በተገባደደው የጥር ወቅት የኢትዮጵያ የቱሪዝምና ባህል ዘርፍን የሚያነቃቁ የማህበረሰብ እሴቶችን የሚያጎሉና ጎብኚዎችን የሚስቡ አያሌ ሁነቶች ተካሂደዋል። ከእነዚህ ውስጥ በአማራ ክልል የተከበሩት የጥምቀት፣ የአገው ፈረሰኞች ክብረበአልና፣ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር የተከበረው ደማቅና ቀልብን የሚስበው የፈረስ ጉግስ ውድድር ይገኝበታል። እነዚህን ሃብቶች በማበልፀግ ፣ በመጠበቅና ባህላዊና ማህበረሰባዊ እሴቶችን ጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግ የቱሪዝም ሃብት ማድረግ እንደሚገባም የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ጎብኚዎችና አመራሮች አመላክተዋል።
የአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል
ክብረ በዓሉ ባሕል፣ ጥበብ፣ ውበት እና ታሪክ በአንድ መድረክ የሚቀርቡበት ልዩ ትዕይንት ነው። የፈረሰኞች ጥበብ በእጅጉ ያስደምማል። ፈረስ ለአዊ ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው።የጥበብ ማሳያውም ሆኖ የሚታይበት በዓል መኾኑ ተመስክሮበታል። የአዊ ሕዝብ ባሕል በውብ አለባበስና አጨፋፈር የሚደምቅበት ቀንም ነው። ክብረ በዓሉ የታሪኩ መነሻም የአገውን ሕዝብ ጀግንነት የሚያወሳ በመሆኑ ድባቡን የተለየ ያደርገዋል። የበዓሉ ታሚዎች ክብረ በዓል አይረሴ እና ድንቅ ትውስታዎችን የሚጎናፀፉበት በመኾኑ የአገው ፈረሰኞች ክብረበዓል ወደፊት ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ የሚኾን ነው። ዘንድሮውም 82ኛው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር በዓል በድምቀት ተከብሯል።
መርቆሬዎስን በደብረታቦር
የፈረሰኛው ሰማእት ቅዱስ መርቆሬዎስን ለመዘከር የሚከበረው የንግሥ በዓል ደብረታቦርን ከሚያስናፍቁ በዓላት አንዱ መሆኑን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በበዓሉ የፈረስ ጉግስ ትርዒት ክብረ በዓሉን በጉጉት እንዲጠበቅ የሚያደርግ ኹነት እንደሆነም ይናገራል። ይህ በየዓመቱ ጥር 25 ቀን በድምቀት የሚከበር ክብረ በዓል ሃይማኖታዊ ክንውኖቹ፣ ባሕላዊ ወጉ ሳቢ ሆኖ ከዓመት አመት የታዳሚዎቹም ቁጥር እያደገ የመጣ ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ነው።
“የፈረስ ጉግስ ባሕል ታሪካዊና አገርን መጥቀም የሚችል ስለኾነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” የሚሉት ደግሞ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የውጪ ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም መልኬ ናቸው።
የሰማእቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ ክብረ በዓልና የፈረስ ጉግስ ትርዒት በደብረ ታቦር ከተማ አጅባር ሜዳ በተካሄደበት ወቅት የፈረስ ጉግስ ባሕል በተመለከተ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳሉት ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ፈረስን በመጠቀም ጠላትን ድል አድርገዋል። ለምሳሌ በዓድዋና በማይጨው ጦርነት ለተገኘው ድል ፈረስ የማይተካ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ነገሥታት ፈረሶቻቸውን “አባ” እያሉ ይጠሩ ነበር። ለአብነትም አፄ ቴዎድሮስ ፈረሳቸውን አባ ታጠቅ፣ አፄ ምኒልክ አባ ዳኛው ብለው ይጠሩ ነበር” ብለዋል።
በሃይማኖት አስተምህሮት ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ተዋጊ በመሆኑ የፈረስ ጉግስ ትርዒቱ ሰማእቱን የሚዘክር እንደሆነ በጥናታቸው ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ደረጃ ተወዳጅ፣ የአባቶችን ታሪክ የሚዘክርና ለሀገር ገቢ ሊሆን የሚችለውን የፈረስ ጉግስ ትርዒት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት ሊሠራበት እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። የፈረስ ጉግስ ባሕል ትኩረት ከተሰጠው ጎብኚዎችን በመሳብ ገቢን ከማስገኘት በተጨማሪ ሀገሪቱን በዓለም ደረጃ እንደሚያስተዋውቅ ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያውያን ድንቅ የኾነውን ባሕላቸውን በመጠበቅ እና በማስተዋወቅ ለትውልድ ሊያስተላልፉት ይገባል” በማለት በስፍራው ተገኝቶ መስህቡን የጎበኘው ሕንዳዊው ዶክተር ቪቬክ ጋንጂ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጠው አስተያየት ተናግሯል። ህንዳዊው ዶክተር ጓደኞቹ እንዲህ ዓይነት ጥንታዊነቱን የጠበቀ በዓል ከኢትዮጵያ ውጭ ዐይተን አናውቅም ብለዋል። ኢትዮጵያውያን የአባቶቻቸውን ተጋድሎ በዚህ መልኩ መዘከራቸው ተገቢ እንደሆነም ነው የገለጸው። ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ወቅት ድንቅ የሆነውን የኢትዮጵያውያን ባሕል ለጓደኞቻቸው እንደሚያካፍሉ እና ሌሎችም መጥተው እንዲጎበኙ እንደሚያስተዋውቁ ሕንዳውያኑ የበዓሉ ታዳሚዎች ገልጸዋል።
የዓለም ቅርስ ምዝገባን በተመለከተ
ደብረ ታቦር የዘመናዊነት ብርሃን የፈነጠቀባት እና የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የበኩርና መናገሻ እንደነበረች በማውሳት የሰማእቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ንግስ እና የፈረስ ጉግስ ትርዒት በደብረ ታቦር የዓለም ቅርስ ሆኖ ሊመዘገብ እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ ናቸው። ካለፉት ነገስታት እና መንግሥታት ያተረፈችው በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ትውፊት አላትም ብለዋል።
ከጋፋት እስከ ሰመርንሃ፣ ከአሪንጎ አቦ እስከ የተክሌ አቋቋም ትምህርት ቤት፣ ከቤተልሄም እስከ ዙር አባ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ቦታዎች ናቸው ብለዋል። በዞኑ እና በደብረ ታቦር ከተማ ዙሪያ የሚገኙትን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ለማስተዋወቅ የቅዱስ መርቆሬዎስ ንግስ እና የፈረስ ጉግስ ትርዒት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ሊመዘገብ እንደሚገባ አቶ ይርጋ ጠይቀዋል። የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናት እና ምርምር እንዲያግዙም ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል። ፈረስ እና የፈረስ ጉግስ በጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ታሪክ ውስጥ አሻራቸው ጉልህ ነው ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ትውልዱን ለማስተማር እና ሀገር ተረካቢ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት እነዚህን መሰል ታሪካዊ እና ባህላዊ ትውፊቶች ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ መውጫ
በመግቢያችን ላይ ለማውሳት እንደሞከርነው በጥር ወቅት በተለይ በአማራ ክልል ውስጥ አያሌ ለጎብኚዎች አስደናቂ ምልከታን የሚፈጥሩ፣ የማህበረሰቡን እሴቶች የሚያጎሉ፣ የቱሪዝም እድገት ላይ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ክብረ በዓላትና ትርኢቶች ይካሄዳሉ። የእነዚህን ሃብቶች ታላቅ ዋጋ መረዳት ኢትዮጵያውያን ለዓለም ህዝብ ያላቸውን ሃብቶች፣ ፀጋዎች፣ የራስ ክብርና ማንነት በአግባቡ ማሳየት እንዲሁም ወደ ኢኮኖሚ አቅም መቀየር ይቻላል። በሰሜኑ ክፍል ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አሁን ከምናገራቸውና ማሳየት ከቻልናቸው የቱሪዝምና ባህላዊ ሃብቶች በእጅጉ የላቁና ያልተዋወቁ እሴቶች አሉን። በመሆኑም ቀስ በቀስ ሃብቶቹን ማሳየትና ማስተዋወቅ ከዚያም አገርና ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014