
– ህብረተሰቡ ወንጀሎችን በመከላከል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው
አዲስ አበባ፡– ባለፉት 11 ወራት በከተማዋ በተደረጉ የክትትል ሥራዎች ያለአግባብ ምርቶችን ሲያከማቹ በነበሩ ዘጠኝ ሺህ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ የከተማዋን የሰላምና ፀጥታ የ 11 ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና ውይይት ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት ፤ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡባት ከተማ ለመፍጠር በሚሠሩ ሥራዎች የሰላም ሠራዊት አደረጃጀት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። ባለፉት 11 ወራት በከተማዋ በተደረጉ የክትትል ሥራዎች ያለአግባብ ምርቶችን ሲያከማቹ በነበሩ ዘጠኝ ሺህ የንግድ ተቋማት ላይ ርምጃ ተወስዷል።
ባለፉት 11 ወራት 32 ሺህ አዲስ የሰላም ሠራዊት መልምሎ ማሠልጠን መቻሉን አመልክተው፤ በዚህም መልካቸውን እየቀያየሩ የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል በተደረገው ጥረት የወንጀል ምጣኔ 43 በመቶ ቀንሷል ሲሉ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ አደረጃጀት ቢሮ ኃላፊ ፍሬህይወት ለማ (ዶ/ር)፤ ባለፉት 11 ወራት ባቀረቡት ሪፖርት፤ ሰላምን የማስጠበቅና ሕግን ለማስከበር የተሠሩ ሥራዎች ሕዝቡን ያሳተፉ መሆናቸው እቅዱን ለማሳካት አስችሏል ብለዋል።
እንደ ፍሬህይወት (ዶ/ር) ገለጻ፤ ርምጃ የተወሰደባቸው የንግድ ተቋማት የተለያዩ የሸቀጣሸቀጥ ምርቶችን በመደበቅ እና መጋዘን ውስጥ በማከማቸት ሀሰተኛ የምርት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት እንዲኖር ያደረጉ ናቸው። እነዚህን እና ሌሎች መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል በተለያየ ጊዜ ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች እና ህብረተሰቡ ሰላሙን ለማስጠበቅ የባለቤትነት ድርሻውን እንዲወስድ በመደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የከተማዋን የሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ ረገድ በከተማዋ የሚገኙ 41 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማቆያ ማዕከላት እና ወደ ክልሎች የመመለስ ሥራ መሠራቱንም ፍሬህይወት (ዶ/ር) ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ በጎዳና ላይ የምናያቸው ዜጎች ወጣቶችና መሥራት የሚችሉ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ ባለፉት 11 ወራት ወደ 42 ሺህ የሚጠጉት የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ማቆያ ማዕከላት እንዲገቡና ቀሪዎች በክልሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የተለያዩ ሥልጠዎችን በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የሰላም ሠራዊት አባላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ስለ ከተማዋ ወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም