( ክፍል ሁለት )
በክፍል አንድ መጣጥፌ ለዛሬው አገራዊ ምክክር እርሾ ነው ብዬ ስለማምነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ታሪካዊ ንግግር እና ስለ «ዴስቲኒ ኢትዮጵያ፤» መንደርደሪያ አቅርቤያለሁ። ይህ መጣጥፍ ከዚያ የቀጠለ ነው። የዴስቲኒ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ቡድኑ የሚመራበትን የሥነ ምግባር ደንብ በጋራ የወሰነ ሲሆን ገለልተኝነት ዋና የሥራቸው መርህ ሆኖ እንዲቀመጥ ተስማምቷል። ኢኒሽየቲቩ ገለልተኛ እና አካታች ሲሆን አብዛኛውን ፖለቲካዊና ፖለቲካዊ ያልሆነውን አመለካከት የሚወክሉ፣ ያገባኛል የሚሉና ተጽዕኖ አምጪ የሆኑ ሰዎች በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተለያዩ ሴናሪዮዎች እንዲቀርጹ ማስቻል ነው።
ምንም እንኳን ለድርድር እና ዕርቅ ሂደቶች ጉልህ አስተዋፅዖ ሊኖረው ቢችልም ሂደቱ ድርድርም፣ ዕርቅም አይደለም። ዋነኛ ግቡም የተለያየ አመለካከት ባላቸው መሪዎች ዘንድ የወንድማማችነት መቀራረብ፣ መግባባት እና መተማመንን ለማበረታታት እና ቢቻል ደግሞ ብዙኃን የሚስማሙበት ርዕይ በመቅረጽ ዘላቂ ሰላም እና ዋስትና በኢትዮጵያ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።
ሂደቱ ሦስት ምዕራፎችን አልፏል፤ እነዚህም 1) ለሴናሪዮ ቀረጻው አባላትን መመልመል፣ 2) ሴናሪዮዎቹ የሚቀረጹባቸውን ሦስት ለሕዝብ ክፍት ያልሆኑ የምክክር መድረኮችን ማካሄድ፤ እና 3) ውጤቱን ለሕዝብ ማሰራጨት ናቸው። ሦስቱ የሴናሪዮ ቡድን የምክክር መድረኮች ከሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት በአርባ ምንጭና በቢሾፍቱ ከተሞች በዝግ ተካሂደዋል። በሁሉም መድረኮች የሴናሪዮ ቡድን አባላቱ በሚገባ ተሳትፈዋል።
በእነዚህ መድረኮች ላይ የቀድሞዋ ሠላም ሚኒስትር ዴኤታ አልማዝ መኮነን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ታገሰ ጫፎ፣ እና የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሤ አስተያየት በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም በሴናሪዮ ቡድኑ ጥያቄ መሠረት በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ምጣኔ ሀብት፣ ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራል ሥርዓት፣ በሥነ ሕዝብ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ ሊሰጡ የሚችሉ ምሁራን ተጋብዘው መረጃ እንዲሰጡ ተደርጓል።
ከዚህ ረጅም ውይይት እና ክርክር በኋላ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚወክሉ እነዚህ 50 የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት በ2032 ዓ.ም ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መልክ ሊኖራት እንደሚችል የሚተነትኑ አራት አማራጭ ሴናሪዮዎችን በስምምነት ቀርጸው በሪፖርት መልክ አቅርበዋል። እያንዳንዱ ሴናሪዮ እንደ አገር ምን ዓይነት ጉዞ ብንከተል ወደ የት ልናመራ እንደምንችል ያመላክታል፤ የእያንዳንዱ የጉዞ መስመር መጨረሻም ምን እንደሆነ በገልፅ ያሳያል። በዚህ ሂደት አጠቃላይ ጉዞ የኢኒሽየቲቩ አስተባባሪዎች ሚና ሂደቱን ማቀላጠፍ እና ከጀርባ ሆኖ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ብቻ የተገደበ ነበረ፡፡
እያንዳንዱ የሴናርዮ ቡድን አባል ይወክለዋል ተብሎ የሚታሰበውን የማኅበረሰብ ክፍል መድረስን ዋነኛ ኢላማ ያደረገና በዓይነቱ ለየት ያለ አቀራረብ ያለው የሥርጭት ስልት ከቡድኑ አባላት ጋር በመመካከር ተነድፏል። በዚህም የሥርጭት ሂደት የሴናሪዮ ቡድን አባላት እንደሚያመቻቸው ተቀናጅተው ሠርተዋል። ከሌሎች አገሮች እንደተማርነው የሴናርዮ ቀረፃው ሂደት የሴናሪዮ ቡድን አባላትን አስተሳሰብ በመቅረጽና እርስ በርሳቸው ያላቸውን መተማመን በማጠናከር አዎንታዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
