ምዕራባውያን አገራትን ኃያል ካደረጓቸው መካከል መገናኛ ብዙኃኖቻቸው ይገኙበታል። አገሮቹ የግዙፍ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ባለቤቶች ናቸው። እነዚህ መገናኛ ብዙሃኑ በየአገሮቹ መንግሥታት የሚዘወሩና በመላ ዓለም እግራቸውን የተከሉ ናቸው። ዓለም አቀፍ በመባልም ይታወቃሉ።
መገናኛ ብዙሃኑ ግዙፍ እንዲሆኑ ላደረጓቸው የየሀገሮቻቸው መንግሥታት ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ለምእራቡ ዓለም የቆሙም ናቸው። መገናኛ ብዙኃኑ የምእራባውያኑ ሆነው ሳለ ዓለም አቀፋዊነቱን አንዴት ሊያገኙት ቻሉ? ዓለም አቀፍ ያረጋቸው ማነው? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።
ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት ‹‹እነ ሲ ኤን ኤንን ዓለም አቀፍ ያልናቸው እኛ ነን›› ብለው ነበር። መገናኛ ብዙሃኑን ዓለም አቀፍ ያደረግንበት ምክንያት ግን በመላው ዓለም ተንቀሳቅሰው ወይም ተገኝተው ስለሚዘግቡ ነው። አዎን! እኔም መገናኛ ብዙኃኑ ሰፊ አካባቢን የሚሸፍኑ መሆናቸውና ፈጣን መረጃ ማቅረብ መቻላቸው ይህንኑ ስያሜ ሊያሰጣቸው ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
መገናኛ ብዙሃኑ ዓለም አቀፍ በመባል ብቻም አይደለም ሲታወቁ የኖሩት። ‹‹ታማኝ የዜና ወይም የመረጃ ምንጭ›› በመባልም ሲገለጹ ኖረዋል። በእርግጥ ከሚደርሱባቸውና ከሚሸፍኗቸው የዓለም ስፍራዎች አኳያ ሲታይ ዓለም አቀፍ መባላቸው ብዙም ላያነጋግር ይችላል።
ታማኝ የመረጃ ምንጭ የሚለው ላይ ግን ወራጅ አለ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እነዚህን መገናኛ ብዙሃን ትንሽ ሆነው እጅ ከፍንጅ አግኝተናቸዋልና። ባለፉት ወራት ከከሀዲውና አሸባሪው ትህነግና ከተባባሪዎቹ ምእራባውያን ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያካሂዱ የነበሩት ዘመቻ ትንሽነታቸውን ገላልጦ አሳይቶባቸዋል። የሚሰሩትም ለዓለም ሕዝብና መንግሥታት ሳይሆን ለምእራባውያኑ መሆኑን በሚገባ ተረድተናል።
በኢትዮጵያ ላይ ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የአገሪቱን ገጽታ በማበላሸት የተቀናጀና በእቅድ ላይ የተመሰረተ ጦርነት ከፍተው ተዋግተዋል። እነዚህ መገናኛ ብዙኃን የአፍሪካን ደካማ ጎን በተለይም የእርስበርስ ግጭትና ጦርነት ሲዘግቡ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው የሚሰሩና የሕዝብ ድምጽ የሆኑ ይመስለን ነበር። ጨዋታው ግን ሌላ ነው፤ ዋና አጀንዳቸው የየአገራቸውን ጥቅም ማስጠበቅ ነው።
በአፍሪካ እንደ እንደነ ቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ ሮይተርስ፣ አልጀዚራ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኒዮርክ ታይምስ፣ ዘ ጋርዲያን… የመሳሰሉ ተጽእኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው መገናኛ ብዙኃን የሉም። እነዚህ የምዕራባውያን መገናኛ ዘዴዎች እና አልጀዚራ ናቸው በመላው አፍሪካ እየተዘዋወሩ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ የሚዘግቡት።
ለዚያም ነው አፍሪካ ችግሮቿ ብቻ ሲዘገቡ የኖሩት። አዎን! እነዚህን መገናኛ ብዙኃን ተረደተናቸዋል። ለአፍሪካውያን ያልቆሙ፣ ለምእራባውያን የቆሙ መሆናቸው ግልጥልጥ ብሎ ታይቶናል። አፍሪካውያን መገናኛ ብዙሃኑን በሚገባ ሊረዷቸው ይገባል፤ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ሊቀስሙ ይገባል።
ይህን የምእራባውያኑ አፍራሽ ዘገባ የሚያረክስ የአህጉሪቱን ገጽታ የሚገነባ የራሳቸው መገናኛ ብዙሃን በሚያስፈልጋቸው ወቅት ላይ ናቸው። በአፍሪካ ጥቂት አገሮች ግዙፍ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉ ቢነገርም፣ መገናኛ ብዙኃኑ ግን ከአገር ቤት የወጡ፣ ድንብር የተሻገሩ አይደሉም።
እናም አፍሪካ እስከ አሁን ተጽእኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት መሆን አልቻለችም። ለምን? እንደሚታወቀው አህጉሪቱ ከፍተኛ በሆነ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ነው የኖረችው፤ ያለችውም። አህጉሪቱ ነውጥና የመንግሥት ለውጥ አያጣትም። በለውጡ ማግስትም መንግስቱን ካለመቀበል ጋር ተያይዞ መቆራቆዝ አለ። የመንግሥት ለውጡ በራሱ በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ አሉታዊም አዎንታዊም ተጽእኖ ያሳድራል። በአህጉሪቱ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር የሚነሱና የሚጠፉ መገናኛ
