በኢትዮጵያ የአቭዬሽን ታሪክ አስከፊ የተባለ የአውሮፕላን አደጋ ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ደርሷል፡፡ በአደጋው የ149 መንገደኞችና 8 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች በድምሩ የ157 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ አደጋው የደረሰው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነውና የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -800 ማክስ የተባለው አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ኬኒያ ናይሮቢ ለመብረር ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱና ሞጆ አዋሳኝ አካባቢ ኤጀሬ በሚባል አካባቢ በመከስከሱ ነው፡፡በአደጋው 8 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች፣ 9 ኢትዮጵያውያን መንገደኞችና 140 የተለያዩ 35 ሀገሮች ዜጎች ህይወት ነው ያለፈው፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የትናንትናው እለት ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆን ባወጀው መሰረት ቀኑ በመላ ኢትዮጵያ እና በመላ አለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጓል፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንዳሉት፤ አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን ከቦይንግ ኩባንያ ከተገዛ አራት ወራትን ብቻ ያስቆጠረና አዲስ ነው ፡፡የበረረውም 1200 ሰአታት ሲሆን በጥር ወርም የቴክኒክ ምርመራ ተደርጎለታል፣ አብራሪውም 8 ሺ ሰአቶችን ያበረረ እና ብቁ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡ረዳት አብራሪውም 200 ሰዓታት የበረረ ነው፡፡
ምንም እንኳን የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ቢሆንም የካበተ ልምድ ያላቸው አብራሪዎችና ሌሎች የበረራ ሰራተኞችን እንዲሁም የአየር መንገዱ ደንበኛ የሆኑ መንገደኞችን ህይወት ማጣት እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ አየር መንገዱ በደህንነትና ቴክኒክ ብቃቱ አለም አቀፍ እውቅና ያለው በመሆኑ አደጋው ዝናውን ከማስቀጠል እንደማያስተጓጉለው መታወቅ አለበት፡፡ለዚህ ደግሞ መላው የድርጅቱ ሰራተኞችና አመራሩ በጽናት ሊሰሩ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በደረሰው አደጋ በእጅጉ አዝነዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አደጋው የደረሰበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ተመልክተዋል፤ ከዚያም መልስ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ የፌዴራል መንግስትና የክልል ተቋማት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። ሀገሮችም በተመሳሳይ ሀዘናቸውን ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እየገለጹ ናቸው፡፡
ሀዘን መግለጹ እንደተጠበቀ ሆኖ የአየር መንገዱን ብቃትና አስተማማኝነት እንደተጠበቀ መሆኑን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመግለጽ ለዝናው መጠበቅ ሊሰሩ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን አደጋውን ከሰሙበት ቅጽበት አንስቶ በእጅጉ አዝነዋል፡፡ለሃዘንምባንዲራቸውን ዝቅ አድርገው ውለዋል፡፡ነገር ግን ትናንት በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ዝቅ ብሎ የተውለበለበው ባንዲራ አየር መንገዳችንን ከፍ አድርጎ ይዞ አሁንም በረራውን ያካሂዳል፡፡ ስለሆነም መላው ዜጎች ለቀጣይ የአየር መንገዳችን ክብርና ዝና መስራት አለብን፡፡ መንግስት የአውሮፕላኑ አደጋ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ለማጣራት ኮሚቴዎች አቋቁሟል፡፡
የቦይንግ ኩባንያም የአየር መንገዱ ጥያቄ ካለ የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ምርመራው ከተደረገ በኋላም ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግም አየር መንገዱ ገልጿል፡፡የምርመራ ውጤቱ በአለም አቀፍ የአቪየሽን ህግ መሰረት ይፋ እስኪሆን በትእግስት መጠበቅም ተገቢ ነው፡፡ አየር መንገዱ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ አደጋው ከደረሰበት አውሮፕላን ጋር የሚመሳሰሉትን አውሮፕላኖች ከበረራ አግዷል፡፡ የእነዚህ አውሮፕላኖች ተመሳሳይ በኢንዶኔዥያ አደጋ የደረሰበት እንደመሆኑም የተጓዦቹን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል አየር መንገዱ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው፡፡አሁንም ለደንበኞቹ ደህንነት የሚሰራ መሆኑን ማረጋገጫ ነው፡፡ አደጋው አየር መንገዱ ለአመታት የገነባውን ዝና የሚንድ አይሆንም። አየር መንገዱ የበረራ ደህንነቱን እንዲጠራጠር የማድረግ አቅምም አይኖረውም።
አሁንም ሌሎች በረራዎቹ ላይ ያደረገው ለውጥ የለም፤ ሊኖርም አይገባም፡፡ ይህም ስራዎች እንደተለመደው መቀጠላቸውን ያመለክታል፡፡አሁንም ብቃቱ ላይ ምንም ጥርጥር የለም፡፡የአደጋውን መንስኤ የማጣራቱ ስራ እንዳለ ሆኖ የአውሮፕላኖቹን እና ሰራተኞቹን ብቃትና ደህንነት ዘወትር ማረጋገጡን በመቀጠል ስራው ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ እንደሚታወቀው፤ አየር መንገዱ በአገልግሎቱ በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት አድናቆት የተቸረውና ለዚህም በርካታ ሽልማቶችን የተጎናጸፈ መሆኑ ይታወቃል። አዳዲስ አውሮፕላኖችን ወደ ስራ በማስገባትም ይታወቃል፡፡ በአውሮፕላን ጥገናም በኩል ከራሱም ተርፎ የሌሎች ሀገሮች አውሮፕላኖችን በመጠገንም ይታወቃል፡፡ አየር መንገዱ ዝና እንዲያተርፍ ካደረጉት መካከልም እነዚሁ ተግባሮቹ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡
በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ እና አሜሪካ እንዲሁም በአንድ ሀገር ውስጥ ወደ ተለያዩ ግዛቶች በመብረር መዳረሻዎቹን እያሰፋ ያለበት ሁኔታም እንዲሁ የብቃቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም አደጋው በዚህ ሁሉ ብቃት ውስጥ ያጋጠመ ክስተት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ አደጋው መጠነኛ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል በማመን ሰራተኞቹም ሀዘኑ እንዳለ ሆኖ በተለመደው የስራ ባህላቸው በመስራት ለአመታት የተገነባውን ገጽታቸውን በማስቀጠል የአየር መንገዱን ዝና ለማስጠበቅ ጠንክሮ መስራት ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2011