እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? በጣም ጥሩ። ልጆች፣ ባለፈው ሳምንት ስለ በየነ አጫውቻችሁ ነበር። አስታወሳችሁ? በበላይ ዘለቀ ቁጥር 2 ትምህርት ቤት በአዕምሮ እድገት ዝግመት ምክንያት ልዩ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ስልጠና ከሚወስዱት ልጆች መካከል አንዱ ስለሆነው በየነ ተጨዋውተን ነበር። አዎ፣ በየነ ጎበዝ፣ ታታሪና የተማሪ ፖሊስ ሁሉ ሆኖ እያገለገለ የሚገኝ ተማሪ መሆኑን ተጨዋውተናል። ዛሬ ደግሞ ስለሁሉም፣ ማለትም ከሱ ጋር ትምህርትና ስልጠናቸውን ስለሚከታተሉት ልጆች በአጠቃላይ እነግራችኋለሁ።
በበላይ ዘለቀ ቀ. 2 ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚገኙት የትምህርት ቤቱ ማህበረሰቦች መካከል በአእምሮ እድገት መዛባት ምክንያት የአካል ጉዳት ያለባቸው ልዩ ተማሪዎች ይገኙበታል። እነዚህ ልዩ ተማሪዎች በቁጥር 34 ሲሆኑ ሁለቱም ፆታዎች የተካተቱበት ነው።
ልጆቹ ወደ በላይ ዘለቀ ቁ.2 ከመምጣታቸው በፊት በቃ አይድኑም፤ ምንም አይነት ሥራ መሥራት አይችሉም፤ የሚያስተምራቸውም ሆነ የሚንከባከባቸው የለም ተብለው እቤት ሲውሉ የነበሩ ናቸው። አንዳንዶቹም ጭራሽ ከቤት እንዳይወጡ ተደርገው ተዘግቶባቸው ሁሉ የሚውሉ ነበሩ። ቤተሰብ በቃ ልጄ አይድንም/አትድንም በማለት ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ከቤት ሁሉ የማያስወጣቸው ነበሩ። ነገር ግን የትምህርት ባለሙያዎች፣ ኃላፊዎች መምህራንና ሌሎች አካላት ባደረጉት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ወላጆች እነዚህን ልጆች እንደ በላይ ዘለቀ ቁ. 2 ትምህርት ቤት አይነቱ እድል ወዳለባቸው ትምህርት ቤቶች እየወሰዱ ማስመዝገብ ጀመሩ። እየተከታተላችሁኝ ነው አይደል ልጆች፤ በጣም ጥሩ።
እነዚህ ይህንን እድል ያገኙ ተማሪዎች እንደ መደበኛው ትምህርት ሁሉ በሙያው የሰለጠነ መምህር ተመድቦላቸው ክትትልና ክብካቤ የሚደረግላቸው ሲሆን፤ የጽሑፍ፣ የንባብ፣ የእጅ ሥራ እና ሌሎች ስልጠናዎችን ሁሉ እየወሰዱ ይገኛሉ። ደስ አይልም ልጆች፣ ሁሉም ልጆች ትምህርት ቤት ውለው፣ ተምረውና ሰልጥነው ሲመጡ ደስ ይላል።
ልጆች የእነዚህን ልጆች ችሎታ የምታደንቁላቸው እቦታው ላይ ተገኝታችሁ የሠሯቸውን ሥራዎች በሙሉ ስታዩላቸው ነው። ምክንያቱም ሁሉንም ሥራዎች እዚህ ጋዜጣ ላይ ማሳየት ስለማይቻል ነው። እዛ ሄዳችሁ ብታዩ የሠሯቸው ሥራዎች ብዙ ናቸው። የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ሠርተዋል፤ እየሠሩም ነው። አትክልት (አበቦችን ሁሉ) ተክለው እየተንከበከቡ ነው፤ አሁንም ሌሎች የእፅዋት አይነቶችን እየተከሉ ናቸው። ኳስ ይጫወታሉ፤ እርስ በርስ ይወዳደራሉ። ከወዳደቁ እቃዎች የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤት የመሳሰሉ ሥራዎችን ይሠራሉ። ብቻ ብዙ ብዙ ነገር ይሠራሉ።
አያችሁ ልጆች፣ እነዚህ አይችሉም፣ አይሠሩም፣ እንደውም ከነጭራሹ አይድኑም የተባሉ የእናንተ እኩዮች ይሄንን ሁሉ ያደርጋሉ። ደስ አይልም ታዲያ ልጆች፣ በጣም ደስ ይላል።
እኔ በላይ ዘለቀ ቁ. 2 ትምህርት ቤት ተገኝቼ ያየኋቸውን ልጆች እናንተም ብታዩዋቸው በጣም ጎበዞች ናቸው። አንዳንዶቹ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱትና ወደ ቤት የሚመለሱት እራሳቸውን ችለው ነው። የማንንም እርዳታ አይፈልጉም። በፊት ምንም መናገር የማችሉት ሁሉ አሁን መናገር ሁሉ ችለዋል። በፊት አካላቸውን ማንቀሳቀስ የማይችሉትና ምግብ እንኳን ሳይቀር ሰው የሚያጎርሳቸው አሁን ሰውነታቸውን በስፖርት በማፍታታቸው ምክንያት እጃቸውን፣ እግራቸውን፣ ባጠቃላይ መላ ሰውነታቸውን ማንቀሳቀስና ምግባቸውንም እራሳቸው መጉረስ ችለዋል። በፊት ከቤት እማይወጡትና ሰው ሁሉ ይፈሩ የነበሩት አሁን ከጓደኞቻቸው ጋር ሲጫወቱ ነው የሚውሉት። ማህበራዊነትን በሚገባ ተላምደዋል።
እኔ ሄጄ ያየሁት የበላይ ዘለቀ ቁ. 2 ትምህርት ቤት ለእነዚህ ልጆች ብዙ ነገር እያደረገላቸው ነው። ቦታዎችን አመቻችቷል፤ የስፖርት መሣሪያዎችን ገዝቶላቸዋል፤ ጥሩ ጥሩ መምህራንን መድቦላቸዋል። ከርዕሰ መምህሩ ጀምሮ የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በሙሉ ፍቅር ይሰጣቸዋል፤ ይከታተላቸዋል። መምህራኖቹም ልክ እንደ ቤተሰብ ነው የሚንከባከቧቸው።
ልጆች፣ እዚህ ጋር አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ አዎ፣ እነዚህ ልጆች የፈለገውን ያህል ቢለወጡና ቢሻላቸውም ልክ እንደ ትምህርት ቤቱና መምህራኖቻቸው ሁሉ ወደ ቤት ሲመለሱም ወላጆቻቸውና አጠቃላይ ቤተሰቡ ተመሳሳይ ክትትልና ድጋፍ ካላደረገላቸው የጤናቸው ሁኔታ እንደ ገና ወደ ነበረበት ይመለሳል። ስለዚህ፣ ያ እንዳይሆንና የልጆቹ የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ እንዲሄድ ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ልጆች እናንተ ትምህርት ቤት፣ ወይም ሰፈር፣ ወይም ጎረቤታችሁም ሆነ ቤታችሁ ውስጥ እንደዚህ አይነት ፍቅር፣ ድጋፍ፣ ክትትል ወዘተ የሚፈልጉ ልጆች ካሉ ልክ እንደ መምህራኑ ሁሉ እናንተም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዳድታደርጉላቸው፤ እሺ ልጆች። ታደርጋላችሁ አይደል? በጣም ጥሩ።
በመጨረሻ ምን ልነግራችሁ እንደምፈልግ ታውቃላችሁ ልጆች፤ አዎ፣ በመጨረሻ ልነግራችሁ የምፈልገው በየአካባቢያችሁ እንደዚህ አይነት ልጆች ካሉ ቤተሰቦቻቸው ወደ በላይ ዘለቀ ቁ. 2 ትምህርት ቤትን የመሳሰሉ ትምህርት ቤቶች ወስደው እንዲያስመዘግቡ እንድትነግሯቸው ነው። ትነግሯቸዋላችሁ አይደል ልጆች፣ በጣም ጥሩ ልጆች፤ በጣም ጥሩ።
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ደህና ሁኑ!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014