በአፍሪካ እግር ኳስ ገናና ስም ካላቸው አገራት መካከል ሴኔጋል አንዷ ነች። የቴራንጋ አንበሶቹ በተለይም ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ባፈሯቸው አስደናቂ ከዋክብት ተጫዋቾች በዓለም እግር ኳስ ላይ ጎልተው ሲጠሩና ሴኔጋልም በፊፋ የአገራት ወራዊ የእግር ኳስ ደረጃ በተለያየ ጊዜ የጎላ ለውጥ አምጥታ በትልቁ አህጉራዊ ውድድር ግን ጣፋጩን ድል አንዴም መጎንጨት ሳትችል ቀርታለች። የሚያሳዝነው የቴራንጋ አንበሶች እኤአ በ2002 የኮሪያና ጃፓን የዓለም ዋንጫ ጭምር ቅኝ ገዣቸው ፈረንሳይን ሳይቀር አሸንፈው እስከ ሩብ ፍጻሜ በነበራቸው አስደናቂ ጉዞ ወርቃማው የእግር ኳስ ትውልዳቸው የአፍሪካ ዋንጫን ለመሳም አለመታደሉ ነው።
በተለይም የቴራንጋ አንበሶች በ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ወርቃማው የእግር ኳስ ትውልዳቸው ለፍጻሜ ደርሶ ዋንጫውን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳም ተቃርበው በመጨረሻ ድሉን በካሜሩን ተነጥቀው እንባቸውን ያፈሰሱበት አጋጣሚ የሚዘነጋ አይደለም። ከዚያም በኋላ የቴራንጋ አንበሶች በአህጉሪቱ ታላቅ የእግር ኳስ መድረክ የሚታወሱበትን ድል ለማግኘት ብዙ ጠብቀዋል።
የያኔው የቴራንጋ አንበሶች ወርቃማ ትውልድ ከስሞ ሌላ አዲስ ወርቃማ ትውልድ ለመተካት ግን ሴኔጋል ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም ማለት ይቻላል። በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ተጽኗቸው የጎላ ከዋክብትን ማፍራት የቻለችው ሴኔጋል ሁሌም ወደ ምትጓጓለት የአፍሪካ ዋንጫ ድል በእጅጉ ለመቅረብ አልተሳናትም። በ2019 የአፍሪካ ዋንጫም ለፍጻሜ ቀርባ አዲሱ የቴራንጋ አንበሶች የከዋክብት ስብስብ በአልጄሪያ አንድ ለምንም ተረቶ ዳግም አንብቷል። ይህም የቴራንጋ አንበሶችን ሁለት የወርቃማ ዘመን የእግር ኳስ ትውልድ በአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ቀርቦ ዋንጫ የማንሳት እርግማን እንዳለበት በተጫዋቾቹም ጭምር እንዲታመን እስከማድረግ ደርሷል።
የቴራንጋ አንበሶች ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ቁጭት ከውስጣቸው ሳይጠፋ ዘንድሮም ከግብ ጠባቂ አንስቶ እስከ አጥቂ መስመር በከዋክብት ያሸበረቀው ስብስብ ለፍጻሜ ደርሷል። ይሁን እንጂ የቴራንጋ አንበሶች ለፍጻሜው ፍልሚያ በአፍሪካ ዋንጫ ሰባት ጊዜ ከነገሰችውና ጠንካራ የተከላካይ አጥር ከገነባችው ግብጽ ጋር መገናኘታቸው ያለፉትን ሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ታሪክ አስታውሶ ስጋታቸውን የጨመረ አጋጣሚ ነበር። እንደተጠበቀውም በእሁድ ምሽቱ የቴራንጋ አንበሶችና የፈርኦኖቹ የፍጻሜ ጨዋታ አሰልጣኝ ካርሎስ ኪሮዥ የገነቡት የተከላካይ መስመር በቴራንጋ አንበሶች የከዋክብት ስብስብ በቀላሉ የሚደረመስ አልሆነም።