በሰው ልጅ ታሪክ የሴራ ፖለቲካ፣ ፅንፈኝነት፣ ዋልታ ረገጥነትና አክራሪነት በጊዜአዊነት የሚጠቅመው ታሪካዊ ጠላቶቻችንን፣ ጥቂት ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን እንጂ አገርንና ሕዝብን አይደለም፡፡ አገርን የሚጠቅመው በጥሞና በእርጋታ መመካከር ማንሰላሰል ነው፡፡ ዜጎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ማንኛውንም ልዩነት ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት ይችላሉ፡፡ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ እና ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ይህን ሀሳብ እውን አድርገውታል፡፡ ብልጽግና፣ ኦነግ፣ ኢዜማ፣ አብን፣ ኦብነግ፣ ወዘተ . በአንድ ጣራ ስር መክረው ዘክረው «የምንመኛት ኢትዮጵያ በ2032 ዓ ም » ራዕይ ይዘው መጥተዋላ፡፡
እውነቱን ለመነጋገር እኔን ጨምሮ እስከ እዚች ዕለት ድረስ ይህ ይሆናል ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም፡፡ ከለውጡ ወዲህ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ ም ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ በዓለ ሲመት ንግግር ጋር የሚስተካከል ታላቅ ክስተት ማክሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2012 ዓ ም ብዙዎቻችንን በአግራሞት እጃችንን በአፋችን ያስጫነ ልዩ ታሪካዊ ሁነት በእስካይላይት ሆቴል ተከውኗል፡፡ በታሪክም በወርቃማ ብዕር ተጽፎ ይገኛል። ምን አልባት በአግባቡ ከተጠቀምንበት የአገራችንን መፃኢ ዕጣ ፈንታ እስከ ወዲያኛው በበጎ መልኩ የሚወስን ይሆናል፡፡ እየታሰበ ላለው አገራዊ ምክክር መሠረት ጥሏል።
«ዴስቲኒ ኢትዮጵያ» ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ላይ ታች ሲል ሲደክምለት የኖረው «የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓ.ም » ን ከ«ንጋት» ጋር ሊሞሽር ታዳሚው በእስካይ ላይት ሆቴል በሰዓቱ ተገኝቷል፡፡ ከጉምቱ ፖለቲከኞች እስከ የማህበራዊ ሚዲያ «አርበኞች» ፤ ከሚኒስትር እስከ ክልል ርዕሳነ መስተዳድር እንዲሁም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የታደሙበት የተስፋ፣ የሕልም « ሰርግ»። ኢትዮጵያን ከራእይዋ የሚሞሽር ድል ያለ ድግስ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ከታዳሚዎች አንዱ ነበር። ተመስጦና በሀሳብ ተወስዶ ስመለከተው አንድ ወጉን አስታወሰኝ፡፡ ካልዘነጋሁ 2003 ዓ.ም በተባ ብዕሩ ያወጋን «ጠጠሮቹ እና ሌሎቹ» ከተሰኘው የጉዞ ማስታወሻ ቅዱስ ዮሐንስ ራእዩን የጻፈበትን ዋሻ ግሪክ «ባለራእይዋን ደሴት» እየጎበኘ በሀሳቡ «… እኔም ምናለ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ራእይ ባየሁ ብዬ ተመኘሁ፡፡
የመጣና የሄደ ሁሉ እንዲህ ትሆናለች እያለ በሌለ ተስፋ ከሚሞላን ቁርጥ ያለውን የነገ ዕጣ ፈንታዋን ዐውቀን በጊዜ ብንገላገል ምናለ፡፡ ከዚህ ጥቁር ዐለት በነጭ ሰሌዳ ተጽፎ አንዳች ራእይ ቢታየኝ ምናለ ፡፡ …» በማለት በሄደበት ሁሉ ይዟት ስለሚዞረው አገሩ ይቃትታል፡፡ ዛሬ ግን ሊገለጥለት ይመኘው የነበረውን ራእይ በእነ «ቲም ንጉሡ» የተገለጠለት ይመስለኛል፡፡
እንደ ነብይ ራእይ ባገሩ አይከበርም ካላልን በስተቀር እልፍ አእላፍ ባለ ራእዮች በዚች ምድር ተመላልሰዋል። ራእያቸውን የሚተረጉም ተቀብሎ የሚፈፅም አላገኙም እንጂ፡፡ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ በጥቁሩ ዐለት በነጩ ሰሌዳ ተጽፎ ባይሆንም በእነ «ዴስቲኒ ኢትዮጵያ » ተገልጦ በ50ዎቹ ወካይ ኢትዮጵያውያን ተተርጉሞ ምን አልባት በአገራችን ታሪክ ስትወሳ በምትኖረው በዚያች ታሪካዊ ዕለት የዚች አገር ዕጣ ፈንታዋ በእስካይ ላይት ሆቴል «የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 ዓ.ም» በሚል ርዕስ ራእይዋ ተገልጧል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ከሁሉም ማዕዘን ሙሉ በሙሉ ሊወክሉ ይችላሉ በተባሉ ዜጎቿ አማካኝነት የተፈጠረ መደማመጥ፣ የልብ ለልብ መገናኘት እና መቀባበል ምን አልባት ከአድዋ በኋላ የመጀመሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በቅንነት እና በየዋህነት አምነን ከተቀበልነው የአገራችንን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ራእይ ተገልጧል፡፡ ድርሻ ድርሻችንን ወስደን የመፈፀሙ የዜግነት ግዴታ የሁላችን ነው፡፡ አገራዊ ምክክር የዚህ እርሾ ቡኬት ነው የምለው ለዚህ ነው።
