
አንዳንድ ከሚያጋብሱት ጥቅም ውጭ የወገናቸው ጤናና ሕይወት ግድ የማይሰጣቸው አረመኔ ሰላቢዎች የወተት እና መሰል ምርቶችን የቆይታ ጊዜያቸውን እና መጠናቸውን ለመጨመር ሲሉ የሞተ እንስሳን ወይም የአስክሬን ማድረቂያ ፎርማሊን እንደሚጨምሩ፤በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የምግብ ኢንስፔክሽን እና ህግ ማስፈፀም ሥራ አስፈፃሚ ሙላት ተስፋዬ ሰሞኑን መግለጻቸው ሸማቹን ያስደነገጠ ነው።
ፎርማሊን ፎርማለዳይድ የያዘ ኬሚካል ነው። በላቦራቶሪ እና በሕክምና ቦታዎች ውስጥ ሬሳዎችን ለማቆየት ጥቅም ላይ ይውላል።አንዳንድ ስነ ምግባር የጎደላቸው (ነጋዴ የሚለው መጠሪያ ስለማይገባቸው ነው፤)ወተቱን ሳይበላሽ ለማቆየትና መጠኑን ለማብዛት ይጠቀሙበታል ።ይህ መርዛማ እና አደገኛ ኬሚካል የጤና ጠንቅ ከመሆን ባሻገር የግድያ ሙከራ ነው።ፎርማሊን የያዘ ወተት መጠጣት የአፍ፣ የጉሮሮ እና የሆድ ድርቀትና ቁስለት ከማስከተሉ ባሻገር ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና የሆድ ህመም ያስከትላል።የመተንፈስ ችግር እና ሳል ከማስከተሉ በላይ፤ኩላሊትንና ጉበትን የመሰሉ የሰውነት ክፍሎች ጭራሽ ሥራ ሊያቁሙና ለሞት ሊዳርግ ይችላል።የነርቭ ስርዓት ሊያዛበና ለካንሰር ሊዳርግ ይችላል።
በተለይ በህጻናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው።የአእምሮ እድገታቸውን እና የእውቀት (ኮግኒቲቭ) እድገታቸውን ያስተጓጉላል።እንዲሁም የመማር፣ የምግብ መፈጨት ችግሮችን እና የበሽታ መከላከል አቅም ያዳክማል።ሌላው የሸማቾችን እምነት ይጎዳል።በወተት ላይ እምነት እንዳይኖር ስለሚያደርግ ስነ ምግባር ያላቸውን ነጋዴዎችና አምራቾች አክስሮ ከገበያ ሊያስወጣ ይችላል።
ሸማቾች ወተት ሕጋዊ ፈቃድ አድራሻ ካላቸው ከታመኑ እና አስተማማኝ ከሆኑ ምንጮች እንጂ በየቤቱ በጀሪካን ከሚያዞር ከመግዛት መቆጠብ አለባቸው።ትክክለኛ ማሸጊያ፣ መለያ እና የማብቂያ ቀናትን አረጋግጦ መግዛት ይመከራል።ሰውነትዎ ንጹህ፣ደህንነቱ የተጠበቀ እና ተፈጥሯዊ አመጋገብ ይገባዋል።በተረፈ ይጠንቀቁ፣ይጠይቁ፣ቤተሰብዎን እንደ ፎርማሊን ካሉ አደገኛ ኬሚካሎች ይጠብቁ።ከጠረጠሩ ሪፖርት ያድርጉ።የእርስዎን ጤናና ሕይወት ብቻ አይደለም የሚታደጉት የማህበረሰብዎን ጭምር እንጂ።
በምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 11/2011 ላይ ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት መከለስ፣ ደረጃውን የማያሟላ ማድረግና በሰው ጤና ላይ ጉዳት ማድረስ፣ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና በብር 500 ሺ ያስቀጣል፤ በሰው ላይ ሞት ካስከተለ ደግሞ በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር ከ30ሺ እስከ 400ሺ ብር ቅጣት ተቀምጧል:: እንዲሁም የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እንደሚያመለክተው፤ በምግብ ላይ ባዕድ ነገር መጨመር እንደስፋቱና እንዳደረሰው ጉዳት አይነት ቅጣት ተጥሎበታል። ከዚያ ያለፈ ችግር ካደረሰም በወንጀል ህጉም እንዲታይ እድል ሰጥቷል:: ሆኖም የማስፈጸም ችግር ስላለ አደጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል::
መቼም የሶስቱ አብርሃማዊ ተከታይ በሆነች ሀገር እነዚህ ጨካኞች የኦርቶዶክስ፣የእስልምና፣የካቶሊክ አልያም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ናቸውና ታላላቁ መጽሐፍት ማለትም ቅዱስ ቁራኑና መጽሐፍ ቅዱሱ ምን ይላሉ።
“አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል።
ምሳሌ 11፥1
“ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!”
