በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተግባር ልምድ አተገባበር አናሳ መሆን ብቁ ኃይል ለማፍራት አላስቻለም

አዲስ አበባ፤– በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተግባር ልምድ አተገባበር አናሳ መሆን ብቁ ኃይል ማፍራት እንዳላስቻለ ተገለጸ፡፡

የከተማ ልማት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተከናወኑ ጥናቶች ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ በዘርፉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚወጡ ምሩቃን ከሥራ በፊት የተግባር ልምምድ የሚሰጥበት ሁኔታ ተመቻችቶ ተከታታይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። ነገር ግን አተገባበሩ ቁልፍ ክፍተቶች የሚታዩበት በመሆኑ በዘርፉ ውስጥ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲገባ ከማድረግ አኳያ መሰናክል ሆኖ ቆይቷል።

በዚህም በዘርፉ ከሀገር ተርፎ ለቀጣናው የሚበቃ ምሩቃን ቢኖሩንም በክህሎት የዳበሩ ባለመሆናቸው በርካታ የውጭ ባለሙያዎች ወደ ሀገር ወስጥ እንዲገቡ አስገድዷል። ይህንን ማነቆ መፍታት አስፈላጊ በመሆኑ ሰፊ የገበያ ጉድለት በሚታይባቸው ብሎም ግዙፍና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን መፈፀም የሚችል አቅም መፍጠር አስፈልጓል ብለዋል።

በተጨማሪ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በኮንስት ራክሽን ዘርፍ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በሚጠበቀው ደረጃ ወደ ኢንዱስትሪው በመግባት አፈጻጸሙን ሊያግዙት አልቻሉም። አብዛኛው የእውቀት፣ የሰው ኃይል ሥልጠና፣ ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ውጤቶች ከእነዚህ ተቋማት የሚቀዱ መሆናቸው ይታወቃል። ነገር ግን ሌላው ቀርቶ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገነቡ ግንባታዎችን መታደግ የሚያስችል ሥራዎችን መሥራት ተስኗቸው ለረጅም ጊዜ ግንባታዎች ሳይጠናቀቁ ታይተዋል። ይህም በዩኒቨርሲቲና በኢንዱስትሪው መካከል በሚጠበቀው ደረጃ ትስስር ላለመኖሩ አመላካች ነው።

በመሆኑም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የገበያ ጉድለት ባለባቸው መስኮች በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ መግባት። እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችን በጥናት፣ ዲዛይንና ማማከር አገልግሎት በማሳተፍ የቴክኖሎጂ አቅም እንዲዳብር ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ለዚህም ለችግሮች ልየታና አብሮ ለመሥራት ከአምስት የምርምርና የሪሰርች ዩኒቨርስቲዎች ጋር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥናት አካሂዷል። በጥናቱም የመፍትሔ ሃሳቦች የተመላከቱና ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ተጨማሪ ግብዓት ተሰጥቶባቸው ወደትግበራ የሚገቡ ይሆናል።

በየኮንስትራክሽን ዘርፍ መንግሥት ከፍተኛ በጀት የሚመደብለትና ሰፊ የግል ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት ነው። ያሉት ሚኒስትሯ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራው ከግብርናው ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር የሚይዝ በመሆኑ ድህነትን በመቀነስ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው።

በመሆኑም ግንባታዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ማድረግ፤ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት እንዲጠናቀቁና ለማድረግ በሀገሪቱ ተፈጻሚነት የሚኖረው የቁጥጥር ሥርዓት አስፈላጊ ነው። ለዚህም በዘርፉ መረጃ የመሰብሰብ፤ የመተንተንና ለውሳኔ በሚያመች መልኩ ለማቅረብ የሚያስችሉ የጥናት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You