አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት ምክረ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ መቋቋሙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጽሕፈት ቤቱ ትናንት ባሰራጨው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ስምንት አባላት ያለው ኮሚቴ የተዋቀረው ከፌዴራል መንግሥት፣ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ነው።
የኮሚቴ አባላቱ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት ከዚህ በፊት የተጠኑ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ እና ህዝቡን በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆን የምክረ ሃሳብ እንዲያቀርቡ አቅጣጫ መቀመጡ ተገልጿል።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል ጥያቄ መፍትሄ ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ መውጣቱ ውዝግብ ማስነሳቱን መግለጫው አስታውሷል። በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን በአግባቡ አለመካለሉ አካባቢው የንትርክ እና የግጭት አጀንዳ ከመሆን ይልቅ የልማት እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገ ጥባቸው አካባቢዎች እንዲሆኑ በማሰብ ችግሩን ጥናት ላይ ተመስርቶ ዘላቆ መፍትሄ ለመስጠት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ቀደም ሲልም ጥናቶች መደረጋቸውን መግለጫው ጠቅሶ፣ ሆኖም ግን በጥናቱ ውጤት ላይ ተመስርቶ ጉዳዩን መቋጨት ባለመቻሉ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ አወዛጋቢ መሆኑ ተመላክቷል።
በመሆኑም በጥናት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ስምንት አባላት ያለው የኮዂቴ አባላት የተመረጡ ሲሆን፣ ዝር ዝራቸ ውም እንደሚከተለው ቀርቧል።
1. ወይዘሮ ሙፈሪሀት ካሚል የሰላም ሚኒስትር ሰብሳቢ
2. ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ፣የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት (አባል)
3. አቶ አህመድ ቱሳ አባል፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ (አባል)
4. ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ (አባል)
5. ኢንጂነር ታከለ ኡማ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ (አባል)
6. አቶ እንግዳወርቅ አብጤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ( አባል)
7. ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ(አባል)
8. አቶ ተስፋዬ ቤልጅግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባው የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር