
አዲስ አበባ፡– ባለፉት አምስት ዓመታት የሕግ ባለሙያዎችን አቅም የሚያሳድጉና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ከ10ሺህ ለሚበልጡ ዳኞችን እና አቃቤ ሕጎችም ሥልጠና መሰጠቱን የሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ገለጸ። በሕጉ ዘርፍ ትልቅ እምርታ የሚያመጣ የዲጂታል ሥርዓት ይፋ መሆኑን የሕግ እና ፍትህ ኢንስቲትዩት አመልክቷል።
የሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ80 የሚበልጡ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን አካሂዷል፤ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ዳኞች እና አቃቤ ሕጎችም ሥልጠና ሰጥቷል ብለዋል።
ኢንስትቲዩቱ የአቅም ግንባታ እና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት አምባሳደር ደግፌ፤ ሥልጠናዎች እንደ ዳኞችና ጠበቆች ያሉ የሕግ ተዋንያንን ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ይፋ የተደረገው የዲጂታል ኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ለባለሙያዎች ሥልጠናዎችን በያሉበት እንዲደርሳቸው በማድረግ የሕግ ዘርፉ ላይ ትልቅ እምርታ ሊያመጣ የሚችል እንደሆነም ገልጸዋል። እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ከዚህ በፊት ሲሰጡ የነበሩ ሥልጠናዎች የሠልጣኞችን በአካል መገኘት የሚፈልጉ በመሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጊዜ እና ወጪን የሚያስወጡ ናቸው። አሁን ላይ ይፋ የተደረገው የዲጂታል ኤሌክትሮኒክስ መተግበሪያ ሠልጣኞች በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው በያሉበት ሥልጠናውን ማግኘት ይችላሉ። ሥልጠናውንም በብቃት ሲያጠናቅቁ በመተግበሪያው ፈተናዎችን በመውሰድ ሰርተፍኬቱን ባሉበት ማግኘት ይችላሉ።
ሥርዓቱን ተጠቅመው ሥልጠናን የሚወስዱ ባለሙያዎች ተመሳሳይ እውቀት እና ወጥነት ያለው ፍርድ ለመስጠት የሚስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ፍትህ ሚኒስቴር ለህብረተሰቡ ትምህርት የሚሰጠው በአካል ለተገኙ በብቻ መሆኑን የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ይፋ በተደረገው ሥርዓት ግን በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን ከማብቃት ባለፈ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ሌሎች ተቋማትም ተመሳሳይ ሥርዓቶችን ቢዘረጉ በየዘርፋቸው ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ (ዶ/ር) ኤርሜያስ የማነብርሃን እንደገለጹት፤ ሥርዓቱ የሕጉን ዘርፍ በላቀ መልኩ ግልፅና ተደራሽ ለማድረግ ይረዳልም ብለዋል።
ለሕጉ ዘርፍ አካላት ብሎም የህብረተሰቡን የንቃተ ሕግ በትምህርትና ሥልጠና ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ በዚህም ፍትሃዊና ዘመናዊ የሕግ አገልግሎት በመስጠት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሕግ እና ፍትህ ኢንስቲትዩት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጀርመን ልማት ድርጅት ጂአይዜድ እና የአውሮፓ ህብረት በጋራ እውን ያደረጉት እንደሆነ ታውቋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም