የተወለዱት በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን ቡልቂ ወረዳ ነው። በንግድ ስራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) በጽህፈት ስራ አገልግሎት እ.ኤ.አ 1969 በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ለአራት ዓመታትም በተማሩበት ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል። የትምህርት ዕድል በማግኘት ወደ አሜሪካ ተጉዘው በንግድ አስተዳደር እ.ኤ.አ በ1976 በዲግሪ ተመርቀዋል። ኑሯቸውን በአሜሪካ መስርተው 22 ዓመታት ቆይተዋል። እ.ኤ.አ በ1995 አገራቸው የተመለሱት አቶ ተመስገን በ1997 ዓ.ም በምርጫ ተወዳድረው ህዝብን ወክለው አገልግለዋል። የ67 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ከሆኑት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባለሙያው ጋር በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አተኩረን ያደረግነውን ቆይታ በዚህ ገጽ እንደሚከተለው እናቀርባለን።
አዲስ ዘመን፡- የፖለቲካ ህይወትዎ የሚጀምረው እንዴት ነው ?
አቶ ተመስገን፡- ከተማርኩበትና 22 ዓመታት ከኖርኩበት አሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎም ኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪዎች ጉዳይ ሀላፊ ሆኜ እሰራ ነበር። የልጅነት ፍላጎቴ እንደ አያቴና አባቴ ህዝብ ለማገልገል ስለነበረ ምርጫው በሚቃረብበት ጊዜ የልጅነት ሃሳቤን ያሳካልኝ ይሆናል በሚል በምኖርበት ቀበሌ ተመዘገብኩኝ። አስፈላጊውን ሁሉ አሟልቼ ወደ ምርጫው ውድድር ልገባ ስል ከአቶ ልደቱ አያሌው ፓርቲ ጥሪ ደረሰኝ። ከአቶ ልደቱ ጋር ተገናኝተንም ተነጋገርን። ስለፓርቲያቸው የፖለቲካ ፕሮግራም፤ መተዳደሪያ ፕሮግራማቸውና ርዕዮተ ዓለም አንብቤ ከተረዳሁ በኋላ ኢዴፓ መድህን ፓርቲን ተቀላቀልኩኝ። ቀጥሎም ፓርቲው ወደ ቅንጅት ተቀላቀለ፤ እኔም የዚሁ ፓርቲ አባል ሆኜ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተመርጬ በነበረው የፖለቲካ ውዝግብ ዘግይቼም ቢሆን በህዳር ወር 1998 ዓ.ም ወደ ፓርላማ ገባሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ለተገኘው ለውጥ ባለቤቱ ማነው ይላሉ? ምንስ ተሰማዎ?
አቶ ተመስገን፡- በአንድ በኩል እኔና እኔን የመሰሉ ሰዎች ለዚህ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለን። ይሄ በሌሎች ታወቀም አልታወቀም ለህዝብ ጥቅም የቆሙ ታገዮች ነበሩ። አሁንም አሉ። አሁን ያለውን ለውጥ ለማምጣት በህይወትም ያሉ የሌሉም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በእዚህ መልክ ሲናገሩ ሰምተን አናውቅም። እኛ በነበርንበት ጊዜ ጥያቄ አትጠይቁ፤ ከጠየቃችሁም በቀላሉ ሊመለስ የሚችል ነው መጠየቅ ያለባችሁ፤ ያንንም በአንድ ደቂቃ ውስጥ ጨርሱ ተብሎ ከፍተኛ ጫና ነበረብን። እንደተቃዋሚ የምታደርጉት እንቅስቃሴ እግራችሁን፤ እጃችሁን ጣቶቻችሁንም ያስቆርጣል እየተባለ በዛቻ ውስጥ አሳልፈናል። አሁን በዶክተር አብይ ጊዜ የመናገር፤ የመዘዋወር፤ ሃሳባችንን የመግለጽ፤ የፈለግነውን የማምለክ፤ ተዘዋውረን የመስራት፤ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ነጻነቶቻችን ተጠብቀዋል። ይህ በኢህአዴግ መንግስት ይመጣል ብለን አላሰብንም። ግን ትንፋሻችን እስካለ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ነጻነት እስኪመጣ ድረስ አብዛኞቻችን ለመታገል ወስነን ነበር። ባላሰብነው ጊዜና ሁኔታ ለውጥ መጥቷል።
