ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ኢትዮጵያ ላይ በአዲስ መልክ የተዋወቀ ፊልም፣ የሥነ ጽሑፍ አላባዊያን ተሰናኝተው ልዩ ኪናዊ ከፍታን ያላበሱት ሲኒማ፣ተዋንያኑ ከልባቸው ሠርተው የተደነቁበት ድንቅ ትወና፣ አስደማሚ የታሪክ ፍሰት ገላጭና አጥረው የሚነገሩት ንግግሮች (dialogs)፣ ከፍ ያለ የፊልም አሠራር ጥበብና ምርጥ ድርሰት በ «ሂሩት አባቷ ማን ነው?» ፊልም ላይ የተስተዋለ ኪናዊ ሂስ ውጤት ነው።
ከዛሬ ሃምሳ ሰባት ዓመት በፊት የተሠራው የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ፊልም የሆነው «ሂሩት አባቷ ማን ነው?» በተሰኘ ፊልም፤ ከ57 ዓመት የረዘመ ጊዜ በኋላ ታላቅ ቦታ አግኝቶ ድጋሚ የሲኒማ ፈርጥ ሆኖ ብቅ ብሏል። ከዘመናት በፊት በፈተና ከመድረክ የራቀው ይህ ታሪካዊ ፊልም ዛሬ ቀን ወጥቶለት በዘመኑ ቴክኖሎጂ ታግዞና ከፍ ብሎ በየሲኒማ ቤቶቹ እየታየ ይገኛል።
እንደ አገር የፊልም ሥራ ጥበብ በሌለበትና ከሱ በፊት ፈፅሞ ባልተሞከረበት በዚያ ዘመን የተሠራው ይህ ፊልም ዛሬ በዘመነኛ የፊልም ባለሙያዎች ዘንድ በተለየ መልክ የሚነገርለት፤ በጥበብ ቤተሰቦች ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሳ እንዴት ሆነ? ፊልሙ ምን ምን የሥነ ጽሑፍ አላባዊያንን አሰናስሎ ነው በዚህ መልክ የሚጠቀሰው? የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ከፊልሙ ጭብጥ የአሠራር ጥበብና የኢትዮጵያ ፊልም ዛሬ ያለበትን የእድገት ደረጃ ከዚህ ፊልም ጋር በተነፃፅሮ በሚያስመለክተው በዛሬ የዘመን ጥበብ አምዳችን የትኩረት ነጥባችን ነው።
«ሂሩት አባቷ ማን ነው?» የተሰኘው የአገሪቱ የመጀመሪያ ፊልም ሆኖና የፊልም ልምድና ቀዳሚ ሥራ ሳይኖር የዚህን ያህል ከፍታ ላይ እንዴት ደረሰ? የሚለው ጥያቄ የብዙ የጥበብ ቤተሰቦች ጥያቄ ነው። በእርግጥም ፊልሙ የተወሰኑ የውጭ አገር ዜጎች አብረው ቢሳተፉበትም ከጽሑፍ እስከ ትወና ድረስ ታላቁን ድርሻ የነበራቸው ግን ኢትዮጵያውያን ናቸው። የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ጣሊያናውያን መሆናቸው በፊልሙ አሠራር ታሪክ ላይ የተፃፉ መዛግብት ያመለክታሉ።
ከሃምሳ ሰባት ዓመት በፊት ነሐሴ 21 ቀን 1957 አ.ም ለእይታ የበቃው «ሂሩት አባቷ ማን ነው?» የተሰኘው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፊልም በጥቁርና ነጭ ፊልም ወይም ምስል የቀረበ ሲሆን፤ በኢትዮጵያዊው ኢላላ ኢብሳ ተፅፎ በግሪካዊው የፊልም አዘጋጅ ላምብሮስ ዮካሪስ ተሰናድቷል። በወቅቱ ፊልሙ አዲስና የመጀመሪያ እንደመሆኑ አገሪቱን ይመሩ በነበሩት ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ነበር ለእይታ የበቃው።
ይህ የመጀመሪያው ባለ 35 ሚሊ ሜትር ተንቀሳቃሽ ልብወለድ ፊልም ለዕይታ ከበቃ ከ57 ዓመታት በኋላ በሸራተን አዲስ ጥር 05/2014 ዓ.ም በዲጂታል መልኩ ተቀይሮና በድጋሚ ተመርቆ በርካቶች አይተውታል። በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች እየታየ ይገኛል።
የፊልሙ አጭር ታሪክ እና መቼት
መቼቱን በአዲስ አበባ፣ ቆቃ፣ አሥመራ ያደረገው ሂሩት አባቷ ማነው ፊልም ታሪኩ የሚጀምረው የዋና ገፀባህሪዋ መነሻ ከሆነችው አዳማ ከተማ ነው። የባላባት ልጅ የሆነችው ሂሩት በአንድ አጋጣሚ ናዝሬት ውስጥ ባለ ማዘጋጃ ትያትር ቤት ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና ሙዚቃዊ ትያትር ልትመለከት በምትሄድበት ወቅት ጉግሳ ከሚባል ዘፋኝ ጋር ትተዋወቃለች።
እያደር ትውውቃቸው ጠንክሮ ፍቅር ይጀምራሉ። ጉግሳና ሂሩት በፍቅር ትንሽ ወቅት እንዳሳለፉ ጉግሳ በወንጀል ተጠርጥሮ ይታሰራል። ነገር ግን ሂሩት ጉግሳ ከመታሰሩ በፊት አርግዛ ነበር። ከጋብቻ ውጪ ማርገዝ እንደ ከፍተኛ ነውር በሚታይባት ኢትዮጵያ ለሂሩት የታያት አማራጭ ጓዟን ጠቅልላ ወደ አዲስ አበባ ማቅናት ነበር። አዲስ አበባ ግን ቄጠማ አንጥፋ ኖር ብላ አልተቀበለቻትም። ለችግር ተዳረገች።
ይሄኔ ለችግሯ መፍትሄ ፍለጋ ለራበው አንጀቷ ማስታገሻ ምግብ መግዣ እንዲሁም ለኑሮዋ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ለማሟላት ትችል ዘንድ ቡና ቤት በሴተኛ አዳሪነት ትቀጠራለች። ፊልሙ ሂሩት በወሲብ ንግድ ተሰማርታ የምታየውን ውጣ ውረድ ያስቃኛል። በኋላም ካፈቀረችው ጉግሳ የወለደቻት ልጅዋን ይዛ በስደት አስመራ ድረስ ስትሄድ እዚያም የሚገጥማትን የሕይወት ውጣ ውረድ መንስዔና ውጤት አከታትሎ እያሳየ እስከ መጨረሻው ልብ አንጠልጣይና ሳቢ በሆነ መልኩ ያስጉዛል። አዳማ ቆቃ ቢሾፍቱና አዲስ አበባና አስመራ የፊልሙ ቀረፃ የተካሄደባቸው ከተሞች ናቸው።
ፊልሙ እንዴት ተዘጋጀ
በወቅቱ ገና የፊልም ጥበብ በኢትዮጵያ ባይተዋወቅም አልፎ አልፎ በቴሌቪዥን የሚታዩ የሆሊውድ ፊልሞች በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበራቸው። በዚያን ወቅት በነበረው ወጣት ከሚያያቸው ፊልሞች በመነሳት አለባበሱ፣ አነጋገሩና የሕይወት ፍልስፍናው ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ማሳደራቸውም ይጠቀሳል። በዚህም ፊልም የማየት ባህል እያደገ መጣ። ዘርፉ የኢትዮጵያውያንን ትኩረት ስቦ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልብ ወለድ ተንቀሳቃሽ ፊልም ለመሰራት እንዲሁም የፊልም ፕሮዳክሽን ኩባንያ ለመመስረት በቃ። ይህ ኩባንያም ሒሩት አባቷ ማን ነው የሚለውን ፊልም ወለደ።
የፊልም ሥራ ኩባንያው በኢላላ ኢብሳና በላምብሮስ ዩካሪስ አሰባሳቢነት 14 አባላት ነበሩት። የኩባንያው ስሙም የሀገር ፊልምና ማስታወቂያ ማኅበር የተሰኘ ሲሆን፣ ኢላላ ኢብሳም ሥራ አስኪያጅ ተደርጎ ተሾመ። ኩባንያው በመጀመሪያ ሊሠራ አቅዶ የነበረው በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትር መኮንን እንዳልካቸው የተጻፈው ‘ሳልሳዊ ዳዊት’ የተሰኘ ፊልም ሲሆን፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሥራው ተቋርጦ የኢብሳ ድርሰት የሆነውን ይህን ፊልም እንደገና ለመስራት ወሰኑ።
ፊልሙ ምን ያህል እንደፈጀ የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም አዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊልሙ ሥራ በሚገልፅ ጽሑፍ የሀገር ፊልምና ማስታወቂያ ኩባንያ 200 ሺህ ብር ከልማት ባንክ ለፊልሙ መስሪያ ብሎ ብድር እንደወሰደ ያመለክታል። የአርትኦቱም ሆነ ፊልሙን የማጠብ ሥራ የተሠራው ጣልያን በሚገኝ የፊልም ላብራቶሪ ሲሆን በ25 ቅጅዎችም ነበር የተዘጋጀው።
ሂሩት አባቷ ማን ነው ፊልም በወቅቱ የገጠመው ፈተና
ይህንን ፊልም የሠራው ኩባንያ የመስሪያ ብድር የወሰደው ከልማት ባንክ በብድር እንደመሆኑ በፊልሙ የተገኘው ገቢ ዕዳውን ለመክፈል አላስቻለውም። በመጨረሻም ልማት ባንክ ለፊልሙ ለሰጠው ገንዘብ መያዣነት ፊልሙን በባለቤትነት ያዘው። በዚህ የተነሳ ፊልሙ ለበርካታ አመታትም ከሲኒማ ራቀ። በብዙ ጥረት አና ትጋት የተሠራው የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ፊልም ለኪሳራ ተዳረገ።
ፊልሙ በፊልም ባለሙያዎች እይታ
ፊልሙ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፊልም ሙያ ትልቅ ቦታ አለው ይላል ደራሲ ዳንኤል ወርቁ። ዳንኤል በዚህ ሂሩት አባቷ ማን ነው በተሰኘው ፊልም ላይ ወደ ዲጂታላይዝ ሲቀየር አብሮ ለተሠራው ሰብታይትል (ንግግሩን በጽሑፍ መግለፅ) የትርጉም ሥራውን በመሥራት በታሪካዊ ሥራው ተሳታፊ ሆኗል። በፊልሙ ላይ አስተያየቱን የሚያጋራን ዳንኤል ፊልሙ ለኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ይናገራል።
ከዛሬ 57 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ፊልም አሠራር ጥበብና የፊልም ደረጃ የት ነበር ብሎ በመጠየቅ ዛሬ ያለበትን ደረጃ መገምገምና ከበፊቱ ብዙ ተምሮ ዛሬ በደንብ መሥራት ይገባል የሚለው ደራሲና ዳይሬክተር ዳንኤል፣ ሂሩት አባቷ ማን ነው የሚለው ፊልም በዘመኑ የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች ልቅም ተደርጎ የተሠራና የተዋጣለት ፊልም መሆኑን ያስረዳል።
በታሪክ አወቃቀሩ በፊልም ጽሑፍ(ድርሰቱ)፣ በተዋንያን የትወና ብቃትና ፊልም አሠራር ጥበቡ ብዙ የምንማርበት መሆኑን በማሳያነት ይጠቅሳል። በዚያ ዘመን የተሠራው የፊልም ጥበብ በዚያው የእድገት ደረጃውና የአሠራር ጥበቡ ይበልጥ እየዘመነና እየተለወጠ መሄድ ይገባው እንደነበር የሚገልፀው ዳንኤል፣ የዛሬ የሲኒማ ሥራ ጥበብና ውጤቱ ግን አርኪ እንዳልሆነ ከሂሩት አባቷ ማን ነው ፊልም ጋር በማነፃፀር ይገልፃል።
ይህ ታሪካዊ ፊልም በኢትዮጵያ የፊልም ሥራ ውስጥ ትልቅ አብዮት የቀሰቀሰ መሆኑን የሚናገረው ዳንኤል፣ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶና ሙያውን አክብሮ ታላላቅ መሰል ሥራዎች መሥራት የሚገባ መሆኑን ይናገራል። ዘርፉ ከተሠራበት እጅግ ከፍ ያለ አገራዊ ጠቀሜታ ያለውና ማኅበረሰብን በሥርዓት ለመቅረፅ የተሻለ አመለካከትና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ያስረዳል።
አማን አምደብርሃን የፊልም ፕሮዲዩሰር ሲሆን፣ የእሱም አስተያየት የተለየ አይደለም። በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ጎልቶ የሚነገረው «ሂሩት አባቷ ማን ነው» የተሰኘው ፊልም የፊልም ከፍታን በዘመኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ ማሳየት የቻለ መሆኑን ይገልፃል። ነገር ግን ከዛሬ 57 ዓመት በፊት በተሠራው ልክ ዛሬ የፊልም ሥራ እድገታችን እጅጉን ተቀዛቅዞና ከእድገት ርቆ መቆየቱን ያስረዳል።
የፊልም ሥራ ጥበብ በጀመረበት ሂደትና የፊልም አሠራር ልህቀት መቀጠል አቅቶት ዛሬ ላይ የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳልቻለ የሚያስረዳው አማን፣ የሚመለከታቸው አካላት ለጥበብ ሥራ በተለይ ለፊልም ሥራ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳል።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳሁን ተመሳሳይ አስተያየት ፊልሙ በቅርቡ በተመረቀበት መድረክ ላይ ገልፀዋል። ዶክተር ሂሩት የፊልም ሥራ ጅማሮውን ያሳመረው ሂሩት አባቷ ማን ነው የተሰኘው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፊልም ትልቅ ጥበብ ማሳያና መሆኑን ያመለክታሉ። ዛሬ ላይ ግን ዘርፉ በሚፈለገው መልክ እና ለአገር ማበርከት የሚገባው ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳልቻለ ለዚህም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል።
አገሪቱ ከፊልም ሥራ ጥበብ ማግኘት እንዳትችል ያደረጋት ትኩረት መነሳቱ መሆኑንም ይገልፃሉ። ሂሩት አባቷ ማን ነው የተሰኘው ፊልምና ሌሎች የኢትዮጵያ ፊልሞች ተመልካች እንዲበቁ ትልቅ ሥራ የነበረው የኢትዮጵያ ፊልም ሥራ ኮርፖሬሽን በአዋጅ መፍረሱ ዋንኛ ምክንያት እንደሆነም ያመለክታሉ። የኮርፖሬሽኑ መፍረስ ቀድሞ በጥሩ መልክ የተጀመሩት ሥራዎች እያበቡ እንዳይሄዱ በዚህም አገሪቱ በዘርፉ እንዳታድግና የፊልም ሥራ ጥበብ እንዲቀጭጭ ዋንኛ ምክንያት አድርገው ይገልጻሉ።
በዚህ ፊልም ላይ አስተያየት የሰጡ ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት የፊልም ሥራ ጥበብ ኃያል ጠቀሜታን በመጥቀስ ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የሂሩት አባቷ ማን ነው ፊልም ዳግም ልደት
በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ተሠርቶ ለእይታ በቅቶ የነበረው ፊልም ያለበትን ዕዳ መክፈል ባለመቻሉ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ40 ዓመታት በላይ ተይዞ ቢቆይም ዛሬ ፀሐይ ወቶለት በድጋሚ ወደ መድረክ መቅረብ ችሏል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባበደረው ገንዘብ የያዘው ፊልም ዕዳውን ሰርዞ ታሪካዊና ለአገሪቱ የመጀመሪያ ፊልም እንደመሆኑ አገራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ በባንኩ ኃላፊዎች ተወስኖ በድጋሚ ለዕይታ እንዲበቃ ሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ቀድሞ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም እየተባለ ይጠራ ለነበረው ተቋም አበርክቷል።
የአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ፊልሙን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ለእይታ እንዳቀረበው በምርቃ መድረኩ ላይ ተጠቁሟል። የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በባለቤትነት ፊልሙን ለተመልካች ለማቅረብ ችሏል። ፊልሙ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በተለያዩ መድረኮችና ሲኒማ ቤቶች ለእይታ እንደሚቀርብ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014