አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈፀመው ወረራ በተለየ ሁኔታ በትምህርት ተቋማት ላይ
ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ተቋማት ወድመዋል፣ ትምህርት ተቋርጧል፣ ቤተሙከራዎችና የአይ.ሲ.ቲ ማዕከሎች ተዘርፈዋል።
በአጠቃላይ በትምህርት ቤት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የሚወስደውን ወስዶ፣ የቀረውንም አበላሽቶ የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዳይቀጥል አድርጎታል።ከእነዚህ ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ውስጥ በአምባሰል ወረዳ የሚገኘው የማርዬ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ እንደአብዛኛው የገጠር ትምህርት ቤት የተጎሳቆለ ባይሆንም ከውጪ ለሚመለከተው ውበቱ ሳታዩኝ አትለፉ የሚያስብል ግርማ ሞገስ አለው።
ጥቅጥቅ ብሎ ባደገው አረንጓዴ ሳር የተሸፈነው ኳስ ሜዳ፣ በረጃጅም ፅዶች ያሸበረቁት መተላለፊያ መንገዶች፣ የቀለም ቅባቸው ከሩቅ የሚጣራው ውብ ሕንፃዎች፣ በቅጥር ግቢው የሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች የመንገደኛን ቀልብ የሚስቡ ናቸው።
ትምህርት ቤቱ ከውጪ ካየሁት በላይ ወደ ውስጥም ገብቼ ስጎበኘው ሙሉ በሙሉ በአረንጓዴ ሳሮች የተሸፈነ፣ የሕንፃዎቹ አቋም ፍፁም ያልተቀየረ፣ እንዲያውም በደማቅ የቀለም ቅብ አሸብርቀው ማዶ ለማዶ ተራርቀው የቆሙ ሕንፃዎች የጎብኚን ስሜት ጎትተው የሚያስቀሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።
ከቅጥር ግቢው እንደገባሁም ከርዕሰ መምህሩ ቢሮ በር ላይ «ማርዬ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1963 ዓ.ም ተመሠረተ» የሚል ማስታወቂያ ተለጥፏል። ይህም ማለት ትምህርት ቤቱ ዕድሜው 50ኛ ዓመቱን ባለፈው ዓመት እንዳከበረ ለአስተዋይ ገላጭ ነው።
ትምህርት ቤቱ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ያደገው በ2003 ዓ.ም እንደሆነም ከስር የሚጠቅስ ጽሑፍ ይታያል። በ1963 ዓ.ም ሲመሠረት ጀምሮ አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ የተማሩ በርካታ ምሁራን መፈጠሪያ ቦታም ለመሆኑ አብረውን በቦታው ተገኝተው የመሰከሩ ሰዎችም ነበሩ።
በአገራችን ትልልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ፕሮፌሰሮች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ኢንጂነሮች የወጡባት ትምህርት ቤት ናት – ማርዬ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ (የቀድሞዋ አንደኛ ደረጃ) ትምህርት ቤት። ይህ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ወደ መሃል አገር በመዝለቅ ባደረገው ወረራ ሳቢያ ብዙ ውድመት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ የደረሰበትን ውድመት ያስጎበኙን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ሺመልስ እርቅይሁን፤ ትምህርት ቤቱ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባለው ዕድሜው ብዙ ጦርነቶች የተደረጉበት ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ዘረፋና ውድመት አስተናግዶ እንደማያውቅ ይገልፃሉ።
ተዘዋውረን በጎበኘንበት ወቅትም የታዘብነው ወራሪው ኃይል በአካባቢው በቆየባቸው ጊዜያት ያወደማቸውና የዘረፋቸው የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎች በርካታ መሆናቸውን ነው። ለምሳሌ ከርዕሰ መምህሩ ቢሮ ጀምሮ ያሉ መስተዋቶች ረግፈዋል፣ በመማሪያ ክፍል ውስጥ ያሉ ፐላዝማዎች ተሰባብረዋል፣ ከቤተመጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ መጻሕፍት ተዘርፈዋል፣ በቤተሙከራ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ማይክሮስኮፖች ተሰባብረዋል፤ ግማሾችም ተዘርፈዋል፣ በአይሲቲ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ኮምፒዩተሮችም እንዲሁ ተነቃቅለው ተወስደዋል፡፡
እንደ ጥቁር ሰሌዳ ያሉ ሌሎች የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎች ተሰባብረው በየቦታው ወድቀዋል።በመምህራን ስታፍ ውስጥ የሚገኙ ኮሜዲኖዎችም ለጊዜው ቢጠገኑም ጉዳት እንደደረሰባቸው ያሳብቃሉ፤ በወረቀት ላይ የሚገኙ መረጃዎች ተቀዳደው ተጥለዋልም።
የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች ከውጭ በኩል መስኮታቸው በተሰካኪ መስተዋት የተሠራ በመሆኑ በቀላሉ ለማፈራረስ ችለዋል። በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት መስኮቶቹ በቆርቆሮ ተሸፍነው ክፍሎቹ አገልግሎት መስጠት ችለዋል። አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ ሕንፃዎቹ ተቦርቡረው ፈራርሰዋል። ወገን እንደ ወገን ማድረግ እንዳለበት በማሳሰብ መምህር ሽመልስ ወደ መማሪያ
ክፍሎቹ ይዘውን ገቡ። በየመማሪያ ክፍሉ ተሰባብረው የተገኙ የተማሪ መቀመጫዎችና ጠረጴዛዎች በአንድ ላይ ተሰብስበው የተቀመጡበትን መጋዘን ክፍልም ለማየት ችለናል። የመማሪያ ክፍሎች ኮርኒሳቸው ተበሳስቶ፣ በራቸው ተገንጥሎ፣ አለፍ ሲልም ግድግዳቸው ላይ በትግርኛ ቋንቋ በተፃፉ ጥቅሶች ተሞነጫጭረው አይተናል። የስነልቦና ጫና ለማሳደር የተለያየ ቦታ ላይ የተለያዩ ጽሑፎች ይታያሉ፡፡
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የመምጣት ሁኔታ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የመላክ ጉጉታቸው፣ ተስፋቸው ተሰብሮ ቢገኝም ሁኔታውን ለመቀነስና ጫናውን ለማርገብ ትምህርት ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ መምህር ሺመልሽ ገልፀውልናል።
በመምህራን ስታፍ ውስጥ የሚገኘው የመምህራን ልዩ ልዩ መረጃዎች ማስቀመጫ ከብረት የተሠራ ሳጥን ተፈልቅቆ ከጥቅም ውጪ በመደረጉ፣ ለጊዜው መጠነኛ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። የአንዱ ሎከር የመስሪያ ዋጋ ወደ 12 ሺህ ብር የሚገመተው በዚህ አሸባሪ ቡድን መውደሙ አጠቃላይ የትምህርት ቤት ማህበረሰቡን እንዳሳዘናቸው መምህር ሺመልስ ገልፀዋል።
አንዳንዶችም ገና ተሠርተው ከመግባታቸው ወራሪው ኃይል በመምጣቱ ጥቅም ላይ ሳይውሉ የወደሙ የመምህራን ሎከሮች እንደተገኙ መምህር ሺመልስ አጫውተውናል። ትምህርት ቤቱ ራሱን የቻለ የንብረት ማስቀመጫ መጋዘን የሌለው በመሆኑ የመማሪያ ክፍሉን የንብረት ክፍል በማድረግ ሲጠቀሙበት እንደነበር የገለፁት መምህር ሺመልስ፤ በውስጡ በሥርዓት ተዘጋጅተው የተቀመጡ ንብረቶች (ደስታ ወረቀቶች፣ እስኪርቢቶዎች፣ ጠመኔዎች እና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች) ተዘርፈው እንዳገኟቸው አብራርተውልናል።
ሌላው በዚህ ክፍል ውስጥ ወላልቆ ያየነው የድምፅ ማጉያ ሞንታርቦ ሲሆን፤ አዲስ እንደነበር አስተውለናል፣ ቴሌቪዥን እንዲሁም ኮምፒዩተሮች ከነአክሰሰሪያቸው ተሰባብረው ወድቀዋል፡፡ ይህ ሁሉ ውድመት የተማሪውን እና የመምህራንን ቅስም የሚሰብር እንደሆነም ርዕሰ መምህሩ አቶ ሺመልስ በቁጭት ነግረውናል።
