ወይዘሮ ትዕግስት ሙሉጌታ ተወልደው ያደጉት ባሌ ክፍለ ሀገር ነው። መንደሯ ትንሽዬ የአርሶ አደሮች መኖሪያ ስትሆን ጉራንዳ ጎርጊስ ትባላለች። ጉራንዳ ተወልደው ያደጉባት ብቻ ሳትሆን ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ያሳለፉባትም ናት። ትዳር መስርተውባታል። ወልደው ከብደውባታል። ሆኖም ባለቤታቸው ያደርሱባቸው በነበረው ከፍተኛ ጥቃት ምክንያት የትዳር ሕይወታቸው ምቹ አልነበረም። ልጆቻቸውን በጤናና በሰላም ማሳደግ እንኳን አልቻሉም። ለዛሬ የእኝህን እናት አስተማሪ ተሞክሮ እናካፍላችኋለን።
‹‹ዛሬም አለሁ›› በሚል ርዕስ በመጀመሪያ መጽሐፋቸው ውስጥ ያለፉበትን የሴትነት ሕይወት ውጣ ውረድ ለማሳተም የበቁት እናት ባለቤታቸው ለበኩር ልጃቸው አካል መጎዳት ሳይቀር ምክንያት እንደሆኑባቸው አውግተውናል። መጽሐፉ ለአካል ጉዳተኛ እናቶችና አሳዳጊዎች በእሳቸው የደረሰባቸውን መከራ የተመለከተውን ታሪክ ይማሩበት ዘንድ እንደጻፉትም ነግረውናል።
ስለ አስተዳደጋቸውና ስለ ትዳራቸው እንዳጫወቱን ያደጉት በእንጀራ አባት እጅ ነው።ትምህርት ቤት አይሄዱም ነበር። በእናታቸው ጥረት በተለይም እጅግ መልካሞች በነበሩት የእንጀራ አባታቸው ቤተሰቦች ግፊት ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ይደረግ የነበረ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በቤት ውስጥ ሥራ ተጠምደው የሚቀሩበት ቀን ይበዛል። ትምህርት ቤት የመግባት ዕድል በማግኘታቸው ቢደሰቱም የእንጀራ አባታቸው እንደ ሌሎቹ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች ለትምህርት ቤት የሚመጥን ልብስ ስላልገዙላቸው የእናታቸውን ትልቅ ቀሚስ ለብሰው ነበር። ሆኖም በዚያን ወቅት የሚያዩት ትምህርት ቤት ገብተው መማራቸውን እንጂ ስላለባበሳቸው ግድ እንዳልሰጣቸው ይናገራሉ።
ሰርክ እናትና አባታቸው ሲጨቃጨቁና ሲጣሉም ሲሰሙ ኖረዋል። ይሄን እየሰሙ ማደግ ያስጨንቃል፣ያስጠብባል፣ ያውክና በትምህርት ገበታ ለሚመጣው ድክመትም መንስኤ ይሆናል። ትምህርታቸውን ከሰባተኛ ክፍል ለማቋረጥም መንስኤ የሆናቸውም ይሄው የእናትና አባታቸው ጭቅጭቅ ነበር። ቀስ በቀስ እናትና አባታቸው የሚጨቃጨቁት በእሳቸው ምክንያት እንደሆነ አወቁ። አባባ እያሉ ሲጠሯቸው ያደጉት እንጀራ አባታቸው ወላጅ አባታቸው እንዳልሆኑም ተረዱ። ይሄ ጥሩ ስሜት አልሰጣቸውም። ውስጣቸው ባዶ እንዲሆንና ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸው ነበር።
እንዳወጉን ለማያውቁትና ፈፅሞ ለማይፈልጉት ሰው ለትዳር የተሰጡትም በእኝሁ እንጀራ አባታቸው ግፊት ነው። ሰውየው በሰፈር ውስጥ በእጅጉ የሚፈራ፣ እየታሰረ የሚፈታ፣ ጉልበተኛና ነውጠኛ ነበር። በጠጪነትም ወደር የለውም። አብዛኛውን ጥፋት የሚያጠፋውና በትዳር ውስጥ በነበሩበት ወቅት ሲደበድባቸው የነበረው በዚሁ በመጠጥ ተገፋፍቶ ነበር። በመሆኑም የትዳር ቆይታቸው ከጫጉላ ጊዚያቸው ጀምሮ የባለቤታቸው የበላይነት የነገሰበት ነበር። አካል ሳይመርጡ ቡጢ ድብደባና እርግጫ ባለቤታቸው ለእሳቸው ጉልበታቸውን እያሳዩባቸው የቆዩባቸው መገለጫዎች ናቸው።
እናታቸው በእንጀራ አባታቸው ግፊት ትምህርታቸውን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጠው ለዚህ ሰው ሊዳሩ ሲሉ ምን አልባት ከእንጀራ አባት የተሻለ ኑሮ ሊገጥምሽ ይችላል ያልዋቸው ግምትም አልያዘላቸውም። ጫናው ከፊቱ የበለጠ ከበደባቸው። ቀን በቀን ዱላ ሰለቻቸው።በአጠቃላይ እንዳወጉን ትዳር ውስጥ ሳይሆን የመከራ አረንቋ ውስጥ ተዘፈቁ። ባለቤታቸው ከሰው ተጋጭተውና ሕግ ተላልፈው በታሰሩ ቁጥር ስንቅ ማቀበሉ አማረራቸው። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በ15 ዓመታቸው የበኩር ልጃቸውንና አካል ጉዳተኛ የሆነችውን ልጃቸውን የወለዱት። ወይዘሮ ትዕግስት ሁለተኛ ልጃቸውን ሲያረግዙም በባለቤታቸው የሚደርስባቸው ድብደባና ጥቃት አልቆመም።
እኝሁ ባለ ታሪክ እንዳጫወቱን ባለቤታቸው በሴቶች ላይ በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት ባላንጣዎቻቸው እሳቸውን ለመበቀል በመፈለጋቸው ቤት ቀይረው ባለቤታቸው እናት አጠገብ መኖር ጀመሩ። ወቅቱ ሁለተኛ ልጃቸውን ያረገዙበት ነበር። እስከ አምስት ዓመት ዕድሜዋ ሙሉ ጤናማ የነበረችው በበኩር ልጃቸው የአካል ጉዳት የደረሰባት በዚህ ወቅት ነበር።
እንዳወጉን በልጃቸው ላይ የአካል ጉዳት የደረሰበት ምክንያት እንዲህ ነው። አንድ ምሽት ጠጥተው ይመጣሉ። የባለቤታቸው ታላቅ እህታቸው ከነባለቤታቸው እጅግ መልካምና ደግ ሰው ናቸው። አይወግኑም፤ ሲደበድቧቸውም ደርሰው ያስጥሏቸዋል። ይገስፁላቸዋልም። ሌላው ቀርቶ በሳቸው ምክንያት ለልጃቸው ከሚያደሉት ከገዛ እናታቸው ጋር ይጣሉላቸው ነበር። በአንፃሩ የባለቤታቸው እናት የእናት ሆድ ሆኖባቸው በልጃቸው አይጨክኑም። የፈለገ ጥፋት ቢያጠፉም ይሸፋፍኑላቸዋል። አንድ ቀን ታድያ ጠጥተው በመምጣት እንደልማዳቸው ይደበድቧቸዋል።
ሲደበደቡ ሁለተኛ ልጃቸውን ነፍሰ ጡር ነበሩ። ቢሞቱስ የሚል ስጋት የገባቸው የባለቤታቸው እህት ታድያ የበኩር ልጃቸውን ትተውላቸው እንዲጠፉና ሕይወታቸውን እንዲያተርፉ ይመክሯቸዋል። ይሄን ከትልቋ ሴት ልጃቸው ጋር ሲመካከሩ ተደብቀው የሰሙት የባለቤታቸው እናት ታድያ ለልጃቸው ሲመጡ ጠብቀው ‹‹ልጅህን ጥላ ልትጠፋልህ ነው›› በማለት ይነግሯቸዋል። ማታ ጠጥተው ይመጡና በሩን በመዝጋት ‹‹ልጅቷን ጥለሽልኝ ልትጠፊ ነው አሉ›› በማለት ያቀፏትን ህፃን ልጅ ከእቅፋቸው በመቀበል መሬት ላይ አስቀምጠው እሳቸውን በዱላ እንቺ ቅመሽ ይሏቸዋል።ድብደባው ከእርግዝናው ጋር ተዳምሮ ራሳቸውን ያስትና መሬት ላይ ይዘረራሉ።
ሁሉም ሲደበድቧቸው እየጮኸች የምታለቅሰው የአምስት ዓመቷ የበኩር ልጃቸው እናቷ መሬት ላይ ሲዘረሩ ስታይ የበለጠ እየጮኸች ታለቅሳለች። አባቷ ደጋግመው ዝም እንድትል ቢያስጠነቅቋትም ዝም ልትል ያልቻለችውን የአምስት ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ታድያ ስካር ባናወዘው መንፈስ ተነሳስተው ይገርፏታል። ግርፋቱ የአምስት ዓመት ልጁን ወላጅ የሚቀጣበት አይደለም። ከባድ ነበር። በመሆኑም ራሷን ስታ ወደቀች። ሆኖም ባለቤታቸው ህፃን ልጃቸውንና ባለቤታቸውን የወደቁበት ትተው እናታቸው ቤት ሄደው አደሩ። እናትና ልጅ እወደቁበት አነጉ። ሕፃኗ ከግርፋቱ ጽናት የተነሳ አንደበቷ እስከ መያዝ ደረሰ። ሲያድር እግሮቿ አባበጡ። ውሎ ቢያድርም ቢያንስ ወጌሻና ሌሎች ሕክምናዎችን ፈጥና ባለማግኘቷ ሁለቱም እግሮቿ ለአካል ጉዳተኝነት ተዳረጉ።
እንግዳችን በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው የሚኖሩት። ወደ አዲስ አበባ የመጡት በአባቷ ጉዳት የደረሰባትን የሰባት ዓመቷን የበኩር ልጃቸውን ለማሳከም ነበር። በአባቷ ጉዳት የደረሰባትንና በወቅቱ ሕክምና ያላገኘችውን ይህችን ልጃቸውን ለማሳከም ለ10 ዓመታት በሰው ቤት ሠራተኝነት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ለ20 ዓመታትም ተሰቃይተዋል።
አካል ጉዳተኛ ልጅን ጫናው እጅግ በከበደ የሰው ቤት ሥራ ውስጥ ቀርቶ በተደላደለ የራስ ቤት ማሳደግ ፈታኝ ቢሆንም ወይዘሮ ትዕግስት ተወጥተውታል። የተወጡት ውሏቸውን በከባድ የሰው ቤት ሥራ አሳልፈው፤ አዳራቸውን ልጃቸውን ለማሳከም የሚረዳቸው ገንዘብ ለማግኘትና ለማጠራቀም ያስቻላቸውን ዳንቴል በመሥራትም ነበር።
ወይዘሮ ትዕግስት እንዳወጉን አብዛኛው ፈተና የገጠማቸው በአካል ጉዳተኛ ልጃቸው ምክንያት ነው። አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሰው ቤት እየሰሩ ልጃቸውን ለማሳካም ሰርክ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መመላለስ ይጠበቅባቸው ነበር። ምልልሱ ይሄን አስመርምሪ፣ ይሄን አምጪ የሚል ነበር። እንዲህ እየተባለና ተኝታ የምትታከምበት አልጋ ሲጠበቅ 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። መሄድ የማትችለውን ልጃቸውን ሆስፒታል ያመላልሱ የነበረው ወንድማቸው እየተሸከመላቸው ነበር። ቀንና ሌቱን በሥራ በማሳለፍ ያጠራቀሙት ገንዘብ ሁሉ አልቋል። ሆኖም ‹‹ባለቀበት ወቅት እግዚአብሄር ረዳኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት፣ ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያገኙት ቲሻይርም የተሰኘውን የአካል ጉዳተኞች የድጋፍ ማዕከል የልጃቸውን ጤና እንደ ታደገላቸው አጫውተውናል። ቲሻይር ባደረገላት ድጋፍ እግሯ ቀዶ ጥገና ተሰርቶላት የተጣመመው ተስተካክሎላታል። ጫማም በልኳ ሰርተውላታል። አሁን ላይ በሁለት ክራንች በመታገዝ ለመንቀሳቀስ በቅታለች። ባሌ ውስጥ “ቡና ጠጡ”ም ትሰራለች።
ወይዘሮ ትእግስት እንዳጫወቱን ታድያ የዚህ ማዕከል አባላት በሳምንት አንድ ቀን ሐሙስ ሐሙስ ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፤ የአካል ጉዳተኛ ልጆችን ይንከባከቡና በሆስፒታሉ ሕክምና እንዲያገኙ ያደርጋሉ። እናም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መመላለስ ሲጀምሩ ያገኙት ድርጅት ልጃቸውን ተረከባቸው። ለአካል ጉዳተኛ ልጃቸው ሕክምና ያወጡት የነበረውን የሕክምና ወጪ ስለሸፈነላቸው ከክፍያ ነፃ ሆኑ።
እንዳወጉን አካል ጉዳተኛ ልጅ ማሳደግ በቃላት ከሚነገረው በላይ እጅግ ከባድ ነው። አካል ጉዳተኛ ልጅ ይዞ ሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራት በፍፁም አይቻልም። ሰው ይፈራል።
‹‹አካል ጉዳተኛ ልጅ አለችኝ። በትንሽ ደሞዝ ቅጠሩኝና ልሥራላችሁ ብዬ ስጠይቅ ’እንዴት ይሆናል’ ይሉኛል›› ይላሉ። በእኛ ሀገር በግለሰብ አሰሪዎች ዘንድ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የተለመደ አይደለም። ሌላው ቀርቶ እንዲህች ዓይነቷን ልጅ እናት ብዙ መከራ አይታ ካሳደገችና ካስተማረች በኋላ ልጅቷ የሥራ ዕድል የምታገኝበት ሁኔታ እጅግ ጠባብ ነው።
በአሁኑ ሰዓት በብዙ መከራ አሳድገው በአይቲ ያስመረቋት ልጃቸው የሥራ ዕድል አለማግኘቷ ማሳያ ነው። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሥራ ሲፈልጉ ካስመዘገቧት በኋላ አይደውሉላቸውም። ‹‹እኔ ተከራይቼ የምኖርባት ቤት እጅግ ጠባብና ትንሽ ቤት ናት። የአካል ጉዳተኛ ልጄ እዚህ ቤት ውስጥ ለመኖር እጅግ ትቸገራለች›› ብለውናልም።ምክንያቱም እሳቸው የሚኖሩበት ቤት የሲንክ መቀመጫ ያለው አይደለም።
ለልጃቸው የሚመቻት ደግሞ የሲንክ መቀመጫ ያለው ቤት ነው። በመሆኑም እዛው ወደ ተወለደችበትና ለመፀዳዳት የሚመቻት ቤት መከራየት ወደ ቻለችበት ባሌ ሄዳ ቡና ጠጡ እየሰራች ትገኛለች። ልጇንም እያሳደጉላትና እያስተማሩላት ይገኛሉ። ልጃቸው ልጇን ትዳር ሳትመሰርት የፍቅር ጓደኝነት ካላት ሰው ብትወልዳትም እሳቸው አባት እያላቸው አባት እንደሌላቸው የሆኑትን ሴት ልጆች ታሪክ ከእሳቸው ጀምሮ ቢነግሯትም፤ እንዲሁም አባት እያላቸው አባት አልባ የሆኑት ልጆች በሚል በፃፉት መጽሐፋቸው ውስጥ ታሪካቸውን ቢያካትቱትም በልጃቸው አልተቆጡም።
እሷ ከደረሰባት የአካል ጉዳት ክብደት አንፃር ከእሳቸው ጋር መኖር ባትችልም የአካል ጉዳተኛ ልጃቸውን ልጅ እሳቸው ጋር በማስቀመጥ በጥሩ ሁኔታ እየተንከባከቡላትና እያስተማሩላት ይገኛሉ።
እሷ በክራንች ብትንቀሳቀስም የደረሰባት የአካል ጉዳት ከበድ ያለና እንደልብ የማያንቀሳቅስ በመሆኑ በተማረችበት መስክ ሥራ በመፈለግ ያግዟታል። እሷ ቡና ጠጡ እየሰራች የዕለት ተዕለት ኑሮዋን እንድትገፋ እያገዟት ናቸው። ወይዘሮ ትዕግስት ልጃቸውን በዚህ መልክ እያገዙ በትምህርቷ የበለጠ እንድትገፋም የማድረግ ሀሳብ እንዳላቸው አጫውተውናል። አጠገባቸው ሆና እንድትማር እንደሚፈልጉም አልሸሸጉንም። ሆኖም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንዲህ እንደሳቸው ልጅ ላለ አካል ጉዳተኛ የሚመች የግለሰብ ቤት በእሳቸው አነስተኛ ገቢ ማግኘት ተግዳሮት ሆኖባቸዋል።
ወይዘሮዋ ‹‹ዛሬም አለሁ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት መጽሐፋቸውም ሆነ ለእኛ ባካፈሉት ሀሳብ እንዳስቀመጡት ወላጆች በመጠጥ ኃይል ተገፋፍተውም ሆነ በሌላ ምክንያት ከባለቤቶቻቸው አልፈው በልጆቻቸው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። በመሆኑም ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ወደ ትዳር ሲገቡ ለማንም ሕይወት መሰናክል እንዳይሆኑ ቀድመው ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል።
ልጆችም አባቶቻቸው በበደሏቸው ቂም መያዝ የለባቸውም። የእሳቸው ልጆች በዚህ ምክንያት በአባታቸው ስም የመጠራት ፍላጎት ባይኖራቸውም ከነችግሩ አባታቸው መሆኑን በማስረዳት እንዲጠሩበት ማድረግ ችለዋል። እኛም የወይዘሮ ትእግስትን ተሞክሮ አስተማሪ በመሆኑ ማንኛውም ሰው፤ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ተጠቅመውበት የልጆቻቸውንም ሆነ የራሳቸውን ሕይወት ስኬታማ ያደርጉበት ዘንድ እነሆ ያልነውን ፅሑፋችንን በዚሁ ደመደምን። መልካም ሳምንት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2014