ፍሬ ነገሩ
አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን (አ.ሳ.ዴ.አ) በ1998 ዓ.ም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ በጎ አድርጎት ማሕበራት ባለሥልጣን ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጠውና ላለፉት 16 ዓመታት በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ከመንግሥት ጋር በመናበብ ዘርፈ ብዙ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት አዎንታዊ ሚናውን ሲጫወት የቆየ ግብረሰናይ ድርጅት ነው።
በሥራውም በርካታ የምስክር ወረቀቶች ከክልል እስከ ፌዴራል መንግሥት እውቅና ተችሮታል። ታዲያ ይህ ድርጅት ለሚሰራው ሥራ ሌሎች ተጨማሪ ቦታ እንደሚያደስፈልገው በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ይቆያል።
በአጋጣሚ ግን PHOGET TO CONTINENTO የተባለ የውጭ አገር ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ሥራ አጠናቆ ሲወጣ የነበረውን ቢሮ እና አጠቃላይ ግብዓት የሚረከበው የመንግሥት ተቋም አሊያም ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ሲፈልግ አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ያገኛል።
ይሁንና ቀጥታ ድርጅቱን ማስተላለፍ ባለመቻሉ ለሚመለከተው አካል አስረክቦ ወጣ። ታዲያ ይህ ድርጅት ሌላ የሚሠራበት አካል በማስፈለጉ ጨረታ ወጣ። በዚህ ጊዜ PHOGET TO CONTINENTO የተባለ ድርጅት ይጠቀምበት የነበረውና ጊዜውን ጨርሶ ትቶ የሄደውን ቦታ ለጨረታ ሲቀርብ አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ከሌሎች አምስት ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ በይፋ በጨረታው አሸናፊ ሆነ።
ነገር ግን በጨረታ ባሸነፈው ቤት እና ቦታ ተላልፎ ርክክብ ባለመደረጉ በቦታ ጥበትና ኪራይ ለመክፈል በገጠመው ችግር ላይ መውደቁን ይናገራል። በተቋሙ የሚገኙ ሕጻናት ለከፍተኛ ችግር እንደተጋለጡና ሜዳ ላይ ለመበተን በቋፍ ላይ መሆኑንም ይገልጻል።
አብንኤዜር ማነው?
አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን (አ.ሳ.ዴ.አ) በ1998 ዓ.ም ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ በጎ አድርጎት ማሕበራት ባለሥልጣን ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጠውና ላለፉት 16 ዓመታት በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ከመንግሥት ጋር በመናበብ ዘርፈ ብዙ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት አዎንታዊ ሚናውን በመወጣት ላይ የሚገኝ የበጎ እራጎት ማሕበር ነው። በተቋማዊ አገልግሎቱ በርካታ ሕፃናትን ከልዩ ልዩ የመንግሥት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ተጋላጭ ሕፃናትን ወደ ማዕከል በማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ ያደርጋል። ለአብነትም የመጠለያ፣ ምግብ፣ የአልባሳት፣ የሕክምና፣ መደበኛና የኢመደበኛ ትምህርት የመዝናኛና ሌሎችም ላይ በማተኮር ይሠራል።
በአሁኑ ወቅት በማዕከል ውስጥ 59 ወንድ እና 44 ሴት በድምሩ 103 ሕፃናት አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ እየደረገላቸው ይገኛሉ። አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በሃዋሳ ከተማ ሦስት የግለሰብ ቤቶችን በመከራየት በወር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) በላይ ለነዚህ ቤቶች ኪራይ ወጪ እያደረገ መሆኑም አስታውቋል።
የቤተሰብ ድጋፍ እና ማሕበረሰብ ድጋፍን በተመለከተ በእነዚህ ዓመታት ዘርፈ ብዙ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቱ ከመንግሥት ጎን በመቆም በልዩ ልዩ አካባቢዎች ለከፋ ችግር የተጋለጡ የማሕበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ለአብነትም በሃዋሳ ከተማ አዲሱ ገበያ በእሳት አደጋ በተቃጠለ ጊዜ አንድ መኪና ሙሉ የአልባሳት ድጋፍ፣ በቀድሞ ሲዳማ ዞን ጭሬ ወረዳ በመሬት መንሸራተት እና ግጭት ምክንያት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች የአልባሳት ድጋፍ፣ ለሀላባ ዞን በጎርፍ ምክንያት ለተጎዱ የማሕበረሰብ ክፍሎች የአልባሳትና የምግብ ድጋፍ፣ በሃዋሳ ከተማ ለሚገኙ በርካታ አካል ጉዳተኞች ዊልቼሮች፣ ክራንቾች፣ መነጽሮች፣ በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦችን ከውጭ አገር በማስመጣት ጥርስ ገጠማ፣ ጌዲኦ ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በኮቪድ-19 ምክንያት ለሃዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ለሃላባ ዞን አስተዳደር ግምቱ ወደ 4,000,000 (አራት ሚሊዮን ብር) የሚጠጋ የምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።
በሃዋሳ፣ በሌሎች የሲዳማ ክልል ወረዳዎች እንዲሁም በቀድሞ ቤንች ማጂ ዞን የሚገኙ 42 ተማሪዎች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን የሚረዱ ናቸው። በድርጅቱ ውስጥ ከሚኖሩ ሕፃናት ውስጥ ተጥለው የተገኙ ሕፃናትን በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ በፍርድ ቤት ውሳኔ ለቤተሰብ ይሰጣል። እስከ አሁን 25 ሕፃናት በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ለፈቃደኛ ቤተሰብ ተሰጥቷል።
ከተለያዩ አካባቢ በመጡ ቤተሰብ ውስጥ በቋሚነት ተቀላቅለዋል። እነዚህም ቤተሰቦች በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ሲሆን ለአብነትም፤ ሃዋሳ፣ በሐረር፣ በጅማ፣ በአዲስ አበባ፣ በሻኪሶ እና ሂርና ከተሞች ይኖራሉ። ድርጅቱ መልሶ ማቀላቀል ላይም በሰፊው ይሠራል።
በልዩ ልዩ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩና ጾታዊና አዕምሯዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሕፃናት ከመንግሥት አካል ተረክበን ቤተሰቦቻቸውን በማፈላለግ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ተደርጓል። በመሆኑም እስከ አሁን ድረስ 72 ሕፃናትና እናቶችን ወደ ቤተሰቦቻቸው መልሶ ማቀላቀል ችሏል። ድርጅቱ በትምህርት ቤት ምገባም በሰፊው ይሠራል።
በዚህ ፕሮግራም በርካታ ሕፃናት በርሃብ ምክንያት መደበኛ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡና ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ከፍተኛ ሥራ ተሰርቷል። ላለፉት አራት ዓመታት በቀድሞ ሲዳማ ዞን፤ በጋሞ ጎፋና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በሚገኙ 51 ትምህርት ቤቶች ላይ በየቀኑ 31 ሺ702 ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ለዚህ ፕሮግራም የሚውል አልሚ ምግቦችን ከካናዳ አገር በማስመጣት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉንም ከድርጅቱ በተገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል። አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ከእነዚህ ተግባራት በተጨማሪም ሌሎች በጎ ተግባራት ላይ በመሰማራት የራሱን ማሕበራዊ ሃላፊነት እየተወጣ ይገኛል።
የደብዳቤዎች ምልልስ
አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን (አ.ሳ.ዴ.አ) ለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ግንቦት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጉዳዩ ‹‹PROGETTO CONTINENTI የተባለ ድርጅት ይጠቀምበት የነበረን ቦታ እና ንብረት ይመለከታል›› በሚል በፃፈው ደብዳቤ፤ ድርጅቱ በአዋጅ 1113/2011 በመዝገብ ቁጥር 0781 ተመዝግቦ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ የቆየ ድርጅት ሲሆን ፤ መዝገብ ቁጥር PC/8.1/4215/2020 በቀን 9/2020 በቀረበው ጥያቄ መሰረት በኤጀንሲው መዝገብ ቁጥር 01/ACSO/3681 በቀን 30 ጥቅምት 2013 ዓ.ም ተዘግቷል።
ስለሆነም ድርጅቱን ይሠጠው የነበረ አገልግሎት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ታሳቢ በማድረግ አብንኤዘር ላፖርት ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን በጊዜያዊነት እንዲተላለፍለት መዝገብ ቁጥር 20/ACSo/3576 በቀን 24/02/2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ለሲዳማ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ ንብረቱን እንዲያስተላልፍ ውክልና መስጠቱ ይታወሳል።
በመሆኑም ክልሉ የተሰጠውን ውክልና በተዋረድ የሰጠ ቢሆንም የማስተላለፍ ሥራው በተገቢው ሰዓት ባለመከናወኑ የማሕበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ከተዘጋው ድርጅት ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ዓላማ ያላቸውን ድርጅቶች በማስታወቂያ በመጥራት (በመጋበዝ) አምስት ድርጅቶች ለውድድር ያመለከቱ ሲሆን፤ ከተወዳደሩት መካከል ቀደም ብሎ ከፌዴራል እና ከክልል የመንግሥት አካል እውቅና እና የምስክር ወረቀት የተሰጠው ነው። ለአብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ዕውቅና ከሰጡ ተቋማቱም መካከል የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሲዳማ ዞን ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሲዳማ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ፣ የሲዳማ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ይገኙበታል።
የምስጋና የምስክር ወረቀት በተመለከተም የሲዳማ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ፣ የሲዳማ ዞን ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ እና የሲዳማ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራውን በመጥቀስ ንብረቱ እንዲተላለፍለት የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎለት የነበረው አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ውድድሩን ያሸነፈ ስለሆነ ግልባጭ የተደረገላቸው የመንግሥት ተቋማት የንብረት ርክክቡን እንድታሳውቁን እየጠየቅን፤ ግልባጭ ያልተደረገላችሁ፤ ነገር ግን የሚመለከታችሁ አካላት የማስተላለፍ ሂደቱ በተገቢው መንገድ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን ሲል ይጠይቃል። ይህም ደብዳቤ ለሚመለከታቸው 14 ተቋማት ግልባጭ ሆኖ ደርሷል።
ርክክብ እንዲፈፀም ሕጋዊ እውቅና ስለመሰጠቱ
ጉዳዩ ‹‹Progeto Contineti›› የተሰኘ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ሲገለገልበት የነበረውን ፕሮጀክት መብትና ግዴታ ጠብቆ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ባሉበት በጊዜያዊነት እንዲረከቡ ስለ መግለጽ ይሆናል በሚል ደብዳቤ የሚቀጥለው ሃሳብ ሰፍሯል።
ከላይ በርዕሱ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ‹‹Progetto Contineti›› የተሰኘ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በታቦር ክፍለ ከተማ ‹‹Integrated Urban Community Based Sustainable Development Project›› በሚል ቀርፆ ከሰኔ 2017 – ሚያዚያ 2020 ድረስ ለሦስት ዓመት ተኩል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመፈራረም ፕሮጀክት እየተገበረ የቆየ ሲሆን ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ፕሮጀክት እየተገበረ አለመሆኑን በመግለጽ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና የከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ወደ ቢሮአችን በጻፉት ደብዳቤ የፕሮጀክቱን ጊቢ ተመሳሳይ ዓላማላለው አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት ተላልፎ ይሰጣቸው በማለት የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮን ጠይቆ፤ ጉዳዩን ለኢፌዴሪ የሲቪል ማሕረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በቀን 03/13/2012 ዓ.ም በቁጥር 1628/ ሲ/ብ/ክ/መ/ፋ/ቢ/ንመ/2 ደብዳቤ ከመምሪያው የቀረበውን ማስረጃ አያይዘን መላካችን ይታወቃል ይላል።
በመሆኑም በጥያቄው መሠረት የኢፌዴሪ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በቀን 24/02/ 2013ዓ.ም በቁጥር 20/ ACSO/ 3576 በፃፈው ደብዳቤ ድርጅቱ ይተገብር የነበሩ ተግባራት ሳይቆራረጡ እንዲተገብሩ በመግለጽ አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ከሃዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር ጊዜያዊ ርክክብ እንድንፈጽም አሳውቋል።
በመሆኑም ርክክቡን መፈፀም እንዲያስችለን ከፋይናንስ ቢሮ እና ከከተማ አስተዳደሩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ የ‹‹Progetto Contineti›› ንብረት ቆጠራ አድርገው ሪፖርት እንዲያቀርቡም ከቢሮአችን በደብዳቤ ቁጥር 4000/ሲ/ብ/ክ/መ/ፋ/NGO/7 በቀን 15/03/2013 አሳውቀናል።
በተሰጠውም ኃላፊነት መነሻ የተቋቋመው ኮሚቴ ፕሮጀክቱ ሲፈጸምበት በነበረ ወቅት ያሉ የሰው ኃይልና ጊዜያዊና ቋሚ ንብረቶችን በመመዝገብ አቅርቧል። ይህንንም ከዚህ ደብዳቤ ጋር የኮሚቴውን ቃለ ጉባኤ 11 ገጽ አያይዘናል። ስለዚህ ኮሚቴው ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ ርክክቡ በጊዜያዊነት ሲፈጸም መብትና ግዴታም ተጠብቆ እንዲፈጸም ወስናነል ሲል ርክክቡ እንዲፈፀም ከውሳኔም ደርሷል ሲል ርክክብ መፈጸም እንዳለበትና ሕጋዊነቱን ጭምር ያብራራል።
ሌላ የተማፅኖ ደብዳቤ
ጉዳዩ:- Progetto Contineti የተሰኘ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ሊገለገልበት የነበረው ቅጥር ጊቢ በጊዜያዊነት ንብረት ርክክብ እንዲደረግ ባለሙያ እንዲመደብ ስለመጠየቅ በሚል በተፃፈ ደብዳቤ እንዲህ ይላል። ከላይ በርዕሱ ለመጥቀስ እንደተሞከረው Progetto Contineti የተሰኘ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በታቦር ክ/ከተማ ‹‹Integrated ዕan Community based Sustainable development project›› በሚል ቀርፆ ከ June 2017 – April 2020 ድረስ ለሦስት ዓመት ተኩል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመፈራረም እየተገበረ መቆየቱ ይታወቃል።
ይሁንና ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ፕሮጀክት እየተገበረ አለመሆኑንና የተፈራረመው የፕሮጀክት ጊዜ እ.ኤ.አ ግንቦት 2020 የተጠናቀቀ ስለመሆኑ ገልፆ ድርጅቱ ሲገለገልበት የነበረውን ቅጥር ጊቢ ተመሳሳይ ዓላማ ላለው አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ሲቪክ ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት ቢተላለፍላቸው በሚል ሃዋሳ ከተማ እስተዳደር ለቢሮችን አሳውቆ ጉዳዩን ለኢፌዴሪ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በቀን 03/13/2012 ዓ.ም በቁጥር 1628/ብ/ክ/መ/ፋ/ቢ/ንመ/2 ደብዳቤ ሊፃፍ በግልባጭ ማሰማታችን ይታወሳል።
በመሆኑም በጥያቄው መሠረት ተገቢውን ለመፈፀም እንዲያስችለን የኢፌዲሪ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በቀን 24 /02 2013 ዓ.ም በቁጥር 20/ ACSo/ 3576 በተፃፈ ደብዳቤ ድርጅቱ ይሠራ የነበረው ተግባራት ሳያቆራረጥ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ከቢሮአችንና ከከተማ አስተዳደሩ ፋ/ኢ/ል/መምሪያ ጋር በመሆን ለአቤኔዘር ሳፖርትግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ጊዜያዊ ርክክብ እንድንፈጽም አሳውቋል።
ስለዚህ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፋ/ኢ/ል/ መምሪያ ከመምሪያው፣ Progetto Contineti ባለድርሻ (parener) ከነበሩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች፣ ከማዘጋጃ ቤት እና ከከንቲባ ጽህፈት ቤት አንዳንድ ባለሙያ በመመደብ ርክክቡ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩሉን እንዲወጣና የተመደቡትን ባለሙያዎች ዝርዝር በአስቸኳይ እንዲያሳውቀን እንጠይቃለን።
የመ/ቤታችን ባልደረባ አቶ ፀጋዬ ዩታሞ ከሃዋሳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ መምሪያ የተመደቡትን፣ /Progetto Contineti/ አስረካቢውን ድርጅት እና ተረካቢውን አቤንዘር ሳፖርትግ ኤንድ ዴቨለፕመንት አሶሴሽን በማስተባበርና በመምራት ጊዜያዊ ርክክቡን በመፈፀም ለጊዜያዊ ርክክቡ የሚረዳ ሪፖርት በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲያቀርቡ አሳውቃለሁ። Progetto Contineti ድርጅት ከዚህ በፊት የቅጥር ጊቢውን ርክከብ ሁኔታ የሚያሳየውንና የፕሮጀክቱን መረጃ አሟልተው በማቅረብ ለርክክብ እንዲያመቻችሁ እየገለጽን ተረካቢውም ድርጅትም ለጊዜያዊ ርክክቡ የሚያስፈልገውን ሎጀስቲክ እንዲያሟላ በዚህ ደብዳቤ ግልባጭ አሳውቀናል ይላል።
የሚኒስቴሩ ደብዳቤ
የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር 098/የ/23/121 መሰረት ለሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በፃፈው ደብዳቤ የቤትና ቦታ ርክክብን አቤቱታ ይመለከታል፤ በሚለው ደብዳቤ አገራችን ኢትዮጵያ ሴቶችና ሕጻናት ከየትኛውም የማሕበረሰብ ክፍል ልዩ ትኩረትና ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን አጽንዖት በመስጠት በየትኛውም የሕግ፣ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና አስተዳደር ሂደት መብታቸውን የሚያስጠብቅ እና ቅድሚያ የሚሰጡ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው አገራችን ትኩረት ሰጥታ የምትሰራበት ጉዳይ ነው።
በተለይም ለችግር ተጋላጭ ሴቶችና ሕጻናት ተገቢውን የማሕበራዊና ኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲደረግላቸውና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ተቀናጅቶ መስራት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመሆን የተሃድሶ አግልግሎትና ተቋማዊ ድጋፍ እንዲመቻች እየተደረገ ይገኛል።
ሴቶችንና ሕጻናትን በመደገፍ የሚታወቅ አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን አገር በቀል ድርጅት በሲዳማ ክልል ለችግር ተጋላጭ ሕጻናትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በቀን 23/10/13 ደብዳቤ ቁጥር ህ/ም/397 የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2013 በጀት ዓመት በሲዳማ ክልል ያደረጋቸውን ምልከታዎች መሰረት በማድረግ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግብረ-መልሶች የሰጠ ሲሆን ከዚህም መካከል አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን አገር በቀል ድርጅት ያለበትን ሁኔታ መሰረት በማድረግ ለችግር ተጋላጭ ሕጻናትን ለመርዳት በሚያደርገው የበጎ አድራጎት ተግባራት የገጠሙትን ችግሮች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲቀርፍለት እና ለሕጻናቱ ዘላቂና ምቹ ዕድገት የሚያደርገውን ጥረት ሊደግፉ የሚችሉ የሚችሉ ሥራዎችን ከክልሉ የሚመለከታቸው መዋቅሮች ጋር እንዲነጋገርበት ከተጻፈው ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ PHOGET TO CONTINENTO የተባለ ድርጅት ይጠቀምበት የነበረውን ቤትና ቦታ ጊዜውን ጨርሶ ትቶ የሄደውን ቦታ ከሌሎች አምስት ድርጅቶች ጋር ተወዳድሮ በመረጠው ቤትና ቦታ ተላልፎ ርክክብ ባለመደረጉ በቦታ ጥበትና ኪራይ ለመክፈል በገጠመው ችግር በተቋሙ የሚገኙ ሕጻናት ለከፍተኛ ችግር እንደተጋለጡና ሜዳ ላይ ለመበተን በቋፍ ላይ መሆናቸው ታይቷል።
ስለዚህም አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ሀገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ የሕጻናት ማሳደጊያ ተቋም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናትን በተለይም ልዩ ድጋፍ የሚሹ ሕጻናትን (አካል ጉዳተኛ ሕጻናትን) የማቴርያል አቅርቦት በማሟላት፣ ተጥለው የተገኙና ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሕጻናትን የመጠለያ፣ ሥነ-ልቦና፣ ጤናና የምግብ ድጋፎችን በማሟላት፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ተፈጽሞባቸው ዘላቂ የተሃድሶና ሥነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ እስከ ዩኒቨርሲቲ አስተምሮ በማብቃት፣ እንዲሁም በማሕበረሰቡ ውስጥ ለችግር ተጋላጭ ሕጻናት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ማሕበራዊ ኃላፊነቱን በእጅጉ የተወጣ ተቋም መሆኑን ክልሉ በሚገባ ይረዳል።
በመሆኑም ይህ ተቋም እያደረገ ያለውን የማሕበራዊ ኃላፊነትና የበጎ አድራጎት ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠልና እየደገፋቸው ያሉ ሕጻናት ለዳግም ችግር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ለማስቻልና የሕጻናቱን መብት፣ ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል የተጠየቀው ቦታና ቤት በአግባቡ በሚመለከተው አካል ታይቶ መፍትሄ እንዲሰጠው እንጠይቃለን። ይህም ደብዳቤ ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጤና፣ ማሕበራዊ፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ግልባጭ እንዲሆን ተደርጓል።
አብንኤዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን የተሰጠው ምላሽ
ድርጅቱ በተለያዩ ወቅቶች ደብዳቤዎችን በመፃፍ ይመለከታቸዋል የሚባሉትን አካላት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም። አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ በዚህ ሥፍራ ላይ ጤና ተቋም ይገነባል በሚል አፋዊ ምላሽ ከመስጠት ውጭ ይህን ነው የሚባል ምክንያት አልቀረበም።
የጤና ተቋም እንዲሰራበት በእቅድ ስለመያዙም ሆነ የመንግሥት ውሳኔ ስለመሆኑ ምንም ማስረጃ የሚሰጥ የመንግሥት አካል እንዳልተገኘ እና ‹‹ቦታው ለሌላ ጉዳይ ይፈለጋል›› ከማለት ውጭ ሕጋዊ ሥርዓት እና ደንብን የተከተለ ምላሽ አልተሰጠበትም።
ምንም እንኳን ድርጅቱ ቀድሞ ቦታው በግብረሰናይ ድርጅት ተመዝግቦ የቆየ ሲሆን እና በአሁኑ ወቅትም አቤኤነዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ተመሳሳይ ሥራ እንዲሰራበት ቢፈቀድም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ምላሽ ለመስጠት አልፈቀዱም። ሌላው ቀርቶ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፃፈው ደብዳቤ የተሰጠው ምላሽ አልታወቀም።
ሰሚ ያላገኘው ጩኸት
እነዚህ ሁሉ ደብዳቤዎች እና ምልልሶች ቢኖሩም ጉዳዩ ይመለከተኛል ደብዳቤዎቹም እውነት ናቸው የሚል አካል ምላሽ አልሰጠም። በሕጋዊ መንገድ እልባት ከማበጀት ይልቅ ሰበብ መፈለግና አንዱን ወደ ሌላው ማላከክ የተለመደ ሆኗል። በተዋረድ እስከ ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘለቀው የትብብር እና የተማፅኖ ደብዳቤ ጠብ የሚል ነገር አላመጣም።
ታዲያ በዚህ ውስጥ አብኤነዘር ሳፖርቲንግ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን (አ.ሳ.ዴ.አ) የተሰኘው ድርጅት በሕጋዊ ጨረታ ያሸነፈውን ጉዳይ አለመፈፀም ሥራው ላይ እንቅፋት ከመፍጠሩም በላይ በየወሩ በመቶ ሺዎች ኪራይ በመክፈል ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጓል።
ይህም በቀጣይ በማዕከሉ የሚገኙ ወላጅ አልባ ሕፃናት እንዳይበተኑና ለ16 ዓመታት በሥራ ላይ የነበረው ድርጅት ጥቅም አልባ አንዳይሆን ስጋት ሆኗል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስለጉዳዩ ለሕዝብ ሚዛናዊ መረጃ ለማቅረብ በማሰብ ለሃዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014