ባለሥልጣኑ ሕገ ወጥ ግንባታ በፈጸሙ ከሶስት ሺህ 195 በላይ ሰዎች ላይ ርምጃ ወስዷል

አዲስ አበባ፡– ባለፉት 10 ወራት ሕገ ወጥ ግንባታ በፈጸሙ ሶስት ሺህ 195 ሰዎች በላይ ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ትናንት በተቋሙ የ 10 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የሚስተዋሉ ደንብ መተላለፎችን መከላከል ሚያስችል ጠንካራ የማስፈጸም አቅም ለመገንባት እሠራ ነው። በዚህም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በከተማዋ የሚፈጸሙ የደንብ መተላለፎችን 64 በመቶ መቀነስ ተችሏል።

ባለሥልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ሕገ ወጥ ግንባታ በፈጸሙ ሶስት ሺህ 195 ሰዎች፣ በ32 ሺህ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች፣ በአንድ ሺህ 121 ሕገ ወጥ የእንስሳት አዘዋዋሪዎች፣ ከ100 ሺህ በላይ ሕገወጥ ማስታወቂያዎች እና በተለያዩ አዋኪ ድርጊቶች የተሳተፉ ከአራት ሺህ በላይ ተግባራት ላይ ርምጃ መወሰዱንም አመላክተዋል።

ተቋሙ በሁሉም መስክ የማስፈጸም አቅሙን ለማሳደግ እየሠራ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በዚህም ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን የመቀነስ፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ተግባራትን የመከላከል ሥራ ተሠርቷል። የሰው ኃይሉን አቅም ለማሳደግም ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶችን በመመልመል እያሠለጠነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ደንብ መተላለፍን ለመከላከል ማህበረሰቡን ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አላካት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የዕቅድና የበጀት ዳይሬክተር ኮሎኔል አድማሱ ተክሌ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ በሠራቸው ሥራዎች የወንዝ ዳርቻዎች ጽዱ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ የደንብ መተላለፍ ቅድመ መከላከል ሥራና መተላለፎች ሲስተዋሉም ቅጣት የማስተላለፍ ርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመው፤ ባለፉት 10 ወራት ከደንብ መተላለፍ ቅጣት 361 ሚሊዮን 631 ሺህ 368 ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል። ከገቢው የኮሪዶር ልማትና የወንዝ ዳርቻ የደንብ መተላለፍ ቅጣት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝም ጠቅሰዋል።

ባለሥልጣኑ ደንብ መተላለፍን ከመከላከል ባሻገር በተለያዩ የበጎ አድራጐት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ 17 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለአቅመ ደካሞች ቤት የመገንባት፣ ማዕድ የማጋራትና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ መሠራቱ ተመላክቷል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You