ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የግዥ ሂደትን ያልተከተለ ክፍያ ተፈጽሟል

አዲስ አበባ፡- በ2013 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር፤ በ2014 በጀት ዓመት 172 ሚሊዮን ብር በድምሩ ከ1 ቢሊዮን 572 ሚሊዮን ብር በላይ የግዥ ሂደትን ያልተከተለ ክፍያ መፈጸሙን የፍትሕ ሚኒስቴር በጥናቱ አመለከተ።

ፍትሕ ሚኒስቴር በተቋማት በሚደርሱ የኦዲት ጥሰቶች፣ የሕጎች አተገባበርና ተግዳሮቶች ላይ የሠራውን ጥናት በትናንትናው እለት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነት መከታተያ አቃቤ ሕግ ኃይለገብ ርኤል አያሌው እንደገለጹት፤ ጥናቱ በ2013 እና 2014 በጀት ዓመት የ87 ተቋማት የኦዲት ሪፖርትን መሠረት በማድረግ እና 14 ተቋማት ላይ ቀጥተኛ ዳሰሳ በማድረግ የተሠራ ነው። በተጠቀሱት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ1 ቢሊዮን 572 ሚሊዮን ብር በላይ የግዥ ሂደትን ሳይከተሉ ተቋማቱ ክፍያ መፈጸማቸው መረጋገጡን ተናግረዋል።

በፋይናንስ አስተዳደር ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩ ጥሰቶች አላግባብ የሚከፈል አበል፤ የተሟላ ሰነድ ሳይኖር ክፍያ መፈጸም፤ ውዝፍ ተሰብሳቢ መኖር እና ያልተሰበሰበ ግብር እና ቀረጥ መኖር መሆናቸውን አቃቤ ሕጉ ገልጿል።

በጥናቱ መሠረት በተጠቀሱት ሁለት ዓመታት 241 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሕጉ መሠረት ተሰልቶ ባለመወሰኑ መሰብሰብ አልተቻለም። የተሟላ ሰነድ ሳይኖር የተፈጸመ ክፍያን በተመለከተ 71 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ 19 ሚሊዮን ብር የአበል መመሪያን ሳይከተል ክፍያ ተፈጽሟል።

ግዥዎችን ከእቅድ ውጪ የመፈጸም፣ ያለ ጥናት እቃዎችን የመግዛት፣ ግዥዎችን ከፋፍሎ የመግዛት እና በቴክኒክ ኮሚቴ የእቃዎቹ ጥራት ሳይረጋገጥ እቃን የመረከብ እንዲሁም ከውል በላይ ክፍያን የመክፈል አካሄዶች በጥናቱ መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

ለሕግ ጥሰቱ ምክንያቶችም የውስጥ የቁጥጥር ሥርዓት አለመጠናከር፣ ጠንካራ፣ ነጻ እና ገለልተኛ የውስጥ ኦዲተር አለመኖር፣ የኦዲት ምክር ሃሳብ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የተጠናከረ የተጠያቂነት ሥርዓት ተግባራዊ አለማድረግ፣ ከሚደርሰው ጉዳት አንጻር ቅጣቱ ተመጣጣኝ አለመሆን፣ የቁጥጥር ማነስ፣ የሕግ ክፍተት፣ የበላይ ኃላፊዎች አስቸኳይ ትዕዛዝ፣ የማሕቀፍ ግዥ ሲፈጸም የጊዜ እና የጥራት ችግር መኖር እና የአስፈጻሚ ተቋማት ጠንካራ ትብብርና ቅንጅት ያለመኖር ክፍተቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።

አቅራቢው የኦዲት ግኝቱ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሰነድ የያዘ አለመሆኑ ፍትሕ ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ክስ እንዳይመሠርት ማድረጉን ገልጸዋል።

ወጥና ጠንካራ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት፣ የውስጥ ኦዲት አደረጃጀት ነጻ፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ ማድረግ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር በሚቀርብለት የውስጥ ኦዲት ሪፖርት መሠረት ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሚሉትም በጥናቱ የተካተቱ ምክረ ሃሳቦች መሆናቸው ተመላክቷል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You