ግዕዝ ለጥበብ

ሀ-ግዕዝ…መጀመሪያ ነበር:: ግዕዝም በመቶ ሰማንያ ሁለት ፊደላት የተቀመረ ጥበብ ነው:: ጥበብ ከግዕዝ፣ ግዕዝም ለጥበብ ሆነ፤ 360 ዲግሪ ሠርቶ:: ግዕዝ የልሳን ሁሉ ቀዳማይ፣ የበኩር ጥበብ ማኅፀን፣ በብርሃን ፀዳል የተጋረደ የጥበብ ልዑላን ዙፋን፣ የታላቅነት በትረ መንግሥት ነበር::

ዕውቀት በአቡጊዳ እየተማሰ፣ ጥበብ በግዕዝ እየተጋዘ፣ የብርሃን ሀገር ተፈጠረች:: ብርሃናማ ሕዝቦች ተወለዱ:: ጥበብንም በረቂቅ መቅረዝ ላይ አኖሯት:: በእማሬ በፍካሬ ሚስጢርን እያመሰጠሩ፣ የሰማይና ምድሩን መጋረጃ እየገለጡ ኖረው ኖረው…አኑረው አለፉ:: ይህን እውነታም አምልጠው ዛሬም ድረስ በሚገኙ ርዝራዦቻቸው ውስጥ የምናረጋግጠው ነው::

በሀገርም በውጭም፣ ድሮም ዘንድሮም ያሉ ምሁራንና የቋንቋ ሊህቃን ብዙ ብለውለታል:: ‹የአዳም ቋንቋ› ካሉትም አንዱ አለቃ ታዬ ናቸው:: “ግዕዝ ከ4ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በጽሑፍ ሲያገለግል የነበረ አፈ ንጉሥ ነበር…” እያሉ ይቀጥሉታል:: እስከ አጼ አምደ ጽዮን ድረስ በንግግር፣ እስከ አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ደግሞ የጽሑፍ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል ነበር:: ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የአማርኛ ቋንቋ መስፋፋትን ተከትሎ የግዕዝ ነገር ቅዝቃዜው እየበረታበት ሄደ:: ከ15ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ደግሞ፤ ግዕዝ ወደ አንድ አንድ አቅጣጫ ማምራት ጀመረ:: ከጽሑፍ አኳያ በሁሉም ዘንድ ቢቀጥልም፣ በንግግር ደረጃ ግን መናገሻው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር:: በኖህ ዘመን ውሃ ተጥለቅልቃ የነበረችው ምድራችን ቆይታ አሁን የምንመለከተውን ማይና የብስ እንደሆነችው፤ ዝኒ ከማሁ…

አይቴ ብሔሩ ለግዕዝ? የግዕዝ ሀገሩ ወዴት ነው? ብዙዎች እንደምናስበው አይደለም:: ግዕዝ ብሔር፣ ነገድ፣ ሃይማኖት…የእኔ፣ የእርሱ፣ የእነርሱ የሚባል ነገር የለውም:: ‹ሀገሪትነ ግዕዝ/ብሔረ አጋአዚ› ግዕዝ ራሱ መኖሪያ ሀገራችን ነው:: ሀገር ደግሞ የሁሉም ልጆቿ እንጂ፤ የብሔር ወይንም የሃይማኖት ብቻ አይደለችም:: “ግዕዝ እንደ ሌሎች ቋንቋዎች በነገድ አልተሰየመም:: ግዕዝ የአዳም ቋንቋ ነው” ብለውታል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ:: ግዕዝ የጥበብ ቋንቋም ጭምር ነበር:: 182ቱም ፊደላት የተቀረጹበት መንገድ እንኳን ዘፈቀደ ሳይሆን ጥበብ ነው:: ስዕላዊ ረቂቅ፣ ቁጥራዊ ቀመር፣ ገሀዳዊ ውክልና አላቸው:: ከዓባይ ምንጭ ጠብታ እስከ ህንድ ውቅያኖስ፣ ከኩሽ እስከ ኑብያ፣ ከአክሱም እስከ ማያ፤ ኢትዮጵያ የለበሰችው የግዕዝን ጥበብ ሐምራዊ ዘርፎች የተነሰነሱባቸው ነበሩ:: ለሥልጣኔ፣ ለጥበብ፣ ለሥነ ፈለግ፣ ለሳይንስ፣ ለሃይማኖት፣ ለፖለቲካ…ግዕዝ መጀመሪያ፣ ግዕዝ አሊፍ ነበር::

አሁን አሁን ይህ ሁሉ ነገር የተገለጠለት ወይንም እየተገለጠለት ያለ ትውልድ የተፈጠረ ይመስላል:: ‹ግዕዝ! ግዕዝ!› የሚል በቁጭት የነደደ ትውልድ ተነስቷል:: ይህ መነሳት ትንሳኤ ግዕዝ፣ የጥበብ አብዮት ነው:: ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሀገር እስከ ባሕር ማዶ ግዕዝን የተጠማ ነው:: ከዚህ መሃል ችቦ ለኳሽ ፊታውራሪ መሆን ለሀገር ትጥቅ፣ ለነገ ስንቅ ማስቀመጥ ማለት ነው:: ከግለሰብ እስከ መንግሥታዊ ተቋማት ድረስ በደቦ ‹ሆ!› ብለው ተነስተዋልና ከተነሱት አንዱም ከዛሬዋ ጽሑፋችን መነሻና መድረሻ ላይ ስምና መልኩ አለበት::

የኢትዮጵያን የታሪክና ጥበባት ብራናዊ ሚስጢራትንና መዛግብትን ታቅፎ ወደፊት ሲያዘገም፣ አሁን በዕድሜው የ81 ዓመት አዛውንት ነው:: የግዕዝን ትንሳኤ ከናፈቁት ጋር እየናፈቀ፣ ከተነሱት ተነስቶ የተኙትንም እየቀሰቀሰ ‹እጅ ከምን› የሚያስብል ዐሻራውን ያኖረና ገና እያኖረ ያለ ግዙፍ መንግሥታዊ ተቋም ነው፤ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት(ወመዘክር):: በእኚያ ሁሉ ዓመታት ውስጥ በተጓዘባቸው መንገዶች፣ በቁጥር በርከት ያሉና በዓይነታቸው በዋዛ የማይገኙ ጥንታዊ ብራናዎችንና አብያተ መጻሕፍትን ከያሉበት ሲያከማች ኖሯል:: ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ወሳኝ የሆኑ ጥንታዊ መዛግብትን በወግ ሰድሮ እናገኘዋለን:: በትንሹ ከ1ሺህ 930 በላይ ጥንታዊ የጽሑፍ ሀብቶችን ሰብስቦ የያዘ ነውና እኚህ ሁሉ እንዲነበቡ ይፈልጋል:: ‹ጥንታዊ› ስንል ታዲያ፣ የተጻፉት በግዕዝ ስለመሆናቸው ነጋሪ የሚያሻን አይደለም:: ዋጋቸው በወርቅ እንቁ የማይተመነውን አንጡራ ሀብት ይዞ የሚገኝ ነውና ስለ ግዕዝ ፊታውራሪ መሆን የሚገባውና የሚጠበቅም ኃላፊነት ነው:: መንገድ ጥርጊያውን ከጀመረ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል::

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፣ ግዕዝን በተመለከተ ከግለሰብ እስከ መንግሥታዊና የግል ተቋማት ድረስ ያንቀሳቅሳል:: ለውጥ ከሳች ርምጃዎቹ ከየአቅጣጫው ቢሆኑም፤ በዋናነት ግን አንድ ችቦ የበራበት የስኬት መንገድ አለው:: ይህም “የግዕዝ ጉባኤ” ይሰኛል:: በፍኖቱ እየመራ ወደ ታላቁ የጥበብ ዓለም እንቅስቃሴ ላይ ነው:: ጉባኤው ዘንድሮ ስምንተኛውን ይዟል:: በጉባኤው ከታየው መንደርና ካሳለጠው ቅያስ ሁሉ እየገባ፣ ከብዙዎች መክሮ አዳዲስ ድልድይና መንገዶችን የሚከፍትበት ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ የእስካሁን መዳረሻ ክንፎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው:: ለዘንድሮው 8ኛው የግዕዝ ጉባኤም፤ ወደ አማራ ክልል አቅንቶ፣ ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሦስትዮሽ ተጣምሮ በሚያዝያ 28 እና 29/2017 ዓ.ም ደሴ ከተማ ላይ ሲያካሄድ ቆይቷል:: መሪ ቃሉም “ናዝልፍ ኅበ አንብቦተ መጻሕፍተ ግዕዝ” ትርጓሜውም “ስለዚህ የግዕዝ መጻሕፍትን እናንብ” የሚል ነው:: ማንበብ የምንችል ግን ስንቶች ነን?

