የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ስብሰባውን በመደበኛ ቦታው አዲስ አበባ ለማካሄድ ሽርጉድ እያለ ነው::ለ34 ጊዜያት በመደበኛነት የተለያየ አጀንዳ በመያዝ ሲካሄድ የሰነበተው ስብሰባ ዘንድሮም ለ35ኛ ጊዜ ሲካሄድ የራሱ የሆኑ አጀንዳዎች ቢኖሩትም የሁልጊዜም መደበኛም ሆነ ኢ መደበኛ ስብሰባዎቹ ቋሚ አጀንዳ ግን አንድ ነው:: እሱም የአፍሪካውያን አንድነት ነው::
የአፍሪካ የአንድነት ጉዳይ ከድህረ ቅኝ ግዛት አመታት ጀምሮ ላለፉት 50 አመታት ሲመከርበት ፤ ውይይት እና ክርክር ሲካሄድበት እንዲሁም ትግል ሲያጠነጥንበት የከረመ አጀንዳ ነው::ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ አሁንም ይህ የታላላቅ አፍሪካውያን ባለራእዮች ህልም እውን ለመሆን ብዙ ርቀት የሚቀረው ሆኗል::
የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ያኔ ሲመሰረት አምስት መሰረታዊ አላማዎች ነበሩት:: እነሱም በአፍሪካ ሀገራት መሀከል ህብረት እና ወንድማማችነትን መፍጠር ፤ ለአፍሪካ ህዝብ የተሻለ ኑሮን ለመፍጠር በሀገራት መሀከል የሚደረጉ ትብብሮችን እንዲፈጠሩ እና እነዲጠናከሩ ማድረግ ፤ የአፍሪካ ሀገራትን ሉአላዊነት ፤ የግዛት አንድነት እና ነጻነት ማስጠበቅ ፤ ማንኛውንም አይነት ቅኝ ግዛት ለማስወገድ እንዲሁም አለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ነበር::
በጥቅሉ አላማው አፍሪካዊ አንድነትን መፍጠር ነበር:: ከዚያም በኋላ በፈረንጆቹ 1999 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረት ሲቀየርም አላማው የነበረው ይህን አንድነት የበለጠ ማፋጠን ነበር::
እንደ አጼ ሀይለስላሴ እና ክዋሚ ንክሩማ ባሉ ልባሞች የተጀመረው ይህ በጎ አላማ ግን አሁንም የታሰበበት ቦታ ላይ መድረስ አልቻለም::በተለይም ከሌሎች አህጉራት ህብረቶች አንጻር የአፍሪካውያን ህብረት ገና ያልተጀመረ ነው ማለት ይቻላል:: ለምሳሌ የአውሮፓ ህብረትን እንመልከት:: የአውሮፓ ህብረት በዋነኝነት የተመሰረተው የህብረቱ አባል ሀገራት ዜጎች፤ ንብረቶች እና ሀሳቦች በአውሮፓ ምድር ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ላይ ነው::
በዚህም መሰረት አንድ አውሮፓዊ ከተወለደበት ሀገር ወጥቶ ሌላ የአውሮፓ ህብረት አባል የሆነ ሀገር ውስጥ ገብቶ የመኖር የመስራት እና ሀብት የማፍራት ሙሉ መብት አለው:: ይህ መብት በኢኮኖሚ አንጻር ሲመነዘር በጣም ከፍተኛ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ ከጠቀስነው የሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአውሮፓ ሀገራት መሀከል ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም በጣም ከፍተኛ ነው።
ለምሳሌ ያህል በ2020 እ.ኤ.አ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት መሀከል የተደረገው ንግድ ከ2.8 ትሪሊየን ዩሮ በላይ ነው::በተመሳሳይ የአፍሪካ ሀገራትን የእርስ በእርስ ግብይት ስንመለከት ግን የምናገኘው ቁጥር አስደንጋጭ ነው::ከ50 በላይ ሀገራት ባሉበት አህጉር በሀገራቱ መሀከል የሚደረገው ግብይት 100 ቢሊየን ዶላር እንኳ አይደርስም::
ይህ ዝቅተኛ የሆነ የእርስ በእርስ ንግድ የሚያመላክተው አፍሪካውያን አሁንም ገና ተባብረን መስራት እንዳልጀመርን ነው:: ተባብረን ካልሰራን ደግሞ አንድነት ብርቅ እንደሆነ ይቆያል::
አፍሪካውያን አንድ ሆነው ድንበሮቻቸውን ከፍተው በነጻነት እንዳይገበያዩ እና ዜጎቻቸው የፈለጉበት ሄደው እንዳይንቀሳቀሱ ችግር ከሆኑባቸው ነገሮች መሀከል ዋነኛው ደግሞ የሰላም እጦት ነው::አሁን አሁን ላይ የአህጉሩ ሀገራት ህጎቻቸውን በማስተካከል ለነጻ እንቅስቃሴ ሁኔታዎችን እያመቻቹ ቢመጡም የሰላም ሁኔታ ግን እንቅስቃሴን አስቸጋሪ አድርጓል::
አሁንም በአፍሪካ ሀገራት መካከልም ሆነ በሀገራት ውስጥ የሚካሄዱ ጦርነቶች የሰላም እጦት መንስኤዎች ናቸው::በተለይም የአህጉሪቱ አንድነት እንቅልፍ የሚነሳቸው ሀገራት እና ቡድኖች ስፖንሰር የሚያደርጓቸው ጦርነቶች የአፍሪካ ራስ ምታት መሆናቸውን ቀጥለዋል::
በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ለመያዝ መሞከር ፤ ፋይዳ ቢስ የሆኑ የተገንጣዮች ትግሎች እና ቅኝ ገዢዎች ባሰመሯቸው የወሰን መስመሮች የተነሳ የሚፈጠሩ ጦርነቶች ብዙ አፍሪካውያንን እየጎዱ ከመሆናቸውም በላይ በአፍሪካውያን መሀከል መተማመን እንዳይኖር እያደረጉ ነው::ስለዚህም ህብረቱ በተሰበሰበ ቁጥር ስለ ጋራ አህጉራዊ ጥቅሞቹ ሳይሆን ስለ ነጠላ ሀገራት ጦርነት በመመካከር እና በመከራከር ብቻ ይገደ ባል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካውያን መሀከል ያሉ የመሰረተ ልማት ትስስሮችም በጣም አነስተኛ ሆነው ይታያሉ:: የአፍሪካ ህብረት በ2053 አጀንዳው በዋነኝነት ከያዛቸው እቅዶች መሀከል ዋነኛው በአፍሪካ ሀገራት መሀከል ፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማካሄድ ነው::
በዚህም መሰረት በእቅዱ ላይ አምስት መሰረታዊ ግቦች ሰፍረው እናገኛለን::እነሱም የአፍሪካን ሁሉንም ሀገራት እና ትልልቅ ከተሞች የሚያገናኙ ፈጣን የባቡር መስመሮች መዘርጋት ፤ የአፍሪካን የሀይል ፍላጎት የሚሸፍነውንና በአለም ትልቁ የሆነውን የታላቁ የኢንጋ ግድብ ፕሮጀክት መገንባት ፤ አንድ የጋራ የሆነ አፍሪካዊ የአየር አገልግሎት መጀመር ፤ የፓን አፍሪካን የኢንተርኔት አገልግሎትን መዘርጋት እንዲሁም የአፍሪካ የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቂያ የጋራ ስርአት መዘርጋት ነው::
እነዚህ እቅዶች በወረቀት ላይ ሲታዩ ውብ ናቸው:: ከተተገበሩ ደግሞ አፍሪካን ወደታቀደው አንድነት እንድትመጣ ሁነኛ እርምጃ ሊሆኑ ይችላሉ:: ነገር ግን ይህን ለማከናወን የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የህብረቱ ከፍተኛ ጥንካሬ ያስፈልጋል::ከዚህም በተጨማሪ አፍሪካውያን ይህን የብዙ ቢሊየን ዶላር ፕሮጀክት ከአይ ኤም ኤፍ ፤ አለም ባንክ እና ምእራባውያን ድጋፍ ውጭ ሆኖ በውስጣዊ አንድነት እና ውስጣዊ አቅም ብቻ ስለሚከውንበት መንገድ ማሰብ የግድ ይላል::
እነዚህ ሁሉ ነገሮቸ እንዲሆኑ እና ንክሩማ ፤ ኔሬሬ እና ጃንሆይ ያቀዷት የተባበረች እና የተዋሀደች አፍሪካ እንድትፈጠር ከሁሉም በላይ የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሀሳብ ማዳበር እና በእያንዳንዱ አፍሪካዊ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው::ፓን አፍሪካኒስት ሳይሆኑ አፍሪካን አንድ ማድረግ ቀርቶ አሁን ባለችበት ቁመና እንኳን ማቆየት አይቻልም::
በምእራባዊም ሆነ ምስራቃዊ አስተሳሰብ ተጠምቆ የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ ባልሆነ መነጽር እያዩ ችግሮቿን መቅረፍ አይቻልም::በአፍሪካውያን አንድነት አስፈላጊነት ላይ ማመን እንዲሁም አፍሪካውያን አንድ መሆን እንደሚችሉ መተማመን አስፈላጊ ነው::ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ ላይ ጽኑ እምነት ያስፈልጋል::
ጦርነትም ይሁን የኢኮኖሚ ድቀት አልያም የተፈጥሮ አደጋዎች አፍሪካውያን በራሳቸው መንገድ ሊቀለብሷቸው እንዲችሉ መስራት ያስፈልጋል::እንደዚያ ሲሆን የአፍሪካ አንድነት ይመጣል::
የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበት ዋነኛ አላማም ይህን ተልእኮ ለማሳካት ነው::በዚህ አንጻር በተለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የያዘችው አቋም የሚበረታታ ነው::ለምሳሌ ያህል በቅርቡ እንኳ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ጉዳዩ በሶስቱ ሀገራት ብቻ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ አሳውቃለች::
እንዲህ አይነት አቋም በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ሊንጸባረቅ ይገባል::በተመሳሳይ በአፍሪካ ህብረት በኩልም የአፍሪካን ችግር ለመፍታት ብቸኛ እና ግንባር ቀደም አካል ህብረቱ መሆኑን አጠንክሮ ማሳወቅ አለበት::ስናጠቃልለው የአፍሪካ ህብረት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሲወራ የከረመውን የአፍሪካውያን አንድነት ከእሳቤ ወደ ተግባር አሻግሮ እውን ለማድረግ የመስሪያው ጊዜ አሁን ነው::ለዚህም የአፍሪካ ህብረት በስሙ ልክ መንቀሳቀስ መቻል አለበት::
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ጥር 29 ቀን 2014 ዓ.ም