አሁን ላይ እንደ አገር በቅድሚያ የሚያስፈልገን ምንድነው? ተብሎ ቢጠየቅ የሁሉም ሠው መልስ ባይሆን እንኳን የአብዛኛው ሠው መልስ ሊሆን የሚችለው ሠላም ነው። በአሁኑ ወቅት አገራችን ሙሉ በሙሉ ሠላም ናት ብሎ ደፍሮ መናገር ባይቻል እንኳን የሚታዩ መሻሻሎች መኖራቸው አብዛኖቻችንን የሚያስማማ ጉዳይ እንደሆነ እምነቱ አለኝ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኑሯቸውን በውጭ አገር ላደረጉ ዲያስፖረዎች ወደ አገራቸው እንዲመጡ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ለውጦች ተመልከተናል። የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ወደ እናት አገሩ መምጣቱም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣በቱሪዝም ዘርፍና ከስነ ልቦናዊ አንጻርም በበጎ መልኩ የሚጠቀስ ሥራን መከወንም ተችሏል። ዲያስፖራው ማኅበረሰብ አገሬን ብሎ መጥቶ በአገሩ ተገኝቶ የገናንና የጥምቀት በዓልን በደማቅ ሁኔታ ከወዳጁና ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ለማክበርም ችሏል። ከዚህ በተጓዳኝም የአገሩን ችግርን በማስቀደም በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉት የተቻለውን አድርጓል።
በአገራችን በሰሜኑ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎችን ጨምሮም ወደ ነበሩበት ህይወት እንዲመለስ በማድረግ በኩልም በገንዘብ፣ በአይነትና በሞራል ድጋፎቹን ያለ ስስት ችሯል። በርካታ የተቋማት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በተለይም የጤናና የትምህርት ተቋማትንም ወደ ቀደመው ሥራቸው እንዲመለሱና ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ያደረጉትን ድጋፍም በአርአያነት መጥቀሰ ይቻላል። ዲያስፖራው መዝናናት እየቻለ ከመዝናናት ይልቅ አገር ትቀድማለች ብሎ የድርሻቸውን መወጣቱን የሚያስመሰግነው ሲሆን መንግስት ይህንን ሁኔታ በማመቻቸትና ጥሪ ማድረጉም የሚያስመሰግነው ነው።
በተለይም እንደ ቢቢሲ፣ሲኤንኤንና ሌሎች የውጭ አገር ብዘኃን መገናኛዎች እንዲሁም እንደ አሜሪካ ኤምባሲን ጨምሮ፤ በአገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ተስፋፍቷል፤ በአገሪቱ ዋና መዲና አዲስ አበባም ሽብር አለ ብለው የሽብር ወሬ ሲነዙ የነበሩትን የውጭ ጠላቶቻችንም አንገት አስደፍቷል። ይባስ ብሎም አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች ተስማምተው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑን የሚታወቅ ነው።
ጉባኤው ውጤታማ እንዲሆንም የተለያዩ ጸጥታ አካላት፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ እንዲሁም የመዝናኛና ቱሪዝም ሥፍራዎች ዝግጅትን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብሎ በሠላም እንዲጠናቀቅ የጠላትን ክፉ ምኞትን ማምከን ከምንም በላይ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑንም መረዳትም ያሻል።
በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መልካም ዜናዎች እየተሰሙ ቢሆኑም አሁንም ቢሆን ግን አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ማሸበሩን እንዳላቆመ መረጃዎች እያመላከቱ ናቸው። ቡድኑ በአፋር ክልል ሽብር መፍጠሩንም በአዲስ መልክ ተያይዞታል። ትግስት መልካም ቢሆንም ሁሉም ነገር ልክ አለውና መንግስት አሸባሪውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳይነሳ ማድረግ ይገባል። ስለ ሠላም ሲባል ብዙ ዋጋ እንደተከፈለ የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይ በአገራችን ሊከወኑ ስለታሰበው ጉባኤም ይሁን ስለ ሌሎች ልማታዊ ሥራዎች ሲባል የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይገባል።
አሸባሪው እስከወዲያኛው እንዲቀበር የሁሉም ሠው ፍላጎት ነው- ከጀሌዎቹ በስተቀር። እንደሚታወቀው የአፌዲሪ መከላከለያ ሚኒስቴር ጦር ወደ ትግራይ ክልል እንደማይገባ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ክልሉ የኢትዮጵያ አንዱ አካል እንደመሆኑም በማንኛውም ሰዓት መግባትም እንደሚችል መንግስት ያስታወቀ ሲሆን ምናልባትም ይህ ውሳኔ በአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ መታለል የደረሰባቸውን የትግራይ ልጆችን ቆም ብለው እንዲያስቡና ለውሳኔ የሚረዳቸው ይሆን ይሆናል።
ምናልባትም ለቡድኑ አላስፈላጊ የህይወት መስዋዕትነትን የከፈሉ ልጆቻቸውን የት አደረጋችሁ? የት አደረሳችኋቸው የሚሉትን ጨምሮ መሰል ጥያቄዎችን እንዲያነሱ የማድረግ አጋጣሚ እድል ሰፊ ነው። ምናልባትም ከዚህ በኋላ ልጆቻችን ለጦርነት አንማግድም ሞኛችሁን ፈልጉ ብለው የመመለስ አቅም እንዲኖራቸው አጋጣሚውን የሚፈጥር ነውና የትግራይ ህዝብ ለሠላም በር ሊከፍት ይገባል።
አሸባሪው ቡድን በዚህ ዘመን ዘግናኝና አሳፋሪ የሚባሉ ሰብአዊና ቁሳዊ በደሎችን በማድረሱ ስለ ሠላም መስማት እየፈለግን ስለ ቡድኑ እኩይነት ሳንፈልግና ሳንወድ በግዳችን እንድንሰማ አድርጎናል። ስለሆነም የትግራይ ህዝብ መንቃት ያለበት ጊዜ አሁን ሲሆን አሸባሪውን ቡድን በቃህ ብሎት ከገባበት ችግር በመውጣት ከወንድሞቹ ጋር በሠላም የመኖሩን መብቱን ማረጋገጥም ግድ የሚለው ወቅት ነው።
ነገር ግን ቡድኑ ዛሬም ነገም ምኞቱና ሥራው አገርን ማሸበርና ህዝቡ በስጋት ውስጥ እንዲናጥ ማድረግ ነው። የአገራችን ሠው ሲተርት ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ይላልና ነገሮች ስር ከሰደዱና መመለስ በማይቻልባቸው ደረጃ ከመድረሱ በፊት ቡድኑ አቅም ሳያገኝ፣ ሳይበረታና ዳግም የማሰቢያ ጊዜ ሳይሰጠው መንግስት ከዚህ ቀደም የወሰደውን እርምጃ ዳግም መውሰድ ይገባል።
አሁን ያለንበት ወቅት እጅግ የበዛ ስክነትና ብስለት ብሎም ቆራጥነት የሚፈልግ ሲሆን መንግስት በሚወስናቸውና በሚያደርጋቸው ድርጊቶች በሠፊው ከመምከር በተጨማሪም የብዙሃኑን ቅቡልነት ማግኘት መቻል አለበት ብሎ ማሳሰብም ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆን ስለ ሠላም ሲባል ሁሉም የድርሻውን የአቅሙን ማበርከት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ጥር 22 ቀን 2014 ዓ.ም