ማንበብ የምናውቃቸውን ፊደላትና ቃላት ማነብነብ ማለት አይደለም:: ‹ማንበብ› የተጻፈውን ተገንዝቦ፣ ከተጻፈው ጀርባ መርምሮ ከዕንቁው ሰምና ወርቅ ላይ የመድረስ ነው:: እኛስ? ገና ፊደላትና ቁጥሩንም ለማወቅ ከሚቸግረን ደረጃ ላይ ነን:: ሆኖም የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ አቡጊዳን ከመቁጠር ነውና እየቆጠርን እናነባለን:: ለማንበብ ከመቻላችን በላይ ፈተናው የማንበብ ልምድን ማዳበሩ ላይ ነው:: የእውነትም እነርሱው ብለውት ይሁን በራሳችን ላይ ስንፎትት “ሚስጥርህን ከኢትዮጵያዊያን ለመሰወር ከፈለግህ መጽሐፍ ውስጥ ደብቀው” የሚል አባባል እስኪፈጠር ተዳርሰናል:: የመጀመሪያው ጥያቄ ግን፤ ሳይቀድሙን ቀድመን አውቀን እናነባለን? ወይንስ ጥቁር ሠሌዳ ፊት ቆመው ‹አ-ቡ-ጊ-ዳ ሄ-ው-ዞ› እስኪሉን እንጠብቃለን?

እንደ ኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት “ናዝልፍ ኅበ አንብቦተ መጻሕፍት ግዕዝ” እሳቤ፤ ግዕዝን ማንበብ፣ ማወቅ፣ መመርመርና መጠቀም ስለምንስ አስፈለገ? ጉባኤውስ በከንቱ ዲስኩር አጀንዳ ለመሙላት? የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ “ግድ ብሎን ስለ ግዕዝ መሰብሰባችን ለታመምንባቸው ነገሮች ፈውስን ፍለጋ ነው:: መድኃኒቱም ግዕዝ ነው:: የዕውቀት የጥበብ መድኃኒት:: የሳይንስ የተፈጥሮ መድኃኒት…ግዕዝን እንደ ሀገር ለመጠቀም ከቻልን፣ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለገባችባቸው ችግሮች ትልቅ መፍትሔ ሊያመጣልን የሚችል ነው:: በግዕዝ ያልተጻፈ ዕውቀትና ጥበብ የለምና ዳግም ወደነበርንበት የዓለም ታላቅነታችን መስፈንጠሪያ መንኩራኩር የመሆን አቅም አለው:: ‹ግዕዝ ግዕዝ› እያልን ከእንቅስቃሴዎቻችን አንዱ የሆነውን ይህን ጉባኤ በየዓመቱ የምናዘጋጀውም ቋንቋውን ብቻ ብለን ሳይሆን፣ በቋንቋው ውስጥ የሚገኙትን ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበባትን በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ የመመለስ ነው” በማለት ነበር ስለ ግብና ዓላማው የገለጹት::

ሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ስዕል፣ የሥነ ፈለግ፣ የታሪክና የኪነ ሕንፃ ጥበብ እንዳላት የምናውቀውና የምናወራው ነው:: በግዕዝ ለም አፈር ላይ በቅሎ፣ በአቡጊዳ እስትንፋስ ነብስ ያልዘራ የለም:: ኢትዮጵያ ታላቅ የነበረችበት ረቂቅ ጥበባዊ ንድፍ ቀለሙ ከግዕዝ ነው:: የኢትዮጵያን የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ ስናነሳ ግዕዝን ጥለን ከሆነ ምንም እንደሌለን እንቁጠረው:: ምክንያቱም የምንናፍቃት ኢትዮጵያ ስሯ ግዕዝ፣ ግንዷም አቡጊዳ ነው:: ኢትዮጵያ የአማርኛን ፊደላት ቀርጻ፣ በዕውቀት በጥበብ ቃኝታ መጻፍና ማንበብ የጀመረችበትን ጊዜ ሩቅ ቢመስለንም፤ ገና 2 መቶ ዓመት እንኳን አልሞላም:: ሌሎቹ የሀገራችን ቋንቋዎች ከብዕር ጋር የተዋወቁበት ጊዜ ደግሞ የቅርብና ሰሞነኛ ነው:: ታዲያ ግዕዝን ጥሎ የ3ሺህ ዘመን ታሪክ፣ ጥበብ…አለኝ ቢሉ ምን ሊረባ? የገባቸው ነጮች ግዕዝን ማጋዝ የጀመሩት እኛ ከጣልንበት እንዳይመስለን፤ ገና በ17ኛው ክፍለ ዘመን ግስ ገሰው ስለ ግእዝ ማጥናት መመርመር ጀምረው ነበር::

ግዕዝን ያበቀለች ለም አፈር ኢትዮጵያ ትሁን እንጂ፤ ግዕዝ ግን በአፍሪካ፣ በተለይ ከሰሃራ በታች በነበሩ ሀገራት ውስጥ በራሱ ልሳን፣ በራሱ ፊደላት፣ ብቸኛው የጽሑፍ ቋንቋ ነው:: የሴሜቲክ፣ የኦሞቲክ፣ ኩሽቲክና የናይሎ ቋንቋዎችንም ጭምር ወደ ጽሑፍ ለማምጣት የሚያስችል ሥርዓትም አለውና ጥበብን ከግዕዝ ስለመቅዳታቸው አጠያያቂ አይደለም:: ለምሳሌ በ1890ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተጻፈው “በሪሳ” የተሰኘው የኦሮሚኛ መጽሐፍ የአጻጻፍ ሥርዓቱ የተቃኘው ከግዕዝ ስለመሆኑ ግልጽ ነው::

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እየሄደበት ያለው መንገድ ‹በርታ!› የሚያስብለው ቢሆንም፤ ከአንደኛ እስከ መሰናዶ ታች ወርዶ ከግንድና ከስሩ እንዲያቆጠቁት ማድረጉ ገና ያልተጀመረ ግን የማይታለፍ ወሳኙ (?) ጥያቄ ምልክት ነው:: የትምህርት ሚንስቴርን በር ማንኳኳትና በጠረጴዛ ዙሪያ ማውጋት ይጠበቅበታል::

የሀገራችን የጥበባት ታሪክ መነሻና መድረሻ ቤታቸው ግዕዝ ነው:: አሁን የደረስንባቸው እያንዳንዱ ጥበባት የተወለዱት ከግዕዝ ነው:: በግዕዝ ቅኔ ሲዘረፍ ነበር፤ አማርኛም ቅኔውን ከግዕዝ ላይ ዘርፏል:: ቅኔ ማህሌት ቆሞበታል:: በትርጉምና በተዋረድ የልኬት ፈጠራ፣ ማነጻጸሪያ ማስፈንጠሪያው ሁሉ ከግዕዝ እልፍኝ ነው:: በቃላት ሰዋሰውም ሆነ በቋንቋ ገለጻው ግዕዝ ከነውበቱ ምሉእ ነው:: ከእርሱው ለመዋስ እርሱን ማራቃችን ስለምን እንደሆን ባይታወቅም፤ ግዕዝ ግን ስለረሱት ብቻ በቀላሉ የሚሞት አልነበረም:: ትንሽ እየቆነጠርን ብዙውን ስንረጭ ብንኖርም፣ አሁን ግን ከምንጩ ቆሞ ንጹሁን መጠጣቱ አማራጭ የለውም::

አንዳንድ ነገሮች በ8ኛው የግዕዝ ጉባኤ… ከምሁራን፣ የቋንቋ ሊህቃንና ከሌሎችም አንደበት ብዙ ነገሮች ተደምጠዋል:: ባቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውም ረቂቅ ምልከታዎችን አስፍረዋል:: ግዕዝ ትናንት፣ ግዕዝ ዛሬ፣ ዕውቀትና ጥበብ…ግልጽና ውስብስብ፣ ብሩህ ተስፋና ጥቁር ደመና፣ ፈገግታና ቁጭት አዘል ስሜቶች… ግራና ቀኝ፣ የላይ ታች መልኮች፣ የተለዋወጡ የሃሳብ ሰበዞች ብዙ ናቸው:: ከቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል፤ የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ በአማርኛው ውስጥ ያሳረፈውን ግዙፍ ዐሻራን የሚዳስስ ነው:: ድግግሞሽን በሚከተለው የግዕዝ የንባብ ባሕል፣ የአብነት ትምህርት የአስተምሮ ሥርዓት ጥበባዊ ፋይዳ፣ ጥበብ-ምግባረ ሠናይት እና ሰው መሆን፣ የዋድላ ቅኔ ሚስጢር በትናንት ዛሬ መነጽር…የሚሉና ሌሎችም ሃሳቦች ቀርበውበታል:: የግዕዝ ተመሳሳይ ፊደላት በአማርኛው ውስጥ ‹ያስፈልጋሉ› ‹አያስፈልጉም› በሚል በሁለት የሃሳብ ጎራ ተከፍለው የሚሞግቱም አሉና ይህን በተመለከተም፣ የአስፈላጊነታቸውን መሠረታዊነት የሚያሳይ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ከነ አመክንዮው ተዳሶበታል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተርና የሥነ ልሳን ባለሙያው ዶ/ር ዮሐንስ አድገ፣ በ8ኛው ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጹሑፋቸውን ካቀረቡት መካከል አንዱ ነበሩ:: እርሳቸውም “በሥነ ልሳን ንጹሕና እድፍ የሚባል ቋንቋ ባይኖርም፤ የዓለም የቋንቋ ምሁራን ግዕዝን ንጹሕ ቋንቋ ነው ይሉታል:: በሰዋሰው፣ በቃላት አገባብ፣ በቅኔ ሀብቱ፣ በሥነ ጽሑፋዊ የገለጻ ውበቱ እጅግ የተለየ የራሱ ማንነት አለው:: በአፍሪካ ብቸኛው የጽሑፍ ቋንቋ ከመሆኑም፤ የኩሽቲክ፣ ኦሞቲክ፣ ናይሎ፣ እንዲሁም ሌሎች የሴሜቲክ ቋንቋዎችን ለመጻፍ የሚያስችል ሥርዓት ያለው ነው” የሚሉ ሃሳቦችን ያነሱ ሲሆን፣ ግዕዝ በፈተናዎች የተከበበ በመሆኑ፣ ዳግም ወደ ሀገራዊ ዙፋኑ ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሰይፍ ይዘው የቆሞ አመለካከቶች መኖራቸውንም በጥናታዊ ጽሑፋቸው ውስጥ ጠቅሰውታል:: ከእነዚህ ጋሬጣዎች መካከልም “ግዕዝ ብሔርና ሃይማኖት የለውም” የሚለውን ሽረው ‹ግዕዝ የእነርሱ ነው:: የእነ እገሌን አንስቶ የእኛን ለማስጣል ነው› ዓይነት የጭለማ ሃሳቦች ይገኙበታል:: ለዚህ የተሳሳተ ትርክት ማሳያነት ያነሱት፤ ጥንቱን በሙስሊሙ ቁርአንና ሀዲስ የተጣቀሰበት፣ በክርስቲያኑ መጽሐፍ ቅዱስና ድርሳናት እስከ ቅኔ የተደረሰበት፣ በአይሁዳዊያኑም…ዝኒ ከማሁ:: እንዲህ ያሉ ግዕዝ ላይ የተጣበቁ አስፈሪ ጮጎጊቶችን ነቅለን ከአዕምሯችን ማውጣት ይኖርብናል:: የሥራዎቻችን ሁሉ መጀመሪያም እኚህን መሰል ትርክቶችን በግንዛቤ ማጽዳት ቢሆን የተሻለ ነው::

በሌላ በኩል ደግሞ በሀገሩ እየተገፋ በውጭዎቹ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው አበባ እየጎዘጎዙለት ነው:: በእንዲህ ከቀጠልን ነገ ከእጃችን መውጣቱም የማይቀር ነው:: እነርሱ ምን አዩበት? እኛስ ምን አጣንበት? የዕውቀትና የአዋቂነት መለኪያ አድርገን የቆጠርናቸው፣ ከሞላ የዓለም ቋንቋ ግዕዝን መርጠው ሲሻሙና ሲራወጡበት እየተመለከትን፣ ‹ሻሞ!› ብለን በምንወረውረው ስናጋፋቸው ግድም አይሰጠንም:: አዋቂዎቻችን ‹ወርቅ ነው› እያሉ የተጋፉበት ግዕዝ ለእኛ እንደ መሬት ላይ ጠጠር የታየን ምን ያህል ሀብታምና ሊቅ ብንሆን ነው?

ዶክተር አወል ሰኢድ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት “ከትምህርቱ ጋር ሀገራዊ የጥበብ ማዕከል መፍጠር ከዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚጠበቅ ነውና ይህን ማድረጋችን አማራጭ የሚወሰድበት አይደለም::… የንባብ ባሕላችን የወረደበት ጊዜ ላይ እንደመገኘታችን፣ በዚህ መድረክ ላይ የተደረጉት በጥናት የተደገፉ ውይይቶች እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመፍትሔ መንገዶችን እንድንፈልግ የቤት ሥራን ጥሎብናል:: ግዕዝ የሁላችንም ነውና በጀመርነው ላይ ሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ አክለን ሌላም እንሠራበታለን” የምትል ሃሳባቸውን ጣል አድርገው ነበር::

ዶክተር አወል እንዳነሱት ሃሳብ ሁሉ፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ማውጣት ያለባቸው የተማረ ዜጋን ብቻ ሳይሆን ማርሽ ቀያሪ ሀገር በቀል የምርምርና የመፍትሔ መንኩራኩሮችንም ጭምር መሆን አለበት:: ዕውቀትና ጥበብን ከግዕዝ እየቀዳን ለሀገራችን የከፍታ መሰላሏን እንሥራ ስንል ለዩኒቨርሲቲዎቻችን ቀስቃሽና ነጋሪ አያስፈልጋቸውም:: ምክንያቱም ይህን እውነታ ከእነርሱ በላይ ሊያውቀውና ሊረዳው የሚችል የለምና:: ለግዕዝ መንገድ ጥርጊያውን ከጀመሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የወሎ ዩኒቨርሲቲም ከግንባር ቀደሞቹ ሊጠቀስ የሚችል ነው:: በ2011 ዓ.ም አሀዱ ብሎ ሲጀምር፣ 15 የግዕዝ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማሩን ቀጠለ:: በስድስቱ ዓመታት ውስጥም በርካቶችን በግዕዝ አስተምሮ አስመርቋል:: በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ለግዕዝ ጥናትና ምርምር ማዕከል የሚሆን የራሱን ግዙፍ ህንጻ በማስገንባት ላይ ይገኛል::

ወሎ የግዕዝ፣ ወሎ የቅኔ ሀገር ናትና እንዲህ ባይደረግ የሼህ ሁሴን ከራማ፣ የአቦ አድባርም አይታረቅ:: በሀገራችን የሥነ ጽሑፍ ጅማሬና እድገት ትልቁን ስፍራ የያዘውና የመጀመሪያው የሀገራችን ዩኒቨርሲቲ የሆነው የሐይቅ እስጢፋኖስ አቡነ ኢየሱስ ሞአ ገዳምም በወሎ ነውና ስለ ግዕዝና ጥበብ በወሎ እንዳያነሱት የለም:: ቅኔ ካሉም ወሎ ነው:: የዋሸራ እና የዋድላ ቅኔያት ከአፍ እንደ ማር ይዝለበለባሉ:: የእዚህም የእዚያም በረካውን ለግዕዝ ትንሳኤ ጥበብ ያድርግልን::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You