መተካካት ያለ ነው። ዘላለማዊ ነገር ባለመኖሩ የማይተ(ካ)ካ ነገር የለም። የማይታደስ ሀሳብም አስተሳሰብም የለም። ካለም ያለው እድል መፈንገል ነው። የነጮቹ ቅኝ አገዛዝ የፖለቲካ ፍልስፍናም ሆነ የዘረኝነት ርእዮት “ካልተፈነገልኩ በስተቀር ….” በማለት ምሎ የተገዘተ ይመስል ራሱን እንደ ኤግል (ንስር አሞራ) እያደሰ አፍሪካን ሲያልብ ሊኖር ይፈልጋል፤ እራሱን “neocolonial power” ተብየው ኒኦ-ኮሎኒያሊዝም (እስካሁን ባለው ሁኔታ የቅኝ አገዛዝ ከፍተኛው የእድገት ደረጃ ነው (በትብብር መስራትን ያጠናክራል ተብየው Neo-corporatismም እንደዛው)።
አፍሪካን የምትታለብ ላም አድርጎ የተቀበለው የቅኝ አገዛዝና እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አራማጆቹ አእምሮ ከዚህ አስተሳሰብ ይወጣ ዘንድ ያልተሰጠው እድል የለም። ይሰጠው እንጂ እሱ ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲሉ፣ ዛሬም በዛን ዘመኑ “አፍሪካን መቀራመት” ውሳኔው ላይ እንደ ተቸነከረ ነው ያለው። መለወጥ አልቻለም፤ ሃሳቡን በተሻለ አዲስ ሀሳብ መተካትም አልቻለም። ድምፃዊው “እዛው ነኝ ለካ … እዛው ነኝ” እንዳለው ዛሬም እዛው ነው ያለው።
ፈጣሪዎቹ ለሰው ልጅ ባልመጠነ መልኩ “ሥልጣኔን” ወደ ሩቅ ሥፍራዎች ለመውሰድ፣ የዘመናዊነትን ጥቅም “ኋላ ቀር” ተብለው ለሚጠሩ ሕዝቦች ለመውሰድ ወዘተ በማለት የሚያቆላምጡት ቅኝ አገዛዝ አፍሪካን ከጥርስም አልፎ በድዱ ግጧታል። የአፍሪካ ሀብት ተዝቆ የማያልቅ ሆነ እንጂ ያልዛቀው ማእድን የለም። የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ጣራ ነክቷል ይባላል እንጂ ደቡብ አፍሪካዊያን ኪስ ውስጥ ድንቡሎ የለም። የኬኒያ ጂዲፒ …. ይባላል እንጂ ያለው እንግሊዛዊያንና ህንዳዊያን ባለ ሀብቶች መዳፍ ውስጥ ነው፤ ቶጎም ያው ነው። ከ29 አፍሪካ አገራት በላይ ቋንቋቸው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተደፍቀው ያልሆኑትን ሆነው እየኖሩ ነው። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
ይህ ያወራንለት፣ ቅኝ አገዛዝ በድዱ ግጦታል የምንልለት ጉዳይ የሀብት ጉዳይ ነው። ጉዳዩን ከአፍሪካዊያን ንፁሀን ሕይወት ጋር አያይዘን ካየነው ደግሞ የበለጠ የሚያንገፈግፍ ነው።
ዓለማችን ካካሄደቻቸው ግዙፍ ጦርነቶች መካከል አንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነቶች የሚያክል የለም። እነዚህ ጦርነቶች ምክንያታቸውም ሆነ ኢላማቸው አፍሪካ አልነበረም፤ ወይም ከአፍሪካ ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ምንም አያገናኛቸውም ብሎ ለአፍሪካውያን ሰላም የሰጠ ነጭ አልነበረም። ሁሉም ለጦርነቱ ሲማግድ የነበረው በቅኝ ከያዛቸው የአፍሪካ አገራት (አፍሪካውያንን) ነበር። ካስፈለገ በ2015 ለንባብ ከበቃው War Losses (Africa) ውስጥ ከ1914 እስከ 1918 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 2ሚሊዮን 350ሺህ አካባቢ አፍሪካዊያን ለማይመለከታቸው ጦርነት ተዳርገዋል የሚለውን ማየት ነው።
ወደ አውሮፓ ተግዘው በወታደርነት ሲያገለግሉ የነበሩ አፍሪካውያንም ቁጥር ቀላል ያልነበረ ሲሆን፤ በዚሁ ጥናት ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ሰሜን አፍሪካ 13.8/19.0 በመቶ፣ ምዕራብ አፍሪካ 15.6/22.2 በመቶ፣ ምስራቅ አፍሪካ 9.2/11.0 በመቶን ይይዛሉ። ይህ በአሜሪካ የጥጥ ምርት ዘመን የነበረውን የጉልበት ሰራተኞችን ጉዳይ ሳይጨምር ማለት ነው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የረገፉ አፍሪካውያን ወታደሮችን መረሳት Africa’s forgotten World War II veterans በሚል ርእስ የዘገበው አፍሪካ ድረ-ገፅ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አፍሪካዊያን ወታደሮች በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ቤልጂየም ማገልገላቸውን አስፍሮታል።
በአሜሪካ ሲቪል ዋር በሚል በሚታወቀው ጦርነት ብቻ በትንሹ 179,000 ጥቁሮች የአሜሪካንን ሠራዊት እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል። ሌሎች 19,000 የሚሆኑ ደግሞ በባህር ኃይል ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። ከእነዚህ መሞታቸው እንኳን የተመዘገበላቸው 40,000 ያህሎቹ ብቻ ናቸው። ሌሎች በበሽታ እንዳለቁ ሁሉ ተደርጎ ነበር ሲገለፅ የኖረው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ ወደ እንግሊዝ ከላከቻቸው የሠራዊት አባላት 150,000፤ በቬትናም ካሰማራቻቸው 300,000 የሚሆኑት ጥቁሮች ነበሩ።
እዚህ ላይ በርካታ ፀሀፍትን ሁሌም የሚያበግነው ለራሳቸው ሰዎች የሰጡትን ክብር፣ ያቆሙላቸውን ማስታወሻ ወዘተ አንዱን እንኳን ከአፍሪካ ሄዶ ለተማገደው ጥቁር አለማድረጋቸው ነው። ይህ ብቻም አይደለም፣ አንድም አፍሪካዊ መሪም ይሁን አንቂ ይህንን ጥያቄ ሲያቀርብ አለመሰማቱ ነው። ጉዳዩ ተቆጥሮ የሚያልቅ ስላልሆነ ለማሳያ ያህል ይህንን ካልን ጊዜው ወደ ፊት ይመጣ ይሆናል ብለን ወደ ሌላው እንዝለቅ።
ሶስተኛው ዓለም፣ ወይም ያላደጉ አገሮች ወይም ጭለማው አህጉር … በሚል የሚጠሩት አፍሪካ የእነሱ የህልውና ምንጭ፤ ለባለ አገሩና አህጉሩ ግን ሲኦል ሆኖ እንዲኖር የዘወትር ፀሎታቸው ነው። ለዚህም ሲባል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
ግራሀም ሀንኮክ በLords of Poverty (ደረጀ ባልቻ “የድህነት ከበርቴዎች” በሚል ርእስ ጥሩ አድርጎ ተርጉሞታል) ዐይን ከሰበከት እያገላበጠ እንዳሳየን በለፀጉ የሚባሉት አገራት አፍሪካንና አፍሪካውያንን ያላደረጓቸው ነገር የለም። በእርዳታና ድጋፍ ስም ያልተፈፀመ ግፍና አፍሪካውያን ያልቀመሱት የመከራ ፅዋ የለም። ይህ ሁሉ የሚሆነው በእርዳታ ስምና በአዛኝ ቅቤ አንጓችነት ሽፋን፤ በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች (ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ይታደጋሉ ተብለው በ1944 የተቋቋሙት አይኤምኤፍ፣ አለም ባንክ እና የመሳሰሉት) አስፈፃሚነት ነበር። አሁንም ይህንኑ ነው በአፍሪካ ላይ ማድረግ የሚፈልጉት። ዛሬም እንደውም በረቀቀ መልኩና በኖኦ-ኮሎኒያሊዝም (አሮጌ ወይን በአዲስ ጠርሙስ እንዲሉ) እና እሱን በሚያስፈፅሙበት ኒኦ-ኢምፔሪያሊዝም መሳሪያ አማካኝነት አፍሪካን መልሰው ለመሰልቀጥ እንቅልፍ አጥተው ውለው ሲያድሩ እየታዘብን ነው።
ለእነሱ የምትታለብ ላም፣ ለባለቤቶቹ ሲኦል ሆና ትቀጥል ዘንድ በአህጉሪቱ በእነሱ ተጠፍጥፎ የተሰራ መሪ፣ በእነሱ ተቀርፆ ስራ ላይ የሚውል ፖሊሲ፣ በእነሱ ተነድፎና ተረቅቆ ተግባራዊ የሚደረግ እቅድ ወዘተ ወዘተ ይፈልጋሉ። ይህ ካልሆነ በውይይት ወቅት ከቃላት ምርጫቸው (የአሜሪካው ትራምፕ ስለ አባይ ግድብ ያሉትን ያስታውሷል) እስከ ውጪ ፖሊሲያቸው ድረስ አገራትን ማፍረስን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው ይሰራሉ። ሶሪያ፣ የመን፣ አፍጋን …. የአሁኑ ዘመን፣ የቅርብ ምሳሌዎች ሲሆኑ፤ ይህ ሁሉ፣ አሁን በሶስት የምእራብ አፍሪካ አገራት የተካሄዱ መፈንቅለ መንግሥቶችን ጨምሮ የኒኦኮሎኒያሊዝም ውጤቶች ናቸው። “ለመሆኑ ኒኦኮሎኒያሊዝም (የኒዮ-ቅኝ ግዛት) ምንድን ነው?” የሚለውን ለመነሻ ያህል ብያኔውን አስቀምጠን እንለፍ።
ቃሉ በመጀመሪያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጥቅም ላይ የዋለው የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች በውጭ አገራት ላይ ቀጣይ ጥገኝነትን ለማመልከት፤ ለምሳሌ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ቀጥተኛ የውጭ አገዛዝ ባበቃበት በላቲን አሜሪካ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች (“neo-corporatism”ን ጨምሮ) እና ዓለም አቀፋዊ እና ሁለገብ ተቋማት (Bretton Woods institutions ይሏቸዋል) ተጣምረው የታዳጊ አሮችን የቅኝ ግዛት ዓይነቶች ለማስቀጠል በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። በታዳጊ አገራት ውስጥ ዕድገትን ለማገድ እና እንደ ርካሽ ጥሬ ዕቃዎች ምንጭ እና ርካሽ የጉልበት ሥራ አድርጎ ለማቆየት በቀድሞ ቅኝ ገዥ ኃይሎች እና በሌሎች ባደጉ አገሮች የተቀናጀ ጥረትን ያካተተ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች ያደጉ አገሮች በግጭቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ የውጭ ኩባንያዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ እና ከሀገራቸው ፍላጎት ጋር ለመስማማት ፈቃደኛ የሆኑ አገዛዞችን ለመጫን ይጠቀሙበታል። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ፣ በተለይ በአሁኑ ዘመን ሰብአዊ መብት ተጥሷል፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዬ ነው ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች ነው።
የአፍሪካ አገራትን በእዳ መተብተብ፣ እንዳይለሙና በእርዳታ ብቻ እንዲኖሩ በስውር በማስገደድና በሌሎች መንገዶች ይገዛሉ። እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ እና የዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ብድሮችን (እንዲሁም ሌሎች የኢኮኖሚ ዕርዳታዎችን፣ ድጋፎችን …) በማድረግ በኒዮኮሎኒያሊዝም አገዛዝ ውስጥ ይሳተፋሉ። ምንም እንኳን እሲያና ደቡብ አሜሪካ የቀመሱት ቢሆንም፣ አፍሪካ ለኒዎኮሎሊዝም ዋነኛ ምሳሌና በከፋ ሁኔታም ተጠቂ ሆና ኖራለች።
ይህ የኒዎኮሎሊዝም (በሰፊ ትርጓሜው የካፒታሊዝም እየተስፋፋ መሄድ (a further development of capitalism) ይሉታል) ዓላማ ነው እንግዲህ፣ በዚህ በዛሬው ዘመን ሳይቀር፣ እነ አሜሪካንን እያክለፈለፈ ያለውና ዓይናቸውን በጨው አጥበው አፍሪካን ለመዋጥ እያሰፈሰፉ፤ ለዚህም በቅድሚያ ኢትዮጵያን ማፍረስ ላይ እየተረባረቡ ያሉት። ይህ ግን ዓለምን የነቀነቀውን “#NoMore movement”ን ወለደ እንጂ ሌላ የፈየደው ነገር የለም። (እዚህ ላይ “የዓለም ኃያላን ዳግም አይናቸውን አፍሪካ ላይ የጣሉት ለምንድን ነው?” የሚለው በበቂ ጥናት የሚመለስ ሆኖ ማለት።) እርግጥ ነው “የአህጉሪቱ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት፣ ድንግል የግብርና መሬት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ አገራት 54 ድምፅ (ፀጥታው ምክር ቤት አለመኖሯን በአስገራሚነቱ ይዘነው)፣ በአህጉሪቱ እየጨመረ ያለው የእስልምና አክራሪነት፣ ስደት አፍሪካን ዳግም የኃያላኑ አይን ውስጥ ያስገቡ ተጠቃሽ ጉዳዮች ናቸው።” የሚሉ የባለሙያ አስተያየቶች አሉ። ይኑሩ እንጂ ለአጠቃላይ ድምዳሜ ግን ወቅታዊ ጥናቶች የግድ ይላሉ።