማራቶንና ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ሁለት አይነት የዓለም ክብረወሰኖችን መዝግቦ እውቅና እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም በወንድና በሴት አሯሯጮች የተመዘገበና በሴት አሯሯጭ ብቻ የተመዘገበ ተብሎ የተለየ ነው። በዚህም መሰረት ወጣቷ አትሌት ለተሰንበት በቫሌንሲያ ያስመዘገበችው የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በሴትና በወንድ አሯሯጮች የተመዘገበ ሲሆን ለዚህም የዓለም አትሌቲክስ እውቅናውን ችሮታል።
ለተሰንበት ባለፈው ነሐሴ በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድራ 1:02:52 በሆነ ሰአት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ የዓለም ክብረወሰኑን ማስመዝገብ ችላለች።
ይህ ክብረወሰን ቀደም ሲል በተመሳሳይ ዓመት በኬንያዊቷ አትሌት ሩዝ ቺፕጌቲች ቱርክ ኢስታንቡል ላይ 1:04:02 በሆነ ሰአት ተይዞ እንደነበር ይታወሳል።
ከወራት በኋላ ግን ለተሰንበት የኬንያዊቷን ክብረወሰን በሰባ ሰከንድ ልታሻሽለው ችላለች። የሃያ ሶስት አመቷ ድንቅ አትሌት ይህን ሰአት በማስመዝገቧ ርቀቱን ከስልሳ አራት ደቂቃ በታችና በስልሳ ሶስት ደቂቃ ውስጥ ያጠናቀቀች የመጀመሪያዋ የዓለማችን አትሌት ሆናለች።
ከዚህ በተጨማሪ በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድራ የዓለም ክብረወሰን ያስመዘገበች አትሌትም ሆናለች። “አዲስ አበባ ላይ ያለው የአየር ንብረት ጥሩ ከሆነና ልምምዴም በመልካም ሁኔታ ከቀጠለ የአለም ክብረወሰን እንደማስመዘግብ አውቃለሁ፣ ወደ ፊት በተመሳሳይ ርቀትና በማራቶን ለመወዳደር ሃሳብ አለኝ፣ ከፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ በፊት ወይም በኋላ እንደምሮጥ ግን እርግጠኛ አይደለሁም” በማለት ለተሰንበት ለዓለም አትሌቲክስ አስተያየቷን ሰጥታለች።
ለተሰንበት የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን ባሻሻለችበት የቫሌንሲያ ከተማ ቀደም ብላ በ2020 በጥሩነሽ ዲባባ ለአስራ ሁለት ዓመታት ተይዞ የቆየውን የአምስት ሺ ሜትር ክብረወሰን ማሻሻሏ ይታወሳል።
በ2021 የውድድር ዓመትም የኣለም ክብረወሰኖችን በመሰባበር የቀጠለችው ለተሰንበት አስደናቂ ብቃት ማሳየት ችላለች። በተለይም ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ በኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና የተመዘገበውን የአስር ሺ ሜትር ክብረወሰን ሰብራ አርባ ስምንት ሰአት ሳይሞላው ለተሰንበት በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያውያን ማጣሪያ ውድድር ሄንግሎ ላይ ማሻሻሏ አይዘነጋም።
ለተሰንበት በቶኪዮ ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር ይህን አስደናቂ ብቃት ደግማ የወርቅ ሜዳሊያ ታጠልቃለች የሚል ግምት በበርካቶች ዘንድ አድሮ የነበረ ቢሆንም፣ በሲፈን ሃሰንና በሌላኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት የባህሬን አትሌት ቃልኪዳን ገዛኸኝ ተቀድማ የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቋ ይታወሳል። የግማሽ ማራቶን ክብረወሰኑንም ያሻሻለችው በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማጣቷ ቁጭት ውስጥ እያለች ነበር። የዓለም አትሌቲክስ ከለተሰንበት የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን ጋር ለዩጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ የግማሽ ማራቶን ክብረወሰንም እውቅና ሰጥቷል።
ለተሰንበት የግማሽ ማራቶን ክብረወሰኑን ከጨበጠች ከወር በኋላ ኪፕሊሞ በኢስታንቡል ግማሽ ማራቶን የርቀቱን የቀድሞ ክብረወሰን በአንድ ሰከንድ በማሻሻል ተመሳሳይ ታሪክ መስራት የቻለ ሲሆን የርቀቱ የቀድሞ ክብረወሰን በኬንያዊው አትሌት ኪቢዮት ካንዲ በ2020 ቫሌንሲያ ላይ በ57:30 የተያዘ እንደነበር ይታወቃል።
በተያያዘ ዜና አትሌት ለተሰንበት ግደይ በነገው እለት ለኬንያዊቷ አትሌት አግኒስ ቲሮፕ መታሰቢያ በተዘጋጀው የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ ይጠበቃል።
ይህ ውድድር በኬንያ ኤልዶሬት ነው የሚካሄደው፡፡ የአገር አቋራጭ ቻምፒዮኗን እንዲሁም የ2017 እና 2019 የዓለም ቻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት አግኒስ ቲሮፕን ለመዘከር የተዘጋጀ ነው። አግኒስ ቲሮፕ ከወራት በፊት በመኖሪያ ቤቷ ሕይወቷ አልፎ የተገኘች ወጣት ኬንያዊት አትሌት እንደነበረች የሚታወስ ሲሆን፣ ነገ እሷን ለማሰብ በተዘጋጀው አገር አቋራጭ ውድድር ለተሰንበትን ጨምሮ በተለያዩ ርቀቶች የዓለም ክብረወሰን ያሻሻሉ በርካታ ኬንያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት/2014