በቅዱስ ላሊበላ የተከበረው የልደት በዓል በቀጣይ በክልሉ ለሚከበሩ በዓላት መነቃቃት የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፡- በላሊበላ የተከበረው የልደት በዓል በቀጣይ በክልሉ ለሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት መነቃቃትን የሚፈጥር እንደሆነ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ በክልሉ የሚከበሩ በዓላት ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበሩ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ጥሪ አቀረበ፡፡

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ዘንድሮ በላሊበላ የተከበረው የልደት በዓል ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ መልኩ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እና ምዕመናን በተገኙበት በሰላማዊ መንገድ በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ ከሚጠበቀው በላይ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የታደሙበት እንደነበር ያመለከቱት አቶ ዓባይ፤ በሰላምና በድምቀት መከበሩ በክልሉ ለሚከበሩ ሌሎች በዓላት መነቃቃት የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር መከበሩ ማኅበረሰቡ የሰላም ባለቤት መሆኑን እንዲሁም በክልሉ የሰላም ስጋት እንደሌለ ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል ።

በቀጣይም በክልሉ በርከት ያሉ የአደባባይ በዓላት እንደሚከበሩ የተናገሩት አቶ ዓባይ የጥምቀትና ቃና ዘገሊላ በዓላት፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል፣ አስተሪዮ፣ የጊዮን በዓል እንዲሁም የመርቆሪዎስ በዓላት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል። የልደት በዓል በድምቀትና በሰላማዊ ሁኔታ መከበሩ ቀጣዮቹ በዓላትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲከበሩ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በዘንድሮው የገና በዓል በላሊበላ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ታድመዋል፡፡ በዓሉም የአካባቢው ማኅበረሰብ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የፀጥታ አካላት በቅንጅት በመሥራታቸው ሰላማዊ በሆነ መልኩ መከበሩን አስታውቀዋል፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብ ቱሪዝምን የገቢ ምንጭ አድርጎ የሚንቀሳቀስ መሆኑን የገለጹት አቶ ዓባይ፤ በዓሉ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አኳያም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት እንደፈጠረም ተናግረዋል። በዚህም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አገልግሎት ሰጭ አካላት ባለፉት ዓመታት አጥተውት የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማግኘት እንዲችሉ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡

በላሊበላ የልደት በዓል አከባበር ባለፉት ዓመታት ከተከሰተው የሰላም እጦት ጋር ተያይዞ ጥሩ ድባብ እንዳልነበረው የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በዘንድሮው ዓመት ግን ከፍተኛ ምዕመናን እና ጎብኚዎች በተገኙበት ተከብሯል፡፡ በዓሉ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ትውፊቱ እንዲጠበቅና ቅርሱም ለትውልድ እንዲተላለፍ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዓሉ ካለፈው ዓመት የበለጠ እንግዳ የተገኘበት፤ በታቀደው መሠረትም በስኬት የተጠናቀቀ መሆኑ በክልሉ ቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረው፤ በቀጣይም በክልሉ የሚከበሩ በዓላት ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበሩ ማኅበረሰቡ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት አቶ ዓባይ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You