ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን እያጋጠሟት እንደሆነ ማስረዳት ለቀባሪው አረዱት ነው። ብዙ ልጆቿ በጦርነትና በኮቪድ ገብራለች። አሁንም ብዙዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው እየተንከራተቱ ይገኛሉ። በድርቅም የተመቱ አካባቢዎች አሉባት። ይሁን እንጂ ሁሉንም መስመር ማለፍ ታውቅበታለችና ያንን ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች። ከመቼውም ጊዜ በላይ አንዱ ለአንዱ ኗሪነትን ከማሳየቱም በላይ ሁሉም የተቻለውን ለሁሉም እያደረገ ይገኛል። የተቸገረው ሳይቀር ለባሰበት እየደረሰም ነው።
ከራሱ አልፎ አፍሪካውያንን ጭምር ለማስተሳሰር በፈታኝ ጊዜ ውስጥ ሆኖ ኑ እንመካከር ሲል ደግሶ ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ እያደረገ ነው። በተለይ ሰላም ለእርሱ ምግቡ እንደሆነ ያውቃልና ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር በየፊናው ተሯሩጧል። ይህንን የጸጥታ ሁኔታ በድርጅታቸው በኩል ቢሆንም ኃላፊነት ወስደው ከሚሠሩትና ቀደም ብለውም ለአገራቸው ሰላምና ጸጥታ የበኩላቸውን ሲያበረክቱ የቆዩት ለዛሬ በ‹‹ ሕይወት ገጽታ ›› አምዳችን ያቀረብናቸው ኢንስትራክተር ፍሬሕይወት ሽታዬ ወይም ብዙዎች በሚያውቋቸው ስማቸው ማስተር ፍሬው አንዱ ናቸው።
እንግዳችን አገር የገጠማትን ፈተና በተለይ በሰላምና ጸጥታው ጉዳይ ደከመኝ ሰለቸኝን ሳያውቁ የሚሠሩ ናቸው። ከዋና አገልግሎት ሰጪነታቸው በተጨማሪ የዲፕሎማሲ ሥራዎችንም ይሠራሉ። በተለይም የእጀባ ሥራና ጥበቃ ሥራው ላይ የአገር የጀርባ አጥንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አሁንም በድርጅታቸው አማካኝነት ለአገር ፈተና የሆነውን የሰላምና ጸጥታ ሥራ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን እየሠሩ ናቸው። እናም ይህ የሕይወት ልምዳቸው ብዙዎችን ያስተምራልና ብዙዎች በሚያውቋቸው ስማቸው እያነሳን ከተሞክሯቸው እንድትቋደሱ ለንባብ አቀረብንላችሁ።
ታዛዡ ልጅ
ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ነው። ጅማ ፈረንጅ አራዳ ውስጥ። በዚያች ሰፈር ብዙ የልጅነት ትዝታዎችን አሳልፈዋል። ቦርቀዋል፤ ብዙ ጓደኞችን አፍርተዋል። የተለያዩ ለዛሬ መሠረት የጣሉባቸውን ሥራዎችም የለመዱት በዚች ከተማ ላይ ነው። ጎረቤቱን እናቴ፣ አባቴ፤ አጎቴና አክስቴ ብለው ብዙ ዘመድ አዝማድ እንዳላቸው አስበው ያደጉባት ሰፈርም ይህቺው ፈረንጅ አራዳ ናት። ምክንያቱም ሁሉም ለሁሉም ቤተሰብ በመሆን ተቆጥተውና ተንከባክበዋቸው ፍቅርን አውርሰዋቸው አድገዋል። ስለዚህም ትዝታቸውን ሲያነሱት ‹‹ዛሬ የኖርኩት እነርሱ በሰጡኝ ፣ በአዋጡልኝ ፍቅርና ባህሪ ነው›› ይላሉ።
ማስተር ፍሬው የዛሬ ሕይወታቸው ጅማሮና መሠረት የተጣለው በዚያች ከተማና ሜዳ ላይ ነው። ምክንያቱም ስፖርትን ወደውና ኖረውት አድገውበታልና። ከጨዋታ ብቻ አንጻርም አይመለከቱትም ነበር። ነገ የሚኖሩበት እንደሚሆን በልጅነት አዕምሯቸው ያስቡታል። እንዳሰቡትም እዚያው ልጅነታቸው ላይ ሆነው እናታቸውን በደንብ ያገዙበት ሙያ ይህ እንደሆነ አይተዋል። በተጨማሪ የበኩር ልጅ በመሆናቸውና አባት ብዙውን ጊዜ ውትድርናው ላይ በማሳለፋቸው ቤተሰባቸውን ማገዝ የእርሳቸው ኃላፊነት እንደሆነ አምነውም ታናናሾቻቸውን ከመቆጣጠር ባለፈ መከታተሉ፤ እንደአባት መምከሩንና መምራቱን የተያያዙት ስፖርት ለእርሳቸው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ምግብ መሆኑን ስለተረዱ ነው።
ባለታሪካችን በባህሪያቸው ቁጡና ተደባዳቢ ቢሆኑም ለሁሉም ሰው ግን መልካም አሳቢ ናቸው። ሰዎችን ማገዝ ከሁሉም ነገር ያስደስታቸዋል። እርሳቸው ባይኖራቸውም ካላቸው ላይ ማካፈል ይወዳሉ። እንደውም በድህነት ውስጥ እንዳሉ እያወቁ እንኳን ከእነርሱ የባሰ ካዩ ማለፍ አይሆንላቸውም። እናታቸው አረቄና ጠላ በማውጣት ነው የሚተዳደሩት። አባትም ከውትድርና ደሞዛቸው ተቆራጭ በማድረግ ነው ቤቱን የሚደጉሙት። ግን ይህም ሆኖ ማንም ለማንም ሰስቶ አያውቅም። ከቤተሰቡ የተማሩት ይህንን ስለሆነ እርሳቸውም ለሌላው የሰፈር ሰው የሚሰስቱት ነገር የለም። በዚህም ሁሉም የሚመርቃቸው አይነት ልጅ እንደነበሩ ያነሳሉ።
ማስተር ፍሬው እናታቸው ብቻቸውን ስለሚያሳድጓቸው በብዙ መንገድ ያግዟቸዋል። አረቄ በማውጣት ጭምር ከእርሳቸው ጎን ነበሩ። እንጨት ፈለጣውማ አይነሳ። ምግብም መሥራቱ እንዲሁ ጥሩ ሙያተኛ ያሰኛቸው እንደነበር አይረሱትም። በዚህ ደግሞ ዘወትር ይመረቃሉ። ይህንን ደግሞ ሲያስረዱ ‹‹የእናቴና አባቴ ምርቃት ብቻ ሳይሆን የሰፈር ሰዎች ምርቃት ጭምር ዛሬን አሳይቶኛል›› ይላሉ። ከነበራቸው ልምድ በመነሳትም መሥራትና ስፖርተኛ መሆን እንዲሁም ሰዎችን ሳይሰስቱ ማገልገል መንገድን እንደሚያቀና ይናገራሉ።
የራስ ጥረት ለህልም
እርሳቸው ቤተሰብን ማስቸገር በምንም መልኩ አይፈልጉም። በተለይ እናታቸውን ማገዝ እንጂ ከእርሳቸው ሳንቲምም ሆነ ሌሎች ነገሮች መቀበል አይሆንላቸውም። በዚህም ትምህርታቸውን ሲማሩ ሊስትሮ እየጠረጉና ሎተሪ እየሸጡ ነው። ማለትም የስፖርት አቅሙና ስልጠናው ኖሯቸው ወደሥራ እስኪገቡ ድረስ። በዚህ ደግሞ ዛሬ ድረስ በእጅጉ ይደሰታሉ። በራሳቸው ጥረት ብዙ ነገሮቻቸውን ለውጠዋልና በድርጊታቸው ይረኩበታልም።
የእንግዳችን የትምህርት ጅማሮ አሃዱ ያለው በዚያው በተወለዱበት አካባቢ በሚገኘው ሄርማታ ትምህርት ቤት ነው። ምንም እንኳን ሥራ ቢበዛባቸውም እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ የደረጃ ተማሪ ሆነው ትምህርታቸውን ተከታትለውበታል። ከዚያ በመቀጠል በጅማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን፤ እስከ12ኛ ክፍል በዚህ ቆይተዋል። ማትሪክ ሲወስዱም ዩኒቨርስቲ የመግቢያ ውጤት ካመጡት መካከል አንዱ ሆነው ነው። በዚህም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጁን መቀላቀል ችለዋል።
በዩኒቨርስቲው የአካውንቲንግ ትምህርት መስክን መርጠው ዓመት ያህል የቆዩ ሲሆን፤ ስፖርት ወዳድነታቸው ግን እንዲቀጥሉበት አላስቻላቸውም። እናም በዚህ ይብቃኝ ብለው ስፖርታዊ ስልጠናዎች ላይ ማተኰሩን ተያያዙት። እንዳሰቡትም በማርሽያል አርቱ በኩል እስከ ማስተር ድረስ የሚያደርስ ትምህርትን ቀስመዋል። ዛሬ ደግሞ ኢንስትራክተር ሆነዋል።
ስፖርታዊ ስልጠናቸውን የጀመሩት ገና በልጅነታቸው ሲሆን፤ በጅማ ከተማ አንድ ቻይናዊ ጋር ነው። መሠረታዊ የስፖርት ትምህርትን ቀስመውበታል። ከዚያም ይህንኑ ትምህርት ለማጠንከር ወደ አዲስ አበባ አቀኑ። ጋልጋሪ ቻይኒሲ ኩንፉ ኢኒስቲትዩት በተባለ ማሰልጠኛ ውስጥ ገብተው ከውጪ በመጡ መምህራን ሰለጠኑ። በከፍተኛ የስፖርት አሰልጣኝነት ተመረቁም።
ትምህርት በቃኝን የማያውቁት ማስተር ፍሬው፤ ሙያውን በጣም ማሳደግ ይፈልጋሉና ወደ ጣሊያን አገር አቀኑ። በዚያም ሁለት ስልጠናዎችን ወሰዱ። የመጀመሪያው በጀነራል ሴኩሪቲ ግሩፕ ውስጥ በሴኩሪቲ ኢንፎርሜሽን ትምህርት መስክ የተመረቁት ነው። ሌላው በኢንስትራክተርነት ማዕረግ በኪዮን ኩንፉ ሰበን ስታር ማማንቲስ ትምህርት ቤት ሚላን ከተማ ላይ የወሰዱት ነው።
በ17 ዓመታቸው በኢትዮጵያ አየር ወለድ የኮማንዶ ኮርስና የፓራሹት ዝላይ ስልጠናናን በመጨረስ የተመረቁት ማስተር ፍሬው፤ በአሜሪካ ሴኪውሪቲ አካዳሚም እንዲሁ የሴኪውሪቲ ኦፊሰር ስልጠናን ወስደዋል። በሽአንጋሪ አሌክሳንደር ኢንተርናሽናል አሶሴሽን ኦፍ ማርሽያል አርትስ የጥቁር ቀበቶ አባል የሚያደርጋቸውን ትምህርትም ቀስመዋል። በተመሳሳይ በካናዳ ማርሻያል አርት አሶሴሽን ስታንዳርድ ሰልጥነው የማስተር ማዕረጋቸውን አግኝተዋል። አሁንም ቢሆን ትምህርት በቃኝ አላሉም። ከስፖርቱ ጋር በተያያዘ መሰልጠን ያለባቸውን ትምህርት ይቀስማሉ። የሁልጊዜ ሥራቸው ማስተማር በመሆኑም ሁልጊዜ እንደሚማሩ ያስባሉ።
ስፖርትን በሥራ
መሥራትን የለመዱትና የወደዱት ገና ልጅ እያሉ እናታቸውን ሲያግዙ ነው። በልጅነታቸው ለቤተሰቡም ጭምር የገቢ ምንጭ ለማግኘት ያልሞከሩት ሥራ አልነበረም። አንዱና ዋነኛው ሊስትሮነት ሲሆን፤ ብዙ ጊዜያትን አሳልፈውበታል። ቀጣዩ ደግሞ ሎተሪ የማዞር ሥራ ነበር። ይህም ብዙ ጊዜ ቤታቸውን ደጉመውበታል። የራሳቸውን ወጪም ቢሆን ሸፍነውበታል። በእርግጥ ቤቱ የሚሞላው በእርሳቸው ገቢ ብቻ አልነበረም። እናት አረቄና ጠላ እየሸጡ የቻሉትን ያደርጋሉ። አባትም ቢሆኑ ምንም እንኳን በዘመቻ ብዙ ጊዜያትን ቢያሳልፉም ለእነርሱ ሳይሆኑ ቀርተው አያውቁም። ከወር ደመወዛቸው ላይ እየቆረጡ በመላክ ቤቱ ሙሉ እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ስለዚህም የቤቱ ደስታ ሁሉም በሚሳተፉበት የገቢ ምንጭ ነው የሚደምቀው። በዚህም ደስተኛ ሆነው ዓመታት እንደተቆጠሩ ያነሳሉ።
ከፍ ብለው በስፖርቱ አቅማቸውን ሲያሳድጉ ደግሞ የገቢ ምንጫቸው በስፖርት ማሰልጠኑ የሚያገኙት ሆነ። ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ከቤተሰቡና ከአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከስፖርቱ ያገኙት ጨዋነትና ስነምግባር ነው። እንደውም ይህ ባህሪያቸው ገና በልጅነታቸው መኪና ከመንዳት አልፈው አለማማጅ ሆነው የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሰፋላቸው ሆኗል። ጣሊያን አገር ከመሄዳቸው በፊት በወቅቱ ውድ የተባሉ መኪኖችን እንዲነዱ አስችሏቸዋል።
በቀጣይ የሠሩበት ቦታ አዲስ አበባ ሲሆን፤ በመሠረታዊ የስፖርት ትምህርታቸው ‹‹ፍሬሕይወት ማርሽያል አርት ሴንተር›› በሚል ትምህርት ቤት ከፍተው ነው። ስሙ ይህ ቢሆንም በወቅቱ ማርሽያል አርት ማሰልጠን አይፈቀድምና ስፖርት ማሰልጠኛ አድርገውታል። ሆኖም ማርሽያል አርቱን ግን በድብቅም ቢሆን ከመስጠት አልተቆጠቡም። የመርካቶ አካባቢ ልጆች እየመጡላቸው ስልጠናውን ይሰጡ ነበር። ነገር ግን ነገሮች እየተሻሻሉ ሲመጡ በይፋ ሥራውን እንዲጀምሩ ሆነዋል። እናም በስፖርት አሰልጣኝና መምህርነታቸው ጣሊያን አገር እስኪሄዱ ድረስ 15 ዓመታትን አገልግለውበታል።
ቀጣዩ የሥራ ሁኔታቸው የሚያደርሰን ጣሊያን ላይ ሲሆን፤ ከ12 ዓመት በላይ የቆዩበትም ነው። መጀመሪያ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሚላን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በማስተማር እገዛ ያደረጉት ባለታሪካችን፤ የኮሚኒቲው ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ማኅበራትን እስከማደራጀትና መምራት ድረስ የሚደርሱ ሥራዎችን አከናውነዋል። ከዚያ በኢታል ፖል ተቀጥረው ከጀነራል ሴኩሪቲ ግሩፕ ጋር በመሆን ሳንሲሮና አካባቢ በሚገኝ ቪአይፒ ሞል ውስጥ በደህንነት ኃላፊነት እያስተባበሩ ከስድስት ዓመት በላይ ቆይተዋል። ይህ ሥራና ትምህርታቸው ሲያልቅ በቀጥታ የጣሊያን ልምዳቸውን ይዘው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ጣሊያንን ትተው የመጡበት ዋነኛ ምክንያት መንፈሳዊ ቅናት ስለያዛቸው እንደነበር ያጫወቱን ማስተር ፍሬው፤ ልክ እንደተመለሱ መጀመሪያ የገቡበት ሥራ ቀደም ብለው ይሠሩበት የነበረውን ጅም ማጠናከርና አስፍቶ መሥራት ነው። በብዙዎች ዘንድ እውቅናን እንዲያገኝም አስችለውበታል። ምክንያቱም ከጣሊያን ሲመለሱ በርካታ የጅምና የስፖርት ማሰልጠኛ መሳሪያዎችን ይዘው መጥተዋል። በዚህም ‹‹ቴክኖ›› የተባለው ጅማቸውን ሁሉም አውቆት እንዲጠቀምበት እድል ሰጥቷቸዋል።
አገር በመንግሥት የጸጥታ አካል ብቻ ነገሮችን ማስተካከል አትችልም። ብዙ ሊያግዟት የሚችሉ ተቋማት መመሥረት እንዳለባቸው የሚያምኑት እንግዳችን፤ የጥበቃና እጀባ ሥራውን ኢት ፖል ሴኩሪቲ በማለት በተደራጀ መልኩ የጀመሩት ይህንን ችግር ይፈታል ብለው ስላሰቡ ነው። በጊዜው ሥራውን ሲጀምሩ ሁኔታው አስቸጋሪና ፈታኝ ሆነውባቸው ነበር። ተስፋ አስቆራጭ ነገሮችም ገጥመዋቸዋል። ነገር ግን በቀላሉ ተስፋ መቁረጥን አያውቁምና በብዙ ትግል ህልማቸውንና የመጡበትን አላማ አሳክተውታል። በዚህም በርካታ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ሆነዋል።
ሥራው 12 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ከባባድ የሚባሉ የመንግሥት ስብሰባዎችን በጸጥታው መስክ ያገዙበት ነበር። ለአብነት የሰኔ 16ቱ የመድረክ ላይ ጥበቃና እጀባ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የተሳተፉበት አንዱ ነው። በጊዜው ብዙ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከማዳን እስከ ማኅበረሰቡን ማረጋጋት ድረስ የደረሰ ተግባር ፈጽመውበታል።
‹‹የግል ጥበቃ በአገራችን አልተለመደም። ሁሉ ነገር በፖሊስ ብቻ መጠበቅ አለበት ተብሎ ይታሰባልም። ይህ ደግሞ ለብዙዎች ፈተና ከመሆኑም በላይ እድገታችንንም ወደኋላ እየጎተተው ነው። በዚህም ነጻና ገለልተኛ የሆነ አካል በዚህ ዘርፍ ካልሠራ በስተቀር መለወጥ አይችልም። ምክንያቱም የውጪ ዜጎች ጭምር የሚፈልጉት የግለሰብ አጃቢና ከመንግስት ጋር ያልተነካካ ጠባቂ በመሆኑ እነርሱን ለመሸፈን አስቸጋሪ ያደርገዋል። ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን እርሳቸው እየሠሩበት ያለው ተቋም ይህንን ችግር የሚፈታ እንደሆነ ያነሳሉ። አሁን አገር ካለችበት ፈተና አንጻርም ብዙ መፍትሄ የሰጠ እንደሆነ ይናገራሉ።
ድርጅታቸው ተጨማሪ የአገር ደህንነት አካል እንደሆነ ያምናሉ። በዚህም ብዙ ለውጦችን እንዳመጡበት ያስባሉ። ለአብነት የሚያነሱትም ኮንሰርቶችና ልዩ ልዩ ነጻ የውይይት መድረኮች ላይ ፖሊስ እንዳይገባ የሚባልባቸውን ክፍሎች እነርሱ መሸፈን መቻላቸውን ነው። በዚህ ድርጊታቸው የአገርና የሕዝቡን ሰላምና ጸጥታ እንዳስከበሩ ይሰማቸዋል። ተጨማሪ አቅም በመሆን ለአገራቸው ገቢ እንዳስገቡም ያምናሉ። ምክንያቱም የውጪ ዜጎች በድረገጻችን በኩል እየመጡ ይህንን አገልግሎት ሲያገኙ ዶላር ያስገባሉ። በተመሳሳይ የሚመጡትንም ሆነ የመጡትን ስለአገሪቱ ደህንነት ተገቢውን መረጃ በመስጠት የዲፕሎማሲያዊ ሥራም ይሠራሉ። ከዚያም አልፈው ቻርተር በመያዝ ላሊበላ ድረስ በመጓዝም ያስጎበኛሉ።
‹‹አገሬ ምንድነው የምታረግልኝ ብዬ አላውቅም። ምክንያቱም ከማሳደግ በላይ ምንም እንድታደርግልኝ አይጠበቅባትም። አስተምራኛለች፤ ማንነትንም ሰታኛለች። ከዚህ ውጪ እኔ ነኝ ለእርሷ ማድረግ ያለብኝ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ሰው ለአገሩ ሲሰጥ ለራሱ እንደሰጠ ማመን አለበት። መለወጥና ራስን መሆን የሚቻለው አገር መጀመሪያ ስትኖር እንደሆነ ማወቅም ይገባዋል። ስለሆነም ሥራችን ሁሉ መከወን ያለበት ከአገሬ አንጻር ታይቶ ሊሆን ይገባል። በሰፊው ስናስብ በሰፊው እናፍሳለንና ይህንን አስበን እንሥራ ሲሉ ይመክራሉ።
የመጨረሻውን በስፖርቱ መስክ የማስተማር ብቃትን የያዙት ማስተር ፍሬው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ማርሽያል አርትን ከመሰረቱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም በአገሪቱ ሁሉም ክፍል በሚባል ደረጃ ይህንን ሙያ አስተዋውቀዋል። ብዙ ወጣቶችንም አሰልጥነው የሙያ ባለቤት አድርገዋል። አሁን ደግሞ በትልልቅ የመንግሥት ስብሰባዎችና ኮንሰርቶች ላይ በጥበቃ እና በእጀባ ሥራ ላይ ብዙ ወጣቶችን አሰልጥነው የሥራ እድል እየፈጠሩ ይገኛሉ። ከ160 በላይ ቋሚ ሠራተኞችን ያሏቸው ሲሆን፤ ሙሉ ኢንሹራንስ ኖሯቸው እንዲሠሩም ያደርጓቸዋል።
ጣሊያን አገር ላይ ሳሉ በሚላን ከተማ ከእነሞሪኖ ጋር ጭምር የሠሩት ባለታሪካችን፤ በአገራቸውም መጥተው የእነቴዲና ጎሳዬ እንዲሁም የሌሎች አገራት ልዩ ተጨዋቾችና ሙዚቀኞች ሲመጡ የእጀባና ጥበቃ አገልግሎትን ይሰጣሉ። ለምሳሌ የቦንባርሊ ኮንሰርት ፤ ሮናልዲኒዮ አገር ውስጥ ሲመጣ የእጀባ ሥራውን ያከናወነው ድርጅታቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ያልተጠቀሱ በርካታ ልዩ እንግዶች ሲመጡም ይህንኑ የጥበቃና የእጀባ ሥራቸውን ያከናውናሉ። ብዙዎቹም ስኬታማ እንደነበሩ ያነሳሉ። በተመሳሳይ የኤምባሲ ጥበቃ ሥራዎችንም ወስደው ከሚሠሩት መካከል ናቸው። ለምሳሌ የጣሊያን ኤምባሲ፣ ትምህርት ቤትና የባህል ማዕከሉ በእነርሱ የሚጠበቁ ሲሆኑ፤ በግለሰብ ደረጃም እጀባ ሲያስፈልግ ይህንን አገልግሎት ይሰጣሉ። በዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይም በዚህ ሥራቸው ተሳታፊ ናቸው። በተወሰነ ደረጃና በተወሰነ ቀን የጥበቃና የእጀባ ሥራ በመሥራት ለስድስት ዓመታት ሲያስተዳድሩት በቆዩት ሸራተን ሆቴል እየጠበቁና እጀባ እያደረጉ እንግዶች በሰላም ወደመጡበት አገር እንዲመለሱ አድርገዋልም።
ጥበቃ ማለት ሰውን፣ ንብረትንና አገርን መንከባከብ እንደሆነ የሚያነሱት እንግዳችን፤ አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታውን ተንተርሰው በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ያለውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በድርጅታቸው አማካኝነት ወጣቱን በማሰልጠንና አልባሳቱን ጭምር በመቻል የአካባቢው ጠበቃ እንዲሆን አስችለዋል። ለዚህ ስኬታቸው ደግሞ ከሠራተኞቻቸው ጋር አንድም ቀን እንደአሠሪና ሠራተኛ ተያይተው አለማወቃቸው ነው። ይህ ደግሞ በነጻ ሥራዎችን አከናውነው እንኳን እንዳይቆጩ አድርጓቸዋል።
በስፖርት ሥራው ላይ ከ30 ዓመት በላይ ያሳለፉት እንግዳችን፤ አሁን በሚፈጥሩት ትውልድ እጅግ ደስተኛ ናቸው። ምክንያቱም ሙያው ያለው ሰው በመቅጠር ራሳቸውን ጨምረው በሚሰጡት ስልጠና ብዙዎችን እያተረፉ ነው። የሥነምግባር፣ የስፖርታዊና የሕግ እንዲሁም የአስተዳደር ትምህርቶችን በመስጠት ሙያተኛ ያደርጓቸዋልናም ይህ የአገር አበርክቷቸውን ስለሚያጎላላቸው ለአገሬ ደርሻለሁ የሚል እምነታቸውን አረጋግጦላቸዋልና ይደሰቱበታል።
እንግዳችን በተለያዩ ስፖርታዊ ተቋማት ላይ በኃላፊነት የሠሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል ማርሽያል አርቱ ላይ ያሳረፉት አሻራ የማያስረሳቸው ነው። የኢትዮጵያ ኡሹ ማርሽያል አርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ስፖርቱን ለማጠናከር በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋልም። በዋናነት የሚጠቀሰው ከሁለት ዓመት በላይ በነበራቸው ቆይታ ለፌዴሬሽኑ ከቻይና መንግሥት ያስመጡት የስፖርት መሣሪያዎች ግብዓት ሲሆን፤ አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ የዚሁ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆናቸው አበርክቷቸውን ሳይቀንሱ እየሰሩ ይገኛሉ።
የቀጣይ እቅድ
በቀጣይ መሥራት የሚያስቡት አንድና አንድ ሲሆን፤ በስፖርቱ ዓለም ኢትዮጵያን ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ ነው። በተለይም በጸጥታና ጥበቃው ዙሪያ ሰፊ ሥራ ለመሥራት እቅድ አላቸው። ጠንካራ ዜጋን የማፍራቱ ሕልማቸው ነው። ምክንያቱም ማትረፍ የሚቻለው ጠንካራ ዜጋ ለጠንካራዋ አገር ማምረት ሲቻል ነው ብለው ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ ትውልዱን በስነምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ያስፈልጋል።
ስፖርቱ ይህንን እንዲያደርግ የሚያስችሉ ተግባራትን መፈጸምም የእቅዳቸው አንዱ አካል ነው። ስለዚህም መጀመሪያ መንግሥት ነገሮችን ቢያመቻችላቸው በተለይም የቦታ ጉዳይን ቢፈታላቸው የሴኪውሪቲ ኮርሱን በስፋት መስጠት ይፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ ማሰልጠኛ ማዕከል መክፈት አስፈላጊ ነውና ያደርጉታል። በተመሳሳይ እንደ አገር የሚያገለግልና ወጣቱን ከአልባሌ ቦታ የሚታደግ ትልቅ የጅም ሴንተር መክፈትም ያስባሉ። ለሀሳቤ እውን መሆን የሚያስችል መንገዶችን መንግሥት ቢያመቻችልኝ ሲሉም ተማጽኗቸውን ያቀርባሉ።
ታማኝነትና ገጠመኙ
ሌብነትን አጥብቀው እንዲጸየፉ ሆነው አድገዋል። በዚህም ምንም አይነት ተአምር ቢፈጠር የተቀመጠና በአደራ መልክ የተሰጣቸውን ገንዘብ አይነኩም። የሠሩት እንኳን ቢሆን በፈቃድ ነው የሚጠቀሙት። ይህ ባህሪያቸው ደግሞ 44 ኪሎሜትር በእግራቸው እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። እናትና አጎታቸውን ጭምር ያቆራረጠም ሆኗል። ነገሩ እንዲህ ነው። ማስተር ፍሬው ክረምት በመጣ ቁጥር አጋሮ አጎታቸው ቤት ማሳለፍ ያስደስታቸዋል።
ሁሌም ጓዛቸውን ጠቅልለው እርሳቸው ጋር በመሄድ ረጅሙን ጊዜ ያሳልፋሉ። ይህ ደግሞ ለአጎታቸው ልዩ ጥቅምን የሚያስገኝ ነበር። ምክንያቱም እርሳቸው ገንዘቡን በደንብ ስለሚቆጣጠሩላቸው ጠጅ ቤት ላይ የሚሠራው ጠጅ ቀጂያቸው ገንዘብ አያታልላቸውም። ይህ ጊዜ በሠራተኛው የሚጠላ ቢሆንም ለአጎት ግን ብዙ ገቢ የሚሰበስቡበትና ደስተኛ የሚሆኑበት ጊዜ ነው። እናም አንድ ቀን በዚህ ነገራቸው የተደሰቱት አጎት በሹክሹክታ ለባለቤታቸው ልጁን መላክ እንደሌለባቸው ይነግሯቸዋል።
ልሂድ ሲሏቸውም ነገ ዛሬ እያሉ ያጓትቷቸዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ ያሉት ባለታሪካችንም ነገሮቹ ስላልተመቿቸው ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በርካታ ገንዘባቸውን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው 1 ብር 05 ሳንቲም መሳፈሪያ እንኳን ሳያነሱ በእግራቸው ጉዞ ይጀምራሉ። ያሰቡበት ቤታቸውም ይደርሳሉ። ግን የጠበቁት ነገር አልሆነም። ምክንያቱም አጎታቸውና እናታቸው ተቀያየሙ። እንዴት 1፡05 ሳንቲም ሰጥተህ አላከውም ሲሉ አኮረፏቸው። ይህ ቢያንገበግባቸውም ታማኝነታቸውን ግን ዛሬ ድረስ ያነሱታል።
ሕይወት ፍልስፍና
ሰው በማንኛውም ጊዜ የማያውቀውን ሥራ መሥራት የለበትም። ምክንያቱም ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው በአካልም በመንፈስም ከእርሱ አልፎ አገሩና ቤተሰቡ ላይ ይደርሳል። አውቆት ከሠራ ግን ብዙ ያተርፍበታል። በተለይም ሰውን በማትረፉ በኩል የማይተካና የማይሞት ሚና ይኖረዋል። ሥራውን ከመቃብር በላይም ያውለዋል የሚለው የመጀመሪያው ፍልስፍናቸው ነው።
ሌላው በስፖርተኝነት ላይ ያላቸው ግንዛቤን ይመለከታል። ይህም ራስን ስፖርተኛ ማድረግ ለተደባዳቢነት መብቃት ሳይሆን ሕይወት ማቃናትና የሕይወት መንገድ ላይ መልካም አሳቢነትን መጨመር ነው ብለው ማሰባቸው ነው። በዚህም ስፖርተኝነትን ከመልካም ስነምግባርና ከአገር ወዳድነት ጋር አስተሳስሮ መኖርና መሥራትን ያምናሉ። የሕይወት መርሃቸው እንዲሆንም ይፈልጋሉ።
በተለመደው የቀን ውሏችን ውስጥ ሕይወታችንን ብሩህ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራትን መፈጸም ሁላችንንም ከሚያስደስቱን ነገሮች የመጀመሪያው ናቸው ብለው የሚያምኑም ናቸው። በተለይ ወቅቱን አስቦ ለሰዎች መልካምና በጎ ነገር ማድረግ ደስተኛ ያደርጋል ብለው ያስባሉ። ጤናማ ሆኖ መኖር የሚቻለው በሰጡ አዕምሮዎች ልክ መቀበል ሲቻል ነው የሚል የሕይወት ፍልስፍና አላቸው።
መልዕክት
በአገራችን ላይ እየሆነ ያለው ነገር እጅግ ዘግናኝና በእኛ ደረጃ መፈጠር ያልነበረበት ነው። ምክንያቱም እኛ አስተዋይና በባህላችን ጭምር ሌሎችን አስተማሪ ነን። እኛ ጀግንነታችንና አክብሮታችን ሰውኛ ባህሪን የተላበሰ ሕዝቦች ነን። ይሁን እንጂ ከየት እንደመጣ በማይታሰብ መልኩ የተለየ ባህሪን አንጸባርቀናል። ብዙ ነገሮቻችንንም አትተናል። እንደውም ሴኩሪቲ አናሊስስ ስሠራ ያገኘሁት አሁን የተካሄደው ጦርነት ባይኖር ኖሮ በመሳሪያው ብቻ የትግራይ ሕዝብ ለሥራ ለእያንዳንዱ ሰው በነቂስ አራት ሚሊዮን ብር ይደርሰው ነበር። በዚህ ደግሞ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገሩንም ይለውጥ ነበር። ግን በጥቂት ሰዎች ነገሩ ከሸፈ። እናም አሁን ወጣቱ መንቃት ይኖርበታል፤ ስለራሱ አስቦ ነገሮችን በማስተዋል መተግበር ላይ ሊደርስ ይገባዋል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው አሁንም ለወጣቱ የሚመክሩት በማንኛውም ወቅት የሚወድመው ገንዘብ የአገር መሆኑን መረዳት እንዳለበት ነው። በብሔር አዚም ተይዞ ይህንን እንዳያስተውል ሆኗልና ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። አገሩንም ከዚህ ውጥንቅጥ ሕይወት ውስጥ ሊታደግ ይገባዋል። ይህንን ሲያደርግ ደግሞ ጠላትን ባለመቀላቀል፤ ሙያውን በመጠቀምና የተቻለውን ሁሉ ለአገሩ በማበርከት ነው ብለዋል።
ሁሉም ሰው መቸኮልን ማቆም አለበት። ምክንያቱም በችኮላ ውስት ብዙ ስህተቶች ይፈጠራሉ። አሁን የገባንበት ፈተናም ከምንም ሳይሆን የመጣው ከችኮላችን የተነሳ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል። በቃኝ ማለትንም መልመድ ይኖርብናል። ለራሱ በቂ ነገር ካለ ስለአገር ማሰብ ተገቢ ነው። ለአገሩ የሚያደርገውን ወዶት መተግበር አለበት። ይህ ሲሆን ደግሞ ኪሳራ ቢመጣ እንኳን አይቆጭም፤ ምክንያቱም ለሰዎች ደርሷል። አገሩንም አግዟል። እናም ለአገር ሲባል ሁሉም በየደረጃ መትጋት እንዳለበት ይመክራሉ። እኛም ምክራቸው ይተግበር በማለት ለዛሬ አበቃን።
ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም