የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለ35ኛ ጊዜ የኅብረቱ መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህ የፓን አፍሪካኒዝም አጀንዳዎችና ልዩ ልዩ ቀጠናዊና አህጉራዊ ትስስር እንደ መወያያ አጀንዳ በተነሳበት ጉዳዮች “አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚሹ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ አቅጣጫ ተቀምጧል።
አፍሪካ ከኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች አጀንዳዎች በተለየ አህጉሩን በባህል፣ በቋንቋና ልዩ ልዩ ስነ ልቦናዊ መስተጋብሮች አንድ በማድረግ ኃያልና የማይበገሩ “አንድ ጠንካራ” ኅብረት መፍጠር እንደሚያስፈልግ የፓን አፍሪካን አስተሳሰብ አቀንቃኝ የሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዋናነት ከኢኮኖሚውና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች በዘለለ በባህል፣ ኪነጥበብና በቱሪዝም ሃብቶች እርስ በእርስ የተጋመደች አህጉር መፍጠር ለሁሉም ነገር መሠረት እንደሚሆን ያምናሉ። በተለይ እጅግ ብዙ ዝንቅ ማንነቶችና ባህላዊ ሀብቶች ያላቸው አገራት በአህጉሩ መኖራቸው ለዚህ እሳቤ ስኬት እንደሚረዳ ነው የሚያነሱት።
አቶ አበረ አዳሙ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና ጋዜጠኛ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ጠንካራ የባህልና የስነ ልቦና ትስስር በአፍሪካውያን መካከል የመፍጠር ዋነኛ ግቡ በኢኮኖሚና በስልጣኔ ጠንካራ አህጉር ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ደግሞ ባህልን፣ ቋንቋን የሚያውቅና የጋራ እሴቶችን የሚያዳብር ፍላጎት ያለው አንድ ማኅበረሰብ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
“በአፍሪካውያን መካከል የባህል ትስስር እንዲኖር ከሚያደርጉ እሴቶች መካከል ስነ ፅሁፍ፣ ኪነጥበብና ሌሎች ልዩ ልዩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ሃብቶች ናቸው” የሚሉት አቶ አበረ፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እየጠነከረ ሲሄድ በአህጉሩ የሚገኙ ባህሎችን፣ ማንነቶችንና በውስጣቸው የሚገኙ ሀብቶችን እርስ በእርስ እያስተሳሰሩና እያስተዋወቁ መሄድ ያስችላል ይላሉ። ይሄ እየሰፋ ሲሄድ ተዛምዶው አሊያም ቤተሰባዊነቱ እየጠነከረ ሄዶ በኢኮኖሚ የዳበረ፣ የበለፀገና ለልመና የማይንበረከክ አፍሪካን መገንባት ይቻላል የሚል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
“ ለምሳሌ ያህል ብናነሳ የቡርኪናፋሶ አጨፋፈርና የሙዚቃ ባህል በአስገራሚ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኘው የአገው (አዊ) ብሄረሰብ ጋር በእጅጉ ተመሳስሎና ተዛምዶ አለው” የሚሉት አቶ አበረ፤ አፍሪካውያን በእጅጉ የተቀራረበና የተመሳሰለ ማንነት ያላቸው ማኅበረሰቦች መሆናቸውን በምሳሌነት ያነሳሉ። በሩዋንዳ የሚገኙ ቱትሲዎችም ቢሆኑ የዘር ግንዳችን ከኢትዮጵያ የሚመዘዝ ነው በማለት ማስረጃዎችን የሚያቀርቡ ሲሆን ከዚህ አንፃር መላው አህጉሩን መቃኘትና ጥናት ማካሄድ ቢቻል ያልተዛመደ ባህልና ያልተጋመደ ማንነት የሌለው ሕዝብ ማግኘት እንደማይቻል ይናገራሉ። ይህን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አፍሪካውያንን ይበልጥ በስነልቦናና በጠንካራ ማንነት ላይ እንዲቆሙ የሚያስችል ባህላዊ ትስስር መፍጠር እንደሚቻል ይገልፃሉ።
“የደራሲያን ማኅበር በ2003 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ደራሲያን ጉባኤ አካሂዶ ነበር” የሚሉት አቶ አበረ በዚያ ጉባኤ ላይ የአህጉሩ ጸሐፍቶች ዋና መቀመጫ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ እንዲሆንና ደራሲዎቹም ስለ አፍሪካ ባህል፣ ማንነት፣ ታሪክና ስነ ልቦና በተደራጀ መንገድ በስነ ጽሑፎቻቸው ላይ እንዲያንፀባርቁ ለማድረግ ሙከራዎች ተደርገው እንደነበር ይገልፃሉ። ይህን ሙከራ በተቀናጀ መልኩ መሬት ላይ ለማውረድና እውን ለማድረግ አሁንም ከመንግሥታቱ ጥረት ባሻገር ሁሉም አፍሪካዊ በአጀንዳነት ሊያንፀባርቀው እንደሚያስፈልግ ነው ምክረ ሃሳባቸውን የሰጡት።
“ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ ነች። መገኛ ብቻም ሳይሆን የስነ ጽሑፍ ፊደል ካላቸው አንዷም ኢትዮጵያ ነች። እኛ አፍሪካውያንም የዓለም ሕዝብ በሙሉ መነሻ ኢትዮጵያ እንደሆነች እናምናለን” የሚሉት አቶ አበረ አዳሙ አብዛኛዎቹ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ስር ከማለፋቸውም በላይ ቋንቋቸው ከራሳቸው ማንነት ያልተቀዳና የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብ የተጫነው መሆኑን ይገልፃሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢትዮጵያውያን ለመላው አፍሪካ ምሳሌ የሚሆን የራሷ ፊደል ያልተበረዘ ባህልና ስነልቦናዊ ጥንካሬ ያለው ማኅበረሰብ ያላት ስለሆነ ይህንን እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅሞ “በፓን አፍሪካ ቅኝት” አንድ አፍሪካን መገንባት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
“ለዚህ ሁሉ መሠረት የሚሆነው የማኅበረሰቡ እሴቶችን የሚያንፀባርቀው ባህል ነው” የሚሉት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት፤ ይህ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የሁሉንም በአህጉሩ የሚገኙ አፍሪካውያን እሴቶችን የሚያንፀባርቁ ተቋማት ሊፈጠሩ እንደሚገባ ይናገራሉ። በመዲናዋ አዲስ አበባ እስካሁን ድረስ የአፍሪካውያንን ባህል፣ ማንነት፣ ሙዚቃ፣ ስነ ጽሑፍና ሌሎች አያሌ እሴቶች የሚያንፀባርቁ ሙዚየም አለመኖሩ በራሱ እንደ ትልቅ ክፍተት ሊታይ እንደሚገባ ያነሳሉ።
ከሰሞኑ በመዲናችን አዲስ አበባ የተሰናዳው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤም “አፍሪካን በባህል” የማስተሳሰር ጉዳይን እንደ ቀዳሚ አጀንዳ አድርጐ በቀጣይ ጊዜያት ሊመክርበትና ውጤታማ ሥራ እንዲከናወንም አቅጣጫ ሊያስቀምጥ እንደሚገባ ጥቆማ አድርገዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአፍሪካ አህጉር የምድራችን ሁለተኛውን ትልቁን የቆዳ ስፋት ከኤሺያ ቀጥሎ የያዘች ሲሆን 54 አገራት በውስጧ አቅፋ የያዘች ነች። ከዚህ ውጪ በእጅጉ አስደናቂ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት፣ ብሔረሰቦች፣ ባህላዊ እሴቶች፣ በርካታ ቋንቋዎች፣ ቅርሶችና አያሌ የመስህብ ስፍራዎች ከየትኛውም አህጉር በላቀ መልኩ የያዘች እንደሆነ ይነገራል። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ከስልጣኔ፣ የምጣኔ ሃብት፣ ከዲሞክራሲና ጠንካራ ኅብረት ፈጥሮ ከኃያላን አገራት ተርታ ከመሰለፍ አንፃር እጅግ ወደኋላ ቀርተዋል የሚባሉ አገራትን አቅፋ እንደያዘች ይነገራል። ለዚህም ነው አያሌ ምሑራን ይህን መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ “አፍሪካዊ መፍትሄ በአፍሪካውያን” በማለት ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ጫና መፍጠር እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን የሚሰጡት። ከዚህ ባለፈ አህጉሩን ለማስተሳሰር በተለይ “ባህልና መሰል እሴቶች” ላይ መሥራት እንደሚገባ አበክረው ይመክራሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014