በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት ከሚካሄዱት ውድድሮች መካከል፤ የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ ይጠቀሳል። ይህም ሴቶች ከወንዶች በእኩል ከሚካፈሉባቸው ውድድሮች በተጓዳኝ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በሚልም ብቻቸውን እንዲወዳደሩ ይደረጋል። የአመራርነት ብቃታቸውም እንዲያድግ ያስችላል የሚል ዓላማም አለው። በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ተረኛ አስተናጋጁም ጅግጅጋ ከተማ ነው። ከትግራይ ክልል በቀር ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር ላይ ከ2ሺ በላይ የሚሆኑ ሴቶች፤ በ10 የስፖርት ዓይነቶች እየተወዳደሩ ይገኛሉ።
በውድድሩ የተሳታፊዎች እንዲሁም የው ድድር መሪ ሴት ባለሙያዎች ቁጥር ያሻቀበ ከመሆኑም ባሻገር የባህል ስፖርት እና የአካል ጉዳተኞች ውድድርም ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲካተት ተደርጓል። ዛሬ አራተኛ ቀኑ ላይ በሚገኘው ውድድር የስፖርት ማህበራት ምን ታዘቡ በሚለው ላይ የዛሬው እትም ትኩረቱን ያደርጋል። የቮሊቦል ስፖርት ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ውድድር ሲካሄድ ቆይቷል። በውድድሩ ላይም ከአፋርና ትግራይ ባሻገር ሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ መሆኑን በኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ ብሩህ ተክለማርያም ይገልጻሉ። ውድድሩ ሙሉ ለሙሉ እየተመራ ያለው በሴት ዳኞች እንዲሁም ሴት ኮሚሽነር መሆኑ በመልካም ጎኑ የሚነሳ ነው።
ይሁን እንጂ በውድድሩ ላይ ለመገንዘብ የተቻለው በተወዳዳሪዎች ብቃት ላይ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ነው። ከዚህ ባሻገር አንዳንድ ክልሎች ላይ ታዳጊዎች የታዩ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሚያሳትፏቸው ተጫዋቾች የተለ መዱ በመሆናቸው ተተኪዎች ላይ እየተሰራ አለመሆኑን ፌዴሬሽኑ ከግንዛቤ ማስገባቱንም ይጠቁማሉ። ከዚህ አንጻር ሲታይ ሁሉም ክልሎች በቮሊቦል ስፖርት ተጠናክረው በመስራት አዳዲስና ታዳጊ ተጫዋቾችን ማፍራት ይኖርባቸዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመስክ ምልከታ ማድረጉን የሚጠቁሙት ባለሙያው፤ በስፖርቱ የተለየ ነገር አለመኖሩን ለመረዳት ተችሏል።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር እየሰራ ሲሆን፤ በተለይ የሴት ክለቦች እንዲጠናከሩ ትኩረት ማድረጉን ይገልጻሉ። ይህ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላም ፌዴሬሽኑ ክልሎችን በመሰብሰብ የተመለከታቸውን ደካማና ጠንካራ ጎኖች ላይ ግብረ መልስ የሚሰጥም ይሆናል። በቮሊቦል የምድብ ጨዋታዎች ነገ የሚጠናቀቁ ሲሆን፤ ዛሬ በምድብ «ሀ» ሶማሌ ከአዲስ አበባ፣ ሃረሪ ከደቡብ ክልል ይጫወታሉ። በምድብ «ለ» ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ከአማራ ክልል እንዲሁም ጋምቤላ ከኦሮሚያ ክልል የሚገናኙ ይሆናል።
በዚህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲካተት ከተደረጉት ውድድሮች መካከል አንዱ የባህል ስፖርት ነው። ውድድሩ በስምንት ክልሎች (74 ልኡካን) መካከል እየተካሄደ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ ናቸው። የውድድር ዓይነቶቹም ገበጣ ባለ12 እና18 ጉድጓድ፤ እንዲሁም በስድስት ምድቦች የትግል ውድድሮች (43-47፣ 48-52፣ 53-57፣ 58-62፣ 63- 67፣ 68-72 ኪሎ ግራም) ናቸው። ፌዴሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ህግና ደንብ አውጥቶላቸው ውድድር የሚካሄድባቸው ስፖርቶች 11 መሆናቸው ይታወቃል።
ከእነዚህ የውድድር ዓይነቶች መካከል አብዛኛዎቹ ሁለቱም ጾታዎች የሚሳተፉባቸው ሲሆን፤ ሴቶች የማይሳተፉት በገና እና በፈረስ ጉግስ ውድድሮች ብቻ ነው። በመሆኑም የዚህ ስፖርት በሴቶች ጨዋታ ላይ መካተት ለእድገቱ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው ኃላፊው የሚጠቁሙት። ውድድሩ እየተመራ ያለው በ9ሴት ዳኞች ሲሆን፤ ተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም አሰልጣኝ፣ ቡድን መሪ እንዲሁም ወጌሻዎቻቸው ሴቶች መሆናቸውን ለመታዘብ እንደቻሉም ይጠቁማሉ። ፌዴሬሽኑ ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ጋር በመሆንም በየዓመቱ ለሁለት ጊዜያት ሴቶችን ብቻ ያሳተፈ የመጀመሪያ ደረጃ የባህል ስፖርቶች የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል።
በዚህም በየዓመቱ 40ሴቶች በአሰልጣኝነት ሙያ የሚበቁ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆንም 25ሴት አሰልጣኞች ብቻ የሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህም የሴቶች ተጠቃሚነት የሚታይና አበረታች መሆኑንም ነው የሚጠቅሱት። ሌላው በዚህ ውድድር የተካተተው የአካል ጉዳተኞች የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ነው። ስፖርቱ በኢትዮጵያ ብዙም ያልተለመደ በመሆኑ ውድ ድሩ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ የቻለ መሆኑን በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ታሪኩ እንዳለው ይጠቁማሉ። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልሎች፤ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፤ የዙር ጨዋታው ዛሬ ይጠናቀቃል።
በውድድሩ ላይ አዳዲስ ተጫዋቾች መታየታቸው እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተጫዋቾቹ ብቃት በማደግ ላይ እንደሚገኝም ታይቷል። ባለሙያው ለተሳታፊዎቹ ቁጥር ማነስ እን ደምክንያት የሚያነሱትም ስፖርቱ ገና በመስፋፋት ላይ እንደመሆኑ በጥቂት ክልሎች ውስጥ ብቻ በፕሮጀክት ደረጃ መሰጠቱን እንዲሁም የትግራይ ክልልን አለመሳተፍ ነው። ስፖርቱ እንዲስፋፋ በፌዴሬሽኑ በኩል ለሁሉም ክልሎች የዊልቸር ድጎማ የሚደረግ ሲሆን፤ በየዓመቱም ዓለም አቀፍ የዳኝነት እንዲሁም የተሳታፊዎችን የጉዳት መጠን የሚለይ ባለሙያ ስልጠና ይሰጣል። ውድድሩ እየተካሄደ ባለበት የሶማሌ ክልል ፕሮጀክት ለመክፈትም የዊልቸር እና ዘመናዊ የቅርጫት ኳስ ቦርድ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ ስፖርቱን ለማስፋፋት በፌዴሬሽኑ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
በብርሃን ፈይሳ