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የሲ.ቢ.ኤስ ጋዜጠኛና የ”NoMore/በቃ!!!” ዓለም አቀፍ የጥቁር ሕዝቦች ንቅናቄ ሃሳብ አመንጪና አራማጇ ሔርሜላ አረጋዊ በቅርቡ እዚህ መጥታ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገችው ቆይታ “አሜሪካ የሽብር ቡድኑን የምትደግፈው የራሷን አጀንዳ የሚያስፈፅም መንግሥት ለመመስረት በማሰቧ ነው። አሜሪካም ሆነች አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት አሁን ባለው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ደስተኛ እንዳልሆኑና ይህም ደግሞ የሆነው እንደ አሸባሪው ሕወሓት የእነርሱን አጀንዳ የሚያስፈፅም መንግሥት ስላልሆነ ነው። የዐቢይን መንግሥት ያልፈለጉት ዐቢይ እጅግ ጠንካራና እርሱ በሚመራት አገር ላይ ለእነርሱ ፍላጎት የማያጎበድድ መሆኑን ስለተረዱ ነው።” ማለቷ ዝም ብላ ከስሜት ተነስታ፤ ወይም ያአገሯ ጉዳይ ሆኖባት ብቻ ሳይሆን እነዚህነና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ታሪካዊና ፖለቲካዊ መሰረቶች ስላሏት ነው።
ይህ የሄርማላ “NoMore/በቃ!!!” ንቅናቄ በንቅናቄነቱ ብቻ የሚቀር አለመሆኑን እያየን ነው። ንቅናቄው ዓለምን ከማጥለቅለቁ፣ መላው ጥቁርን በአንድ ከማሰለፉም ባለፈ መሬት ወርዶ በተግባር እየታየ ሲሆን፣ ለዚህም የሰሞኑ የማሊ የፈረንሳይኛ ቋንቋን ከብሔራዊ ቋንቋነት ማውረድና የፈረንሳይን ጦር ባይኔ እንዳላይ ማለቷና አምባሳደሩን ከአገሯ ማስወጣቷ የ”በቃ!!!” እንቅስቃሴና እንደ አድዋው (ልክ እንደ ኢትዮጵያዊነት/ኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ) ሁሉ የአሁኑም ዘመን የኢትዮጵያ አርአያነት ውጤት ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። ይህ ደግሞ በሌሎች፣ አዲሱ ቅኝ አገዛዝ ሊውጣቸው ባሰፈሰፈባቸው አገራት ስለ መቀጠሉ ምንም መጠራጠር አይቻልምና የኒኦ-ኮሎኒያሊዝምም ሆነ (New Imperialism) የኒኦ-ኢምፔሪያሊዝም አምላኪዎች ከወዲሁ አቋማቸውን ሊፈትሹ፣ “የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዬ ነው” የሚሉትንም ፈሊጥ መልሰው ሊመረምሩ ጊዜው ግድ ይላቸዋል።
ይህ ጸሐፊ በአንድ ወቅት “ያልተጻፈው ሕግ እና አሜሪካ” በሚል ርእስ በዚሁ ጋዜጣ ላይ፤ “አሜሪካ ሀብታም ነች፤ አሜሪካ ኃያል ነች። አሜሪካ የዓለም ሁሉ የበላይ ብቻ ሳትሆን የዓለም ፖሊስ ነች፤ አድራጊ ፈጣሪ፣ ሿሚና ሻሪ፤ አጉራሽና አልባሽ ወዘተ አድርጋ እራሷን አስቀድማ በመሾሟ ምክንያት ይሄው እውቅና በዓለም ተሰጥቷት ያሰበችውን ሁሉ ስትሆን ኖራለች። መሾምም ሆነ መሻር፣ ማግኘትም ሆነ ማጣት፤ መሞት ሁሉ ሳይቀር አሜሪካ ካልፈቀደች እንደማይሆን አድርጎ ዓለም ሁሉ ተቀበለ። ተቀብሎም የማይሻር ታሪክ፣ የማይገሰስ ማንነት አድርጎት አረፈው። ይህንን መልካም አጋጣሚ የተጠቀመችው አሜሪካም እነሆ፣ “ኧረ እንዳሻሽ ..” እንዳለው ዘፋኙ እንዳሻት ስትሆን ክፍለ ዘመናት ተፈራረቁ። 21ኛው ክፍለ ዘመን ባተ።” በማለት ጽፎ ነበር። አሁንም እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለፍትህና ለዓለም አቀፍ የሕግ የበላይነት እጅ ሲሰጥ፤ አሜሪካም አደብ ስትገዛ አልታየምና አቋም የሚያስቀይር ነገር አልተገኘም።
የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ በመጋቢት 2020 ንግግራቸው ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩሲያና ሌሎች አገሮች አፍሪካን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ከፍተኛ ፉክክር እንዲያቆሙ” ያስጠነቀቁ ቢሆንም እስካሁን ኒኦኮሎኒያሊዝም ክንፉ ሊሰበር አልቻለም። እዚህም እዛም ሲፈልጉ በመንግሥት ግልበጣ፣ ሲያሻቸው ደካማ መንግሥት በመፍጠር፣ አልሆን ካላቸው በቀለም አብዮት፣ የሽብር ቡድን በማቋቋም ወይም በመደገፍ …. ብቻ በተገኘው ሁሉ አፍሪካን ከመዳፋቸው ላለማውጣት ግብ ግብ ውስጥ ከሆኑ ቆይተዋል። ለዚህ ደግሞ የጅቡቲው መናኸሪያቸውን ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው። ቀይ ባህር … ቀይ ባህር … የሚሉትንም እንዲሁ።
ይህ የምእራባውያን አፍሪካን፣ በተለይም ግንባር ቀደም ነች ተብላ የምትፈራውን ኢትዮጵያን የመደቆስ ነገር በቀድሞው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስና አዲስ ተድላ ዳጎስ ያሉ መጸሕፍት ውስጥ ተገቢውን ስፍራ ይዞ በበቂ ማስረጃ የተብራራ ርእሰ ጉዳይ ነውና እነሱን መመልከት እያደረጉ ያሉት ጥቃት አዲስ የተጀመረ አለመሆኑን መረዳት ይቻላል።
የስካር ሁኩ እስኪመስል ድረስ አሜሪካ እየባሰባት እንጂ እየተሻላት አይመስልም። አፍሪካ ከእጄ ከወጣች አለቀልኝ አይነት የሞት ሽረት ትግል እስኪመስል ድረስ እየተጋጋጠች ትገኛለች። (Françafrique) ማለትም “French Africa” (የፈረንሳይ አፍሪካ) በማለት የሰው ምድር እንደራሷ አድርጋ ስትበዘብዝ የኖረችው ፈረንሳይም በዚሁ ሰሞን አይታም፣ ሰምታም፣ ገምታም ይሁን ተንብያ የማታውቀው ተቃውሞ ከማሊ እየገጠማት ይገኛል። ይህ ደግሞ በሌሎቹም ስለ መቀጠሉ ምልክት እንጂ ሌላ አይደለም። (ለነገሩ እኮ አፍሪካን እንግሊዝኛ ተናጋሪ እና ፈረንሳይኛ ተነጋሪ (አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ) በማለት ለሁለት አይደል እንዴ የቅኝ ግዛት ዘመን የከፈላት?) ይህ ነገር ይብቃንና እናጠቃለው።
ትናንትናና ከትናንት በስቲያ (ጥር 28 እና 29) 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንም አሳልፏል። የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ “የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር በማሰብ አሸባሪው ሕወሓትን ሲደግፉ የነበሩ የውጭ ኃይሎች የአዲስ አበባን ገጽታ የማበላሸት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትን ያህል አህጉር አቀፍ ጉባኤ መካሄዱ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት የነበራቸውን ፍላጎት እና ተስፋ የሚያከስም” መሆኑን፣ እንዲሁም “የጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ኢትዮጵያን በሚመለከት እየታየ ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቀየር የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ዕድል” እንደሚፈጥር መናገራቸውን አስታውሰን፤ እንዳሉትም የነበረውን የአመለካከት ዝበት መቀየሩን ጠቅሰንና፣ ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ በአውሮፓ አገሮች ውስጥ ብቅ ያለው አዲስ የቅኝ ገዥዎች ሰብአዊነት የጎደለው የኒኦኮሎኒያሊዝም ፍልስፍናን እና ኒኦ-ኢምፔሪያሊዝም ከምድረ አፍሪካ ጠራርገው የሚያስወጡበትን ስልት በመቀየስ የተሳካ ሥራ የሚሰሩበት የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው፤ ኒዮ-ቅኝ ግዛትም ለፍትህና ርትእ እጅ የሚሰጥበት ዘመን እንዲሆን በመመኘት ነው።
አፍሪካ ታሸንፋለች!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም