መንደርደሪያ፤
ማንኛውም ቤተሰብ በአውራነት የሚታይ አንጋፋ አባል እንዳለው ሁሉ አገራትም እንዲሁ “ታላቄ” ለመባል የማያንሱና የብኩርና ክብር መቀዳጀት የሚገባቸው ፊት ቀደሞች እንደሚኖራቸው ማሰቡ በተፈጥሯዊ ይሁንታ የሚታይ ብቻ ሳይሆን አሜንታ የሚገባው ቅቡል እውነታ ጭምር ነው። ይህንን ሐቅ መሠረት በማድረግም ኢትዮጵያ በበርካታ አኩሪ ታሪካዊ ምክንያቶች የተነሳ የአፍሪካ አገራት የበኩር ልጅ ነች ቢባል ማጋነን አይሆንም። በጥቁር “ዕንቁዋ” የአፍሪካ ምድር፤ በምሥራቅ አቅጣጫ ደምቃ የምትታየው ኢትዮጵያ የነጻነት ቀንዲል በመሆን ለአፍሪካውያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ብርሃን ስትፈነጥቅ መኖሯም የደማቅ አሻራዋ ተጠቃሽ እውነታ ነው።
ከፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ በፊት “ፓን ኢትዮጵያኒዝም” የሚል መርህ ተጠንስሶ እንደነበር ታሪክ እማኝነቱን ይሰጣል። ጥንስሱ ይበልጥ መብላላት የጀመረው ከአድዋ ድል በኋላ በተገኘው አኩሪ ገድል ነው። ይህንን እውነታ የሚመሰክሩ ብዙዎች፤ በክቡሩ የታሪክ ወጭታችን ውስጥ እጃቸውን በመስደድ፤ “እኛም አለንበት” እያሉ ታሪኩን ለመቃረጥና ለመሻማት የሚሞክሩትና “ለንቅናቄው መጸነስ ማህጸኖቹ እኛ ነን” እስከ ማለት የደረሱም ጥቂቶች እንዳልነበሩና እንዳልሆኑ ብናስታውስ በሃሜትነቱ ሳይሆን በታሪካዊ ትዝብትነቱ ሳይበጅ አይቀርም።
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ግንቦት 14 ቀን 1955 ዓ.ም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸው ውስጥ ብዙ ጉዳዮችን የዳሰሱትም ይህንኑ እውነታ ለወንድም አገራቱ መሪዎች አስረግጠው ለመግለጽ በማሰብ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። “ከትናንትናዋ አፍሪካ ወደ ነገዋ አፍሪካ” የሚለው ተጠቃሽ ንግግራቸው በርካታ ሃሳቦችን የተሸከመ እንደነበርም በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ በአድናቆት ጭምር ሲስተጋባ ተደምጧል።
በድርጅቱ ምሥረታ ሰሞን በተደጋጋሚ ሲጠቀሱና ሲወደሱ የነበሩት የእኛው ንጉሠ ነገሥት “ነዎሩ!” ተሰኝተው ከሌሎች መሪዎች በደመቀ መልኩ እንዲከበሩና እንዲደነቁ ያስቻላቸው ተግባራቸው ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡትን የኅብረቱን 33 ያህል መሥራች አገራት መሪዎች በማግባባትና በማቀራረብ ወደ አንድ ጥላ ሥራ ማሰባሰባቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ሊታወሱ የሚገባቸው ጉዳዮችም እንዳሉ የዛሬው ትውልድ ሊገነዘብ ይገባል።
እግረ መንገዱንም ከተጠቀሱት 33 አገራት መካከል በዚያ የኅብረቱ ምሥረታ ታላቅ ጉባዔ ላይ በመሥራችነት ስማቸውንና ፊርማቸውን ያኖሩት 31 አገራት ብቻ ሲሆኑ ሁለቱ አገራት (የሞሮኮው ንጉሥ ዳግማዊ ሐሰን እና የሪፐብሊክ ኦፍ ቶጎ መሪ) በተጠቃሹ ታሪካዊ ሰነድ ላይ ፊርማቸው አልተገኘም፤ ወይንም ይህ ጸሐፊ ባመሳከረው ሰነድ ላይ ተዘሎ ሊሆን ይችላል።” የፊርማ ነገር ከተነሳ አይቀር በወቅቱ የተለየ አትኩሮት ተሰጥቶት ብዙ መገናኛ ብዙኃን ይቀባበሉት የነበረው “ቀኃሥ” በሚል አጽርኦት ቃል ተቆላልፎ የሠፈረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ፊርማ እንደነበር በአንዳንድ ሰነዶች ላይ በስሱ ተጠቅሷል።
ደርግ ከታላቁ ቤተመንግሥት የውጭው አጥር ላይ ለማንሳት ሞክሮ ያልተሳካለትን፣ የኢህአዴግ መንግሥት ቁብ ሳይሰጥ አሻግቶ ያኖረውን፣ የብልጽግናው መራሔ መንግሥት በወርቃማ ቀለም ያደመቀውን የንጉሡን ስም የሚወክሉትን ሦስት ሆሄያት (“ቀኃሥ”) ማየት የፈለገ ዜጋ የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮችን ለመጎብኘት ሲሄድ ዐይኑን ወደ ጥንታዊው የምኒልክ ቤተ መንግሥት አጥር አሻግሮ ወርወር ቢያደርግ ለመግለጽ የተሞከረውን እውነታ በቀላሉ መረዳት ይችላል።
ታሪካችን በብዙ “ያለመታደሎች የታጀለ ሆኖ” የራሳችንን እያንቋሸሽን የሌሎችን ማሞጋገስን እንደ ባህል የመቁጠር አገራዊ ሕመማችን ተፈውሶ ቢሆን ኖሮ ንጉሠ ነገሥቱ በአገዛዝ ዘመናቸው የሠሯቸው በርካታ ስህተቶች እንደተጠበቁ ሆነው መልካሙ ስማቸውና ተግባራቸውም ጎን ለጎን ገንኖና ደምቆ በተነገረላቸው ነበር።
በኢትዮጵያ የሕንድ ማኅበረሰብ አባላት ያሠሩትና በሲኒማ ኢምፓዬር ፊት ለፊት በሞገስ ቆሞ የነበረውና በደርግ ዘመን በትዕዛዝ እንዲፈርስ የተደረገውን የንጉሠ ነገሥቱን የመታሰቢያ ሐውልትና በመላው አገሪቱ ይገኙ የነበሩትን መሰል ሐውልቶች እንዳልባሌ ማፍረስ እብደት እንጂ ምን ይባላል። በስማቸው ይጠሩ የነበሩ ተቋማት ስያሜዎችም እንዲሰረዙ የመደረጉ እንቆቅልሽ ምን ነበር። መታሰቢያቸውን ከምድር ላይ ለማጥፋት? አይሄሄ! መንግሥታዊ ጅልነት ይሏል እንዲህ ነው።
በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ቅጥረ ግቢ ውስጥ የታላቁ አፍሪካዊ አባት የክዋሚ ንክሩሁማ ሐውልት እንዲቆም በአህጉሪቱ መሪዎች በሙሉ ድምጽ በተወሰነበት ወቅት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሐውልትም ጎን ለጎን እንዲቆም ሃሳቡ ሲቀርብ በወቅቱ የነበሩት የአገራችን መሪዎች ሽንጣቸውን ገትረው እንደተቃወሙና በኋላም እንደነገሩ ተውሸልሾ እንዲቆም የተደረገው በብዙ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንና የአፍሪካ መሪዎች ግፊትና ጥረት እንደነበር ያጫወቱኝ ነፍሰ ሄር ወዳጄ ክቡር ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ነበሩ – “ነፍስ ይማር!”።
በጋና ዋና ከተማ አክራ በሚገኘው የንክሩሁማ ማዕከል ጎብኝዎች ወደ ውስጥ ዘልቀው ሲገቡ መጀመሪያ ፊት ለፊት የሚታየው ክዋሚ ንክሩሁማና ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጎን ለጎን ቆመው የተነሱት ፎቶግራፍ ነው። ግራና ቀኝ የተከበቡትም በጋና እና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ከዓመታት በፊት ይህንን ታሪካዊ ማዕከል በጎበኘሁበት ዕለት ልቤን የኩራት ሙቀት ለብ ቢያደርገውም በአገሬ ለንጉሡ የተሰጠው ተቃራኒ አመለካከት ትዝ ብሎኝ እንዳዘንኩ ግን መሸሸግ አልፈልግም።
በአቻዎቻቸው የአፍሪካ መሪዎች ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ክብርን ተጎናጽፈው የነበሩት ንጉሠ ነገሥት የመጨረሻ ፍጻሜያቸው ምን እንደነበረ ስለሚታወቅ ደጋግሞ ማስታወሱ ሀዘን መቀስቀስ ስለሚሆን በድርበቡ ብቻ ዘክሮ ማለፉ የሚሻል ይሆናል። ጀግና ትውልድና ፈሪሃ ታሪክ የገባቸው ምሑራንና ፖለቲካኞች በተነሱ ጊዜ ግን ከእኚህ ታላቅ የአገራችን መሪ ላይ የተገፈፈው ማዕረግና መታሰቢያ ዳግም እንደሚታደስ ተስፋ ይደረጋል። ለማንኛውም ስለ ፓን አፍሪካ ፍልስፍናና የትግል ታሪክ ባለፉት ቀናት በእጅጉ ብዙ ሲነገርና ሲተነተን ስለሰነበተ ይህ ጸሐፊ አንዳንድ የግሉን ገጠመኞችና ትዝታዎች ብቻ እየቆነጣጠረ ማስታወስን መርጧል።
በቀዳሚ መታወቂያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ በዛሬ ስያሜው የአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤትን ከኢትዮጵያ በማስነሳት ወደ ሌላ የአፍሪካ አገር እንዲሰደድ ለማድረግ ያልተፈነቀለ ድንጋይና ያልተሞከረ ሴራ አልነበረም። ዛሬም ድረስ የሴራው ጉሽ ስለመጥለሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ሌሎች የሚያውቁትን ሊጠቅሱ ይችላሉ ይህ ጸሐፊ ግን የገጠመውን አንድ አሳዛኝ ክስተት ቢያስታውስ ወቅቱ ይፈቅድለታል።
በኮሎኔል ሙሐመድ ጋዳፊ የመጨረሻ ዓመታት ግድም ይህ ጸሐፊ በተጋባዥነት የተገኘበት አንድ ታላቅ ጉባዔ በሊቢያዋ ታዳጊ ከተማ በሲርት ተደርጎ ነበር። ይህቺ ከተማ የኮሎኔሉ የትውልድ ከተማ እንደሆነችና የመጨረሻ የሕይወት ፍጻሜያቸውም በዚያችው ከተማ እንደተጠናቀቀ እናስታውሳለን። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚለው ስያሜ በአፍሪካ ኅብረት እንዲተካ ሃሳብ የቀረበውና ሌሎች በርካታ ውሳኔዎችም በአህጉሪቱ መሪዎች የተወሰነው ሴፕቴምበር 9 ቀን 1999 ዓ.ም በዚህችው ሲርት ከተማ እንደነበርም ይታወሳል።
ይህ ጸሐፊ የተገኘበት ያን መሰሉ የአፍሪካ ታላላቅ ደራሲያንና ምሑራን ጉባዔ እንዲከናወን ትዕዛዝ የተሰጠው በቀጥታ ከኮሎኔል ሙሐመድ ጋዳፊ እንደነበር ብዙ ተሳታፊያን የተረዳነው እዚያ ከደረስን በኋላ ነበር። የጉባዔው ዋና ዓላማ የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምሑራንን በአንድ ጣራ ስር ለማሰባሰብ ተፈልጎ እንደሆነ ቢገለጽም ድብቅ ዓላማው ግን ጉባዔተኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ለማግባባት ነበር።
ይህ ጸሐፊ ቀደም ሲል በተሰጠው ፕሮግራም መሠረት በሊቢያዋ ዋና ከተማ ደርሶ ወደ ሲርት የሚደረገውን የ448 ኪ.ሜ ቀሪ ጉዞ ለመቀጠል ቢፈልግ ማን ያስተናግደው። ለዚህ ጉዳይ የተመደቡት አስተባባሪዎች ተቀብለው ሊያስተናግዱት ባለመፈለጋቸው በአካባቢው ሊገኙ አልቻሉም። የነበረው አማራጭ በራሱ ውሳኔ በማያውቀው አገር የኮንትራት መኪና ይዞ መጓዝ ነበር። ጉዞው ደግሞ በሌሊት የሚደረግ ስለነበርና ከሾፌሩ ጋር በቋንቋ ያለመግባባቱም ተደራርቦ እንደምን ሊፈትን እንደሚችል መገመቱ አይከብድም።
ለማንኛውም እንደ እሳት በሚንቀለቀለው ረሞጫ በረሃ ውስጥ የሌሊቱ የመኪናው ጉዞ ተጠናቆ ሊነጋጋ ሲል ሲርት ደረስን። የመንገዱ ጥራትና ውበት አጃኢብ የሚያሰኝ መሆኑን ባልጠቅስ ሕሊናዬ ይወቅሰኛል። ለማንኛውም እዚያ እንደደረስኩ ማን አለሁ ይበለኝ። ጥቂት ሰዓታትን በአንድ መናኛ ሆቴል ውስጥ እንደነገሩ በማሳለፍ ሲነጋጋ ለስብሰባ በተዘጋጀው ቅንጡ ሆቴል ደረስኩኝ። ሆቴሉ የአፍሪካ መሪዎችም የተሰበሰቡበት ነበር። ጋባዦቼ እንደነገሩ ከተቀበሉኝ በኋላ ወዲያው እኔ የተዘጋጀሁበት ጽሐፍ ሊቀርብ እንደማይቻል ተገለጸልኝ። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊነቴ ነበር። የተጋበዝኩት ጋና በሚገኘው የመላው አፍሪካ ደራስያን ጽ/ቤት በኩል ስለነበር ከኢትዮጵያ ሰው እንደሚገኝ አልጠረጠሩም ይሆናል።
በአጭሩ ለመግለጽ ያህል ያ ሁሉ ሰው የተጋበዘው ኢትዮጵያን እንዲያወግዝና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ለማግባባት ነበር። ይህንን ሴራ እንደተረዳሁ የተፈጠረው ግብግብና ንትርክ በቀላሉ በውሱን የጋዜጣ አምድ የሚገለጽ ስላልሆነ አልፈዋለሁ። ለማንኛውም ክርክሩ ተጧጡፎና ተጋግሎ የተጠናቀቀው ጥቂት ደቂቆች ተሰጥተውኝ ሰላምታ አቅርቤ ብቻ እንድወርድ ቢሆንም የመጣው ይምጣ በማለት መድረኩን ለሃሳቤ መግለጫና ለአገሬ ክብር ተከራክሬ በማሸነፌ እንደማንም ዜጋ ኩራት ይሰማኛል። እጅግ የሚያሳዝነው ግን ወደ ሊቢያ ለመሄድ የትብብር ደብዳቤ የጠየቅኋቸው የወቅቱ ሚኒስትር ዴኤታ የሰጡኝን አሳፋሪ መልስ እዚህ መጥቀሱን አልወደድኩትም።
ከአፍሪካ አንድነት ጽ/ቤትና አሁንም ከአፍሪካ ሕብረት መቀመጫነት ኢትዮጵያ እንድትነጠል የሚደረገው ሴራ አክትሞለታል ማለት አይቻልም። ይህን መሰሉ ተንኮል ወደፊትም ይቀራል ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ እንደ አገር ምን አላደረግንም ምንስ ማድረግ ይጠበቅብናል።
አንዳንድ ሃሳቦችን ልፈነጣጥቅ። የቀዳሚ ዘመናትን ጥረቶች ከማክፋፋትና ከማራከስ ተቆጥበን ታሪካዊ ሌጋሲያችንን አጠንክረን እናስጠብቅ። ለራሳችን ታሪክ ራሳችን ጠላት አንሁን። በትምህርት ካሪኩለማችን ውስጥም አገራችን ከአፍሪካ ኅብረት ጋር የነበራትንና ሊኖራት የሚገባትን ቁርኝት በአግባቡ ለልጆቻችን እናስተምር።
አዲስ አበባ የአፍሪካውያን የፖለቲካ መዲና ብቻ ሳትሆን የታሪክ፣ የባህል፣ የቱሪዝምም ሆነ የንግድ ማዕከል እንድትሆን መንግሥት አጥብቆ ይሥራበት። በተለይም በወረተኛነት የምትታማው አዲስ አበባ ልብ ትግዛና ለአፍሪካ አገራትና ታሪኮቻቸው ቋሚ መዘክሮችን በማደራጀቱ ትትጋ። ለምሳሌ፤ ቀደም ሲል ሳይታሰብበትና ሳይመከርበት በግብታዊነት ተወስኖ ለአፍሪካ አገራት የተሰየሙት ጎዳናዎች መለያ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ከነጭራሹስ የመንገዶቹ ስያሜ ሰሌዳ በቦታው ላይ እንደነበረ ይገኛል? አይመስለኝም። እንኳንስ መንገዶቹ በየአገራቱ ስም ሊጠሩ ቀርቶ ምልክቶቹ ራሳቸው በቦታቸው ስለመገኘታቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
አዲስ አበባ የአፍሪካውያን መዲና ነች ካልን በታላላቅ አደባባዮቻችን ላይ እንደ አንዳንድ አገራት ተሞክሮ የየአገራቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለው ቢውለበለቡ ምን ክፋት ይኖረዋል። ታላላቆቹ የአፍሪካ አባቶች እንዲታወሱስ ምስላቸውን በአደባባዮቻችን ላይ በቋሚነት ሰቅለን ለወጣቶቻችን ብናስተዋውቅ አይበጅ ይሆን? ሁልጊዜም ሽር ጉዱ የመሪዎች ስብሰባ ብቻ ሲከናወን ሳይሆን በአዘቦቱ ቀናትም ተረጋግተን መሬት የሚይዝ ተግባር ሊከናወን እንደሚገባ ማሳሰቡ አግባብ መስሎ ታይቶናል። ለአፍሪካ አህጉራችን ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም