አፍሪካ በተለይ በ19ኛው ክፍለዘመን መባቻ ላይ በአብዛኛው በቅኝ ግዛት ስር እንደነበረች አይዘነጋም። ይህ የቀጥታ የቅኝ አገዛዝ ዘመን ካበቃ ከግማሽ ምዕተአመት በኋላ ደግሞ በአብዛኛው በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር መውደቋን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። ለዚህ ዋነናው መሳሪያ ደግሞ ኢኮኖሚ ነው።
አሁን የምንገኝበት የ21ኛው ክፍለዘመን ለሰው ልጅ ምቹ የሆኑ በርካታ አወንታዊ ጎኖች ያሉት የመሆኑን ያህል በርካታ ተግዳሮቶችም ያሉበት ነው። በተለይ አፍሪካን የመሰለች ድሃ አህጉር በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች። በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ክስተቶች ከ1.3 ቢሊዮን የዘለሉትን አፍሪካውያን ለጉስቁልናና ለከፋ የኑሮ ሁኔታ ሲዳርጉ ይስተዋላል። በተለይ የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት አንጻር አፍሪካውያን ከፍተኛ ተግዳሮት አለባቸው። ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ ኢኮኖሚን ማሳደግ የግድ ነው። ይህ ደግሞ በየዘርፉን ከፍተኛ ትግል ይጠይቃል።
አፍሪካን ከቀጥተኛ የቅኝ ግዛት ማላቀቅ የቻሉ ጀግኖች አፍሪካውያን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ተስኗቸዋል። በዚህ የተነሳ በርካታ አፍሪካውያን፤ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ሲሰቃዩ ኖረዋል። በአንድ በኩል ቅኝ ገዢዎች ጥለው በሄዱት ቁርሾ አፍሪካውያን ርስ በርሳቸው ተባብረው የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ድህነት ከማሸነፍ ይልቅ ለግጭትና ለንትርክ ሲዳረጉ፤ በሌላ በኩል በውስጣቸው ባለው ችግር ኢኮኖሚያቸው ሲዋዥቅ ቆይቷል።
ድህነትና ርሃብም የአፍሪካ መገለጫ እስከመሆን ደርሷል። በዚህ አህጉር በድርቅና ይህንን ተከትሎ በሚከሰት ርሃብ የሚሞቱ እንስሳትና ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ለአብነትም በአሁኑ ወቅት 16 የአፍሪካ ሃገራት በደረሰባቸው የተፈጥሮ መዛባትና ተያያዝ ችግሮች ምክንያት ለከፋ ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ከአፍሪካ ሕብረት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች ናት። ከማእድናት ጀምሮ ለእርሻ ምቹ የሆነ ሰፊ መሬት እና ይህንን ሊያለማ የሚችል ወጣት ሃይል አላት። ከዚህም አልፎ በነዳጅ ክምችትም ቢሆን አፍሪካ ከራሷ አልፋ ሌሎች ዓለማትን እስከመመገብ የሚደርስ ሀብት የተጎናፀፈች ናት። ይሁን እንጂ እነዚህን የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም።
በሌላ በኩል አፍሪካውያን ያላቸውን ሀብት በአግባቡ አስተባብረው ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉት ትግል ጅምሩ አመርቂ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ እየተጓዘ እንዳልሆነ ምሁራን ይተቻሉ። ለአብነትም አፍሪካውያን ዛሬም ኢኮኖሚያቸውን አስተባብረው ከመስራት ይልቅ በአብዛኛው በሌሎች አህጉራት ላይ እንዲንጠለጠሉ እድርገዋል የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።
በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተመሰረተውና በኋላ ወደአፍሪካ ሕብረት የተለወጠው ተቋምም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም ገና ብዙ ፈተናዎች አሉበት። ያም ሆኖ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍ አፍሪካን ከድህነት ለማውጣት እየጣረ ይገኛል። በዚህ መሰረት የሕብረቱ አባል አገራት በአጀንዳ 2063 “የአፍሪካን ኢኮኖሚ በማስተባበር ከድህነት መውጣት” የሚል እቅድ ይዘዋል። ከዚህ አንጻር የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አንዱ ጅምር እንቅስቃሴ ነው።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ገበያ ለአፍሪካውያን ትልቅ ድህነትን የማሸነፊያ መንገድ እንደሆነ የሕብረቱ መሪዎች ይናገራሉ። በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙ መሪዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ አጽንኦት በመስጠት የንግግራቸው ማዕከል አድርገውታል።
መሪዎቹ እንደገለፁት አፍሪካውያን ከድህነት ለመውጣት ኢኮኖሚያቸውን በማቀናጀት ትልቅ ካፒታል መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የንግድ ቀጠና ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።
በዚሁ የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ፍሊክስ አንቶኒዮ ሲስኬዲኒ እንዳሉት አፍሪካውያን ከድህነት ለመውጣት ካፒታላቸውን በማሳደግ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ እንደ አፍሪካ ነጻ ገበያ አይነት እድሎች ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት ዋና ፀሃፊ ምዋኬሌ ሜኔ እንደሚሉት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አፍሪካ በንግዱ ዘርፍ የተጋረጠባትን የተወዳዳሪነት ተግዳሮት ለመፍታት አይነተኛ መሳሪያ ነው። ከዚህም ባሻገር የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጠናከር እና የአፍሪካን ልማት ለማፋጠን የሚኖረው አንድምታ ትልቅ ነው።
ይህ ዘርፍ 1 ነጥብ3 ቢሊዮን ሕዝብ ላላት አፍሪካ ትልቅ ትርጉም አለው የሚሉት ዋና ፀሃፊው በዚህ ዘርፍ በአግባቡ ከተሰራ ከአፍሪካም አልፎ በዓለም ላይ ትልቁ የነፃ ገበያ ዘርፍ በመሆን ለሌሎች ዓለማትም ትልቅ ሞዴል መሆን የሚችል ነው።
የአፍሪካ ነፃ የገበያ ማዕከልን ለማቋቋም በሩዋንዳዋ ኪንሻሳ በ2018 በተደረገው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያን ጨምሮ አርባ አገራት እስካሁን ስምምነቱን በማፅደቅ ፈርመዋል። በዚህ ስምምት መሰረትም በአፍሪካ የጋራ የሸቀጣ ሸቀጥ እና የአገልግሎት ዘርፍን በማጣመር የኢኮኖሚ ቅንጅትን በመፍጠር የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ይሰራል። ዘርፉም ከ3 ነጥብ4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ አኮኖሚን እንደሚያንቀሳቅስ ይጠበቃል።
ዋና ፀሃፊው እንደሚሉት ይህ እውን እንዲሆን የመሪዎች ቁርጠኝት ወሳኝ ነው። በተለይ ይህ ስራ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግን ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ መሪዎች ለዚህ ዘርፍ እድገት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል። በዚህ የጋራ ገበያ ላይ በተለይ ታሪፎችን መቀነስ እና በዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መለየትና መፍታት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የዓለም ባንክ በ2019 ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከሆነ፣ አፍሪካ እአአ በ2035፤ 450 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ትችላለች። በዚህ ወቅት አጠቃላይ የወጪ ንግድ መጠኑ በ29 ከመቶ የሚያድግ ሲሆን የአህጉሩ የወጪ ንግድ ደግሞ ወደ 81 ከመቶ ከፍ ይላል። ከዚህም ባሻገር ከአፍሪካ ውጭ ያለው የወጪ ንግድ በ19 ከመቶ ያድጋል። ይህ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው አንድምታ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ነው።
ይህ ስራ አጠቃላይ 30 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ከፍፁም ድህነት የሚያወጣ ሲሆን 60 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ደግሞ ከመካከለኛ ድህነት በማውጣት መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተርታ የሚያሰልፍ ነው። ይህ እንደአፍሪካ ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ ያሳያል።
በሌላ በኩል አሁን በአህጉር ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆኑ የንግድ ስምምነቶች አሉ። ከነዚህ ጋር እንዴት ይሰራል በሚል ለሚነሳው ጥያቄም ዋና ፀሃፊው ምላሽ አላቸው። እሳቸው እንደሚሉት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ገበያ ባህርይ ሌሎችን በመግፋት ሳይሆን በትብብር መንፈስ መስራት ነው።
ለምሳሌ በአፍሪካ ደረጃ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (ኢሲኤ)፣የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ)፣ የደቡብ አፍሪካ አገራት ማህበረሰብ (ሳድክ) እንዲሁም ሌሎች አህጉር እና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ የትብብር ማዕቀፎች አሉ። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ገበያም ከነዚህ ጋር ለመስራት የሚስችለውን የንግድ ሕግ በማውጣት በትብብር ይሰራል።
በአፍሪካ ያለው ኢኮኖሚ ትልቅ የመሆኑን ያህል ከዚህ ዘርፍ አፍሪካውያን በአግባቡ እየተጠቀሙ እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ከጋዝ ጋር በተያያዘ አፍሪካውያን የራሳቸውን የነዳጅ ፍላጎት ለመሸፈን የሚያስችል በቂ አቅም ቢኖራቸውም አብዛኞቹ ነዳጅ አምራች የአፍሪካ አገራት ምርታቸውን ወደ አውሮፓና ሌሎች አህጉራት ኤክስፖርት ያደርጋሉ። ከዚህም አልፎ በአፍሪካ በአንዱ አገር ያለው ምርት ወይም ሀብት በሌላው የማይገኝበት ክፍተት ቢኖርም አንዱ የሌላውን ክፍተት ከመሙላት ይልቅ ወደ ውጭ የማየት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ አፍሪካ ኢኮኖሚ በቀጥታ ለአፍሪካውያን ጥቅም እንዳይሰጥ እያደረገ ነው።
ለምሳሌ በ2017 የአፍሪካ የውስጥ የወጪ ንግድ 16.6 ከመቶ ብቻ ነበር። ይህም ማለት ከ83 ከመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ውጭ ይላካል ማለት ነው። ከዚህ ውስጥ 68 ከመቶ ወደ አውሮፓ፣ 59.4 ከመቶ ወደ ኤዥያ እንዲሁም 59.4 ወደ አሜሪካ ይልካሉ። ሆኖም በመልክአ ምድራዊ ቅርበትም ሆነ ከመሰረተ ልማት አንጻር የቅርብ ጎረቤት አገራት ክፍተቶቻቸውን መሸፈን ቢችሉ ምን ያህል የኢኮኖሚ ብክነትን ጭምር ማስቀረት እንደሚቻል መገንዘብ ይቻላል።
በአፍሪካ ሕብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ እና ኢንዱስሪ እና ማእድን ዘርፍ ኮሚሽነር የሆኑት አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ እንደሚሉት አፍሪካ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቃ የሯሷን የፋይናንስ አቅም መፍጠር አለባት። ለዚህ ደግሞ እንደ አፍሪካ ነፃ የንግድ ገበያ አይነት እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር አለባት የሚሉት ኮሚሽነሩ ከዚህም ባሻገር ከአሰራር ጋር ተያይዞ ችግሮች አንዳሉ ጠቁመዋል። ለአብነትም ከግብርና ጋር በተያያዘ የአፍሪካ አገራት ለዘርፉ ከሚመድቡት በጀት ጀምሮ ችግሮች አሉ። በአፍሪካ ለዚህ ዘርፍ የሚመደበው በጀት በአብዛኛው ከ2-5 ከመቶ ብቻ ነው። በአንፃሩ የበለፀጉት አገራት እስከ 10 ከመቶ ይመድባሉ። ስለዚህ በዚህ ላይ መሰረታዊ ልውጥ ሳይመጣ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ማምጣት አዳጋች ነው።
በአጠቃላይ አፍሪካ እነዚህና መሰል የኢኮኖሚ አማራጮችን በመለየት እና ሀብትን በማስተሳሰር ከድህነት የምትወጣበትን መንገድ ፈጥና ካላስተካከለች የምዕራባውን ጫና እያየለ መሄዱ አይቀሬ ነው። ይህ ደግነሞ አፍሪካ ራሷን ለመከለከል በማትችልበት ሁኔታ መልሳ በሌሎች ቅኝ ገዢዎች ስር እንድትወድቅ ያደርጋታል። በመሆኑም ከዚህ ችግር ለመውጣት ትክክለኛው አማራጭ ሀብት በማሰባሰብና ኢኮኖሚን በማቀናጀት በጋራ መስራት ነው። ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በአንድነት መቆም አለባቸው።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2014