ፈርኦኖቹ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ሦስት ጨዋታዎችን ከመደበኛው የጨዋታ ጊዜ ውጪ በተጨማሪ ደቂቃዎች አሸንፈው ለፍጻሜ መድረሳቸው ይታወቃል። ጠንካራዋ ኮትዲቯርንና አዘጋጇ ካሜሩንን በሩብ ፍጻሜና ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በመለያ ምት አሸንፈው ለፍጻሜ የደረሱት ፈርኦኖቹ የፍጻሜውንም ጨዋታ በተመሳሳይ መንገድ ደምድመው ለስምንተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ፍላጎት እንደነበራቸው በግልጽ ከጨዋታቸው መረዳት ይቻል ነበር።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይም የሊቨርፑል የፊት መስመር ከዋክብት ሳዲዮ ማኔና ሞሐመድ ሳላህ ለሴኔጋልና ግብጽ በተቃራኒ ተሰልፈው የሚፋለሙበት መሆኑ የዓለምን ሁሉ ትኩረት ስቦ ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ አምስት ደቂቃዎች ማኔ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ፈርኦኖቹን በሩብ ፍጻሜና ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በርካታ የመለያ ምቶችን በማዳን ታሪክ የሰራው ግብ ጠባቂው ሞሐመድ ጋባስኪ ማክሸፉ የቴራንጋ አንበሶችን ውጥረት ውስጥ ከቶ ነበር። ሙሉ ዘጠና ደቂቃውና ተጨማሪው ሰላሳ ደቂቃ ካለግብ ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ምት ሲያመሩም ፈርኦኖቹ እንደለመዱት አሸንፈው የቴራንጋ አንበሶች የእውነትም በፍጻሜ ጨዋታ እንዳያሸንፉ እርግማን ያለባቸው መስሎት ነበር።
ያምሆኖ እግር ኳስ ሁሌም ባልተጠበቁ ክስተቶችና በተአምራት የተሞላ ስፖርት ነውና መለያ ምት ለፈርኦኖቹ ፊቱን ሲያዞር በመደበኛው የጨዋታ ጊዜ ፍጹም ቅጣት ምት ያከሸፈው ማኔ የመጨረሻዋን የማሸነፊያ ምት አስቆጥሮ ሴኔጋልን ለአፍሪካ ዋንጫ ድል አብቅቷል። የቴራንጋ አንበሶችም ሁለቴ ለፍጻሜ ደርሰው ሳይሳካላቸው ቀርቶ ያፈሰሱት እንባ በሦስተኛው ታብሷል። ማኔ በመጨረሻም የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ሲመረጥ የቡድን አጋሩ ኤድዋርድ ሜንዲ ኮከብ ግብ ጠባቂ እንዲሁም ስምንት ግቦችን ያስቆጠረው ካሜሩናዊው ቪንሰንት አቡበከር ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን በቅተዋል።
እኤአ 2002 ላይ የቴራንጋ አንበሶቹ ለፍጻሜ ደርሰው ዋንጫውን በካሜሩን ሲነጠቁ ተጫዋች የነበረው አሊው ሲሴ የሴኔጋል አሰልጣኝ በመሆን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሶ አልተሳካለትም ነበር። አሁን ግን ለዚህ ስኬት በቅቷል። ፈርኦኖቹ በታሪካቸው የአሁኑን ጨምሮ አስር ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ቀርበው ሰባት ጊዜ ዋንጫውን ወስደዋል። ፈርኦኖቹ ከዚህ ቀደም ለፍጻሜ ቀርበው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ዋንጫ የተነጠቁ ሲሆን ከስልሳ ዓመት በፊት ፈርኦኖቹ ለዋንጫ ቀርበው በኢትዮጵያ የተሸነፉበት የመጀመሪያ ታሪክ ሆኖ ይታወሳል። ሁለተኛው በ2017 በካሜሩን የተነጠቁበት ሲሆን ሴኔጋል ይህን ታሪክ በእሁዱ የፍጻሜ ጨዋታ ተመሳሳይ ታሪክ ተጋርታለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2014