እነ «ቲም ንጉሡ» ከአመታት እልህ አስጨራሽ ጥረት እና መቃተት በኋላ የተገለጠላቸውን ራእይ ከእነትርጉሙ አስረክበውናል፡፡ ዘመኑንም ሆነ ትውልዱን ሊዋጅ የሚችል ራእይ ስለሆነ በጊዜ የለም ስሜት ወደ መሬት ልናወርደው ይገባል፡፡ ታላቁ መፅሐፍ ራእይ የሌለው ትውልድ ይጠፋል ማለቱ ራእይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ በዓለማዊ ሕይወትም ስለ ራሳችን፣ ቤተሰባችን፣ ማህበረሰባችን፣ አገራችን ከፍ ሲልም ዓለማችን ልናሳካው፣ ልንደርስበት የምንፈልገው ራእይ አለን፡፡ ዴስቲኒ ኢትዮጵያዎች ወይም «ቲም ንጉሡ » የተገለጠላቸው ራእይ በ50ዎቹ ደቀ መዛሙርት ተተርጉሞ «ብሩህ ተስፋ ከፊታችን ነው !!! እርሱን ዕውን ለማድረግ እንነሳ !!!» በሚል ርዕስ ከወካይ ዜጎች ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዲህ ቀርቧል ፡፡
1 . ተስፋ በሚጣልበት ለውጥ ውስጥ መሆናችንን ብናውቅም በተቃራኒው ከመቼውም ጊዜ በላይ አገራችን መንታ መንገድ ላይ የምትገኝ በመሆኗ ሁላችንም ዛሬ ለመጓዝ የምንመርጠው የትኛውም መንገድ የአገራችንን ዕጣ ፈንታ በእጅጉ የሚወስን መሆኑንና እንደአገር ነገ የሚገጥመን ዕጣ ፈንታ በዋነኝነት በጃችን ላይ እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡
2 . ከሁሉ አስቀድሞ በመጪዎቹ 20 ዓመታት ውስጥ አገራችንን ኢትዮጵያን ሊገጥሟት የሚችሉ፣ መንገዳቸውና መጨረሻቸውም የተለያየ አራት አማራጭ ዕጣ ፈንታዎች (ሴናሪዮዎች) ከፊታችን እንደተደቀኑ ተረድተናል። እነዚህን ንጋት፣ የፉክክር ቤት፣ አፄ በጉልበቱ እና ሠባራ ወንበር ብለን የሰየምናቸው ሲሆን ከነዚህ ሴናሪዮዎች መካከል ሦስቱ በሁላችንም ዕይታ መልካም አማራጮች አለመሆናቸውን ተገንዝበናል። በሌላ በኩል ንጋት / dawn/ ብለን የሰየምነው ሴናሪዮ በአብዛኛው ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል በጎ አማራጭ መሆኑን አይተናል።
3 . ይህ ‘ ንጋት ’ ብለን የሰየምነው ሴናሪዮ ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ቢሆንም ቁጭ ብሎ የሚጠብቀን ሳይሆን ከእያንዳንዳችን ከወዲሁ ትልቅ ኃላፊነት ያዘሉ ተግባራትን የሚጠብቅብን መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም ደግሞ የሴናሪዮ ቡድኑ አባላት ቁርጠኞች መሆናችንንና ይህም የጋራ አቋማችን እንደሆነ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን። ቁጭ ብለን በመጠባበቅ የማይገኘውን ‘ ንጋት ’ ዕውን ለማድረግ ታዲያ ፈጽሞ መተው ያሉብን ተግባራት መኖራቸውንና ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዳችን በጽንኣት ልንወስዳቸው የሚገቡን እርምጃዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል።
4 . ሁላችንም የምንፈልጋትን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ፈጽሞ መተው ያለብን አንድ ዐቢይ ወቅታዊ ጉዳይ አለ። ይኸውም በአገራችን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን ግጭትና ብጥብጥ፣ እርሱንም ተከትሎ የሚከሰተውን የዜጎች ህልፈተ-ሕይወትና የሕዝብ መፈናቀል ከግምት ውስጥ በማስገባት በአገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ደረጃ የምንገኝ የፖለቲካና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሪዎች የምንሰነዝራቸውን ጥያቄዎች፣ በመድረክ የምናደርጋቸውን ንግግሮችና እርስበርስ የምናካሂዳቸውን የሃሳብ ልውውጦች ኃላፊነት በተመላበትና በሰለጠነ መንገድ ለማራመድ እንድንችል እንመክራለን። እኛም ይህንኑ ለማድረግ ተስማምተናል። ቀሪውንና የመጨረሻ ክፍል በነገው ዕትም ይዤ እመለሰላሁ።
አገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !
አሜን ፡፡
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014 ዓ.ም