ብዙሃን ማየት የተለመደውም ለእዚሁ ነው። አንዳንዴ የአዲስ መንግሥት መምጣት አንደ አሸን የሚያፈላቸውን ያህል ብዙም ሳይቆዩ ብን ብለው እንዲጠፉ ያደርጋቸዋል። እንደየመንግሥቱ ባህሪ የመገናኛ ብዙሃኑ ባህሪ የተለያየ ሲሆን ይስተዋላል።
በአንዳንድ አገሮች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ልሳን ናቸው፤ የግል መገናኛ ብዙኃን ደግሞ (በተለይ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ) ጭፍን ተቃዋሚና ግጭት አቀጣጣይ ሲሆኑ ይስተዋላል።
በዚህ ላይ ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የእርስበርስ መወነጃጀል ሲጨመር መገናኛ ብዙሃኑ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ተጽእኖ መገመት አይከብድም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚንቀሳቀስ መገናኛ ብዙሃን እንኳን ዓለም አቀፍ ደረጃ ሊደርሱ የአገሬው ሕዝብ የሚያምናቸውም አይደሉም።
እውነታም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። አንድ መገናኛ ብዙኃን ተፅዕኖ ፈጣሪና ተወዳጅ የሚሆነው ደግሞ መጀመሪያ በአገሩ ሕዝብ ተወዳጅ ሲሆን ነው። የአገሩ ሕዝብ ካጣጣለውና ከናቀው ዓለም ምን ይሁነኝ ብሎ ይቀበለዋል? ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳው እንዴት ያከብደዋል እንደሚባለው ነው ነገሩ።
እናም እንደ አገር ትልቅ መገናኛ ብዙኃን መፍጠር ካልተቻለ አህጉሪቱን ለመታደግ ደግሞ እንደ አህጉር መሞከር ያስፈልጋል። ለእዚህም አፍሪካውያን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን ሃሳብ ተቀብለው መሥራት ውስጥ መግባት አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በአፍሪካ ሕብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገኝተው እንዳሉት፤ አፍሪካውያን እንደ አህጉር ገጽታቸውን የሚያስተዋውቁበት እና የሚገነቡበት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሚነዙትን ሀሰተኛ መረጃ የሚያመክኑበት የራሳቸው የሆነ ተጽእኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሃን ሊኖራቸው ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ብቻ ሳይሆን በዓለም መገናኛ ብዙኃን በኩልም ተገቢውን ውክልና ልታገኝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
‹‹አፍሪካውያን ስለራሳችን ታሪክ ራሳችን ማውራት፣ ገጽታቸውን መገንባት ቅድሚያ ስራችን ሊሆን ይገባል›› ሲሉ ገልጸው፣ አፍሪካ ሕብረት የራሱን የመገናኛ ብዙኃን ተቋም እንዲያቋቁምም ሃሳብ አቅርበዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አዲስና አፍሪካውያን ፈጥነው ወደ ሥራ ለማስገባት ሊንቀሳቀሱበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
አፍሪካውያን በምእራባውያንና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ሀሰተኛ መረጃ እየተናጡ ባሉበት፣ ከፉ ክፉ ገጽታቸው ብቻ እየተመረጠ በምእራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን በሚዘገብበት በዚህ ዘመን፣ አፍሪካ የራሷ ሚዲያ በአፍሪካ ሕብረት ስር እንዲኖራት ማሰብ አፍሪካን ከምእራባውያን መገናኛ ብዙኃን ሴራ መታደግ ነው።
በተለይ ለአህጉሪቱ አገሮች አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝንና የምእራባውያንን ጣልቃ ገብነት ለመከላከልና ገጽታቸውን ለመገንባት የዚህ መገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ ይሆናል።
ይህ ብቻ ግን የአፍሪካን የመገናኛ ብዙሃን ችግር ይፈታል ተብሎ መታሰብ የለበትም። በየአገሮቹ ያሉት መገናኛ ብዙሃን ካለባቸው ውስብስብ ችግር መታደግም ያስፈልጋል። አህጉሪቱ አፍሪካዊ ሚዲያ እንዲኖራት ከማን ምን ይጠበቃል? ከተባለ ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል ነው መልሱ።
መንግሥታት ለመገናኛ ብዙኃኑ የሚሰሩበትን ነፃነት መስጠት ይኖርባቸዋል፤ መገናኛ ብዙሃኑም በየአገሮቹ ለሚዲያው በተዘጋጁ ህጎች መሰረት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ከሕዝብ ደግሞ በራስ አገር ተቋም መኩራትና የራስን ማመን ይጠበቃል።
በአህጉርቱ አገሮች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ መፍጠር ከተቻለ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙኃን የማይፈጠርበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014