ኤጀንሲው አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ ታግዞ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በስፋት እየሠራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ የሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ዩኒየኖች በቴክኖሎጂ ታግዘው ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በስፋት እየሠራ መሆኑን የክልሉ ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍሮምሳ አበራ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ኤጀንሲው የፋይናንስ፣ የማዳበሪያ፣ የመካናይዜሽን እና የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ድጋፎችን በማድረግ ለአርሶ-አደሩ ምርታማነት አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው፡፡

ኤጀንሲው በምርጥ ዘር አቅርቦት እና ሥርጭት እንዲሁም በገበያ ትስስርም ላይ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል 117ሺ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፤ እንዲሁም 111 ዩኒየኖች እንዳሉ ጠቅሰው፤ የአርሶ-አደሩን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የአርሶ-አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከሚደረግ ድጋፍ በተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም እንደሚሠሩ ያመለከቱት አቶ ፍሮምሳ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር እንደሚከናወንና ክትትል እንደሚደረግበትም አስረድተዋል።

በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በኩል የአርሶ-አደሩን ምርት በመሰብሰብ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቱ እየተረጋገጠ ነው፤ ከዚህ አንጻር እንደ ሰሊጥ፣ ቡና፣ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር የመሳሰሉትን ወደ ውጭ የመላክ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡

ኤጀንሲው ወደ ውጭ በላከው ምርት ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወደ መሠረታዊ ማኅበራቱ በማምጣት የትርፍ ክፍፍል የሚያደርግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የገበያ ሂደት አርሶ-አደሩ በመጀመሪያ ሽያጩ ገቢ ካገኘ፤ ወደ ውጭ ተልኮ ከሚገኘው የምንዛሪ ገቢ የትርፍ ክፍፍል እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የአርሶ-አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ የሚያግዙ ተግባራት ሁሉ ይከናወናሉ ያሉት አቶ ፍሮምሳ፤ ምርቱን በወቅቱ ለመሰብሰብ እንዲችል የኮምባይነር እና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግለት ገልጸዋል፡፡ የአርሶ-አደሩ የፋይናንስ ጥያቄ እንዲመለስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እና ከሌሎች ባንኮች ጋር በትብብር እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

ከገበያ ትስስር አንጻር፤ ወደ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ እና ወደ ሌሎችም ምርቱ የሚፈለግባቸው ክልሎች እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት፤ ዩኒየኖች እና ከተለያዩ ሸማቾች ጋር ጠበቅ ያለ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ትስስር በማድረግ ኤጀንሲው አስፈላጊ የግብርና ምርቶችን እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በገበያ ትሰስሩ ዋነኛ ተጠቃሚው አርሶ-አደሩ መሆኑንም አመልክተዋል። አርሶ-አደሩ የልፋቱንና የሠራበትን የድካሙን ዋጋ እንዲያገኝ ሲደረግ የማምረት አቅሙም በዚያው ልክ ያድጋል ብለዋል፡፡

በክልሉ 21 ዞኖች ምርት ሳይበላሽ ለማቆየት የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉላቸው ዘመናዊ መጋዘኖች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ ምርት ከአርሶ-አደሩ በስፋት እየተሰበሰበ መሆኑን አመልክተዋል። እንደ ጅማ፣ ኢሉአባቦር እና ቡና በስፋት በሚመረትባቸው ቦታዎች ምርቱ ተሰብስቦ ወደ ማዕከላዊ መጋዘን መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ቡና አምራች ዩኒየን ቡናን ፈጭቶ እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ እየላከ መሆኑንም ገልፀው፤ እሴት ከመጨመር አኳያ ደረጃቸውን የጠበቁ ስድስት የዱቄት ፋብሪካዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You