የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ሕዝብ በእጅጉ እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች መካከል የሸቀጦች ዋጋ መናርን ተከትሎ የመጣው የኑሮ ውድነት አንደኛው ነው። ይህንን ችግር ለማቃለል መንግስት ስኳር፣ ስንዴ እና ዘይትን የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦችን በድጎማ ከውጭ ቢያስገባም፤ የድሃው ማሕረሰብ ህልውና በኑሮ ውድነት ምክንያት ገደል አፋፍ እንደተከለ ዛፍ አስጨናቂ ሆኖ ቀጥሏል። ለመሆኑ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ የሚመለከተው ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምን ይላል? ስንል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ መስከረም ባሕሩን አነጋግረናል ።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነት ሲነሳ ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መጠየቅ የግድ ነው። መሥሪያ ቤቱ የኑሮ መውድነት ላይ ምን እየሠራ ነው?
ወይዘሮ መስከረም፡– የኑሮ ውድነት ስንል በዋናነት ሕብረተሰቡ በዕለት ተዕለት የሚጠቀምባቸው የፍጆታ ዕቃዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ላይ ለይተን እየሠራን ነው። ዘይት፣ ስኳር እና የስንዴ ምርቶች ላይ ለረዥም ጊዜ በመንግሥት የዋጋ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው። አሁን ደግሞ እነዚህን ምርቶች ጨምሮ በነፃ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት የመውጫ ስትራቴጂ ተነድፏል። ቀደም ሲል በመንግሥት ብቻ ይሠራጩ የነበሩ ምርቶች ነጋዴዎች በተለይ አምራች ነጋዴዎችም እየተሳተፉ ምርቱ በብዛት እንዲቀርብ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። ይህ መንግሥት ከገበያው ላይ እጁን አንስቶ ሌላ ሥራ እንዲሰራ ያስችላል።
ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴና ነዳጅን ጨምሮ መንግሥት ዋጋ ለማረጋጋት የውጭ ምንዛሬን መድቦ እንዲቀርቡ ከማድረግ ባሻገር ምርቶቹ ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የአገር ውስጥ አቅርቦት ከፍ እንዲል የማድረግ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ከተጨማሪ እሴት ታክስም ነፃ በማድረግ ዘይት፣ ስኳር፣ የስንዴ ዱቄት (መኮረኒ፣ ፓስታ እና ዳቦ) ሌሎችንም ሕብረተሰቡ በብዛት የሚጠቀምባቸው ምርቶች ሊተኩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡትን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ጥናት ተደርጎ ወደ ተግባር ከተገባ የተወሰኑ ወራት ተቆጥረዋል።
ምርቱን የዲያስፖራ አካውንት ያላቸው ማናቸውም ሰዎች እንዲያስገቡ እየተደረገ ነው። ስለዚህ ከዋጋ ንረት አንፃር እየተሠራ ነው። ምክንያቱም ዋጋ የሚንረው በአቅርቦት ማነስ ነው። ምርቱ በብዛት ገበያ ላይ ካለ ከፍላጎቱ ጋር የተጣጣመ ይሆናል። የዋጋ ውድድሮች ይኖራሉ። እጥረት ሲፈጠር ግን ውድድር አይኖርም፤ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪዎች ፣ ማከማቸት፣ ምርቶችን ከገበያ ማውጣት በነጋዴዎች ላይ ይስተዋላል። ስለዚህ መንግሥት በዋናነት ትኩረት አድርጎ በአገር ውስጥ ምርት እንዲጨምር የማድረግ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ምርቱ ከተገኘ በኋላ ሥርጭቱን በሚመለከት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በመንግሥት ተፈቅዶ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተባሉ ምርቶችን ሥርጭት ይከታተላል። የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የተባሉትን ሶስቱ የምግብ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመኑን የመቆጣጠር ስራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንደገለጹት መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ አለ። ከበፊት ጀምሮ ዋጋ ሲተምን ዋጋው ከመረጋጋት ይልቅ የበለጠ ያሻቅባል። እዚህ ላይ የእርሶ ሃሳብ ምንድን ነው?
ወይዘሮ መስከረም፡- በጥናት ተደግፈው በተመረጡ ምርቶች ላይ መንግሥት የዋጋ ተመን ሊያደርግ ይችላል። አቅርቦቱ ምን ይሁን የሚለውንም ስትራቴጂክ ሆኖ ይወስናል። አዋጁ ላይ በተቀመጠው መሠረት በጥናት በተለየው ልክ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ውሳኔ ተሰጥቶ ክትትል ይደረጋል።
መንግሥት ያለምክንያት ወደ ቁጥጥር አይገባም። አዝማሚያውን አይቶ ነው። የሥርጭት ሥርዓቱ ወይም አቅርቦቱ ላይ ችግር እንዳለበት በጥናት ሲያረጋግጥ ወደ መወሰን ይሔዳል። አቅርቦት ለማሟላት ወይም አቅርቦት ኖሮ የሥርጭት ሰንሰለቱ ችግር ያለበት ሲሆን የሕዝቡን ፍላጎት አይቶ ምናልባት ሕገወጥ ደላሎችም ምርቱን የሚያወጡበት ሁኔታ ካለ፤ ጥናት አድርጎ በተመረጡ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ዋጋ ሊተምን አሊያም ከቀረጥ ነፃ ይግቡ ሊል አሊያም የአገር ውስጥ ምርት እንዲበዛ ሊወስን ይችላል። ይህንን ሲያደርግ አንዳንዴ ነጋዴውም ያለአግባብ ይዘጋጃል። ምርቱን ከገበያ ሙሉ ለሙሉ የማውጣት፣ የማከማቸት ተግባር የሚፈጽሙ ያጋጥማሉ። መንግሥት ሲተምን ዋጋው ይጨምርልኛል ብለው የሚገምቱም ይኖራሉ። ወይም ምርቱ ሲጠፋ ነጋዴውም ያለአግባብ ትርጉም ሰጥቶት የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖራል።
በሌላ በኩል ተጠቃሚው ሕብረተሰብም ስለ እነዛ ዋጋዎች በይበልጥ ትኩረት የሚሰጠው ምናልባት መንግሥት ትመና ካደረገ ትኩረት ሰጥቶ በሚዲያዎች ካስተዋወቀ በኋላ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የሲሚንቶ ምርትን ከወሰድን እንደአጠቃላይ የነበረ የሥርጭት ሂደት ችግሮች እንደነበሩበት በተከታታይ ጥናቶች ተደርገዋል። እንደአጠቃላይ ለረዥም ጊዜ ጥናቶች ሲደረጉ ከአቅርቦት ባሻገር ክፍተቶችም ነበሩ።
ሂደታቸውም ችግር ነበረበት። ፋብሪካዎች አካባቢ የግብዓት ችግር ነበር። ከዛ ባሻገር የሚወጡ ምርቶችም ለሕብረተሰቡ ለማድረስ ተገቢ ያልሆነ የሥርጭት ሒደት ነበር። ስለዚህ መንግሥት ያንን ለመፍታት ሲገባ ሕብረተሰቡ ቅርብ የነበረውን ዋጋ ላይረዳ ይችላል። ወይም በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውንም ተፅዕኖ ሳይረዳ ተፅዕኖውን መንግሥት እንዳደረገ የሚያስብ የተወሰነ ሰው ይኖራል ብዬ አስባለሁ።
ሌላው መዘንጋት የሌለበት ነጋዴው የሚያደርገው አግባብነት የሌለው ተፅዕኖ መኖሩ ነው። ምርት ሙሉ ለሙሉ ከገበያ የማውጣት የማከማቸት ምናልባትም መመሪያ እና ስትራቴጂ ከሚያስፈፅመው አካል ጋርም ተገቢ ያልሆነ የጥቅም ትስስር ውስጥ በመግባት የሚፈጥሯቸው ችግሮች ይኖራሉ። ነገር ግን ጥናት ተደርጎ የሚገባው ቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ነው። እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ፈቶ አቅርቦትን አሻሽሎ ውጤት ለማምጣት ነው።
እውነት ለመናገር መንግሥት በሚሠራው ሥራ ብዙ መሻሻሎች አሉ። የዘይት ምርቶች ዋጋ ስናይ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ቅርብ ጊዜ ጨመረ እንጂ መንግሥት ረዥም ጊዜ በጣም እንዳይወጣ አድርጎ ይዞት ስለነበር የተረጋጋና ተመሳሳይ ዋጋ ነበረው። ከቅርብ ጊዜ በኋላ ሁሉንም ከውጭ እያስገባን መቀጠል የለብንም በሚል እዚህ ያለውን አምራች ለማበረታታት ፋብሪካዎችን ገንብተን አገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጥረን ማምረት እንችላለን በሚል በእቅድ ድፍ ድፍ የምግብ ዘይት ይግባ ተባለ ነገር ግን ድፍድፉ በሚመጣበት ጊዜ፤ የፈጠረው ጫና አለ። ቀደም ሲል ታክስ ያልነበረባቸው ምርቶች ታክስ እንዲከፍሉ ተወስኗል። ታክሱ በየጊዜው የሚጨምርበትም ሁኔታ አለ። እርሱ እንደአገር ያሳደረው ተፅዕኖ አለ እንጂ ከ2003 እና ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለረዥም ጊዜ መንግሥት ቁጥጥር ለማድረግ ጣልቃ ከገባ በኋላ የዘይትን ገበያ አረጋግቶታል።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ለረዥም ጊዜ የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ 300 ብር አካባቢ ነበር። አሁን ግን ከ600 ብር በላይ በመሸጥ ላይ ይገኛል። አሁን ላይ ይህን ያህል ዋጋው የጨመረው የተጣራው ዘይት ላይ በተጣለበት ታክስ ምክንያት ነው?
ወይዘሮ መስከረም፡- አዎ! ቀደም ሲል ታክስ አልነበረም። ሌላው የተወሰነ ያልተጠናቀቀ ድፍድፍ እንዲገባ ሲደረግ ምርቱን የሚሸጡ አገሮችም ድፍድፉ የምግብ ዘይት የሥራ ዕድል ስለሚፈጥርላቸው መሸጥ አይፈልጉም። የተጠናቀቀውን ብቻ እንድንወስድላቸው ይፈልጋሉ። በእኛ በኩል ደግሞ በተጣራው ዘይት ላይ ታክስ ጥሎ ከዛ ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ሁኔታ አለ። ሌላው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኮቪድ በኋላ የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር እና የአምራቹ ማነስም ዘይት ላይ ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹ ምርቶች ዋጋቸው እንዲጨምር አድርጓል ። ከእዚህ ውጪ ከዛ የሚመጣው ዘይት ላይ እያንዳንዱ ወጪዎች በሥነሥርዓት ይታሰባሉ ። ተገቢ ያልሆነ ወጪ በፍፁም አይያዝም፤ ከአሥር በመቶ በታች የሆነ የትርፍ ህዳግ ተሰልቶ ይተላለፋል።
የዘይት ዋጋ መጨመር የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለ። ነገር ግን በአገር ውስጥ ቢመረት ውድድርን ይፈጥራል። አብዛኛው ሕብረተሰብ የአገር ውስጡን ይጠቀማል። ስለዚህ ሌላው ሲያቀርብ ተመጣጣኝ ዋጋ ይኖራል።
የስንዴ ምርትም ተመሳሳይ ነው። አምና ከግዢ ጋር ተያይዞ ክፍተት ያጋጠመ ቢሆንም ከዛ በፊት ግን ለረዥም ጊዜ የስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ መረጋጋት ተፈጥሮ ቆይቷል። ድጎማም ይደረግ ነበር። ከአንድ ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መንግሥት ለፋብሪካ በ550 ሲያቀርብ ነበር። አንዳንዴ የሚረብሹ ሲያጋጥሙ እንጂ መንግሥት አጥንቶ ጣልቃ ሲገባ እና አቅርቦትን ሲያሻሽል አብዛኛው ዋጋ እንዲረጋጋ ማድረግ እንደሚችል መውሰዱ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ ሲሚንቶ ላይ መንግሥት ዋጋ ሲተምን በጥቁር ገበያ ከእጥፍ በላይ ዋጋ ጨምሮ ሲሸጥ ነበር። አንዳንዴም ከመንግሥት በኩል ለማረጋጋት ሲሞከር በተቃራኒው የተለያዩ ሴራዎች ይኖራሉ። በሌላ በኩል እጃቸው ረዥም የሆኑ ነጋዴዎች ወይም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ አካላት የፋብሪካዎች ማሽኖች ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ እጥረት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በዚህም ሕብረተሰቡ ችግር ውስጥ ይገባል። ከዚህ አንጻር መንግሥት ጣልቃ ባይገባ ይሻላል የሚባልበት ጊዜም አለና በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ መስከረም፡- በእርግጥ የዋጋ ንረት የሚያጋጥመው የአቅርቦት እጥረት ሲኖር ነው። አንዱ መሰራት አለበት ብዬ የማምነው አቅርቦት ላይ ነው። ፋብሪካዎች ግብዓታቸውን አሟልተው በሚፈለግባቸው ልክ ማምረት እንዲችሉ የተለያዩ መንገዶች መኖር አለባቸው። ለምሳሌ ከቀረጥ ነፃ ሲሚንቶ የሚገባባቸው መንገዶች ኖረው በተጨማሪ የሥርጭት ሰንሰለቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል።
ውስን በሆነ ምርት ላይ ዋጋ ንሮ ነበር ትክክል ነው። እነዛ ውስን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ ጥረት ይደረጋል። ነገር ግን ምርቱ ውስን ስለሆነ በየቀዳዳው ሕገወጥ ነጋዴ ያገኘዋል። ያ ህገወጥ ነጋዴ ደግሞ ሕብረተሰቡ ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ በየትኛውም ዋጋ ይገዛዋል። ነገር ግን እጥረት ስላለ እያንዳንዱ ጋር ደርሶ ለመቆጣጠር ከባድ ነበር። ለዛ ነው ዋጋው ተጋኖ የነበረው። አሁንም እንደዛ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር ሲያጋጥም አቅርቦቱን ከፍ አድርጎ ሰንሰለቱን ማሻሻል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዴ እጥረቶች የሚያጋጥሙት በሴራ ነው። ለምሳሌ ሆን ብሎ የሲሚንቶ ፋብሪካ እንዳይሰራ የሚያደርግ አካል ይኖራል። ይህንን ለማወቅ እና ለመቆጣጠር ከደህንነት እና ከፖሊስ ጋር መስራት የግድ ሊሆን ይችላል። ተቋማችሁ ከሌሎች ተቋማት ጋር በትሥሥር ይሠራል?
ወይዘሮ መስከረም፡- ከሌሎች ተቋሞች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ላይ እንደውም ጠንካራ ነን። ከመደበኛው ሥራ በተጨማሪ ከዋጋ መረጋጋት ባሻገር በአብዛኛው ሥራዎች የሚሠሩት በግብረሃይል ነው። የፌዴራል የዋጋ ማረጋጋት ግብረ ሃይል አለ። ይህ 17 መሥሪያ ቤቶችን የያዘ ነው። ደህንነቱን ጨምሮ የፀጥታ ሃይልንም ይይዛል። ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አሉ። በዋጋ ማረጋጋት ላይ ያላቸውንም ሚና ያውቃሉ። በፌዴራልም ሆነ በከተማ ደረጃ መሥራት ያለባቸውን ይሠራሉ። በክልልም በዚሁ መልኩ ይሠራሉ።
ንግድ ላይ የፀጥታ ሃይሉ ወሳኝ ነው። ቅንጅት ላይ ችግር የለም። ይቀናጃል፤ እርምጃ መወሰድ ካለበትም ይወሰዳል። ሲሚንቶም ሆነ ሌላም ላይ በቅንጅት ይሠራል። በተለይ መንግሥት ዋጋ የተመነባቸው ላይ ንግዱ በዚህ መልኩ ይሂድበት በሚባልበት ጊዜ ነጋዴውም ከሚያሰራጨው አካል ላይ ሰርቆ ወደሌላ አካባቢ ለመውሰድ ጥረት ያደርጋል። እዚህ ላይ ክትትል ይጠይቃል። ከፖሊስም ፣ ከደህንነትም ጋር በጋራ ይሠራል። ነገር ግን የሕብረተሰቡም ድጋፍ ያስፈልጋል። ለሊት እና ቀን ተቆጣጥሮ አይቻልም። የሚያሰራጨው አካል በተቻለ መጠን የወረቀት ውል ይገባል። ስብሰባ ተጠርቶ መመሪያ ይሰጠዋል። ነገር ግን ቁርጠኛ ሆኖ በተሰጠው ሃላፊነት ልክ ይሠራል ወይ ሲባል አይደለም። ችግር ያለባቸው አካላት አሉ። ስለዚህ እኔ ብሆን ብሎ አስቦ መስራት ካልተቻለ ንግድ ቢሮ በሚያደርገው ቁጥጥር ብቻ ውጤታማ መሆን አይቻልም።
ነገር ግን መረሳት የሌለበት ብዙ ይለፋል። ተቆጣጣሪ የምንላቸው ባለሙያዎችም ይሠራሉ። አንዳንዴ ተቆጣጣሪውም ሆነ ነጋዴው በሃላፊነት ካልሠሩ ከነጋዴ ጋር ተመሳጥረው የሚያገኛትን ሳንቲም ካሰበ ከባድ ነው። ስለዚህ ዋናው እምነት ነው። ሁሉም በእምነት ቢሠራ ተቆጣጣሪም አያስፈልግም ። ጅምላ አከፋፋይም ሸማች ማሕበርም ለሕብረተሰቡ ቢያደርስ ችግር አልነበረውም። ነገር ግን ሁሉም ቀዳዳውን እየፈለገ የሚሰጥበት፤ በድጎማ የመጣው ፍጆታ ለሕብረተሰቡ በተጋነነ ዋጋ የሚሸጥበት ሁኔታ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞም ቢሆን ዋጋ መተመን እንዴት መፍትሔ ይሆናል? የዋጋ ንረት ከአቅርቦት እጥረት ጋር የሚገናኝ ነው። ዋጋ ከመተመን ይልቅ እጥረት ባለበት አካባቢ አቅርቦትን በሰፊው ማመቻቸት አይሻልም?
ወይዘሮ መስከረም፡– ትክክል ነው። በዋናነት በትልቁ መሠራት ያለበት አቅርቦትን ማሻሻል ነው። ዋጋ መተመንም ሆነ ኮታ መደልደል ጊዜያዊ መፍትሔ ነው። በዘላቂነት አጠቃላይ የዋጋ ንረትን መከላከል የሚቻለው በአቅርቦት ብዛት ነው። ለምሳሌ ዘይት ላይ ከላይ እንደገለፅኩት በተወሰነ መልኩ ያላለቀለት ዘይት ይምጣ እና ፋብሪካዎች ይጨርሱት ተባለ። ሰብስበን አምራቾችንም ሆነ አስመጪዎችን አነጋግረናል። እንደእስከ አሁኑ የውጭ ምንዛሪ እየተመደበ እና እየተመንን አንቀጥልም። የራሳችሁ ግብዓት ማዘጋጀት አለባችሁ። ብለን የተወሰኑት መሬት ወስደው የቅባት ዕህል ለማዘጋጀት እየሞከሩ ነው።
ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ተቋምም አለ። ከእርሱ ጋር ተቀናጅቶ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ባሉበት ስንጋገር የቆየን ሲሆን፤ በራሳቸው ጥሬ እቃ ዝግጁ እንዲሆኑ ተነግሯቸዋል። ነገር ግን አሁን ባለው አጭር ጊዜ እነርሱ በራሳቸው መሸፈን ከቻሉ፤ እና ሌሎች አምራቾችን ወደ ገበያው ካመጡ አይደለም አገር ውስጥ ወደ ውጪ መላክ የሚችሉበትን አቅም መፍጠር ይችላሉ። በራሳቸው ግብዓት መሔድ ቢችሉ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ይቀንሳል፤ አቅርቦት ይጨምራል፤ እነርሱ ላይ ሌሎች አምራቾች ይፈጠራሉ ስለዚህ ዘይት በዚህ ደረጃ ነው።
ስንዴን በሚመለከት መንግሥት የያዘው አቅጣጫ ይታወቃል። በአገር ደረጃ የሚመረተው ምርትና ያለው ፍላጎት ላይ ጥናት ተደርጓል። ምርቱ ፍላጎቱን የሚሸፍን አይደለም። እስከ አሁን ፍላጎትን ለማሟላት በእህል ንግድ አማካኝነት ከውጭ በማስገባት እንዲሸፈን ሲደረግ ቆይቷል። ነገር ግን አሁን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ እንዲሸፈን ታስቧል። በተለይ ቀደም ሲል ስንዴ የሚያመርቱ አካባቢዎች ተለይተው የሶስት ዓመት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።
የስንዴ ምርት ማለት በብዙ መልኩ ፓስታ፤ መኮረኒም ሆነ ዳቦ ላይ ሊታይ ይችላል። ስለዚህ ሌሎች ላይ የሚያሳድረውንም ተፅዕኖ ይቀንሳል። የጤፍም ሆነ የበቆሎ ገበያ ላይ በጎ ተፅዕኖ ያሳድራል። ስለዚህ እዚህ ላይ እየተሠራ ነው። ዘይትንም እየተመንን መቀጠል የለብንም። 40 ሚሊዮን ሊትር እየተደጎመ ይገባ ነበር። አሁን ግን ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ከ10 በመቶ አይበልጥም። የግል የዲያስፖራ አካውንት ያላቸው አስመጪዎች አስገብተው ጤናማ በሆነ መልኩ ካሰራጩ ዋጋን አንቆጣጠራቸውም፤ ነገር ግን የተጋነነ እንዳይሆን ባልተጋነነ ትርፍ ለሕብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ነፃ ሆነው እንዲነግዱ ማስቻሉ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ አጋጣሚዎች በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ መንግሥት ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ ገበያው ከመረጋጋት ይልቅ ይወደዳሉ። ለምሳሌ የሴቶች የንፅና መጠበቂያና የሕፃናት የዱቄት ወተት ለዚህ ማሳያ ናቸው ፤ ታክስ የመቀነስ፣ ቋሚ ዋጋ የመተመን እና ሌሎች ተቀራራቢ መፍትሔዎች ሲወጡ ውጤቱ በተቃራኒው ይሆናል። ለምሳሌ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ በችርቻሮ ከ25 ብር ወደ 45 ብር አድጓል። እያንዳንዱን ነገር እንይ ከተባለ ይህም ያጋጥማል። ቸርቻሪዎች አስመጪዎች ጨምረዋል ይላሉ። አንዳንዴ ሞኖፖል ማለትም አንድን ምርት አንድ አካል ብቻ የሚያመጣበት ሁኔታም ችግር ይፈጥራል። መንግሥትም ታክስ ቀንሶ ሕብረተሰቡም ተጎድቶ ምን ዋጋ አለው? በዚህ ላይ ሃሳቦት ምንድን ነው?
ወይዘሮ መስከረም፡– ማንኛውም አካል የትኛውንም ዓይነት ንግድ መነገድ ይችላል። የንግድ ገደብ የለም። የንግድ ፈቃድ የሚሰጠው በእኛ መሥሪያ ቤት ሥር ነው። በፊት መንግሥት በድጎማ ብቻ ያቀርብ በነበረበት ሰዓት ፈቃድ አይሰጥም ነበር። አሁን ግን ማንኛውም የዲያስፖራ አካውንት ያለው ከቀረጥ ነፃ ሳይቀር ማስገባት እንዲችል ፈቃድ ተሰጥቷል። የውጭ ምንዛሪውን ግን የሚያገኝበት የራሱ መንገድ ሊኖረው ይገባል። ለምሳሌ ውጪ ሆኖ የራሱ ሥራ ኖሮት በሁለት ዓመት ውስጥ እንቅስቃሴው ምን ያህል እንደሆነ ይታያል። ምክንያቱም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ይታወቃል፤ ያለንን ሰጥተን ችግር እንዳያጋጥም ቀድሞ ይጣራል። ያ እድል ክፍት ነው። ነገር ግን የተወሰኑ ምርቶች በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ከተያዙ ለምን ይህን ያዛችሁ ማለት አይቻልም መብታቸው ነው። ውድድር ነው። ሰዎቹ አቅም ኖሯቸው ከያዙት ገበያን በበላይነት መያዝ ይችላሉ። በበላይነት የያዙትን ገበያ ያለ አግባብ መጠቀም ግን አይችሉም። ለምሳሌ ገበያ ያወጡትን ምርት ለከሌ አልሸጥም ለእከሌ እሸጣለሁ ማለት አይችሉም። ያመጡትን ምርት ለማንኛውም ፈቃድ ላለው አካል ሁሉ መሸጥ ግዴታቸው ነው። በዚህ መሸጥ አለብህ ብለው ማስገደድ አይችሉም። ነፃ ገበያውን የሚፃረሩ ከሆነ በአዋጁ መሰረት ቁጥጥር ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን በበላይነት ለምን ያዝክ ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ገበያን በበላይነት የተቆጣጠረ አካል 10 ብር የገዛውን ዕቃ ገዢ ከተገኘ 1000 ብር ሊሸጡ ይችላል? ይህን ትክክል ነው ? መከላከልስ ትችላላችሁ?
ወይዘሮ መስከረም፡– አምጥቶ ለምን በዚህ ያህል ብር ሸጥክ ማለት ላንችል እንችላለን። ነገር ግን እንዲህ አይነት ሰው ሲኖር እርሱ የሚሰራውን አይቶ ሌላ ነጋዴ ሊፈጠር ይችላል። አንዳንዴ የሸማች መብት ሲባል ይህንን በተጋነነ ዋጋ አልገዛም ማለትን ማካተት አለበት። ወይም ነጋዴው በራሱ ያንን ሊያስተካክል ይችላል። አንዳንዴ ሸማቹም ጋር ያለማነፃፀር፣ ተጋኖ ሲሸጥ ለምን ያለማለት አለ። ሁለት ሶስት ቦታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። አንዳንዴ በአሠራር ብቻ ሳይሆን ሸማቹም ሕገወጥ አሠራሩን ማስቆም ይችላል። ገበያን በበላይነት ከመያዝ አንፃር በክትትል ላይገኝ ይችላል። ነገር ግን ጥቆማ ሲያጋጥም ቁጥጥር እና ክትትል ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለዋጋ ንረት እንደዋና ምንጭ ከሚጠቀሰው የምንዛሬ እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ባሻገር የቤትም ሆነ የመሸጫ እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የኪራይ ዋጋ ንረት እንደመንስኤ ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያት የግል ትምህርት ቤት ክፍያ፤ የግል የጤና ተቋማት ክፍያ እነዚህ ሁሉ የአገልግሎት ግብይት ውስጥ በመሆናቸው እናንተን ይመለከታሉ። ምክንያቱም ነጋዴው 30 ሺህ ብር ሱቅ ተከራይቶ፤ የኪራዩን ዋጋ እቃው ላይ መበተኑ አይቀርም። በዚህ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምን ይሠራል?
ወይዘሮ መስከረም፡– ልክ ነው። የትኛውም ነጋዴ ወጪውን ዕቃው ዋጋ ላይ መበተኑ አይቀርም። እኔ ግን ወደዚህ የሥራ ዘርፍ የመጣሁት በቅርብ ጊዜ ነው። እዚህ ላይ ተሰርቷል ማለት አልችልም። በአብዛኛው በሚበሉ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ነገር ግን ባለኝ መረጃ ትምህርት ላይ በአብዛኛው ትምህርት ሚኒስቴር ወይም የከተሞች የትምህርት ቢሮዎች ከወላጆች ጋር ሆነው የክፍያ አሠራሩን ያወጣሉ።
ከወላጅ ጋር ተመካክሮ በአመት መጨመር እንዳለበት ያስቀምጣሉ። የቤት ኪራዮች ላይ መንግሥት የሚያወጣቸው አንዳንድ ህጎች አሉ። የከተማ ከንቲባዎች ከሚመለከታቸው ዘርፎች ጋር ይሠራሉ። ነገር ግን እዛም አካባቢ የሰዎች የቤት ፍላጎት ከፍ ማለት እና ያሉ ቤቶች ውስን መሆን ዋጋውን ያንራሉ። በእርግጥ ከተሞች ሲያድጉ የሱቆች ዋጋ መናር ያጋጥማል። ነገር ግን እዚህ ላይ የተሠራ ነገር ስለሌለ ብዙ ማለት አልችልም።
አዲስ ዘመን፡- የነዳጅ መጨመር፤ በሸቀጦች ዋጋ፣ ትራንስፖርት ላይ ተፅዕኖ ስላለው ዋጋን ያንራል እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ መስከረም፡- ነዳጅን እንሰራበታለን። ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አለ። የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የመሸጫ ዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል። የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያም ይኖራል። የነዳጅ መጨመር በሌሎች ምርቶች ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አያስከትልም ማለት አይቻልም። ነገር ግን ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ ባያመጣም ምክንያት ያደርጉታል እንጂ በኪሎ ሜትር ሲሰላ እጅግ በጥቂት ሳንቲም ይጨምራል በሚንቀሳቀሰው ዕቃ ላይ ሲሰላ ደግሞ የሚያስከፍለው ዋጋ በጣም ትንሽ ነው። ነገር ግን በተለይ ነጋዴዎች ያለአግባብ ይጠቀሙበታል። በእርግጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው ማታ እና አንዳንዴ ቀንም ከታሪፍ ውጪ ለጭነት ያስከፍላል። ያንን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ነገር ግን ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ የተጋነኑ ጭማሪዎች ተገቢነት የጎደላቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ
ወይዘሮ መስከረም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014