ይህ ወራሪ ኃይል ምን ያህል አገርን እንደሚጠላና አገርን ለማፈራረስ ያለመ ቡድን እንደሆነ ያሳየበትን ሁኔታ ሲገልፁም ቡድኑ የአገሪቱን ባንዲራ ከተሰቀለበት ምሰሶ ላይ አውርዶ እንደቀደደውና ከጥቅም ውጪ እንዳደረገው አሳይተውናል። በሚያድጉ ሕፃናት ዕጣ ፈንታ ላይ ይህን ያህል ጉዳት ማድረስ ከሰብዓዊ ፍጡር የሚጠበቅ ባለመሆኑ እጅግ እንዳሳዘናቸውም አልደበቁም። እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለፃ፤ የትህነግ ወራሪ ቡድን በወቅቱ ትምህርት ቤቱን ካምፕ አድርጎት እንደቆየና የትምህርት ቤቱን ትልልቅ ሀብቶች፣ ንብረቶች ከፊሎቹ ወድመው፣ የተረፉት ተጭነው ተወስደዋል።
እንደ ፕሪንተር ማሽን፣ ኮፒ ማሽን፣ ፕላዝማዎች፣ የተማሪዎች መማሪያ ኮምፒዩተሮች፣ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። የተማሪ መቀመጫ የነበሩትን ኮባይንድ ዴስኮችን በመፍለጥ ለማገዶነት ሲጠቀሙበት እንደቆየም ርዕሰ መምህሩ አጫውተውናል። በአጠቃላይ ግምታቸው ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ የትምህርት ቤቱ ግብዓቶች መውደማቸውን በተመለከተም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በዝርዝር አሳውቀናል ብለዋል። ነገር ግን እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍና ምላሽ እንዳልተገኘ ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የግል ባለሀብቶች ይህን ትምህርት ቤት እንዲታደጉት በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል። በከተማው ወራሪው ቡድን በቆይታው ከግለሰብ እስከ ተቋም ድረስ ዘረፋና ውድመት ሲያደርስ ቆይቷል። የወራሪ ቡድኑ ወደ አካባቢው መምጣትን በተመለከተ ርዕሰ መምህሩ በበኩላቸው ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት እንዳስከተለባቸው ከደረሰባቸው ገጠመኝ በመነሳት እንደሚከተለው አጫውተውናል።
ወቅቱ የመምህር ሺመልስ አባት በጠና የታመሙበት ጊዜ ነበር፤ በዚያኑ ሰሞን ደግሞ የትህነግ ወራሪ ቡድን ወደ አካባቢው ድንገት ይገባሉ፡፡ ማህበረሰቡ ደግሞ ቤቱን ዘግቶ ከብትና ፍየሎቹን ይዞ ወደ ዋሻ አቅንቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በሰፈሩ አንዳችም ጎረቤት አልነበረም።
መምህር ሺመልስም የታመሙ አባታቸውን ጥለው መውጣት ስለከበዳቸው ብቻቸውን በቤት ውስጥ ይቀራሉ። ከጥቂት ቀን በኋላ አባታቸው ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ በዚህ ጊዜም ከጎረቤት ተለይተው ብቻቸውን እንዲቀብሩ ተገደዋል፡፡
ይህ ደግሞ የማይረሳ ጠባሳ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ እንደርሳቸው ያለ ችግር ያጋጠማቸውና ወደ ጫካ ማምለጥ ያልቻሉ ጥቂት ሰዎች በዙሪያቸው ባይኖሩና ባያጽናኗቸው ኖሮ ዛሬ በሕይወት መቆየት እንደማይችሉም ነው በእንባ ጭምር የሆነውን ክስተት የሚያስታውሱት፡፡
በመጨረሻም ከእዚሁ የትምህርት ተቋማት ውድመት ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አቤ በቅርቡ ከአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ነፃ የወጡ የትምህርት ተቋማት ያሉበትን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ወራሪው ቡድን በአማራ ክልል በቆየባቸው ወደ ሰባት በሚሆኑ ዞኖች ከ4ሺህ170 በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በዚህም ወደ 1ነጥብ 9 ሚሊዮን ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። በተጨማሪም ከ116,000 በላይ መምህራን የዚህ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። አቶ ወንድወሰን እንደሚሉት፤ የነበረው ሁኔታ ትምህርት ለማስጀመር በጣም ከባድ ነው።
ጠላት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም በወቅቱ መጠለያ ብቻ ሆነው ሲያገለግሉ ስለነበር ትምህርት ተቋርጦ ነበር። በእነዚህም ትምህርት ቤቶች ያሉ ግብዓቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ስለዚህ በጥቅሉ በትምህርት ሴክተሩ ላይ የደረሰው ጉዳት በጣም ከባድ ነው። እናም ይህን ውድመት ወደነበረበት ለመመለስ ወደ 20ነጥብ2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። እነዚህን ነገሮች በአንድ ጊዜ መሟላት በጣም ከባድ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ የትምህርት ሥራ ለነገ የሚባል አይደለም። ባለው ሁኔታ ትምህርት መጀመር አለበት፡፡
ትምህርት ቤቶቹን በሂደት ወደነበሩበትና ከዚያም በላይ ይቀየራል፡፡ አሁን ግን ይህን ሁሉ ማሟላት ስለማይቻል ባለበት ሁኔታ ትምህርት ማስጀመር ያስፈልጋል የሚለውን ሀሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት አቅጣጫ በማስቀመጥም ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ጥቁር ሰሌዳ፣ ጠመኔ፣ መማሪያ መጻሕፍትና መምህራን ካለን ድንጋይ ላይም ተሆኖ፣ ዛፍ ጥላ ስርም ተቀምጦ የትምህርቱ ሥራ መጀመር አለበት የሚለው አቋምም የሁሉም በመሆኑ ሥራው እንደተጀመረም አስረድተዋል፡፡
የጠላት ዓላማ እንዳይሳካ ሁሉም መምህራን፣ ተባባሪ አካላትም ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ያሉት ኃላፊው፤ በእልክ ጊዜ ሳይባክን ወደ ሥራ መግባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ከታኅሣሥ 16 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 15 ድረስ በሁለት ሴሚስተር አዲስ ካላንደር ተዘጋጅቶ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩን ሥራ ጀምረዋል።
ነገር ግን አሁንም ትምህርት ለማስጀመር አስቸጋሪ የሆኑባቸው እንደ ሰሜን ወሎና ዋግኽምራ ያሉ አካባቢዎች እንዳሉ ተናግረዋል። ትምህርት ከማስጀመር ጎን ለጎን ደግሞ የትምህርት ቤት ግብዓቶችን የማሟላት እና ወደነበሩበት የመመለስ ሥራ እየተሠራ ነው።
አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከነበረው ጉዳት አንፃር በቂ አይደለም። በመሆኑም ተጨማሪ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል አቶ ወንድወሰን። በዚህም እስካሁን ትምህርት ቢሮው ለስምንቱ ዞኖች፣ ለአራቱ መምህራን ኮሌጆች ወደ 20 ሚሊዮን ብር በተማሪ ቁጥር በማስላት ድጋፍ አድርጓል። ይህም ትምህርት ለማስጀመሪያ ያክል ብቻ (የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ ጠመኔና አንዳንድ ወሳኝ ነገሮችን) ለማገዝ የተደረገ ነው። በተጨማሪም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችም የተገኙ ደብተርና እስኪርቢቶዎችንም ለማሰራጨት ተሞክሯል።
በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ዩኒሴፍና ሌሎች ተባባሪ አካላት ያደረጉት ተሳትፎ የጎላ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ መምህራን የአዕምሮ ጤናና የስነልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛል።
ስልጠናውን መውሰድ የሚገባቸው ከአንድ መቶ ሺህ በላይ መምህራን ቢኖሩም ከሀብት ውስንነት የተነሳ ሦስት ሺህ የሚጠጉ መምህራን ብቻ ስልጠናውን ወስደዋል። ስለዚህም አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እኛም እንደ ማርዬ ዓይነት ትምህርትቤቶች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች አሉና ድረሱላቸው በማለት ሀሳባችንን ቋጨን።
በዘላለም ግርማ
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014