የወደቀ እንጨት ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ ኢትዮጵያ ሥር ሰድዶ ከኖረ በሽታዋ መላቀቅን ፈልጋ “ከዘላዓለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት” በማለት መቀነቷን ባጠበቀችበት ቅጽበት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ እንቅፋቶች እግር በእግር ተከታትለው ሲንጧት ከራርመዋል፡፡ አንድ ችግሯን ስትሻገር ሌላው ችግሯ ከፊት እየቀደመ በፈተናት ጊዜም ኢትዮጵያ አፍጣጭ ገልማጯ በዝቶ ምጧ እንደበዛባት ሴት በጽኑ ተጨንቃ ላለፉት በርካታ ጊዜያት ስትቃትት ሰነባብታለች፡፡
በአገሪቱ ከዛሬ ሶስት ዓመታት ወዲህ የታየው ፖለቲካዊ ለውጥ ለብዙዎች ብሩህ ተስፋን ያስታጠቀ ቢሆንም ጥቂቶች ግን ጥቅማችን ተነካ በሚል አጀንዳ እየቀረጹ እዚህም እዚያም የሕዝብ ሮሮና ብሶት እንዲበረታ ብዙ ሺ ኮሽታዎችንና መደናገጦችን ፈጥረው አልፈዋል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል የአንበጣ መንጋ መከሰቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ የሆነው ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም እንዲሁ ሌላኛው እንቅፋት በመሆን የሰዎችን ጤና ከመጉዳት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ እየተናጠች ባለችበት ወቅት ታዲያ “የግፍ ግፍ አንገፍግፍ” እንዲሉ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለሰማይ ለምድር የከበደውን ክህደት በአገር ላይ መፈጸሙ ትልቁና ታሪክ የማይረሳው በደል ነው፡፡ ቡድኑ ካደረሰው በደል በላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በፍርደ ገምድልነቱ በርካታ ጫናዎችን በአገሪቱ ሲያደርስ ቆይቷል፡፡
“ውሻ በበላበት ይጮሃል” እንደሚባለው ሆነና ነገሩ ዓለም አቀፍ የሆኑ ትላልቅ ብሎም ስመ ጥር የሆኑ ሚዲያዎች ሳይቀሩ የኢትዮጵያን እውነት ወደ ጎን በመተው ለአሸባሪው ቡድን በመወገን በወቅቱ በርካታ ዘገባዎችን ሲሰሩ ታዝበናል፡፡ ታዲያ በሰሩት ዘገባ ሁሉ የጥቅም ተጋሪ መሆናቸውን ከማሳበቅ ባለፈ ትዝብት ላይም ወድቀው በመመልከታችን የኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ ልቦችን አጠይሞ አልፏል፡፡
ይሁንና እውነቷን ይዛ በእውነት የቆመችው አገር ኢትዮጵያ ግን ዛሬም በቁርጥ ቀን ልጆቿ ትግል የተጋረደባትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በእውነተኛ ምስክርነት በመግፈፍ የተጫነባትን የቆሸሸ ስም በመልካም ሥራዋና በጀግንነቷ መቀየር ችላለች፡፡ ከመጋረጃው በስተጀርባ ያለችው ሰላማዊ ኢትዮጵያ መታየት ችላለች፡፡ በርካቶች ትናንት ኮቪድ 19 ካደረሰው ጫና በበለጠ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ባለው ጦርነት ምክንያት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የጸጥታ ችግር አለ በማለት የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዳይደረግ ግፊት ሲያደርጉ ሰነባብተዋል፡፡
በርካታ ጫናዎችን ተቀብላ ስታስተናግድ የቆየችው ኢትዮጵያ “ሙያ በልብ ነው” እንዲሉ የቤት ሥራዎቿን በመሥራት ሰላማዊ ሁኔታን ፈጥራለች፡፡ ስለኢትዮጵያ የሚወራው ሁሉ ገጽታን የማበላሸትና የማጠልሸት ስትራቴጂ መሆኑን ለመግለጽም ዲያስፖራው ወደ እናት አገሩ እንዲገባ የተደረገው ጥሪ የመንግሥት ትልቁ ስኬት ሆኑ አልፏል፡፡ ዲያስፖራውም ‹‹ጠሪ አክባሪ ተጠሪ ተከባሪ›› በማለት ጥሪውን ተቀብሎ ወደ አገር ቤት በመግባት መሬት ላይ ያለውን እውነት ከመረዳት ባሻገር በኮቪድ 19 እና በጦርነት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ችሏል፡፡ ከዚህም ባለፈ 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ላይ ያለምንም የጸጥታ ችግር መከናወን እንደሚችል እማኝ መሆን ችለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሚካሄድ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በአካል ማካሄድ ሳይቻላቸው ቀርተዋል፡፡ ጉባኤውን በህብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች የሉም በማለት ሙግት ገጥመው የነበሩ አካላት በርካታ ጫናዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ በሰራችው የጀግንነት ሥራ እንዲሁም ባደረገችው ከፍተኛ ዲፕሎማሳዊ ጥረት መሪዎችን በአካል የሚያገናኘውን ጉባኤ በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ላይ ሊካሄድ ተወስኗል፡፡
ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ በተለይም በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ውንጀላዎችን የሚያነጻ ይሆናል፡፡ ከዚህም ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል፡፡ ታዲያ አዲስ አበባም እንግዶቿን ለመቀበል ከወዲሁ ብቁና ዝግጁ ሆና መጠበቅ ያለባት መሆኑ የግድ ነው፤ በተለይም ለጉባኤው ስኬት የጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛና ቱሪዝም ሥፍራዎች የኢትዮጵያን ገጽታ በሚገነባ መልኩ በቂና ተግባራዊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
እንግዶች በኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ቆይታ ስኬታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተውና ተናበው ፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በተላበሰ መንገድ እንግዶችን መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት የህብረቱ አባል አገራት በኢትዮጵያ ላይ ሲደረግ የቆየውን ጫና ወደ ጎን በመተው ለህብረቱ ህግና መርህ በመግዛት ጉባኤው በህብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ በአካል እንዲካሄድ መወሰናቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው መሆኑን መንግሥት ያምናል፡፡ በመሆኑም እንግዶቹ በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታ ሰላማዊ እንዲሆን በመሥራት አምነው የመጡትን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማሳየት ይጠበቃል፡፡
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራ ከያዛቸው አማራና አፋር ክልሎች በሽንፈት በተወገደ ማግስት አይሆንም ያሉት ሆኖ፤ አይሳካም የተባለው ተሳክቶ፤ ዲያስፖራው ወደ እናት አገሩ ገብቶ፤ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት 35ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ መቻሉ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ነበራዊ ሁኔታ አንጻር ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ስኬት ለማጣጣም በተገኘው ድል ከመኩራራት ባለፈ ቀሪ የቤት ሥራዎችን በአግባቡና በጥንቃቄ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
የወቅቱ ዓለማቀፋዊና አገራዊ ሁኔታዎች በፈጠሩት ቀውስ በእጅጉ ተጎድቶ ለከራረመው የቱሪዝም ዘርፍ አጋጣሚው የሚፈጥረው ዕድል ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለምና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ትናንት የቱሪዝም ፍሰት እንዳይኖርና ባለሃብቱ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ እንዳያለማ የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉ የቆየ ቢሆንም ዛሬ የህብረቱ አባል አገራት ጉባኤው በአካል አዲስ አበባ እንዲካሄድ ማድረጋቸውም የሚለውጠው በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ክስተቶች ይኖራልና የተገኘውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
እናት አገር ኢትዮጵያ ሕመሟ ያመማቸው፣ ሀዘኗ ያሳዘናቸው፣ ምጧ የጨነቃቸውና ቁስሏ የጠዘጠዛቸው በርካቶች የመኖራቸውን ያህል” በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” እንደሚባለው ከውስጥም ከውጭም ያሉ ተንኳሾቿ በድሏ ማግስት ሊጠግ ያለ ቁስሏን እየነካኩ ማመርቀዛቸው የሚገመት ነውና ጉባኤው በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቅ እንዲችል እያንዳንዱ ዜጋ በገጽታ ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስና ነገሮችን በአንክሮ በመከታተል ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሊሠራ ይገባል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 23/2014