የትምህርት ተቋማት የአንድ አገርና ሕዝብ ብቻ ሳይሆኑ አጠቃላይ የሰው ልጅ ሰብዓዊ ተቋማት ናቸው። የትምህርት ተቋማት በማንም ላይ ምንም አይነት ልዩነት አያደርጉም። አድርገው ከተገኙም፣ በትህትና ስንገልፀው ቢያንስ ግፍ ነው።
የትምህርት ተቋማት የእውቀት ምንጭ፣ የሙያዎች ሁሉ መፍለቂያ፣ መገኛዎች ናቸው። በመሆናቸውም ፍጥረት ሁሉ ወደ እነሱ ያመራል፤ ፍጥረት ሁሉ አይኑን እነሱ ላይ ይጥላል፤ ፍጥረት ሁሉ ስለ እነሱ ቸር ቸሩን መስማት ይፈልጋል። ከተፈጥሮ የተጣላ ካልሆነ በስተቀር፣ ፍጥረት ሁሉ የእነዚህን ተቋማት ክፉ ማየትም ሆነ መስማት አይፈልግም።
ዛሬ ዛሬ በአገራችን ሆን ተብሎ፣ ታስቦበትና ታቅዶ ተቋማቱን እየተፎከረ ማውደም ተጀመረ እንጂ የትምህርት ተቋማት ከእምነት ተቋማት ባልተናነሰ መልኩ የሁሉም እምነት፣ የሁሉም ፍቅር፣ የሁሉም ባለቤትነት ወዘተርፈ እኩል የሚንፀባረቅባቸው ናቸው። በመሆናቸውም የሁሉም ናቸው። መግቢያችንን እዚሁ ላይ እንግታና ወደ ተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ እንሂድ።
በዛሬው አምዳችን ሽፋን ያገኝ ዘንድ የፈለግነው በርእሳችን ጠቆም ያደረግነው “በላይ ዘለቀ ቁጥር 2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት”ን ነው፤ እንግዳችንም የትምህርት ቤቱ ዋና ርእሰ መምህር ዳንኤል መንቴ ናቸው።
በላይ ዘለቀ ቁ.2 ት/ቤት የሚገኘው ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ሲሆን ቀደም ካሉት የትምህርት ተቋማት አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ ከመዋእለ ህፃናት ጀምሮ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ፣ በሶስት ሳይክል የሚያስተምር ሲሆን፤ ለየት የሚያደርገው ከእነዚህ ሳይክሎች (ደረጃዎች) በተጨማሪ “አካቶ”ን አካቶ መገኘቱ ነው። (አካቶ ማለት፣ ፍንጭ ለመስጠት ያህል፣ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህፃናት (አካል ጉዳተኞች፣ የአእምሮ ችግር ያለባቸው …..)፣ ከሌሎች ጤናማ ከሆኑት እኩዮቻቸው ጋር በአንድ ትምህርት ቤት በማካተት፣ ከፍላጎታቸውና ከዕምቅ ችሎታቸው ጋር የተጣጣመ ትምህርት እንዲሰጣቸው ማድረግ (እነሱን የሚያካትት ፕሮግራም በማዘጋጀት) ማለት መሆኑን እንያዝ።)
በእነዚህና ሌሎች መሰል ትምህርታዊ ምክንያቶች ሰሞኑን በትምህርት ቤቱ ተገኝተን ከትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ከአቶ ዳንኤል አመንቴ ጋር ውይይት አድርገናልና እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ዋና ርእስ መምህር ዳንኤል እንደሚናገሩት በላይ ዘለቀ ቁ.2 ትምህርት ቤት ከቀደምቶቹ አንዱ ሲሆን የገፅታ ግንባታ ስራ ባለመሰራቱ ምክንያት ብዙም ያልተባለለት፤ ምናልባትም በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ሳይቀር ብዙም ተመራጭነት ያልነበረ ትምህርት ቤት ነበር። “ወልዶ መጣያ” ተደርጎም የታሰበበት ጊዜም ነበር። እንደ ዱርያ መዋያም ነበር የሚታየው። የተማሪዎች ስርአት አልበኝነትም ይታይበት የነበረ ትምህርት ቤት ነበር። የሚመዘገብ ጠፍቶ አምስት ስድስት ክፍሎች ሁሉ ባዶ ነበሩ። ተማሪ ወደዚህ አይመጣም፤ ወይም ወላጅ ልጁን ወደዚህ አምጥቶ አያስመዘግብም ነበር።
ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ሰዓት የገፅታ ግንባታ ስራ በመሰራቱ፣ የአጥር ግንባታ በመከናወኑና ሌሎችም፣ በፖስተር የማስተዋወቅ ስራዎች ሁሉ ሳይቀሩ በመሰራታቸው ምክንያት ተቋሙ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል። አሁን ክፍሎች በሙሉ ተይዘዋል።
አሁን፣ የአካባቢውም ሆነ በርቀት ያሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደዚህ ትምህርት ቤት በማምጣት እያስመዘገቡ ነው። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ሲሆን፤ አንድም ባዶ ክፍል አይገኝም፤ የለም።
በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ 2ሺህ 100 ገደማ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ያሉ ሲሆን፣ በመምህራንም በኩል ምንም እጥረት የለም፤ በተሟላ መልኩ ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል። የክበባት ቁጥር 12 ሲሆን ሚኒ ሚዲያን የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ የተማሪዎች ባህርይ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር፣ የመማር ፍላጎታቸው እንዲቀሰቀስ፣ አጠቃላይ ግንዛቤያቸውን ለማሳደግ … በጥሩ ሁኔታ በመስራት ላይ ናቸው። ምርጥ ታሪኮችን፣ እንደ አሊባባ አይነት ሰዎችን ጥረትና ስኬት የሚተርኩ ተረኮችን እናነብላቸዋለን። ይህም የአስተሳሰብ ለውጥ እያመጣና እየተዳከመ የነበረውን የተማሪው የመማር ፍላጎት እንዲቀሰቀስ እያደረገ ነው።
የተማሪዎች የመማር ፍላጎት የማጣት ነገር በሚመጣበት ሰዓት የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ለመቀስቀስ፣ የማወቅ ጉጉታቸውን ለማሳደግ ስመ-ጥር፣ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን በመጋበዝ ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግር እንዲያደርጉ ያደርጋል።
በትምህርት ቤቱ አስተዳደር የሚዘጋጅ ሽልማትም አለ። ከአንድ እስከ አስር (ቶፕ 10) ለሚወጡ ተማሪዎች ሽልማት ይሰጣል። ይህም ብዙዎቹን እያበረታታና ሽልማቱን ለማግኘት እንዲሰሩ እያደረገ ያለ ማንቂያ በመሆን ውጤት እያመጣ ነው።
ርእሰ መምህር ዳንኤል የትምህርት ጥራትን በተመለከተም፣ በእኛ በኩል ያለው አሰራር የመንግስትን ካሪኩለም ማስተማር ነው። በዛ በኩል ምንም ችግር የለም። የመጻሕፍትም ሆነ መምህራን እጥረት የለም። በተቋም ደረጃ የትምህርት ጥራት እንዳይጓደል እየሰራን ነው በማለት ይናገራሉ። ይህ ማለት በትምህርት ቤት ደረጃ ማለት ነው።
ሌላኛውና በርእሳችን “መንታ ሰብእና” ያልንለት የበላይ ዘለቀ ቁጥር 2 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪ ገፅታው የልዩ ትምህርት ፕሮግራምን በተጨማሪነት መያዙ ነው።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ርእሰ መምህር ዳንኤል መንቴ እንደሚናገሩት ይህ በአሁኑ ሰዓት 34 ተማሪዎች ያሉት የልዩ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥና እድገት እያመጣ፤ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ልጆችም በከፍተኛ ደረጃ እየተሻሻሉ፣ እየተለወጡና የባህርይ ለውጥ እያመጡ ነው።
የልዩ ፕሮግራም (በእርግጥ “ልዩ” የሚለው ስያሜው አይደለም። ፕሮግራሙ ቤተሰብን ሲያስጨንቁ የነበሩ ችግሮችን የመጋራትና የማገዝ፤ በሳይንሳዊ መንገድ የአእምሮ ዝግመት ችግር ያለባቸውን ልጆች የባህርይ ለውጥ እንዲያመጡ የማድረግ ተግባር ነው) በከፍተኛ ደረጃ ማህበረሰባዊ ችግሮችን እየፈታ ያለ ፕሮግራም ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ወደ እዚህ የሚመጡት ልጆች በተሟላ የጤንነት ሁኔታ ላይ ያሉ አይደሉም። የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ናቸው። ቤተሰቦቻቸው “አይ በቃ አይድንም” ብለው ቤት ውስጥ ደብቀው ያስቀመጧቸውን ሁሉ ነው ወደ እዚህ ተቋም (በአካባቢው ሌሎች ትምህርት ቤቶችም አሉ) እንዲመጡና ይህንን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ያለው። ወላጅ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑትን ልጆቹን ከደበቀበት በማውጣት ወደ እኛ እያመጣ ነው። ልጆቹ የአእምሮ ጤና፣ የመስማት፣ የመናገር፣ አካላቸውን ማዘዝ፣ ማንቀሳቀስ (በራሳቸው እጅ ሁሉ መመገብ) የማይችሉ ናቸው።
ሰውነታቸውን ማንቀሳቀስ፣ እራሳቸውን ችለው ምግብ እንኳን መመገብ የማይችሉ ልጆች ዛሬ ተለውጠው ራሳቸውን ችለው እየተንቀሳቀሱና ተጨማሪ ስራዎችንም መስራት ወደ መቻሉ እየሄዱ ነው። (በትናንትናው እለት በዚሁ ጋዜጣ “ልጆች” አምድ ላይ ያወጣነውን፣ የበየነን ታሪክ ያነቧል።) የእጅ ስራ ይሰራሉ። ከነበሩበት የአእምሮ እድገት ውሱንነት እየወጡ ያሉም አሉ።ስለ “አካቶ”ዎቹም የሚሉት አላቸው።
በአሁኑ ሰዓት ከአካቶ ፕሮግራም ወጥተው ወደ መጀመሪያው ሳይክል ተሸጋግረው ከ1ኛ እስከ 4ኛ (የመጀመሪያው ሳይክል) ክፍል በመማር ላይ ያሉ አሉ። ማህበራዊ ሕይወትን እየተላመዱ ነው። ከእኩዮቻቸው ጋር እየተጫወቱ ነው። አካውንት ሁሉ የከፈትንላቸው አሉ። እራሳቸውን የመቻል ስራ ሁሉ እየሰሩ ነው። የቤተሰብ እገዛ ካገኙ ምንም ችግር የለባቸውም።
ራሳቸውን ለመቻል እየሰሩም ያሉ አሉ። ለምሳሌ የሞባይል ካርድ እንዲሸጡ አድርገናል። መምህራን በሙሉ ካርድ የሚገዙት ከእነሱ ነው። የተለያዩ ስራዎችንም በመስራት ላይ ናቸው።
የአእምሮ እድገት ውሱንነት የሚታይባቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያመጡ ነው። ለምሳሌ ያ የምታየው ስጋጃ (በእጃቸው በራቸው ላይ የተነጠፈን ጥሩ ምንጣፍ እያሳዩ) በእነሱ የተሰራ ነው።
ልጆቹን በተመለከተ ከመጠን በላይ ጫፍ የወጡ ይመጣሉ፤ በሂደት ግን እየተገሩ፣ ማህበራዊነትን እየተዋሃዱ ይመጣሉ።
ይህ የሚያሳየው እነዚህ ልጆች እራሳቸውን ችለው ሰርተው መኖር የሚችሉ መሆናቸውን ነው። ያንን ለማምጣትም ነው ትምህርት ቤቱ በዚህ አይነት መንገድ እያሰለጠናቸውና ድጋፍና ክትትል እያደረገላቸው ያለው። ለውጥም እየታየ ነው። የቤተሰብ ድጋፍ ከታከለበት ደግሞ የበለጠ ለውጥ ይታያል። የአንዳንዶቹ ችግር የቤተሰብ ድጋፍ ያለ ማግኘት ነው። ያንን እንዲያደርጉ ከቤተሰብ ጋር ስብሰባ እየጠራን እየተነጋገርን ነው። እየተግባባን፤ እየተጋገዝንም ነው።
አንዳንድ ወላጆች ልክ እንደ መደበኛው ተማሪ አይነት ለውጥ እንዲያመጡላቸው በመፈለግ እየመጡ ምንም አትሰሩም ይሉናል። አብዛኛው ቤተሰብ ደግሞ ስቃዩ ሁሉ እንደ ቀነስንለት ስለሚያውቅ ያመሰግነናል። ባጠቃላይ በየጊዜው ስብሰባ እየጠራን ከወላጆች ጋር እንወያያለን፤ ያለው አመለካከት ጥሩ ነው።
የልዩ እገዛው ፕሮግራም የሚተዳደረው በመንግስት በጀት ነው። በተጨማሪም ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ድጋፍ ያደርጋሉ። የራሱ የሆኑ የሰለጠኑ፣ ምሩቅ፣ የመንግስት ቅጥር የሆኑ መምህራን አሉት። ትምህርቱ የመሰጠው በእነሱ ነው።
የዚህ ፕሮግራም ትልቁ ችግር በአንድ ወገን ጥረት ብቻ ልጆቹ የሚለወጡ አለመሆኑ ነው። ልክ የትምህርት ቤቱንና መምህራኑን አይነት ጥረትና ድጋፍ ከቤተሰብ፣ ማህበረሰብ … ብዙ ይጠበቃል። ብዙ ልጆች ካሉበት የጤና ችግር ከወጡ በኋላ ተመልሰው ወደ እዛው እየሄዱ ነው። ይህ ደግሞ ምክንያቱ ልጆቹ የቤተሰብ ድጋፍና ክትትል አለማግኘታቸው ነው። አሁን ትልቁ ችግር ይህ ነው። ልክ እንደ መምህራኑ ሁሉ ከቤተሰብም ድጋፍና ክትትል የሚደረግላቸው ልጆች ወደ መደበኛው የትምህርት እርከን እየተሸጋገሩና ውጤትም እያመጡ ነው። ይህ የሚያሳየው ልጆቹ የቤተሰብም ሆነ የማንኛውም አካል ተገቢው ድጋፍና ክትትል ከተደረገላችው በቀላሉ ካሉበት የአእምሮ እድገት ውሱንነትም ሆነ አጠቃላይ የጤንነት ችግሮች በቀላሉ ሊወጡ የሚችሉ መሆኑን ነው።
እንደ ዋና ርእሰ መምህር ዳንኤል ማብራሪያ በልዩ ድጋፍም ሆነ አካቶ ፕሮግራም የታቀፉት ልጆች ከሌሎች፣ ለመደበኛ ተማሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ጥሩ ነው፤ የሚያገላቸውም የለም። እነሱም እራሳቸውን አያገሉም። አብረው ነው የሚጫወቱት። ብሄራዊ መዝሙር ሁሉ ይዘምራሉ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 23/2014