ኢሳይያስ 5፥20
“እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።”
1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31፤
ቅዱስ ቁራን ደግሞ፦
ሱራ 83÷1-3
“ለሰላቢዎች ወዮላቸው::”ይለናል።
ከጥንት ጀምሮ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ምግብን ከሌሎች ነገሮች ጋር መደባለቅ የተለመደ ተግባር ሆኖ ቆይቷል:: በተለይም ነጋዴዎች በትንሽ ወጪ ብዙ ትርፍ የማግኘት ዓላማ በመያዝ ውኃን ከወይን ጋር መደባለቅ፣ ከወተት ውስጥ ቅቤውን በማውጣትና ከውኃ ጋር በመደባለቅ መሸጥ የመሳሰሉት ተግባራት ከጥንታዊ የሮማውን ሥልጣኔ ጀምሮ ሲታይ የቆየ ተግባር እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተለይ በሀገራችን ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መደባለቅ በብዛት እየተስተዋለ ያለ ተግባር ነው::
የሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችም መሰል ተግባራትን በብዛት ሲዘግቡ ይስተዋላል:: በተለይም በርበሬን ከሸክላ ጋር፣ እንጀራን ከጀሶ፣ ሰጋቱራን ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር፣ ዘይት፣ ቅቤ፣ ማርና የመሳሰሉትን ምግብ ነክ ምርቶች ካልተገቡ ባዕድ ነገሮች ጋር መደባለቅን የመሰሉ ተግባራት ሲፈጽሙ የቆዩ አካላትና ተግባሩ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ዕቃዎች ጭምር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሰፊ ሽፋን ሲሰጡ ይስተዋላል:: ታዲያ እነዚህ የተያዙ ግለሰቦችና ንብረቶች በሕግ ፊት የሚዳኙት በምን አግባብ ነው? በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕጎች ምን ይላሉ? አተገባበሩስ? የምግብ ደኅንነት በጠቅላላው፦
ምግብ ደኅንነት ላይ የሚሰጠው ትኩረት በማደግ ላይ ባለ የሰው ልጆች ፍላጎት ውስጥ እየተከሰተ ነው:: ክርስቲያን ኤለንና ፍሬንዝ የተባሉ አጥኝዎች ‹‹ኒውትሬሽን ፉድ ሴፍቲ ኤንድ ኮንስዩመር›› (አመጋገብ የምግብ ደኅንነትና የሸማቾች ጥበቃ) በተሰኘው ጥናታቸው እንዳረጋገጡት በዓለማችን 852 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከምግብ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች በተለይም ጥራቱንና ደረጃውን ያልጠበቀ ምግብ በመመገብ፣ ከምግብ ንጥረ ነገሮች ጋር የተገናኙ ችግሮች፣ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ችግሮች ተዳርገው እንደሚገኙ ያመላክታሉ::
በዚህም የተነሳ በርካቶች በተለይም ከሳህራ በታች ባሉ ሀገሮች ቀደም ሲል ባልተለመደ ሁኔታ እንደ ካንሰር፣ ኮሌስትሮል፣ ኩላሊት፣ ደም ግፊትና የመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየተጠቁ ይገኛሉ:: ለዚህም በዋነኛነት እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ ምግቦች ይገኙበታል::
እዚህ ጋር ሊታይ የሚገባው ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ ምን ማለት ነው? ሙሉ ለሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብስ አለ ወይ? የሚለውን ነው:: ምግብን በጠቅላላው ደኅንነቱ የተጠበቀ (ሴፍ) ነው ብሎ መናገር አስቸጋሪ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጥናቶች ያሳያሉ:: ጆርናል ኦፍ ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የተሰኘው መጽሔት ‹‹ፉድ ሴፍቲ ኤንድ ናቹራል ኳሊቲ ፎር ዘ ፐሪቬንሽን ኦፍ ነን ኮሚዩኒኬብል ዲዝዝስ›› በተሰኘው ጽሑፉ እንዳስነበበው፣ ሙሉ ለሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ (ሴፍ) ምግብ አለ ብሎ መደምደም አስቸጋሪ እንደሆነ ያስቀምጣል:: ይልቁኑ በተወሰነ ሁኔታና ጊዜ ውስጥ የቀረበው ምግብ ከብክለት የፀዳ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ማጣራቱ የተሻለ እንደሆነ የዘርፉ አጥኝዎች ያሳስባሉ::
የምግብ ደረጃ፦
የምግብ ደረጃ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ በመንግሥት ወይም በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚጣልና ሸማቹ ኅብረተሰብ ላይ ከምግብ ብክለት ወይም ጥራት ጉድለት መነሻነት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ቀድሞ ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውል የአሠራር ሥርዓት ነው:: የምግብ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ዋነኛ ጠቀሜታ በተለይ ተጠቃሚው ከገበያ በሚጠቀማቸው ምግብ ነክ ምርቶች ላይ መተማመን እንዲኖረውና በምግብ ማምረት፣ ማስቀመጥና ማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ፣ ነጋዴዎችና ድርጅቶች እነዚህን አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች አሟልተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑና የተባለውን አስገዳጅ ደረጃ የማያሟሉ አካላት ላይ ተገቢውን የዕርምት ርምጃ ለመውሰድ ያስችላል::
በኢትዮጵያ አስገዳጅ የምግብ ደረጃ የመስጠት ኃላፊነትና ሥልጣን ለኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን የተሰጠ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት 1970 ዓ.ም. ጀምሮ ለምግብ ነክና ለሌሎችም ምርቶች አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የማውጣት፣ የካሊብሬሽን ሥራዎች፣ የጥራት ቁጥጥር፣ የላቦራቶሪ ፍተሻና የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት የመስጠትና መሰል ሥራዎችን እንዲሠራ ተልዕኮ በመያዝ፣ በአሁኑ ወቅት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል::
ይሁንና በተለይ ከምግብ ነክ ምርቶች ጋር ተያይዞ የሚሰጡ አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በምግብነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን ችላ ያለ እንደነበር በተለይ ቀደም ሲል በዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ:: ይልቁንም እንደ እንጀራ፣ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቅቤና የመሳሰሉ በማኅበረሰባችን ዘንድ በስፋት ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ሳይወጣላቸው የቆዩ በመሆኑ፣ ከመሰል የምግብ ዓይነቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የጥራትና ተያያዥ ችግሮችን በሕግ አግባብ እልባት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት በአሉታዊ መልኩ ተፅዕኖ ሲያሳርፍበት ቆይቷል::
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰል ችግሮችን ለመፍታት በጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን እንጀራን ለመሰሉ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የምግብ ምርቶች ላይ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የመስጠት ሥራ የተሠራ ቢሆንም፣ ከቅንጅታዊ አሠራርና ሌሎች ወደ ኋላ በስፋት በምንመለከታቸው ምክንያቶች የተነሳ ከምግብ ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥፋቶችን በሕግ አግባብ የማረም ሥራ ውጤታማ መሆን ሳይቻል ዘልቋል::
ሕጎቻችን፦
የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነድን ጨምሮ የሀገራችን ሕገ መንግሥትና ሌሎች ትላልቅ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የሰው ልጅ የሰብዓዊ መብት ዝርዝር ውስጥ ምግብ የማግኘት መብትን አካተው ይገኛሉ:: የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ በግልጽ መንግሥት የሀገሪቱ መዋዕለ ነዋይ በፈቀደው መጠን ለዜጎቹ ምግብንና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት የሚያስችለው ፖሊሲ ቀርጾ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አስቀምጦ ይገኛል::
ይሁንና ምግብ የማግኘት መብት ካለ ጤንነት መብት ብቻውን ሙሉ ሊሆን አይችልምና ምግብ ከማግኘት መብት ጎን ለጎን ዜጎች ጤናው በተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ መኖር የሚችሉበትን አግባብ መንግሥት በቻለው አቅም እንዲያመቻች የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 89(8) ላይ በግልጽ ደንግጎ ይገኛል:: ይህንንና ሌሎች የሕገ መንግሥት ክፍሎችን በመመልከት መንግሥት ለኅብረተሰቡ ምግብ የሚያገኝበት ብቻ ሳይሆን ጤናማ ምግብ የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት መረዳት ይቻላል::
ስለሆነም ይህንን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የወንጀል ድንጋጌ ይዘት ያላቸው ድንጋጌዎችን ያካተቱትን በተለይ የምግብ መድኃኒትና ቁጥጥር አዋጅ (በግንባር ቀደምትነት)፣ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅና የኢፌዴሪ ወንጀል ሕጎችን ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ በመጠኑ ለማየት ተሞክሯል::
የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ፦ስለ አንድ ስለ ተወሰነ ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የሚመለከት ሕግ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ልዩ ሕጎች (Special Laws) እየወጡ፣ በተለይ ለሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት ይሞከራል:: በያዝነው ጉዳይም ምግብነክ ድንጋጌዎች በተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተበታትነው ከሚቀመጡ ይልቅ ምግብንና ምግብ ነክ ጉዳዮችን የሚመለከት ልዩ ሕግ ወጥቶ ችግሮችን በዚህ ማዕቀፍ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ምግብ ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር ካለው ቁርኝትና ከምግብ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችም በግለሰቦች እንዲሁም በማኅበረሰብ ጤና ላይ ሊያሳድር ከሚችለው ዘርፈ ብዙ ችግር አንፃር አሌ የማይባል ተግባር ነው::
ይሁንና ይህንን በሚመለከት በሀገራችን በሥራ ላይ የዋሉት ሕጎች በተለይም አዋጅ ቁጥር 661/09 እና ይህንን አዋጅ አሻሽሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1112/12 የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጆች ሕጎችን በተጠቃለለ መልኩ ከማቅረብ አንፃር አዎንታዊ ሚና የተጫወቱ ቢሆንም፣ በተለይ ሕጉ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር ጉልህ ክፍተቶች ይስተዋሉባቸዋል:: በተለይም ከወንጀል ድንጋጌዎች አንፃር በአዋጁ ሊካተቱ የሚገባቸው ነጥቦች በተገቢው መንገድ መካተት አለመቻላቸውን ማስተዋል ይቻላል::
እዚህ ጋር በትኩረት የምናየው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ጉዳይ ነው:: በጣም በሚገርም ሁኔታ አዲሱ የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ተግባርን የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል አድርጎ አልደነገገውም:: በሀገራችን ኢትዮጵያ ይልቁንም በመዲናዋ በአዲስ አበባ በየወቅቱ የምንሰማቸው አሰቃቂና የሰውን ሰብዓዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ተግባራት፣ የምግብን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ ለመመልከት በወጣው ምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂነታቸው ያላካተተ መሆኑ ግርምትን የሚፈጥር ነው::
በአዲሱ የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ 1112/12 አንቀጽ 67 በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ቁጥጥር የሚደረግበት ምርት ደረጃውን ያልጠበቀ ወይም የአስተሻሸግ ጉድለት እንዲኖረው በማድረግ ወይም አስመስሎ በመሥራት ያመረተ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ያከማቸ፣ በጅምላ ያከፋፈለ ወይም በችርቻሮ የሸጠ ወይም ለኅብረተሰቡ ያቀረበ›› ከሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጎ ይገኛል::
ይሁንና የድንጋጌውን ይዘት ስንመለከተው ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት ደረጃውን ያልጠበቀ አድርጎ ማምረት በወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ቢሆንም፣ ይህ የወንጀል ተጠያቂነት ዕውን የሚሆነው በቅድሚያ ድርጊቱ የተፈጸመው ቁጥጥር በሚደረግበት ምርት ላይ ነው:: ይህ ምርት አስገዳጅ ደረጃ በሚመለከተው ተቋም የወጣለት ሲሆንና ከዚሁ ከተቀመጠለት ደረጃ በታች ሆኖ የተመረተ እንደሆነ ከድንጋጌው መንፈስ መረዳት ይቻላል::
ሌላው የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትለው አስተሻሸግ ላይ ጉድለት ማድረግ ወይም አንድን ምርት አስመስሎ መሥራትን ያካትታል:: እነዚህ ሁሉ ተግባራት የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ቢሆንም፣ በሀገራችን በስፋት የሚታየው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ደባልቆ ለገበያ የማቅረብ ተግባር በቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የተከለከለ ስለመሆኑ አልተደነገገም:: ይህ ደግሞ አዋጁ መሬት ላይ ያለውን ችግር በሚገባ ያልቃኘ ስለመሆኑ እንዲሞገት አድርጎታል::
በዚህ ነጥብ ላይ ምናልባት በተቃራኒው ሊነሳ የሚችለው ክርክር ደረጃውን ያልጠበቀ ምርት ማምረት፣ የአስተሻሸግ ብልሹነት ወይም አስመስሎ መሥራትን በወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ተግባራት ተደርገው መደንገጋቸው፣ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅንም ያካትታል የሚል ሊሆን ቢችልም፣ አንድን ምግብ ከመነሻው ከደረጃ በታች ነው ብሎ ለመበየን ለምርቱ የተቀመጠ አስገዳጅ ደረጃ ሊኖር እንደሚገባ እሙን ነው::
ምክንያቱም የተቀመጠ ደረጃ በሌለበት ከደረጃ በታች ነው ብሎ ማለት አይቻልም:: በሀገራችን ደግሞ አሁን ላይ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቀው ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ምግቦች በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ ኅብረተሰቡ ለዘመናት ሲያዘጋጃቸውና ሲመገባቸው የቆዩ፣ አስገዳጅ ደረጃ ለማውጣትም ሆነ በደረጃው መሠረት እየተሠሩ ስለመሆናቸው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መደባለቅን በተለየ መንገድ መያዝ እንደሚያስፈልግ ያመላክታል::
የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ፦
በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጁ ከምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጁ በተሻለ ሁኔታ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ለሚለው ሐሳብ በግልጽ ሽፋን የሰጠ ሲሆን፣ በአዋጁ አንቀጽ 30 ንዑስ ቁጥር 10 ‹‹ለሰው ጤናና ደኅንነት አደገኛ የሆኑ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃቸው ከተቀመጡላቸው ደረጃዎች የወረዱ፣ የተመረዙ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ፣ ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ማዘጋጀት ወይም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ የተከለከለና የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር መሆኑ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል::
አዋጁ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን በግልጽ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር ተደርጎ መደንገጉ እንደ መልካም ጎን ሊታይ የሚገባው ቢሆንም፣ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ለሚለው ሐረግ ተገቢው ትርጉም በአዋጁ ላይ ተሰጥቶት አናይም:: ይህ አለመሆኑ ደግሞ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው:: ለምሳሌ የእንጀራ ዱቄት ወይም የጤፍ ዱቄት ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው መቼ ነው?
የዳሰሳ ጥናቱ በተደረገበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ መምሪያ የእንጀራ ዱቄትን ከጀሶ፣ ከካሳቫ፣ በቆሎን ከመሳሰሉ ሌሎች የእህል ዘሮች ጋር ተደባልቀው ተገኝተዋል:: በዳሰሳ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ አካላት ለዚህ ሐረግ የተለየ ትርጉምና መረዳት እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል:: ሙሉጌታ ጽጌ ብርሃን የተባሉ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ማለት ለምግብነት በሚውል ምርት ላይ ሌላ ለምግብነት ሊውል የማይችል ነገር ሲደባለቅ ነው የሚል መረዳት አላቸው:: በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ተቋም ውስጥ በደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ ሆነው የሚሠሩት አቶ ሰለሞን ሙሉ ብርሃን በበኩላቸው፣ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው ያለ ደንበኛው ዕውቅና ከዋና ንጥረ ነገሩ ውጪ የሚጨመር ሌላ ማንኛውም ውህድ ነው በማለት ይገልጸዋል::
እዚህ ጋር ልንመለከተው የሚገባው ምንም እንኳን የሸማቾች ጥበቃ አዋጁም ሆነ የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር አድርገው የደነገጉ ቢሆንም፣ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው መቼ ነው? የሚለው በሕጎቹ ላይ ተገቢው ትርጉም ያልተሰጠው በመሆኑ ሕጉን ለማስፈጸም በተቋቋሙ የተለያዩ ተቋማትና ባለሙያዎች ስለ ጉዳዩ ያለው ግንዛቤ የተለያየ እንዲሆን ይህም ሕግን በማስፈጸም ሒደት ውስጥ ጉራማይሌ የሆነ አረዳድ እንዲኖር አድርጓል::
የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ፦
በዚህ ነጥብ ላይ የሌሎች ሀገሮች ሕጎች ምን ይመስላሉ? የሚለውን ስንመለከት፣ ከሀገራችን የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ ጋር አቻ የሆነው የማሌዥያ የምግብ ሕግ ግልጽ ትርጉም የሰጠ ሲሆን፣ ይኸውም ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው የምግቡን የምግብነት ደረጃ ሊያወርዱ የሚችሉ ወይም በየትኛውም ሁኔታ ከነባሩ የምግብነት ደረጃ አንፃር ዝቅ ያለ የንጥረ ምግብ ይዞታ እንዲኖረው የሚያደርግ ከሆነ፣ ምግቡ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል ሊያስብል እንደሚችል ተደንግጓል::
የሲንጋፖር የምግብ ሕግ ደግሞ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው የምግብነት ይዘቱን የሚቀንሱ ንጥረ ነገሮች መጨመር ወይም መደባለቅ ብቻ ሳይሆን በምግቡ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን አንዳንድ ይዘቶችና ንጥረ ነገሮችን አለማካተት ጭምር በትርጉም ተካቶ ይገኛል:: ስለሆነም የሀገራችን ሕጎችም ከዚህ አንፃር የሚታይባቸውን ክፍተት ቢያርሙ፣ ሕግን በማስፈጸም ሒደት ውስጥ እየተከሰተ ያለውን የመናበብ ችግር ሊፈታ ይችላል::ለዚህ መጣጥፌ‹‹ጀሶ ያበሉን የት ደረሱ?››በሚል ርዕስ ሪፓርተር ላይ ያስነቡብን ፍሬሰላም አባተ የተባሉ ጸሐፊ እና አዲሱን ወዳጄን የAIዩን ቻት ጂፒቲን ተጠቅሜያለሁ ።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም