ብርሃን ፈይሳ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ላይ በሚያስመዘግቧቸው ድሎች ይታወቃሉ። ታላቅ ክብርን እንዲቀዳጁ ምክንያት የሆናቸው ግን በየጊዜው በሚሰባብሯቸው የዓለም ክብረወሰኖች ነው። ይህ ደግሞ ለረጅም ዓመታት ያልተደፈሩ ክብረወሰኖችን ከመስበር ባሻገርም ለረጅም ዓመታት ከእጃቸው ሳይወጣ የሚቆይም ነው። እንደተለመደው ሁሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታትም ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን በማስመዝገባቸው አድናቆት እየተቸራቸው ይገኛል። አትሌት ሳሙኤል ተፈራ እና አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የግላቸው ያደረጓቸው አዳዲስ ክብሮችም፤ ኢትዮጵያውያ በዓለም ደረጃ ያስመዘገበችውን የክብረወሰን ቁጥር ወደ አስር ያሳደገ ሆኗል።
ይሄ ሰዓትን አሻሽሎ መግባት በርቀቱ የቁጥር አንድነት ማዕረግ ከማስገኘቱም ባለፈ፤ ለአትሌቱ የትልልቅ ውድድሮችን በር ይከፍትለታል፤ የስፖንሰሮችን ፍላጎት ይስባል። በዛሬው እትምም በወንድ አትሌቶች የተሰበሩትን ክብረወሰኖች እንመለከታለን። ኢትዮጵያ በታወቀ ችበት የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ዘርፍ ፈጣን ሰዓቶች የተመዘገቡት በአንድ አትሌት ነው። ይህ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ልዩነት በ5ሺ እና 10ሺ ሜትሮችን ክብር የግሉ ማድረግ ችሏል።
እ.አ.አ በ2004 ሄንግሎ ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ በ5ሺ ሜትር የተሳተፈው አትሌቱ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር የረገጠው በ12ደቂቃ ከ37ሰከንድ ከ35 ማይክሮ ሰከንድ ነው። በቀጣዩ ዓመት በከባድ ሁኔታ ውስጥ የነበረው አትሌቱ የውድድር ዓመት አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም አቋሙን እያሻሻለ በመሄድ በሄልሲንኪው የዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሜትሮች ሻምፒዮን መሆን ችሏል። በቀናት ልዩነት ብራሰልስ ላይ በተካሄደው ሌላ ውድድርም በ10ሺ ሜትር ተሳታፊ ሆኖ ነበር። ክብረወሰን በሰበረበት በዚህ ውድድር ላይም ርቀቱን ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ 26 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ከ53 ማይክሮ ሰከንድ ፈጅቶበታል።
20ሺ ሜትር የሚሸፍነው ውድድር ክብረወሰን የተያዘውም በኢትዮጵያዊው አትሌት ሲሆን፤ ይኸውም በሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ነው። ወቅቱም እ.አ.አ በ2007 ኦስትራቫ ላይ በተካሄደው ውድድር ሲሆን፤ ርቀቱን የሮጠውም 56 ደቂቃ ከ25ሰከንድ ከ98 ማይክሮ ሰከንድ ነበር። በዚያው ዓመት በዚያው ከተማ በአንድ ሰዓት የቻሉትን ያህል ርቀት ለመሸፈን በሚካሄደው ውድድር ላይም በተመሳሳይ ክብረወሰኑ የተያዘው በአንጋፋው አትሌት ነው። ኃይሌ ክብረወሰኑን በስሙ ያስመዘገበውም 21ሺ285 ሜትር በመሮጡ ነው። ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በሚያዘጋጀው የቤት ውስጥ ውድድሮችም በተመሳሳይ በርካታ ክብረወሰኖች በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሰብረዋል።
በመካከለኛ ርቀት ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት የቆየው ክብረወሰን ከቀናት በፊት በኢትዮጵያዊው ወጣት አትሌት መሻሻሉም የሚታወስ ነው። የ20ዓመቱ ሳሙኤል ተፈራ በበርሚንግሃም የተካሄደውን የ1ሺ500 ሜትር ውድድር ለማጠናቀቅ 3ደቂቃ ከ31ሰከንድ ከ04 ማይክሮ ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን፤ ሰዓቱን በ14ሰከንዶች ነው ያሻሻለው። ከሳምንት በፊት የተሰበረው ሌላኛው ክብረወሰን ደግሞ በአንድ ማይል ርቀት ሲሆን፤ ቁመተ መለሎው ዮሚፍ ቀጄልቻ ደግሞ የክብሩ ባለቤት ነው። ዮሚፍ በቦስተን በተካሄደው ውድድር ላይ በሞሮኳዊው አትሌት ሂቻም ኤል ግሩዝ ለሁለት አሥርት ዓመታት የቆየውን ክብረወሰን ከእጁ ለማስገባትም 3ደቂቃ ከ47ሰከንድ 01ማይክሮ ሰከንድ ሮጧል።
በ5ሺ ሜትር የሪከርድ ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቤት ውስጥ ውድድር የርቀቱ ክብር የግሉ ነው። አትሌቱ የክብረወሰን ባለቤት የሆነው በበርሚንግሃም እ.አ.አ በ2004 በተካሄደው ውድድር ሲሆን፤ የገባበት ሰዓትም 12ደቂቃ ከ49ሰከንድ ከ60 ማይክሮ ሰከንድ ነበር። ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ውጪ በሚዘጋጁና በማህበሩ ደረጃ በተሰጣቸው ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያውያን የክብረወሰን ባለቤት ናቸው። እ.አ.አ በ2011 ድሪባ መርጋ የ8ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የተሳተፈ ሲሆን፤ 21ደቂቃ ከ51ሰከንድ ደግሞ ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሰዓት ነው።
በ10ማይል የጎዳና ላይ ሩጫ ክብረወሰን በአንጋፋው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እ.አ.አ በ2005 ሲያዝ ለረጅም ዓመታት ሊበገሩ ካልቻሉት መካከል የሚጠቀስም ነው። ኃይሌ የክብረወሰን ባለቤት የሆነውም ባስመዘገበው 44ደቂቃ ከ24ሰከንድ በሆነ ሰዓት ነው። በቤት ውስጥ የ2ሺ ሜትር ውድድርም በተመሳሳይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 4ደቂቃ ከ49ሰከንድ ከ99ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት የተያዘ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
በብርሃን ፈይሳ