አቶ መለስ፤ የእርሳቸው መንደር ልጆችና ሌሎች በቡድን አፍነውን መናገር አይቻልም ነበር። ከእነርሱ አስተሳሰብ ውጭ ማሰብ አይቻልም፤ ይህንን ያደረጉ ሰዎች ይታሰራሉ፤ ይገረፋሉ፤ ይሰደዳሉ። በእዚህ ውስጥ ነው የኖርነው፤ በመናገር ብቻ አገር ጥለን እንድንሄድ የሚደረግበት፤ ዜጎች በተለይም ወጣቶች እድሜ ይፍታህ የታሰሩበት፤ በመንገድ ላይ በጥይት የተገደሉበት አስተዳደር ውስጥ ነበር የኖርነው፤ ለእኛ ዶክተር አብይ ከሰማይ ነው የወረደልን፤ እግዚአብሄር የላከው ነው። በርግጥ ከፍተኛ ለውጥ አለ። ወደ ኋላ የሚመልሰን ነገር የለም። ወደፊት ነው የምንቀጥለው፤ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ሁላችንም ባቅማችን ለዶክተር አብይ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እያደረግን አገር እየገነባን እንቀጥላለን። የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻና ገለልተኛ በሆነ የምርጫ ቦርድ ቁም ነገር ያለውና ታማኝነትን ያተረፈ ምርጫ አካሂዶ መሪውን እስኪመርጥ፣ ምክር ቤቱንና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን እስኪያቋቁም ድረስ ድጋፋችን አይቋረጥም። እርሳቸው ኢትዮጵያን ሊያተርፉ ከሰማይ የወረዱ፤ በጸሎት የተገኙ ናቸው። ይህንን ተቀብለን መቀጠል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች አሁን ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ (በተስፋና በስጋት) የምትገኝ አገር ናት ይሏታል። ይሄንን እርስዎ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ተመስገን፡- ይሄንን ለውጥ የማይፈልጉ እዚህም እዚያም ያሉ፤ ስልጣን ያጡና የነበረው የግፍ አገዛዝ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ቡድኖች የሚሉት ነው። በስራ ላይ ያሉና የተገለሉ፤ በተለያዩቦታዎች ረብሻና አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚጥሩ ግለሰቦችና የተደራጁ ሰዎች አሉ። ህዝቡ ለ27 ዓመታት ታፍኖ የኖረ ነው። በርግጥ አንዳንድ አለመግባባቶች እየታዩ ናቸው። ይህ ከጊዜ በኋላ የሚያቆም ነው። እውነቱን ሲረዱት፤ እንዲሁም ወገንተኛና ዘረኛ ያልሆነ አመራር እየመራን እንደነበር ሲገነዘቡ ይቀዘቅዛሉ። ካልቀዘቀዘ ግን የህግ የበላይነት መስመር መያዝ ይገባዋል። የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላምና ደህንነት የሚፈታተኑ አካላት ለህግ ቀርበው የሚጠየቁበት ስርዓት መፈጠር አለበት። ሁሉም በይቅርታና በመደመር አስተሳሰብ መታለፍ የለበትም። የህዝቡን ኑሮ የሚያውኩ፤ ለአደጋ የሚጥል አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖች ለህግ መቅረባቸው የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ እንደ ፓርቲና እንደ መንግስት ቁልፍ ጥንካሬዎቹና ድክመቶቹ ምንድን ናቸው? ለውጦቹንስ እንዴት ይመለከቷቸዋል?
አቶ ተመስገን፡- ዶክተር አብይን ከፓርቲው ነጥዬ ማየት እፈልጋለሁ። ሁለቱም ለእኔ አንድ አይደሉም። ፖለቲካ ውስጥ በነበርኩበትና ከእዚያም ውጪ ኢህአዴግ ህዝብ የሚያሳድድ፤ የሚያስር፤ የሚገርፍ፤ የእርሱን መስመር ያልተከተሉትን የሚያጠፋ፤ ቂመኛና ጉልበተኛ ፓርቲ ነበር። አሁን ለውጥ አለ የሚለውን ብዙም አላውቅም። ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅር ተለውጠዋል የሚለውንና እነዚህ ጨቋኞች ከፖለቲካ ሜዳው ተገልለዋል የሚለውን እርግጠኛ አይደለሁም። ወደፊት በስፋት እናገራለሁ። የመናገር መብታችንን ይገድቡ የነበሩ፤ ምርጫ በሰላም እንዳይካሄድ፤ ውጤቱ እንዲዛባ ያደረጉ የኢህአዴግ ሰዎች በአምባሳደርነት ተሹመዋል። ዶክተር አብይ አንዱን አማካሪያቸውን ብቻ ሰምተው ያደረጉት ወይም ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል። የፈለጋቸውን መሾም ስለሚችሉ፤ ግን በእነዚህ ተሿሚዎች የተረገጠው መብታችን መታወቅ አለበት። ህዝቡ የእነሱን ማንነት ማወቅና በትክክል መረዳት ይገባዋል።
እንዲሁ የሚታለፍ አይደለም። ወደፊት በስፋት እመለስበታለሁ። ከዚህ ውጭ ዶክተር አብይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከእድሜውና ከልምዱ የዘለለ ነው። አሁንም እርሱ ኢህአዴግ ውስጥ ያለ የኢህአዴግ ሰው ነው። እኔ ግን እርሱን እንዳልኩት ከፓርቲው ውጭ አድርጌ ሳስብ ነው በጣም ብዙ አድናቆቴን የምሰጠው፤ ፓርቲው ግን ብዙ ከፍተኛ ወንጀል ያለበት ነው። የገረፈ፤ የገደለ፤ ያስገደለና ህዝብ እንዲሰደድ ያደረገ ፓርቲ ነው። አሁን ለውጡን ለመገምገም ጊዜው አይደለም። ወደ ፊት የሚታይ ነው። አሁን ላለው ሁኔታ ግን መልካም ሂደት ነው። እኔ ለኢትዮጵያ የምመኘው ሰላም፤ አንድነት፤ ተስፋና ነጻነት ነው። እነዚህ ይመጣሉ ብዬ እገምታለሁ። ግን የዴሞክራሲ ሂደቱን የሚቆጣጠሩ የዴሞክራሲ ተቋማት አልተገነቡም። አንዳንድ ቦታ ከላይ ለውጥ ተደርጓል፤ ግን ከታች መዋቅሩ በሙሉ መስተካከል አለበት አመራሩና የመስሪያ ቤቱ መዋቅር መስተካከል አለበት። ይህ እስኪሆን ጊዜ ይፈጃል በትእግስት መጠበቀ ያስፈልጋል። ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ አመራር በመሆን መጥታለች፤ ጥሩ ነው። ግን ወደ ወረዳ፤ ዞንና ክልል ስንሄድ የሚደርሱብን በደሎች ነበሩ። ፖሊስ ለሚደርሱብን በደሎች ፈጥኖ የሚደርስልን ሁኔታ አልነበረም። የዴሞክራሲ ተቋማት እንደገና ሊታዩ ይገባል። አንድ ፓርቲ እንዲያገለግሉ ተደርገው ነው የተደራጁት፤ ወደ ጂንካ ስጓዝ መንገድ ላይ አስቁመው የምርጫ ቅስቀሳ የሚደረግበትን በራሪ ወረቀት ተቀምቻለሁ። እንዲህ አይነት ስህተት መደገም የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግን ያቋቋሙት አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች በውስጣቸውና እርስ በእርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት እንዴት ይታዘቡታል?
አቶ ተመስገን፡- ሌሎቹ ፓርቲዎች ህወኃትን ሊታገሉ የሚችሉበት ደረጃ ላይ አልነበሩም። ሙሉ በሙሉ ህወኃትና የአቶ መለስ ‹ኔት ወርክ› ነበር ይመራ የነበረው፤ ሶስቱ ብሄራዊ ድርጅቶች የፖለቲካ ተዋጽኦ አለ ለማለት ያህል የተሰባሰቡ እንጂ ያን ያክል ሊታገሉ የሚችሉ ስብስብአልነበሩም።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሊሰሯቸው ይገባሉ የሚሏቸውን ቢዘረዝሩልኝ?
አቶ ተመስገን፡- የህግ የበላይነትን ማስከበር አለባቸው። ባለፈው ጊዜ አንድ ከፍተኛ የመንግስት አመራር ፍርድ ቤት እንዲቀርብ መጥሪያ ደረሰው። ‹‹የመንግስት ስራ ይበዛብኛል ልመጣ አልችልም›› ብሎ የመለሰበትን ሁኔታ በጋዜጣ አንብቤያለሁ። ነውር ነው፤ እንደዚህ አይባልም። ከፍርድ ቤት መጥሪያ ሲደርስ ማንም ቢሆን መታዘዝ አለበት። ሶስቱ የመንግስት አካላት እኩል ስልጣን እንዳላቸውና ተጠባብቀው መስራት እንደሚገባቸው የማይረዱ ስላሉ እሱ ላይ መስራት ያስፈልጋል። አንድ ሰው በፍርድ ቤት ተከስሶ ጥፋተኝነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ነጻ መሆኑ የሚረጋገጥበት አገር መሆን አለበት። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ነህ ምናምን የሚባልበት አገር ሊሆን አይገባም። ፍርድ ቤት የሚቆመው ግለሰቡ እንጂ አንድ ሰው በህግ ሲጠየቅ በብሄራችን ላይ ያነጣጠረና ብሄርን ለማጥቃት ነው የሚለው አስተሳሰብ መጥፋት አለበት። ህገ መንግስቱ እውን የሚያደርገው የግለሰብን መብትና ግዴታ ነው።
ጥፋት የሚያጠፋው ግለሰቡ እንጂ ብሄሩ አይደለም። አንዳንድ ግለሰቦች በተጠረጠሩበት ወንጀል ሲፈለጉ በብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ጀምረዋል። ይህንን ማስተካከል ይገባል። ህገ መንግስቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነው ይላል። ሊሆን አይችልም። ህገ መንግስቱ የግለሰቦችን መብትና ግዴታ ማስጠበቂያ ትልቁ መሳሪያ ነው። የግለሰቡን መብትና ግዴታ የምታስከብርበትን ካስጠበቅክ የብሄሩንም አስጠበቅክ ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች መስተካከል አለባቸው። በአንድ በኩል በሰዎች መካከል ልዩነት የሚፈጠርበትን ነገር እያነገስን፤ በሌላ በኩል የህግ የበላይነት ማረጋገጥ አይቻልም። የህግ የበላይነት የሚረጋገጠው የግለሰቦችን መብት ማስከበር ሲቻል ነው። ስለዚህ ህገ መንግስቱ በግለሰብ መብት ላይ ያተኮረ መሆን አለበት። ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው እንዲናገሩ፤ እንዲፈላሰፉ፤ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲመሩና እንዲጽፉ መበረታታት አለበት። በአመራርነት ማንም ቢመጣ የዴሞክራሲ ተቋማት የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያገለግሉ ሆነው መዋቀር አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአንድ ወቅት በምክር ቤት የተለያዩ ጥያቄዎች ካቀረቡ በኋላ ‹‹በመጨረሻም የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት አመራር ኢትዮጵያዊ ቁመና እንዲኖረው እጠይቃለሁ›› ብለው ምላሽ አላገኙም ነበር። አሁን በአመራሩ ብሄራዊ ተዋጽኦ ለማድረግ የተወሰደውን እርምጃ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ተመስገን፡- ይህ ጉዳይ ከውስጤ ሲበላኝ የነበረ ጉዳይ ነው። ያኔ የመከላከያ ሰራዊት፤ በተለይም የመከላከያ አመራሩ የኢትዮጵያን ህዝብ በሚወክል መልኩ የተዋቀረ አልነበረም። በአብዛኛው አቶ መለስ የራሳቸው ብሄር በሆኑ ሰዎች ላይ ባተኮረ መልኩ ነበር ያዋቀረው፤ ይህ ሁልጊዜ ይከነክነኝ ነበር። ሌሎች ሰዎችም ይህንን ጥያቄ ለማንሳት በጣም ችግር ነበረባቸው። በምክር ቤት በቀጥታ አቶ መለስን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን በጀት የማጽደቅ ችግር የለብንም በተለይ አመራሩ የኢትዮጵያን ህዝብ ስብጥር መምሰል አለበት አልኳቸው። ይህ ብቻ አይደለም። በውጭ አገር እያለሁም ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲስተካከል ጽፌያለሁ። የብሄር ብሄረሰቦች አገር ነው እያላችሁ የአንድ ብሄር የበላይነት ያለው መከላከያ ሰራዊት አመራር ተገቢ አይደለም ብያለሁ። ዶክተር አብይ አስተዋይ መሪ ነው፤ ችግር መኖሩን ተገንዝቦ አስተካክሎታል። ያኔ የጠየቅኳቸው ነገሮች አሁን መልስ አግኝተው ተስተካክለው ተመልክቻለሁ። ለምን እንዲህ ይደረግ እንደነበር አላውቅም።
አዲስ ዘመን፡- በፌዴራሊዝም ስርዓት ላይ ያለዎ አቋም ምን ይመስላል?
አቶ ተመስገን፡- ፌዴራሊዝም በብዙ አገሮች ላይ የሚሰራ የአስተዳደር ስልት ነው። ለህዝብ አብሮ መኖር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ የመንግስትስርዓት ነው። ስርዓቱ ችግር የለበትም። ችግሩ ከመጀመሪያው ሲጠነሰስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰራ ተደርጎ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቡን በክልል አጥረው የቋንቋ ፌዴራሊዝም ነው የተገበሩት፤ ቋንቋ ሁልጊዜም ቢሆን ችግር አለው። ይህንን እነርሱም ይረዳሉ። በአፓርታይድ ስርዓትም ቋንቋ ችግር ነበረበት። በሰዎች መካከል ቅራኔ ማስፈን ካስፈገ ቋንቋውን መለየት ነው። ይህንን እነ አቶ መለስ በትክክል ይረዳሉ። ዋናው ትልቁ አደረጃጀት የአከላለል መሰረታቸው ቋንቋ ነው። አገር ውስጥ ያ ሁሉ ችግር ሊነሳ የቻለው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም በመሆኑ ነው እንጂ የህዝቦችን የመኖር ታሪክ፣ መልክአ ምድርን እና ሌሎች ታሪካዊ ትስስሮችን መሰረት አድርጎ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ፤ ችግር ውስጥ አንገባም ነበረ። አነስተኛ ቁጥር ያለው ህብረተሰብ ብዙ ቁጥር ያለውን ህብረተሰብ እንዲያስተዳድር ህጋዊ በሚመስል መንገድ ህገ ወጥ ስራ የተሰራበት የመንግስት አስተዳደር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመድብለ ፓርቲ ላይ ያለዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ተመስገን፡- መድብለ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጣ ሁሉም ነገር መልኩን ይለውጣል። አስፈላጊ ነው። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ለዴሞክራሲ ስርዓት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ምክንያቱም ፓርቲዎቹ ርዕዮተ ዓለማቸውን ለህዝብ አስረድተው ህዝብ አማራጭ ይኖረዋል በሚል እሳቤ ነው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚፈለገው፤ የእውቀት ፉክክር፤ ህዝቡን የማገልገል ፉክክርና የቁጥጥር ስርዓት ይዘረጋል። በጥቅሉ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በመኖሩ ህዝቡ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይታሰባል። በኢትዮጵያ ውስጥ ግን መተዳደሪያ ደንባቸው፣ ርዕዮተ ዓለማቸውና የፖለቲካ ፕሮግራማቸውም አንድ አይነት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ ኢህአዴግ ግማሹን ተለጣፊ አደረገው። አብዛኞቹ በተፎካካሪ ፓርቲነት ፍቃድ ያወጡና የኢህአዴግ ተለጣፊዎች የሆኑ ናቸው። ምርጫ አያካሂዱም። አንዳንዶቹ ላለፉት 10 ዓመታት ያላቸው አንድ ሰብሳቢ ወይም አንድ ፕሬዚዳንት ነው። መራጭም የላቸውም። ቤተሰቦቻቸው ብቻ ናቸው የሚያውቋቸው፤ እነዚህ ሰዎች ግን ኢህአዴግ ፈረንጆችን በሚያነጋግርበትና በሚፈልጋቸው ቦታ ተቃዋሚ ሆነው ይቀርባሉ። ለይስሙላ እንጂ ምንም አስተዋጽኦ የላቸውም። ይህንን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም ያውቃል። መንግስት በሚሰራው ስራ ሲሞግቱ፣ ሲጽፉና ሲናገሩ ሰምተን አናውቅም። ፍቃድ ያወጡት በምርጫ ጊዜ የሚሰጠውን ገንዘብና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ለመቀራመት እንጂ፤ ያን ያህል ግንዛቤ ያላቸው ፓርቲዎች አይደሉም። ቢኖሩም በጣም ጥቂት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ለውጡን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር 103 ደርሷል። አብዛኞቹም ብሄርን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ምን ቢያደርጉ ይመክራሉ?
አቶ ተመስገን፡- እንደኔ ሃሳብ ህብረ ብሄራዊ ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል። አሁን እየተለወጠ መሄድ አለበት። ያለንበት ክፍለ ዘመን የግሎባላይዜሽን ነው። አለም አንድ መንደር እየሆነች፤ እየጠበበች የመጣችበት ስልጣኔ ውስጥ ነን። በብሄር እየተደራጀን የምንታገልበት ጊዜ አልፏል። ለአገርም ጥቅም የለውም። አብረን ማሰብና መስራት ይቻላል። አንድነታችን ጉልበታችን ነው። ተከፋፍሎ አያዋጣም። ከክልላዊ አመለካከት መውጣት ይገባናል። በተለይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮቹ ይህንን ለመለወጥ መነሳት አለባቸው። በመረጃ ሃይል አለም አንድ እየሆነች ባለበት ጊዜ እኛ ወደ መንደራችን መመለሳችን የትም አያደርስም። የሚያዋጣው ህብረ ብሄራዊነት ነው። እንዲያውም ይህም በቂ የማይሆንበት ጊዜ እየመጣ ነው። ስለምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት እየተወራ ነው። ሰፊ የሆነ የህዝብ ተሳትፎና የኢኮኖሚ ውህደት የሚጠይቅ ነው። ሰዎች በቋንቋና በባህል የሚከፋፈሉበት ዘመን እያበቃ አንድ ሆነው ወደ ስልጣኔ እየሄዱ ባለበት ጊዜ ወደ ትንሿ ጉድጓድ አትመለስም። በመሆኑም መጣመርና ህብረ ብሄራዊ መሆን ያዋጣል።
አዲስ ዘመን፡- አዳዲስ የፖለቲካ አማራጭ የለም ወይ? ብዙዎቹ በቀድሞ አስተሳሰብ ላይ ነው ያሉት፤ ለምንድን ነው?
አቶ ተመስገን፡- እርሱ ከባህላችን ጋር ተይያዞ የመጣ ነው። እኛ አንድ ነገር ከያዝን የለውጥ አስተሳሰብ ለማሰብ ይከብደናል። ምክንያቱም ህዝቡ በሚያውቀው መንገድ መጓዝ ይመርጣል። የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሉም። እኛም ይሄንን አላደረግንም። ወደፊት አዲስ አስተሳሰብ ሊመጣ ይገባል። ስለአደረጃጀት፤ ስለኑሮ፤ ስለኢኮኖሚያችንና ስለማህበራዊ ግንኙነታችን ወጣ ያለ ሃሳብ የሚያስቡ ሰዎች ሊመጡ ይገባል። እድገት ያለው እዚያ ውስጥ ነው። ሁላችንም በህብረተሰቡ አመለካከት ውስጥ ወድቀናል። ቀድሞ በነበረው ሃሳብ ቀጥሏል። ይህ ሊቀየር ይገባል፤ እንጂ ለወጥ ያለ አደረጃጀትና ፍልስፍና የሚከተል የለም። ወደዚህ መምጣት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያንና የኤርትራን እርቅ እንዴት አዩት? በቀጣይስ ግንኙነቱ እንዴት መመራት አለበት?
አቶ ተመስገን፡- እንዴት ሊሆን ይችላል ተብሎ ሲሰጋ የነበረው አለምን በሚያስደምም ሁኔታ ዶክተር አብይ ፈትቶታል። ግን አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት አገር ነን። ግንኙነታችን እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያም ኤርትራም ራሳቸውን የቻሉ አገራት ናቸው። ወደፊት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሲዳብርና ሲጠነክር የሁለቱ አገራት ህዝቦች የተለያዩ ውሳኔዎችን ሊወስኑ ይችላሉ። እስከዚያው በህግ ማዕቀፍ ውስጥ የምንቀሳቀስ መሆን አለብን። ወደፊት የህግ ማዕቀፉ የማያስፈልግበት ደረጃ ልንደርስ እንችላለን። አሁን ግን ሁለቱም (Sovereign Nations) ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ አገራት ስለሆኑ በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መንቀሳቀሳቸው አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ይላሉ? የመፎካከሪያ ሜዳውንስ ምቹና ፍትሃዊ ከማድረግ አኳያ የተጀመረውን ስራ እንዴት ይመለከቱታል ?
አቶ ተመስገን፡- ድሮ ኮሮጆ ይሰርቅና ያሰርቅ የነበረው፤ ፍርድ ቤቱን በእጁ ጠምዝዞ ይዞ የነበረው ኢህአዴግ በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ይኖራል ብዬ አልገምትም። መቶ በመቶ ማሸነፍ አለብኝ ብሎ የሚታገል ኢህአዴግ ይኖራል ብዬ አልገምትም። እስከዚያው ድረስ መልካም ሪፎርም ያደርጋል ብዬ እጠብቃለሁ። ያ ካልሆነ ግን አስቸጋሪ ነው። አሁን የበፊቱ አይነት አካሄድ አይሰራም። እንደዚያ አይነት ነገር የምንሸከምበት ጊዜ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብም አይፈቅድም። ኢህአዴግ በቂ ማስተካከያ አድርጎ የመፎካከሪያ ሜዳውን ነጻና ገለልተኛ ለሆነ ምርጫ ቦርድ አስረክቦ ራሱ እንደአንድ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሳተፍበት ሁኔታ ነው የሚኖረው፤ እንደ መንግስትም እንደ ፓርቲም የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ሊመጣ ነው። በመሆኑም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። አሁን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንደሚሰሩ እገምታለሁ። አዲስ ዘመን፡- በምክር ቤት ቆይታዎ አላደረግኩትም ብለው የሚቆጩበት ነገር አለ? አቶ ተመስገን፡- በምትሰጠኝ ሁለት ደቂቃ የመናገሪያ ዕድል የኢትዮጵያን ህዝብ መንፈስ ለመያዝ ሞክሬያለሁ። ህዝቡ ብዙ የታመቀ ነገር እንዳለኝ ሊገነዘበኝ ሞክሯል። እኔ ግን የተናገርኩት በቂ ነው ብዬ አላምንም። ስለኢኮኖሚው፣ ስለኢህአዴግና ስለአቶ መለስ በበቂ ሁኔታ አልተናገርኩም። ህዝብን የማንቃት ስራ፤ ህዝቡ በመብቱ እንዲጠቀም ትውልድን በማዳን ስራ ተሳታፊ እንዲሆን የማድረግ ጥረቴ የፈለግኩትን ያህል አልሄደልኝም። የህዝብን መብት ይቅርና የራሴንም መብት ማስከበር የማልችልበት ሁኔታ ውስጥ ነበርኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
አቶ ተመስገን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011
በዘላለም ግዛው