የቀለማት ህብር፤ የብዝሃነት ምድር፤ የሁሉም መገኛ … አፍሪካ … አፍሪካዊነት ሲነሳ በርካታ ጉዳዮች ቢነሱም ሰሞነኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን መነሻ አድርጌ ህብረቱ የተመሰረተበት አላማ ምን ነበር? አሁንስ ምን ላይ ይገኛል? የሚለውን ሀሳብ ላነሳ ወደድኩ።
የቀደሙት ልባም የአፍሪካ አባቶች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ሲመሰርቱ ዋነኛ አላማቸው በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ ሀገሮችን ነጻ ማውጣት ነበር:: በወቅቱም የተሳካ ስራ ለመስራት የሁሉም የተባበረ ክንድ በመኖሩ ድርጅቱ ሲመሰረት 32 ነጻ ሀገራት ብቻ የነበሩት ሲሆን አሁን 55 ሀገሮችን እንዲያቅፍ ሆኗል።
ይህ ታላቅ ድርጅት በወቅቱ በቅኝ አገዛዝ ለሚማቅቁ ሀገሮች ተገቢውን ወታደራዊ ድጋፍና ስልጠና መስጠቱን ታሪክ የሚዘክረው ሀቅ ነው። ለአብነት ያህልም የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ /ANC/ አፓርታይድን እንዲዋጋና ZANU እና ZAPU የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዚምባብዌን ነጻ እንዲያወጡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሳሪያና ወታደራዊ ስልጠና አበርክቷል:: አፓርታይድን ለማውገዝ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ በአህጉሪቱ እንዳይበር ማዕቀብ መጣሉና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በማሳመን የተመድ አካል የሆነው የአለም የጤና ድርጅት /WHO/ ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጣ ማድረጉ ታሪክ ከመዘገባቸው የድርጅቱ ስኬቶች ተጠቃሽ ናቸው::
አንድነትን ወዳድ ነፃነት ናፋቂ መሪዎች የመሰረቱት ይህ ድርጅት ሰላምንና ደህንነትን በማረጋገጥ በኩልም የተሻለ አፈፃፀም ያለው ሲሆን በሶማሊያ ሌሎች ድርጅቶች መስራት ያልቻሉትን የሰላም ማስከበር ስራ መስራቱንም ታሪክ አይዘነጋውም። አልሸባብን ከሞቃድሾና ከኪስማዩ በማስወጣት በሶማሊያ በህዝብ ተቀባይነት ያለው መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲመሰረት ማድረጉም ከስኬቶች መካከል በጉልህ ቀለም የተፃፈ ነው። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል አስተዋጽኦ የማይናቅ ነበር። በዳርፉርም የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሌሎች የተሻለ አፈጻጸም እንደነበረውም ይነገራል። በዚምባብዌ ድህረ ምርጫ የተከሰተውን ብጥብጥ የአፍሪካ ኅብረት ዘግይቶም ቢሆን በብቃት መፍታት ችሏል:: ይህም ሰላማዊ አህጉር እንድትኖር ከሚደረግ ስኬታማ ጥረት መካከል ተጠቃሽ ነው።
ስድስት አስርቶችን ሊደፍን የተቃረበው ድርጅት እንደ ጥንካሬው ሁሉ ድክመቶችንም አላጣም:: በእርግጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት አንግቦት ከነበረው አባል ሀገራቱን ከቅኝ ገዥዎች ነፃ የማውጣት ተልዕኮ አንስቶ እስከ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ድረስ ከዛም ቀጥሎ በሌሎች አበጀህ የሚያስብሉትን ስኬቶች ተጎናፅፏል::
ያም ሆኖ መንገዱ አልጋ በአልጋ የሆነለት ወይም ሁሉን ተግዳሮቶች በስኬት የተወጣ ተቋም አይደለም:: ይልቁንም አሁንም የህብረቱን መሪዎች ትኩረት የሚሹ ችግሮች ያሉት ነበር:: የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋነኛ ድክመት ለውጭ ርዕዮተ አለም ያለው ከፍተኛ ተፅዕኖ ተጋላጭነት ነው:: ምንም እንኳን የድርጅቱ መርህ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የማይጋብዝ ቢሆንም ይህ መርህ በተግባር ሲተረጎም አልታየም:: ድርጅቱ የገለልተኝነትን መርህ እንደሚከተል አስቀምጦ ነበር፤ ግን አብዛኞቹ የአባል ሀገራት የሚነከሩበት አዙሪት ይህ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በድርጅቱም ላይ የራሱን ጥላ ሲጥል ታይቷል።
ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት መርህ ምክንያት በአምባገነናዊ መንግስታት ግፍና ጭፍጨፋ ሲካሄድ ድርጅቱ በዝምታ አልፏል:: በዚህም የዩጋንዳውን ኢድአሚን ዳዳን መጥቀስ ይቻላል:: ድርጅቱ አፍሪካን ከነጮች አገዛዝ ነጻ ቢያወጣም ከአህጉሪቱ ከፈለቁ አምባገነን አመራሮች ማላቀቅ አልቻለም ነበር:: በዚህም እውነተኛ የህዝቦችን ነፃነት ማረጋገጥ ተስኖት መኖሩም የሚታይ ሀቅ ነው።
ህብረቱ በአንዳንድ ሀገራት ያሉ ግጭቶችን ማስቆም አልቻለም:: ናይጀሪያ በትልቅ ሀገር ሆና ሳለች በየቀኑ በግጭት የምትታመስ ሀገር ሆናለች:: ኮንጎም ከተራ ዘራፊዎች እስከ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች በየቀኑ የሚፋለሙባት በተፈጥሮ የታደለች ግን በዚያው ልክ የተረገመች ሀገር ሆናለች:: በግብጽና በሊቢያ በተከሰተው የአረብ አብዮት ህብረቱ አቋም በመያዝ ቀዳሚ መሆን ሲገባው የውጭ ኃይሎች ቀዳሚ ሲሆኑ ታይቷል:: በኬንያና በዚምባብዌ ምርጫን ተከትሎ የተነሳውን የእርስ በእርስ ብጥብጥ በመግታት በኩልም መዘግየት ታይቶባታል:: ምንም እንኳ በዚምባቤዌ ዘግይቶ የተሳካ ስራ ቢሰራም::
የአፍሪካ ህብረት እነሆ ከስኬቱም ሆነ ከልምዱ ለመማር የሚያስችለው የ59 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ሆኗል:: እናም የወደፊት አቅጣጫውን ሲተልም ያለፈውን ጉዞ ዞር ብሎ ማየት፤ የቆመበትን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቆ መረዳትና መጭውን አቅርቦ ማሰብ ይጠበቅበታል::
አባል አገራት ‹እንቢ ባርነት› ብለው አንዱ ለአንዱ ድጋፍ ሳይነፍግ ከላያቸው ላይ ያስወገዱትን የቅኝ ተገዥነት ቀንበር ዛሬ በእጅ አዙር ሲጣልባቸው ለምን ይሆን ሀይ ማለት የተሳናቸው?
አየሯ ተስማሚ፣ ምድሯ ሁሉ ሀብት የሆነችን አህጉር በአንድ አሰባስቦ ህዝበ እርስ በእርሱ እየተደጋገፈ አንዱ የሌላውን እሴት እያከበረ ለጋራ ጥቅም የጋራ ልማትን ማሰብ አጀንዳቸው ማድረግ አይገባቸው ይሆን? ይህን ጥያቄ ለአባል ሀገራቱ ትተን ኢትዮጵያም የአፍሪካ መዲናዋ ኢትዮጵያም እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም የአፍሪካዊነት አርአያነቷን ታሳይ ዘንድ እመኛለሁ።
ከቅኝ ግዛት ራሷ ለመላቀቅ ቀዳሚ እንደሆነች ሁሉ ሰላምን በማስፈን፣ አንድነቷን በማስጠበቅና ኢኮኖሚዋን በማሳደግ የሁሉ መሪ ልትሆን ይገባታል። የሁሉ ሰብሳቢ የሁሉ አቃፊ አፍሪካዊነትን ተራኪ እንደመሆኗ ልጆችን ሁሉን በአንድ በእኩል የምታኖር የሁሉ ምቾት የሆነች ሀገር ልትሆን ያሻታል። ‹‹የታላቋ አፍሪካ መዲና ነኝ›› የምትል ከሆነ ከኢትዮጵያዊያኑ አልፎ አፍሪካዊያኑም ዳር ድንበሯ ድረስ ‹‹ከየት ነህ? ወዴት ነህ?›› ሳይባሉ ሊንሰራፉበት ይገባል።
እንደመነሻው ሁሉ በጎ ሀሳብ ያነገቡ፤ አሳሪና ጠፋሪ ቅኝ ገዥ ሀሳቦችን ከላያቸው ላይ አሽንቀንጥረው የጣሉ፤ ወደ እድገትና ወደ ታላቅነት የሚገሰግሱ የህብረ ቀለማት ስብጥር የሆኑ አፍሪካውያን ልጆች ለእናት አፍሪካ እንዲኖሯት ያስፈልጋል::
ብስለት
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014 ዓ.ም