በዓለም አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ የሚገኘውን የሴቶች ቀንን አስመልክቶ፤ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በተያዘው ዓመት ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት እንደሚመርጥ አስታውቋል። በዚህም ሴት ስፖርቱን በትልቅ ደረጃ መምራት እንደምትችል በማሳየት ተምሳሌ እንደሚሆንም በድረ-ገጹ ጠቁሟል። እ.አ.አ በ2016 ማህበሩ ሴቶችን በየትኛ ውም የስፖርት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ መካተት እንደሚገባቸው በደንቡ ላይ አካትቷል።
በዚህም መሰረት ስድስት ሴቶች በማህበሩ ካውንስል እንዲካተቱ ተደርጓል። ይህንን ቁጥር በአንድ ለማሳደግም በተያዘው ዓመት የታቀደ ሲሆን፤ እ.አ.አ በ2023 ደግሞ ቁጥራቸውን አስር ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ በዘገባው ተጠቁሟል። በ2027ደግሞ በካውንስሉ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ እኩል እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።
ማህበሩ የጀመረውን ይህንን እንቅስቃሴ በሁሉም አገራት ፌዴሬሽኖች እንዲሁም በኮን ፌዴሬሽኖች ውስጥ እንዲለመድ በሴቶች ኮሚቴ በኩል እየሰራ ይገኛል። ለምክትል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውም በእጩነት ብቃት ያላቸው ሴቶችን ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህንን አስመልክቶም ያለፉትን 12 ወራት ሴቶችን የአመራርነትና አስተዳደራዊ ስልጠናዎች ለአምስት ኮንፌዴሬሽኖች ተሰጥቷል።
ይህንን አስመልክቶም የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ «የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ በማህበሩ ያለውን የጾታ እኩልነት ለማረጋገጥ ያለንን ቁርጠኝነት ስንገልጽ በደስታ ነው። በርካታ ሴቶች ወደ ስፖርት አመራርነት እንዲመጡ ማበረታታት አስፈላጊ ነው። አሰራራችንም ይህንን እንደሚፈልግ መታወቅ አለበት። በምርጫዎች ላይ ለሴቶች እኩል የተሳታፊነት ዕድል ይሰጣል፤ በኃላፊነት እና የተለያዩ እርከኖችም ቦታዎቹም ላይ ሴቶች በእኩል ቦታ እንዲያገኙ እንሳራለን።
በእኔ እምነት በየትኛውም ተቋም ጠንካራ እንዲሆን የሴቶች ተሳትፎ መጨመር ይገባል» ሲሉም ገልጸዋል። የተቀመጠውን ግብ ማሟላት አስፈላጊ ነገር ይሁን እንጂ በዕውቀት እንዲታገዙ ፕሮግራሞችን መቅረጽ ያስፈልጋል። በዚህም በቴክኒካል ጉዳዮች፣ በህክምና፣ በአሰልጣኝነት እንዲሁም በአመራርነት ማሳተፍ ይቻላል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ የየሃገራቱ ፌዴሬሽኖች እንዲሁም ኮንፌዴሬሽኖቹ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ፕሬዚዳንቱ አያይዘው ጠቁመዋል። አትሌቲክስን ከሌሎች ስፖርቶች ለየት የሚያደርገው በሁለቱም ጾታዎች አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ርቀቶችና የውድድር ዓይነቶች እንዲሁም የውድድር ቁሳቁሶቹ ተመሳሳይ በመሆናቸው ነው።
በሁለቱም ጾታዎች የሚደረጉት ውድድሮች አንድ ዓይነት ሲሆኑ አሸናፊ የሆኑት አትሌቶችም በእኩል መጠን ተሸላሚዎች ናቸው። ከሜዳ እና መም ባሻገርም ሴቶች በአትሌቲክስ ስፖርት አመራርነት መምጣታቸው እየጨመረ መሆኑም በዘገባው ተጠቁሟል። በማህበሩ ዋና መስሪያ ቤት ካሉት ሠራተኞች መካከል 51በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ መካከል 40በመቶ የሚሆኑት በአመራርነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የሴቶች ወር መከበሩን ተከትሎም ለሚቀጥሉት ሳምንታት የሴት አትሌቶችን ብቃት እንዲሁም በሜዳ ላይ የነበራቸውን ሁኔታ የሚዳስሱ ዘገባዎች እንደሚወጡም ነው የተጠቆመው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
በብርሃን ፈይሳ