የዋጋ ግሽበት ይሉት የኢኮኖሚ ስካር ወይም እብደት ጉሮሮ ላይ እንደተሰካ የአሣ አጥንት፣ አይን ውስጥ እንደገባ የብርጭቆ ስባሪ ፣ ጫማ ውስጥ እንደገባ እሾክ ኢትዮጵያን ሰቅዞ በመያዝ ቁም ስቅሏን እየሳያት ነው።
የዋጋ ግሽበቱ ከነገ ዛሬ ይስተካከላል በሚል ኢትዮጵያውያን በተስፋ ቢጠብቁም ተስፋቸው እንደ እለተምፅዓት ቀን ሆኖባቸዋል።
የዋጋ ግሽበቱም የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ከቀን ወደ ቀን ወደ ሲኦልነት እየቀየረው መሆኑን እየተመለከትን ነው። ለችግሩ የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች ቢወስዱም፤ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሕመም አክሞ በሽታውን ማሻር የሚያስችል ግን አንድም ሁነኛ መፍትሔ አልተገኘም ። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ እ.ኤ.አ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ከቀን ወደ ቀን እጅጉን እየተባበሰ ነው። ታዋቂው የጉተንበርግ ዩኒቨርሲቲ ባጠናው ጥናት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየታመሰ መሆኑን አመላክቷል።
የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርቶች የሚያጠናክሩት ይሄንኑ ሐቅ ነው። በተለይ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው አይነት የዋጋ ግሽበት እንዳጋጠማት የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ያሳያል።
በ2014 ዓ.ም የመስከረም ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ወርሐዊ ሪፖርት አመላክቷል። በዚሁ ወር የምግብ ነክ ዋጋ ግሽበት ደግሞ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 42 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ይህ የዋጋ ግሽበት የፈጠረው ድንጋጤ ሳንለቅ በጥቅምት ወርም 33 በመቶ የነበረው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት በኅዳር ወር ወደ 35 በመቶ ማደጉ ተሰምቷል።
በሰዎች የቀን ተቀን ሕይወት ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የምግብ ፍጆታ ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወር ከነበረው 28 በመቶ በኅዳር ወር ተባብሶ 41 በመቶ መድረሱም፤ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ እንዳደረገው እየተነገረ ነው።
በተለይ በዳቦና እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም ተጠናክሮ ቀጥሏል። የሩዝ፣የእንጀራ፤ የዳቦ፤ የጤፍ፤ የስንዴ፤ የማሽላ፤ የበቆሎ፣ የገብስ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓስታና ማካሮኒ ዋጋ በፍጥነት ጨምሯል። ሥጋ፣ የምግብ ዘይት ፣ ወተት፤ አይብና ዕንቁላል፤ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም እና የመሳሰሉት ምግብ ነክ ነገሮች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከመጠን በላይ በማደጉ እነሥጋ፣ የምግብ ዘይት ፣ ወተት፤ አይብና ዕንቁላል፤ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም እና መሰል ነገሮች እጅግ የተጋነነ ዋጋን በመያዛቸው እነዚህን ምግቦች ገዝቶ መጠቀም በተለይ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ እርከን ላይ ለሚገኙ ዜጎች የቅንጦት ምግቦች ከሆኑ ውለው አድረዋል።
አሁን አሁን ደግሞ በመካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚባለውም የማኅበረሰብ ክፍል እነኝህ ምግቦች ቅጦንት እየሆኑበት መምጣት ጀምረዋል።
በአገራችን የሚታየው የኢኮኖሚ ስካር አንድምታው ምንድን ነው ? መፍትሔውስ ምን ይሆን? ስንል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አናሊሲስ ባለሙያን አቶ ቴዎድሮስ ገብሩን አነጋገርን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ ፤ የዋጋ ግሽበት ማለት በምግብ እና ምግብ ነክ ባልሆኑ በሸቀጣሸቀጦች እንዲሁም ዜጎች ሕይወታቸውን ለማስቀጠል በሚጠቀሟቸው አገልግሎቶች ላይ የሚታይ ዋጋ እድገት የመጠን መግለጫ ነው። የዋጋ ግሽበት
ሲጨምር የገንዘብ የመግዛት አቅም ይቀንሳል። የዋጋ ግሽበት ሲቀንስ ደግሞ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ይጨምራል ወይም ባለበት ይቆማል። የዋጋ ግሽበትና የገንዘብ የመግዛት አቅም በተቃራኒ አቅጣጫ የሚጓዙ (Inversely Related) ናቸው። አንዱ ሲጨምር ሌላኛው ይቀንሳል።
የዋጋ ግሽበት(Inflation) የሚፈጠረው በሁለት ዐቢይ ምክንያቶች ነው ። አንደኛው የማምረቻ ወጪ መጨመር (cost push factor) ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የተጠቃሚው መጠን መጨመር ( demand pull factor) ነው። የአምራቾች አጠቃላይ የምርት ወጭ (production cost) እየጨመረ በሄደ ቁጥር አምራቾች ወይም አቅራቢዎች በምርት ሂደት የሚያወጡትን ወጪ ለመሸፈን በአመረቱት ምርት ላይ ዋጋ ይጨምራሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዋጋ ግሽበት እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። በሌላ በኩል የተጠቃሚው መጠን መጨመር (demand pull factor)የሚባለው ላይም የሚፈጠረው የዋጋ ግሽበት የተጠቃሚው ፍጆታ እየጨመረ ሲሄድ የሚፈጠር ነው ። ይህ ማለት ብዛት ያለው ብር ወደ ገበያው ውስጥ ሲገባና የሸቀጥ ወይም የአገልግሎት መጠን ደግሞ ሲቀንስ ወይም ባለበት ሲቆም የሚፈጠር ግሽበት ነው።
ይህም ማለት ተጠቃሚው አንድን እቃ ለመግዛት እጁ ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠ ገንዘብ ሲኖረው የእቃው አቅርቦት ግን ባለበት ከሆነ ወይም ከቀነሰ እጥረት (Scarcity) ስለሚፈጠር ተጠቃሚው ተጨማሪ ብር አውጥቶ እቃውን ይገዛል ማለት ነው። የተጠቃሚው የመግዛት ፍላጎት(Demand) ሲጨምር የገበያው የአቅርቦት መጠን ሲቀንስ የእቃ ዋጋ ይጨምራል፤ በዚህም የተነሳ የዋጋ ግሽበት ይፈጠራል።
በኢትዮጵያ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ግን ከእነኝህ ሁለት አመክንዮች ውጭ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ቴዎድሮስ፤ በእኛ አገር ለሚታየው የዋጋ ግሽበት ዋነኛው መነሻ እንደ አገር ያለንበት ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።
የኮቪድ ወረርሽኝ እና የኢትዮጵያ ብር ዶላርን የመግዛት አቅሙ እንዲቀንስ መደረጉ ደግሞ ሌሎች አመክንዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዓለም ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መገደቡ ይታወቃል። ይህ ደግሞ ካለፈው ሁለት ዓመታት ጀምሮ የዓለምን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንዲሽመደመድ አድርጎታል።
አሁንም የኮቪድ ተጽዕኖ በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ሙሉ በሙሉ ሊቀረፍ አልቻለም። በአገራችን በተመሳሳይ ወረርሽኙ በፈጠረው ተጽዕኖ የኢኮኖሚ ዕድገቱ እክል ገጥሞት ቆይቷል። ይህ የኮቪድ ተጽዕኖ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።
ከኮቪድ ወረርሽኝ በተጨማሪ እንደአገር ያለንበት ያልተረጋጋ ፖለቲካ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ደረጃ ከማወኩም በተጨማሪ ለጦርነት የሚወጡ ወጭዎች ከፍተኛ በመሆናቸው ከባድ የዋጋ ንረት አስከትለዋል። ጦርነቱ ያሳደረው ጫና ቀላል አይደለም ሲባል የጦርነት መጨረሻ የአገር ሰላምን ያረጋገጠ ካልሆነ በስተቀር ፤ በጦርነት የመጨረሻው ሂደት እንደ ፋብሪካ ግብዓት በመጨመር ምርት የሚገኝበት አይደለም። በውጊያ ወቅት የሚተኮሱ ተተኳሾ በሙሉ በውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ናቸው። መሠረታዊ ለሆኑ ፍጆታዎች መውጣት የነበረባቸው ወጭዎች ለተተኳሽ በወጡ ጊዜ የመሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት እንቸገራለን።
ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል። ከዚህ ዓመት በፊት በነበሩ ለ20 ዓመታት ለመከላከያ ያወጣናቸው ወጪዎች ቢደመሩ በዚህ ዓመት ካወጣነው በታች እንደሚሆኑ አያጠራጥርም።
ይህ ማለት አሁን በአገራችን ያለው ጦርነት የዋጋ ግሸበትን በመፍጠር በኩል ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ጠቋሚ ነው ። ሌላው በሶስተኛነት የጠቀሱት ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ብር ዶላር የመግዛት አቅሙ እንዲቀንስ መደረጉን ነው።
እርግጥ ነው ዶላርን የምንዛሪ አቅም በጨመርን ጊዜ ወደ አገራችን የሚመጡ ኢንቨስተሮችን በከፍተኛ ደረጃ ይሳባሉ። ይህ ማለት ደግሞ ወደ ውጭ የምንልካቸውን ምርቶች በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያስችላል ማለት ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ብር ዶላርን የመግዛት አቅም በወረደ ቁጥር የዋጋ ግሽበቱንም ማባባሱ የማይቀር ነው።
አሁን በተጨባጭ በአገራችን የምናየውም ይሄንኑ ነው። እነኚህ ሶስት ነገሮች ተደማምረው በተለይ በታችኛው የኑሮ ደረጃ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ሕዝብ ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ችግር እየዳረጉት መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ይገልጻሉ።
መፍትሔ እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ፤ የአገራችን ኢኮኖሚ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ካደረሰበት ተጽዕኖ ሳይላቀቅ እና የአገራችን ብር ዶላርን የመግዛት አቅሙ እየተሽመደመደ ባለበት ሁኔታ «በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ» እንዲሉ ወደ ጦርነት ገባን።ጦርነቱ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱን እጅግ በከፋ መልኩ አባባሰው ።
አሁን ላይ ለሚስተዋለው ዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት ደግሞ ጦርነቱ ስለመሆኑ የግድ የኢኮኖሚ ተንታኝ ባለሙያ መሆንን አይጠይቅም። ስለዚህ አሁን ላይ የገጠመንን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ ወይም ባለበት ለማስቆም የጦርነቱን ሁኔታ በሰከነ መልኩ በማየት እና ለሰላም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ በመክፈል ጦርነቱ የሚቋጭበት ዘዴ መፈለግ አማራጭ የሌለው ነው ።
ጦርነቱ ሲካሄድ ኢኮኖሚውን የሚጎዱት ለጦርነት የምናወጣቸው ወጭዎች ብቻ አይደሉም ።ሰላም ከአገራችን በጠፋ ቁጥር የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ አገራችን መምጣት ያቆማሉ። ምክንያቱም ጦርነት ላይ ባለች አገር ኢንቨስተር ምን ሊያደርግ ሊመጣ ይችላል? ጦርነት የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ አገራችን እንዳይመጡ ከማድረጉም ባለፈ የውጊያ ቀጠና ከምንላቸው የሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች ይሰበሰብ የነበረው የገቢ ታክስ አሳጥቶናል።
ይህንን ገቢ አገሪቱ ማግኘት አለመቻሏ ኢኮኖሚያውን ለችግር መዳረጉ የማይቀር ነው ። ስለዚህ ጦርነቱ የሚቆምበት አግባብ ቢፈጠር የሚቀንሰው ለጦርነቱ የምናወጣው ወጪ ብቻ ሳይሆን ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ይገኝ የነበረው ገቢ ማግኘት እንድንችል ያደርገናል።
የተረጋጋ ፖለቲካ የሚፈልጉ የውጭ ኢንቨስተሮችም በከፍተኛ ደረጃ ወደ አገራችን ይስባል። ሌለው የዋጋ ግሽበቱን ሊቀንሱ ወይም አሁን ካለበት ሳይባባስ ባለበት እንዲቀጥል ሊያደርጉ ከሚችሉ ነገሮች መካከል ከውጭ የሚገቡ ሸቀጣ ሸቀጦችን እና ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮችን መጠን በመቀነስ ወደ ውጭ የሚላኩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እና ምግብ ነክ ነገሮች የሚጨምሩ ሁኔታዎችን እና አሠራሮችን መዘርጋት ነው ። በተለይ አሁን ላይ ለቅንጦት እና መሰል ነገሮች ከውጭ የምናስመጣቸውን ነገሮች ወደ አገራችን እንዳይገቡ ለተወሰነ ጊዜ ማገድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ መሠረታዊ የሚባሉ የሰው ልጆች ፍጆታዎች ላይ መንግሥት ለተወሰኑ ጊዜያት ድጎማ ቢያደርግ እና መሰል እርምጃዎች ቢወሰዱ ምን አልባት አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት ቢቻል መቀነስ ካልሆነ ደግሞ አሁን ካለበት ማቆም እንደሚቻል ያስረዳሉ። ሦሥት አይነት የዋጋ ግሽበት ደረጃዎች አሉ የሚሉት ባለሙያው፤ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፣ ከአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ባንክ እና ከዓለም ባንክ ሪፖርቶች በመነሳት አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከመካከለኛ ደረጃ አልፎ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እየሄደ መሆኑን እንደሚያሳይም አብራርተዋል። ጤናማ (normal) የዋጋ ግሽበት የሚባለው ከአምስት በመቶ በታች ነው ።
ጤናማ (normal) የዋጋ ግሽበት ከሌለ በአንድ አገር ውስጥ ዕድገት የለም ማለት ነው ። ነገር ግን የዋጋ ግሽበቱ ከአምስት በመቶ በበለጠ ቁጥር በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና እየበረታ ይሄዳል። አሁን ላይ በአገራችን ያለው የዋጋ ግሽበት ከአርባ በመቶ በላይ ነው ። ይሄ ደግሞ ከባድ ነው ። የከፋ ወደሚባለው የዋጋ ግሽበት ደረጃ እያደረስን ነው።
የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ የሚስችሉ የመፍትሔ እርምጃዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ ነገሮች ይኖራሉ። ከመንግሥት ቁጥጥር ስር ውጭ የሆኑ ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችም አሉ። ስለሆነም የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ ወይም ሳይጨምር ባለበት ለማስቆም ቢያንስ መንግሥት በእጁ የሚገኙ ሁሉንም አማራጮችን መጠቀም አለበት ።
በዚህም ኢትዮጵያ የገጠማትን የኢኮኖሚ እብደት ወይም ስካር ማስቆም እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014