ሰላም ውሎ ማደር፣ ሰርቶ መብላት፣ ለፍቶ ሃብት ማፍራት፣ ወልዶ መሳምና ማሳደግ… እነዚህና ሌሎችም የሰው ልጅ ማህበራዊ እውነቶች ተረት የሆኑባቸው፤ ወጥቶ መግባት ብርቅ፣ ያፈሩትን ንብረት በአንድ ጀንበር ማጣት እና ወልደው የከበዱበትን፣ ሰርተው ሃብት ያፈሩበትን ቀዬ ለቅቆ እንደዋዛ መፈናቀል እጣ ፈንታቸው የሆነባቸው ዜጎች ተበራክተዋል። ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያን ሳይቀሩ እንደ ሕጻን እንክብካቤ፣ እንደ አዛውንት ክብር፣ እንደ እናት ፍቅር ተነፍጓቸው በሰቀቀን ሕይወትን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን በሰሜኑ በአማራ እና አፋር፣ ምዕራብ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል አካባቢዎች ከዕለት ዕለት ቁጥራቸው እየጨመርም ይገኛል።
ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል … የሆነባቸው እነዚህ ወገኖች፤ በጥፋት ጋብቻ በተሳሰሩት የሕወሓት እና ሸኔ የሽብር ኃይሎች ሲወጉና ሲደሙ፤ ሃብት ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፤ ከሞቀ ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር ሲጋለጡ፤ በጥቃቱም ክቡር ሕይወታቸውን ሲያጡ መመልከት አሁን ላይ እየተለመደ የመጣ ይመስላል። እነዚህ ስለነገ ማሰብ ቅንጦት፤ ዛሬን አልፎ ለገን መመልከት ሕልም እየሆነባቸው የመጡ ወገኖቻችን ታዲያ ከዚህ ሰቀቀንና ችግር ለመሻገር የሁላችንንም ያልተቋረጠ እገዛ ይሻሉ።
የመጀመሪያው የእገዛችን መገለጫ ሊሆን የሚገባው እነዚህን ወገኖች በግፍ ከሚያፈናቅሏቸው፣ ከሚዘርፏቸውና ከሚገድሏቸው የሽብር ኃይሎች መታደግ ነው። እነዚህ የሽብር ቡድኖች የሽፍትነት ባህሪያቸው፣ የደም ጥማታቸው ውል ባላቸው ቁጥር ከተሸሸጉበት ጎሬና ዋሻ እየወጡ የንጹሃንን ደም ማፍሰስ፣ ንብረት መዝረፍና ማውደም፣ እንዲሁም ማፈናቀላቸው በቃ ሊባል ይገባዋል።
ለዚህ ደግሞ ትልቁ የቤት ሥራ የሚሆነው የጸጥታ ኃይሉ እና መንግሥት ላይ ሲሆን፤ የየአካባቢው ማህበረሰብም እነዚህን የሽብር ቡድኖች ያሉበትን እና እንቅስቃሴያቸውን በመከታተል ለጸጥታ ኃይሉ ተገቢውን ትብብር ማድረግ ይኖርበታል። ምክንያቱም ዛሬ ላይ አሸባሪው ሕወሓት በሰሜኑ በተለይ በአፋር ክልል፤ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በወለጋ አካባቢ በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙት ግፍና በደል ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ይገኛልና።
አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች ለወራት በነበረው የወረራ ቆይታው በኋላ በሽንፈት አካባቢውን ለቅቆ ቢወጣም፤ አሁን ላይ ዳግም የተሰጠውን የማሰቢያ ጊዜ ከመጠቀም ይልቅ ጊዜውን ለትንኮሳና ለዳግም ወረራ እያዋለው ይገኛል። በዚህም በአፋር በአብዓላ እና አካባቢዎቹ ላይ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ቤተ እምነቶችን ጨምሮ በርካታ ንብረት እንዲወድም በማድረግ ላይ ይገኛል፤ በርካታ ንጹሃንን ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጓል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያን ጭምር ተፈናቅለው ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ አድርጓል።
በተመሳሳይ በጥፋት ጋብቻ የተዛመደው የሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በወለጋ በርካታ ንጹሃንን እየገደለ፣ እያሳደደ፣ ሃብት ንብረታቸውን እየዘረፈና እያወደመ የምድር ሲዖልን እንዲኖሩ እያደረገ ይገኛል። የዚህ የሽብር ቡድን የጥፋት በትር በእናቶች፣ በሕጻናት፣ በአረጋውያንና ሌሎችም ንጹሃን ላይ ክፉ ጠባሳን አሳርፏል፤ ቤተ እምነቶች ደፍሯል፣ ሌሎች የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን አፈራርሷል። ሺዎች ከሞቀ ቀያቸው ተፈናቅለው በየጉራንጉሩ ተሸሽገው የከፋ ሕይወትን እንዲገፉ ፈርዶባቸዋል።
ታዲያ እነዚህ ሁለት የሽብር ኃይሎች በዚህ መልኩ በንጹሃን ላይ ፈርደው የጥፋት ክንዳቸውን አፈርጥመው ሲንቀሳቀሱና ንጹሃንን ኢላማ አድርገው ሲሰሩ እያየን እስከመቼ ዝም እንላለን? እስከመቼስ ሞትና መፈናቀል ለእነሱ የተሰጠ የሕይወት ዕጣ ፈንታ ሆኖ እስኪሰማቸው በቸልታ እንመለከታቸዋለን? እስከመቼስ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ የስቃይ እንባ እያነቡ የማይሽር የሕይወት ጠባሳን እያዘሉ እንዲያልፉ እንዲሆን እንፈቅዳለን? እስከመቼስ የሽብር ቡድኖች በንጹሃን ላይ በሚፈጽሙት የጥፋት በትር ሕልውናቸውን እንዲያስቀጥሉ እድል እንሰጣለን?…
በዚህ መልኩ “እስከመቼ?” ብለን ልናነሳና ልንጠይቅ የምንችላቸው በርካታ ጥያቄዎችና ጉዳዮች ሊኖሩን ይችላሉ። ነገር ግን ጥያቄም ሆነ የሃሳብ ጋጋታ ብቻውን ለእነዚህ ወገኖች ከችግራቸው ሊያሻግራቸው፤ ከሰቆቃቸው ሊያላቅቃቸው አይችልም። እነዚህን ወገኖች ከችግራቸው ሊያሻግር፤ ከሲቃ ድምጻቸው ሊያላቅቅ የሚችለው ከቃል ያለፈ ተግባር ሲገለጥና ከጫጫታ ያለፈ ጠንከር ያለ ድምጽን ማሰማት ሲቻል ብቻ ነው። በመሆኑም ስለእነዚህ ወገኖቻችን መንግሥት እንደ መንግሥት ሊወስን፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ በቃ ሊል የግድ ይላል።
ምክንያቱም ለሰው ልጅ የመጀመሪያው ጉዳይ በሕይወት መኖር ነው። እነዚህ ወገኖቻችን ግን ዛሬን ውለው ስለማደራቸው እርግጠኛ አይደሉም። ምክንያቱም ደም የጠማቸው ነፍስ ነጣቂ ተኩላዎች ዘወትር እያንዣበቡባቸው፤ በለስ ሲቀናቸውም ጥማታቸውን እያረኩ ነፍሳቸውን እየነጠቋቸው ናቸው። ሞትን ፈርተው መኖርን የናፈቁቱ ደግሞ በጠፍ ጨረቃ ከሌላ ሞት ጋር እየተጋፈጡ መሰደድ እጣፈንታቸው የሆኑትም፤ ከሞት ያልተናነሰ ሕይወትን በየሥፍራው እንዲገፉ ሆነዋል።
በመሆኑም የእነዚህን ወገኖች ደህንነት መጠበቅ፣ በሕይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብታቸው በሽብርተኞች መዳፍ ላይ እንዳይወድቅ የማድረግ የመጀመሪያውን ኃላፊነት መንግሥት ሊወጣ ይገባል። በንጹሃን ዜጎቼ ላይ የሚደርስ ግድያና መፈናቀል በቃ ሊል የግድ ይላል። ይሄን ሊያረጋግጥ የሚገባው ደግሞ በየአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች የተሰጣቸውን ግዳጅ በተገቢው ሁኔታ እንዲወጡ ማድረግ አንዱና ቀዳሚው እርምጃ ሊሆን ይችላል።
መንግሥት በዚህ መልኩ በቃ ብሎ ከወሰነ እና ተልዕኮ ሰጥቶ ካሰማራ፤ ሌላው በወገኔ ላይ የሚፈጸም ግፍና በደል በቃ ብሎ እነዚህን የጥፋት ኃይሎች አደብ ሊያስገዛና ሊያጠፋ የሚችለው የጸጥታው ኃይል ነው። ይህ ኃይል በየደረጃው እና እንደተሰጠው ኃላፊነት መጠን ወገኖቹን የመታደግ ትልቅ አደራ ያለበት አካል ነው። በመሆኑም ዛሬ በአፋርም፣ በኦሮሚያም በንጹሃን ላይ እየሆነ ያለውን ግፍና በደል መቋጫ እንዲያገኝ ማስቻል ከጸጥታው ኃይል የሚጠበቅ የወገኔ ሞትና ስደት ይብቃ የሚል ኃላፊነት መገለጫ ነው።
በዚህ ሁሉ ሂደት ግን በየአካባቢው ያለው ማህበረሰብ በወገኖቼ ላይ የሚደርስ ስቃይ ይብቃ ብሎ እነዚህን የሽብር ቡድኖች ተግባር ከማውገዝ ባለፈ፤ የቡድኖቹን እንቅስቃሴ በንቃት በመከታተልና ለጸጥታ ኃይሉ መውጫና መግቢያቸውን ማመላከት አጋዥ በመሆን የንጹሃን እህት ወንድሞቹ ሰቆቃ ማብቂያ እንዲፋጠን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
በዚህ መልኩ ሞትና ስደታቸው ይብቃ ብሎ መስራት ከተቻለ፤ ቀጣዩ የቤት ሥራ የሚሆነው አካባቢዎቹን የበለጠ ሰላም ማድረግና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደቀያቸው በመመለስ ማቋቋም፤ ማጽናናትና የሥነልቦና ስብራታቸውን መጠገን ይሆናል። በዚህ ረገድ የእነዚህን ወገኖች ሞትና መፈናቀል የማህበራዊ ሚዲያ ገበያ ማድመቂያ እና የዩቱዩብ ገቢ ማግኛ ከማድረግ ይልቅ፤ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የእለት ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይ አበርክቶ ያለው አንዳች ቁምነገር ለመስራት መረባረብም የተሻለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
እናም ሁሉም በዚህ መልኩ የወገኖቼ ሞትና መፈናቀል፣ ስደትና እንግልት በቃ ብሎ የየራሱን የቤት ሥራ ወስዶ ሲሰራ፤ በቃ ብሎ የተነሳበትን ዓላማ ማሳካት፤ የወገኖቻችንን ሰቆቃ እንዲያበቃ ማድረግ ይቻላል። ይህ እንዲሆን ሁሉም በሙሉ ልብና እምነት በወገኖቼ ላይ የሚፈጸም ሞትና ማፈናቀል በቃ ብሎ መነሳት ይኖርበታል!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014