ስለ ኑሮ ውድነት መነገር ከጀመረና ችግሩም ስር እየሰደደ ጫናው ከበረታ ጊዜያቶች ተቆጥረዋል። የዘርፉ ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ምክንያቶችን በማንሳት የመፍትሄ ሃሳቦችን ቢጠቁምም፣ መንግሥትም ለውጥ ያመጣል ያላቸውን አማራጭ እርምጃዎችን ቢወስድም የኑሮ ውድነቱ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መሄዱን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል።
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ እስካሁንም ያልተወገደው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ለዓለም ኢኮኖሚ መዳከም አንዱ ተግዳሮት በመሆኑ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል። ኢትዮጵያም የዚሁ ወረርሽኝ ሰለባ በመሆኗ ኢኮኖሚያቸው ከተጎዳባቸው የዓለም አገራት አንዷ ሆና ትጠቀሳለች። ጫናውን ለመቋቋም መንግሥት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል።
ይሁን እንጂ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በአሸባሪው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ(ሕወሓት) የተከፈተው ጦርነት ለኢኮኖሚው መዳከምና ለኑሮ ውድነቱ ተጽዕኖው ከፍተኛ እንደሆነ አይዘነጋም።
ከዚህ በተጨማሪ ምዕራባውያኑ በአገሪቱ ላይ በተለያየ መንገድ ባደረሱት ጫናዎች ምክንያት ፖለቲካል ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖው በርትቷል። በነዚህ ምክንያቶች የተንገራገጨውን ኢኮኖሚ መንግሥት መልሶ በመገንባት ማነቃቃት ያስችለኛል ያላቸውን የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም እየሠራ ይገኛል። ከሰራቸው ሥራዎች መካከልም በጦርነቱ ምክንያት የተዳከመውን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት የመደበው ተጨማሪ 122 ቢሊዮን ብር በጀት ይጠቀሳል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የፀደቀው ተጨማሪ በጀት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚኖረው ፋይዳ እንደምን ያለ ነው? ስንል ላነሳነው ጥያቄ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ዳዊት ወይሶ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
መንግሥት አጠቃላይ የሚያስፈልገውን ገቢ ብድሮችን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የሚሰበስብ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት መንግሥት ቀድሞ መሰብሰብ ያለበትና ከተለያዩ ቦታዎች ተሰብስቦ መምጣት ያለበት የመንግሥት በጀት በሁለት ምክንያቶች ያልሰበሰበበትና ቅናሽ ያሳየበት እንዲሁም በእጅጉ የተጎዳበት ሁኔታ ስለመኖሩ አስረድተዋል።
ከእነዚህ ሁለት ምክንያቶች አንዱም በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በትግራይና በአማራ ክልሎች መሰብሰብ የነበረበት ግብር በተገቢው መንገድና በተፈለገው ጊዜ መሰብሰብ አልተቻለም።
ሁለተኛ ከውጭ የሚመጡ እርዳታዎች የቀነሱበትና የተቋረጡበት ሁኔታ የነበረ መሆኑን በመጠቆም በተለይም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙ ብድሮች በአንድም በሌላ ምክንያት መቋረጡንና ይህም በአንድ በኩል የመንግሥትን ገቢ የቀነሰ ሲሆን በተመሳሳይ ደግሞ የመንግሥት ወጪ የጨመረበትን ሁኔታ የፈጠረ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
‹‹ወጪ የጨመረው ጦርነት በሚጠይቀው ፋይናንስ እንዲሁም ከጦርነት ጋር ታያይዞ በጦርነቱ አካባቢ መንግሥት መሥራት ባለበት የመልሶ ግንባታና ወጪ የጨመረበት ሁኔታ ነው ያለው›› ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ድርቅና የተለያዩ የጸጥታ ችግሮች የመንግሥትን የፍጆታ መጠን የሚፈልግ መሆኑን በማስረዳት በአሁኑ ወቅት 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማጽደቅ አስገዳጅ እንደሆነም ይናገራሉ ።
የጸደቀው ተጨማሪ በጀት ከአስገዳጅነቱ ባለፈ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው በጀቱ በኢኮኖሚው ውስጥ ለሚኖረው ፋይዳና እንዴት ፋይናንስ ይደረጋል ፍሬሕይወት አወቀ የሚለው ዋናውና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ። መንግሥት እነዚህን ሁለት ነጥቦች በሚገባና በጥንቃቄ ማየት እንዳለበት ጠቁመዋል። በቀዳሚነት በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ከምርትና ምርታማነት በላይ ኢኮኖሚ ውስጥ የተረጨው ገንዘብ ለኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል።
ስለዚህ ወደ ኢኮኖሚው የሚረጨው ገንዘብ በጥንቃቄ ካልተመራ በአገሪቱ እየተባባሰ ያለውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ የሚያንረው በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻዋል ብለዋል። መንግሥት በአሁኑ ወቅት ያጸደቀው 122 ቢሊዮን ብር ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ለመከላከያ የሚውል መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዳዊት፤ መከላከያን መገንባት ደግሞ ቁልፍ ጉዳይ ነው መሆኑን ያስረዳሉ።
ይህም አገሪቷ ጠንካራ የሆነ ሠራዊት መገንባት እንድትችል ያደርጋታል። ነገር ግን አብዛኛው በጀት ወደ ኢኮኖሚው የሚገባ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ሀብቱ ኢኮኖሚውን መልሶ ከመገንባት አንጻር የተወሰነ አሉታዊ ተጽዕኖን የሚያሳድር ይሆናል።
አብዛኛው በጀት ወደ ምርትና ምርታማነት የሚገባ ባለመሆኑና መልሶ ግንባታ ላይ የሚውለው ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ በተፈለገው መጠን ኢኮኖሚውን ላያጠናክር ይችላል። ስለዚህ መንግሥት የግሉን ዘርፍ በማይጎዳ መንገድ በጥንቃቄ ማየት ያለበት ተጨማሪውን በጀት እንዴት ፋይናንስ ማድረግ እንዳለበት ነው። ለዚህም የተለያዩ መንገዶችን ለመጠቀም ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።
በተለይም በሚወስዳቸው እርምጃዎች የበለጠ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና ተጨማሪውን በጀትም ምርታማነት ላይ በማዋል የተጎዳው ኢኮኖሚ መልሶ ማገገም እንዲችል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አለበት። ኢኮኖሚው በቶሎ ማገገም እንዲችል ፋይናንስ ከማድረግ አንጻር በተቻለ መጠን ከውጭ እርዳታ የሚገኝ ቢሆን የተሻለ ነው ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ የውጭ ግንኙነቶችን በማጠናከር ፋይናንሱን ከውጭ በብድር ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ማሳካት ከተቻለም ሁለት ዋና ዋና ጥቅሞችን ማትረፍ የሚቻል መሆኑን ያስረዳሉ።
አንደኛ አገር ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን የገንዘብ ጭማሪ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ስለዚህ ፋይናንሱ ከውጭ የሚገኝበትን ማንኛውንም ዕድሎች አሟጦ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል::
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ምዕራባውያኑ ብድር ላይሰጡ የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሚኖር ጠቁመው ነገር ግን ኢትዮጵያ መልካም ፖለቲካዊ ግንኙነት ካላት እንደ ቻይና፣ ህንድና መሰል አገራት መጠቀም ትችላለች። እነዚህ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ካላቸው መልካም ግንኙነት የተነሳ ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› በማለት ማበደር የሚችሉ በመሆናቸው ፖለቲካል ኢኮኖሚውን በማጠናከር ከአገራቱ ጋር በትብብር መሥራት የሚያስፈልግ ነው ይላሉ።
መንግሥት ካጸደቀው ተጨማሪ በጀት ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ለመከላከያ ሠራዊት የሚያውል ቢሆንም በተወሰነ መንገድ ወደ ካፒታል ዘርፍ ላይ እንዲውል ማድረግ የተጎዳውን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት ያስችላልና ቢታሰብ መልካም ነው ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ ከዚህም ባለፈ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሚያስችል መልኩ ምርትና ምርታማነት ላይ በስፋት መሥራት ጠቃሚ እንደሆነም አመላክተዋል። ጦርነት የተከሰተበት ማንኛውም አገር በተለይም የመጀመሪያዎቹ አንድ ሶስት ወራት ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበትና ምርትና ምርታማነት የሚቀዛቀዝበት ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑ የሚታወቅ መሆኑን ዶክተር ዳዊት ይጠቅሳሉ። በአገሪቱ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነትም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያደረሰ በመሆኑና ኢኮኖሚውን መልሶ ለመገንባትም እስከ አምስት ዓመት ሊፈጅበት እንደሚችል ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢኮኖሚው ሊያገግም የሚችልበትን ዓመት በማሳጠር አምስት ዓመት የሚፈጅ ከሆነ እስከ አንድና ሁለት ዓመት እንዲያገግም ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በጦርነት የተጎዳን ኢኮኖሚ ማገገም እንዲችል በሚደረገው ጥረት ውስጥም እያንዳንዱ ዜጋ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ያነሱት ዶክተር ዳዊት፤ የመልሶ ግንባታ ሥራው በመንግሥት ብቻ የሚቻል አይደለም።
መንግሥት መልሶ ለመገንባት የሚጠይቀው በጀት ትልቅ ነው። ይህን ትልቅ በጀት ለማግኘት በሚደረገው ጥረት የሚኖሩ መንገዶች ሁሉ ጤናማ ሊሆን የግድ ነው። ነገር ግን ጤናማ በሆነ መንገድ መጓዝ ካልተቻለ ይህም ሌላ ችግር ይወልድና ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› አይነት ችግር እንዳይገጥም ጥንቃቄን ማድረግን ይጠይቃል።
ስለዚህ በቀዳሚነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለጦርነቱ እንደተረባረበው ሁሉ መልሶ ግንባታው ላይም የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የማንንም ግፊት መጠበቅ ሳያስፈልገው ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በአንድም በሌላ የተዳከመው ኢኮኖሚ በአጭር ጊዞ ሊያገግም ይችለል። ‹‹50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለ50 ሰው ጌጡ ነው›› እንደተባለው፤ እያንዳንዱ ማሕበረሰብ ሊተባበር ይገባል።
በተለይም የማሕበረሰቡ መገልገያ የሆኑ የጤና ተቋማት፣ ትምህር ቤቶችና መሰል የማሕበራዊ ተቋማትን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶ በመገንባት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ከመንግሥት ባለፈ የእያንዳንዱን ዜጋ ርብርብ የሚጠይቅ ነው። እዚህ ላይ በአገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶችና በተለይም በውጭ አገር የሚኖረው ዲያስፖራ ትናንት ለሉዓላዊነቱ ያደረገውን ርብርብ አሁንም የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ከመገንባት አንጻር ሰፊ ጥረት በማድረግ በመልሶ ግንባታው ላይ አሻራውን ሊያኖር ይገባዋል። በተለይም ጦርነቱ የተካሄደባቸውና በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች አምና በበቂ ሁኔታ ማምረት ስላልቻሉ ረሃብ ይከሰታል ተብሎ ይታሰባል።
ስለዚህ መንግሥት የሚመጣውን ጉዳት ከወዲሁ ገምቶ መዘጋጀትና እፎይታን የሚሰጡ የተለያዩ ዕርዳታዎችን አሰባስቦ መጠባበቅ ይኖርበታል። አርሶ አደሩ መመገብ ከቻለና ጤናው ከተጠበቀ ጤናማ ሆኖ ለቀጣዩ ጊዜ ማምረት እንዲችል ዛሬ ላይ ጤናው እንዲጠበቅና በምግብ እንዳይጎዳ ማድረግ የግድ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ከመንግሥት ጎን በመሆን ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በጋራ መሥራት ይጠበቅበታል ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ ጎን ለጎንም ጦርነት አካባቢ ያለው ማሕበረሰብ ከፍተኛ የሆነ የሥነልቦና ጉዳት የደረሰበትና የራሱ የሆነ ጭንቀት የሚፈጥርበት በመሆኑ መልሶ ለመገንባትና በቀጣይም ማምረት እንዲችል የሥነልቦና ድጋፍ ያስፈልገዋል። ይህንንም ጎን ለጎን መሥራት ይገባል በማለት ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014