ትውልዳቸውና እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። ነፃነት ጮራ እና ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በአካውንቲንግ ዘርፍ ዲፕሎማ አግኝተዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግና ፋይናንስ እንግሊዝ አገር ከሚገኝ ደርቪ ዩኒቨርሲቲ የተቀበሉ ሲሆን ከስኮትላንዱ ኤድንበርግ ቢዝነስ ስኩል ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። እንዲሁም አሜሪካ ከሚገኘው ማሃራሺ ማኔጅመንት ዩኒቨርሲቲ በኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ተጨማሪ ማስተርስ ሰርተዋል።
በተጨማሪም ከእንግሊዝ አገር ቻርተርድ አካውንታንትነት አለማቀፍ እውቅና ያለው ሰርተፍኬት ያገኙ ሲሆን በአዕምሮ ቋንቋ ቅመራ (Neuro Lingustic programing) ዘርፍ ሥልጠና ወስደዋል። ኢ.ኤ.ደብሊው ቶማስ በተባለ ኩባንያ በኦዲተርነት ለጥቂት ዓመታት የሰሩት እኚሁ እንግዳችን አፍሪካ ህብረት ውስጥ ተቀጥረው ሱዳን፣ ሴንትራል አፍሪካና የመሳሳሉት የአፍሪካ አገራት ተዘዋውረው አገልግለዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቢዝነስ አማካሪ ድርጅት ከፍተው የማማከር ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በአዕምሮ ቋንቋ ቅመራ (Neuro Lingustic programing) በተባለ ሳይንስ የማነቃቂያ ስልጠናዎችን በመስጠት አገራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡም ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የአዕምሮ ቋንቋ ቀማሪ የሆኑትን አቶ ዳንኤል አያሌውን የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ በመጀመሪያ ስለ አዕምሮ ቋንቋ ቅመራ (Neuro Lingustic programing) ምንነት ያስረዱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ዳንኤል፡- በመሰረቱ ‹‹የአዕምሮ ቋንቋ ቅመራ ›› ትክክለኛ ሳይንሳዊ ስሙ Neuro Lingustic programing የሚል ነው። በአማርኛ ቀጥታ ትርጓሜ ስለሌለው በራሴ ተነሳሽነት ነው ‹‹የአዕምሮ ቋንቋ›› የሚል ስያሜ የሰጠሁት። ይህ የሳይንስ ዘርፍ በዋናነት ውጤታማ የሆኑ ሰዎች ምንአይነት አስተሳሰብ፤ ምንአይነት ተሞክሮ ነው ያላቸው? የሚለውን ነው የሚያጠናው። በተጨማሪም ሰዎች አዕምሯቸውን በመጠቀም የሚፈልጉት የእድገት ደረጃ ወይም ለውጥ ማምጣት ይችላሉ የሚለውን ይተነትናል።
ሰዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ሲባልም ንቁና ድብቅ የሚባሉ የአዕምሮ ክፍሎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ሳንችል ማለት ነው። ብዙ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ሲያደርጉም ሆነ ሲወስኑ አይታዩም።
ይህ ደግሞ እርካታ ያለው ህይወት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። አስበሽ አለማድረግሽ ደግሞ በቅሬታ ውስጥ ያለ ህይወት እንድትኖሪ ያደርግሻል። ሁልጊዜም ቢሆን ለራስሽ አቅጣጫ የማትሰጪ ከሆነ የምትሰሪያቸው ስራዎች እርካታም ሆነ ደስታ አይሰጡሽም። በዚህም ምክንያት ረጅም መንገድ መሄድ አትቺይም። ስለዚህ ይህ ስልጠና የሚረዳው ንቁም ሆነ ንቁ ያልሆነውን የአዕምሮ ክፍል በማሰራት ሰዎችን ብቁ ለማድረግ ነው።
በተለይም ድብቁ የአዕምሯቸው ክፍልን ተጠቅመው የሚያስቡትን ነገር እንዴት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚችሉ ያሳያል ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኒኮች አሉ። ለምሳሌ ደፋር ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራዊ የሆኑ ቴክኒኮች አሉ።
ይህ ዘርፍ ከሌሎች ግላዊ እድገት መንገዶች የሚለየው በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ማስቻሉ ነው። በተጨማሪም ከማወቅ በዘለለ እውቀትሽ ወደ ውስጥ እንዲሰርፅና ወዲያው ለውጥ እንድታመጪ ያደርግሻል።
አንዳንድ ለውጦች ጊዜ ይፈጃሉ። ለምሳሌ በገንዘብ ራሴን ልቀይር ካልሽ ጊዜ ይወስዳል፤ ምክንያቱም ተጨማሪ ነገር ነው ወደ ህይወትሽ የምታመጪው። ነገር ግን ከሀሳብ ከስሜት ጋር የተያያዙ ነገሮችን በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ መልካም ለውጥ ማምጣጥ የሚያስችል ጥልቅ የሆነ መስክ ነው። በነገራችን ላይ ይህ መስክ በይፋ ስራ ላይ መዋል የጀመረው ከ1970 ዓ.ም ወዲህ ነው።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እያደጉ የመጡ ሰፊ እና እንደየችግሩ የተለያየ መፍትሄ መስጠት የሚችሉ መንገዶች ያሉት መስክ ነው። ከዚህም ባሻገር በጣም ጉልበት ያላቸው ቴክኒኮችና ሃሳቦች ያሉት የጥናት ዘርፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ በምን አጋጣሚ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በሙያው ወደማሰልጠን ስራ የገቡት?
አቶ ዳንኤል፡- በአዕምሮ ቋንቋ ሳይንስ አለም አቀፍ እውቅና ያገኘሁት በ1999 ዓ.ም ቢሆንም በዘርፍ ስልጠና እሰጥ የነበረው በትርፍ ጊዜዬ ብቻ ነበር። በተጨማሪም ግለሰቦች ራሳቸውን የሚያሳድጉበትን ስልት እንዲያዳብሩ የሚያደርግ ስልጠና በነፃ ስሰጥ ነበር። በተለይም ከአራት ዓመት በፊት ወደአዲስ አበባ ስመጣ የሚያበረታቱ ነገሮች በማየቴ የቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለመክፈትና የአዕምሮ ቋንቋ ትምህርትንም በዚያው ለመስጠት አስቤ ነበር።
በኋላ ላይ ግን መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የቢዝነስ አዕምሮ ልማትን በአማካሪ ድርጅቴ ሥር ለመስጠት ወስኜ ነው ወደዚህ ስራ የገባሁት። ባለፈው ዓመት ሥልጠናውን በይፋ የጀመርኩ ሲሆን እስካሁን በርካታ ታላላቅ የተባሉ የቢዝነስ ሰዎች አሰልጥኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ የሳይንስ ዘርፍ ከስልጠና ባለፈ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ትምህርት የማይሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስፋት ህብረተሰቡ ጋር ለመድረስና የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ተግዳሮት አይሆንም?
አቶ ዳንኤል፡- ልክ ነው፤ አንቺም እንዳልሽው ይህ ኒሮሊንጉስቲክ ፕሮግራም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ እንደአንድ የትምህርት ዘርፍ የሚሰጥ አይደለም። ግን ደግሞ የተወሰኑ ሰዎች በማስተርስና በዶክትሬት ደረጃ ጥናታቸውን የሚሰሩ አሉ። በተለይም እንግሊዝ ውስጥ በስፋት ጥናት ይደረግበታል።
በተመሳሳይ ደግሞ ሳይኮቴራፒስቶች እንደአንድ የጥናት ዘርፍ ከሌሎች ትምህርቶች ጋር በመሆን ይሰጣል። ስለዚህ ይህ ስልጠና የሚያገለግለው ራስን ለማብቃት ነው። በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ የሚሰጡ ትምህርቶች በዋናነት የሚያጠነጥኑትና የሚያተኩሩት እውቀት ላይ ብቻ ነው። ይሄኛው ግን ያለንን እውቀትና አቅም ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችል ነው። እኔም የበለጠ ትኩረት ያደረኩት ከራሴ በመነሳት ሰዋዊ ልማት ለማምጣት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ዳንኤል፡- ከራሴ ተነስቼ ነው ማለቴ እኔ ራሴ ከዚህ ቀደም ፍርሃት እና ራስን መግለፅ ያለመቻል ችግር ነበረብኝ። ያንን የራሴን ችግር ለመፍታት ስል ነው ያጠናሁት። ስለዚህ ብዙዎቻችን በተማርነውና ባለን እውቀት ልክ ሆነን ራሳችንን አናገኘውም።
ይህም በስራችንም ሆነ በህይወታችን ላይ እርካታ እንዳይኖረን ያደርጋል። እኔም ያንን ጎዶሎ ማንነቴን ለመሙላት ስል ነው ከዚህ ቴክኖሎጂ ጋር የተዋወቅሁት። የራሴን ችግሮች በዚያ መልኩ ከፈታሁኝ በኋላ ሌሎች በዚህ ችግር የሚጠቁ ሰዎችን ማገዝ አለብኝ በሚል መነሻ ነው ወደ ስልጠና የገባሁት።
ግን ደግሞ ምንያህሉ ሰው በተጨባጭ ለውጥ ያመጣል የሚለው ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ነው የሚሆነው። በአለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ ሰፊ ጥናት ባለመኖሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ስልጠናው መሰጠት አለበት? ለሚለው ነገር እርግጠኛ አይደለሁም። ግን በግለሰብ ደረጃ በስፋት ሊሰጥ ይችላል። ምክንያቱም ሃገር ማሳደግ የሚጀምረው ከግለሰብ ነው። አንድ ሃገር ሃብታም ህዝቦች ኖሯት ደሃ ልትሆን አትችልም። ግን የተፈጥሮ ሃብት ኖሯቸው ደሃ የሚባሉ ሃገሮች አሉ።
ስለዚህ የተፈጥሮ ሃብት ሳይሆን ህዝቡ ነው አንድን አገር ሃብታም የሚያስብለው። ህዝቡ ሃብታም፣ የነቃ፣ የበሰለ፣ ራሱን መግራት የሚችል፣ በደመነፍስ የማይንቀሳቀስ ከሆነ አገሪቷ መጨረሻ ላይ የህዝቦቿ ነፀብራቅ ነው የምትሆነው። ስለዚህ ትልቁ ትኩረቴ ‹‹ኢትዮጵያን ከፍ እናድርግ፤ በአንድ ጊዜ አንድ ሰው›› የሚል መፈክር ይዤ ነበር።
እያንዳንዳችን ራሳችንን መቀየር ከቻልን፤ ቤተሰባችንና አካባቢያችን ብሎም አገራችንን እንቀይራለን። በአጠቃላይ በዚህ ፅንሰሃሳብ ነው ግለሰቦችን ወደ ማሰልጠን የገባሁት። እርግጥ ነው መስኩ እምብዛም ስለማይታወቅ ሰዎችን ማግኘቱ በራሱ ከባድ ነው። አሁን ግን ያሰለጠናቸው ጥቂት ሰዎችን ላይ ያገኘነው ለውጥ የሚበረታታ በመሆኑ ተደራሽነታችንን
የበለጠ እናሰፋለን ብለን ነው የምናምነው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የንግድ ስራ የሚመራው ባህላዊና ኋላቀር በሆነ ዘዴ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዚህ ዘርፍ የሰለጠኑ ስኬታማ የንግድ ሰዎችን ለማፍራት የቀደመው አሰራርና አመለካከት ማነቆ አልሆነባችሁም?
አቶ ዳንኤል፡- በጣም ጥሩ ሃሳብ ነው ያነሳሽው፤ እንዳልሽው አብዛኞቹ የንግድ ሰዎች ስራውን እያከናወኑ ያሉት ከቤተሰብ በወረሱት ተሞክሮ ነው፤ አልያም ደግሞ በሆነ አጋጣሚ ጀመረውት ነው። እንዳልሽው ይህ አስተሳሰብ ለማንኛውም ለውጥ እንቅፋት ነው። እንደእድል ሆኖ ግን እኛ እስካሁን ያሰለጠናቸው አብዛኞቹ ሰዎች ሥራ ፈጣሪዎች ናቸው።
ይህ ግን የሆነ እኛ ፈልገነው ሳይሆን እንዳጋጣሚ ነው። እነዚህ ሰዎች ይዘውት ከመጡት ተሞክሮ አኳያ ውስጣቸው ያለና መግራት የሚፈልጉት ነገር እንዳለ እንረዳለን። ከዚህ አኳያ የኒሮሊንጉስቲክ ፕሮግራም ትልቁ ፋይዳ የሚሆነው ሰዎች ለአዳዲስ ነገሮች ወይም አሰራሮች ክፍት እንዲሆኑ ማገዙ ነው። አዳዲስ አሰራሮችን ለመሞከር የበለጠ ደፋር እንዲሆኑ ያደርጋል።
ከምቾት ቀጠናቸው እንዲወጡና ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል። በተለይም ከተለመደው አሰራር በመውጣት ግልፅ የሆነ የህይወት መስመር እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
የኢትዮጵያውን የአኗኗር ዘይቤ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር በጣም ወደኋላ የቀረን ነን። እናም አዳዲስ ነገሮች ሲመጡ የመጠራጠር ሁኔታ አለ። አንዱ ይሄ ቴክኖሎጂ የሚያገለግለው ሰዎች እንደየሁኔታው ተለዋዋጭ እንዲሆኑ፤ አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ ጉጉት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው ላይ ተግብረውትም ውጤት እንዲያመጡ የሚረዳ ነው።
እንዳነሳሽው ያደጉት አገራት ህዝቦች ለአዳዲስ ነገሮች ክፍት ስለሆኑ ነው ቶሎ ብለው ወደተግባር ለውጠው የሚጠቅማቸውን ይዘው የሚቀጥሉት። እኛ አገር አንድ አዲስ ነገር ሲመጣ ቢሰራም ባይሰራም የመጀመሪያ ተግባራችን መቃወምና ማጣጣል ነው። ገና በሃሳብ ላይ እያለ በእርግማናችን ብዛት መሬት ላይ እንዳይወርድ እናደርገዋለን። ስለዚህ ፈጠራ የሚባል ነገር የለም።
ሳይፈጠር ገና መከላከያ ካበጀንለት እንዴትም ብሎ አዲስ ነገር ልናመጣ አንችልም። ወደአደጉት አገር ስትሄጂ አዲሱ ነገር ተተግብሮ ካለቀ በኋላ ያመጣው ጉዳት ወይም ስጋት ተጠንቶ ህግ የሚወጣለትና ክልከላ የሚደረግበት። ስለዚህ ይህንን ስልጠና ሰዎች በወሰዱ ቁጥር እንዲህ አይነቱን ኋላቀር የሆነ አስተሳሰብ ማስወገድ ይቻላል።
ምንአልባት የኢትዮጵያን የቀደመ ስልጣኔ ብናይ አባቶቻችንን እነ አክሱምና ላልይበላን መገንባትና የቀደመ ስልጣኔን ማምጣት የቻሉት አዲስ ነገር ከመሞከር የመጣ ነው እንጂ የሚመጣውን ሁሉ በመንቀፍና በመከልከል አልነበረም። እነዚያ አባቶች በወቅቱ ከነበረው አስተሳሰብ በላይ ማሰብና የወደፊቱን ማየት በመቻላቸው ነው። አሁን ያለውም ትውልድ ለአዳዲስ ነገሮች አዕምሮውን ክፍት ማድረግ መቻል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ የጥናት ዘርፍ አኳያ ለውጥ እንዴት ነው የሚተረጎመው? በኢኮኖሚ ማደግ ብቻውን ለውጥ መጥቷል ልንል እንችላለን?
አቶ ዳንኤል፡– ለውጥ በአጠቃላይ ወደፊትም ወደኋላም ሊሆን ይችላል። ከዚህ አኳያ ለውጥ ሁልጊዜ ጥሩ ላይሆን ይችላል ማለት ነው። ግን ደግሞ እድገት ስንል ወደፊትን ነው የሚያመላክተን።
እንዳልሽው ሰዎች ለውጥ አመጡ የምንለው የኢኮኖሚ እድገት ስላመጡ ብቻ አይደለም። እኛ በምናሰልጥንበት መስክ ህይወት በራሷ ሰፋ ተደርጋ ነው የምትተረጎመው። አዕምሮ፤ ጤና፤ ተክለሰውነት፤ ማህበራዊ ህይወት መስተጋብር ሁሉ ተደምረው ነው የሚታዩት። አንድ የንግድ ሰው ገቢው
ጨምሮ ግን ደግሞ ጤና ከሌለው አልያም ቤተሰባዊ ግንኙነቱ መልካም ካልሆነ አድጓል ልንለው አንችልም። እነዚህን ነገሮች አጣጥሞ መሄድ ያስፈልጋል። ለገንዘብ ብለሽ ጤናሽን ማጣት የለብሽም።
እርግጥነው ገንዘብ በህይወታችን ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው። በተለይ በእኛ አገር ደረጃ ገንዘብ ወሳኝ ስፍራ አለው። ግን አጠቃቀሙን ካላወቅን እና ሌሎች በተጓዳኝ መሄድ የሚገባቸውን አጣምረን መሄድ ካልቻልን እድገታችን ትርጉም አልባ ነው የሚሆነው። ትልቁ ነገር ግን ከትናንት ዛሬን ተሽሎ መገኘት ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ ስልጠና ላይ የምጠቀምበትን ምሳሌ ልጥቀስልሽ። ህይወታችን የምኖረው በሶስት ደረጃ ነው። የመጀመሪያው ‹‹ግብ ግብ›› የሚባለው ነው፤ ይህም ማለት ህይወታችንን ለማቆየት የምናደርገው ትግል ነው። ብዙ ጊዜ ለሰዎች የምመክረው እዚህ አይነቱ ሂደት ውስጥ ብዙ መቆየት እንደሌለባቸው ነው። በህይወታችን ተግዳሮት የሆኑብን ነገሮች ብቻ ለዓመታት እያወራን ልንዘልቅ አይገባም። ለምሳሌ የገንዘብ ችግር አለብኝ እያሉ አስር ዓመት መኖር የለብንም።
ይህንን ችግራችን መፍታትና ወደ ሌላኛው ማለፍ ይገባናል። ነገሮችን በቁጥጥራችን ስር አድርገን ማሻሻል አለብን። ሁለተኛው ጉዳይ ነፃነት ነው፤ ከዚህ ችግር ውስጥ ወጥተሽ ራስሽን ከፍ ያለ ደረጃ ስታደርሺ የምትፈልጊውን ነገር፣ በምትፈልጊው ቦታ፤ ከምትፈልጊው ሰው ጋር፤ በምትፈልጊው መጠን ማደግ ስትችይ ነው። ለምሳሌ ደፋር መሆን ባለብሽ ቦታ ደፋር ስትሆኚ፤ ቁጥብ መሆን ባለብሽ ቦታም ቁጥብ ስትሆኚ ነው ነፃነትሽ አስጠብቀሻል ሊባል የሚችለው። በራሳችን ማድረግ የምንችልበት ቦታ ስንደርስ ነፃነት ላይ ደርሰናል ማለት ነው።
ሌላው ግን ከዚህ የላቀ ሕይወት አለ፤ ይህም አስተዋፅኦ ነው ብዬ አስባለሁ። ራስሽን ነፃ አድርገሽ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ስትችይ፤ ሌሎች ሰዎች ካሉበት የግብግብ ህይወት ነፃ ወጥተሽ ሌሎችን ከጫና በማውጣት እነሱም ሌሎችን እንዲያግዙ ማድረግ ከቻልሽ ከፍ ያለ የህይወት ደረጃ ላይ ደርሰሻል ማለት ይቻላል። እናም እድገትን የማየው በዚህ መልኩ ነው። ግለሰብ ላይ የምናመጣቸው ለውጦች የበለጠ ከፍ ብለው ይታያሉ። ምክንያቱም አስቀድመን እንዳልነው አንድ አገር ሃብታም የምትባለው ህዝቦቿ ሃብታም ሲሆኑ ነው።
በተመሳሳይ ጤነኛ አገር ኖሯት፤ በሽተኛ ህዝብ ሊኖረን አይችልም። እንደእኔ እምነት እያንዳንዱ ግለሰብ ላይ የምናመጣው ለውጥ ነው ትልቋ አገር ለውጥ ማስመዝገብ የምንችለው። ስለዚህ ብዙዎች የየራሳቸውን ችግር መፍታት ከቻሉና ሌሎችንም በመርዳት አስተዋፅኦ ማበርከት ከቻሉ የመጓተት ሳይሆን የመደጋገፍ ባህላችን እየዳበረ ይመጣል።
እናም እንደእኔ እምነት አንዳችን ሌሎቻችንን የማንሳት ሃይልና ግልፅ የሆነ ባህል ማዳበር ከቻልን ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ የማንደርስበት ምክንያት የለም። ብዙ ጊዜ እንዳውም በአለምአቀፍ ደረጃ ‹‹ሰዎች ለራሳቸው ሃላፊነት ቢወስዱ ሃገሪቷ ራሷን ትመራለች›› እንደሚባለው ሁሉ እያንዳንዳችን በሃላፊነት መንቀሳቀስ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ምሁራን በአንድ አገር ውስጥ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ በመጀመሪያ እያንዳንዱ ሰው የአዕምሮ ሰላም ሊኖረው ይገባል ብለው ያምናሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ዳንኤል፡- እስማማለሁ። ምክንያቱም የሌለን ነገር መስጠት አንችልም። ስለዚህ እንደተባለው ሰዎች አዕምሯቸው ሰላም ያለመኖር በአገር ደረጃ ሰላም ለማምጣት ከባድ ነው የሚሆነው።
አዕምሮው ሰላም የሆነ ሰው የሌሎችን ሃሳብ መግዛት ይችላል። ከዚህ አኳያም ያደጉት አገራትን ተሞክሮ ማየት ካስፈለገን የመቻቻል እድላቸው ከፍ ያለ ነው። አንቺ አንድ ሃሳብ ስታመጪ ያንን ሃሳብ ባልቀበለውም ለድብድብ ግን አልዳረግም። የአንቺን ሃሳብ ማክበሬ በራሱ በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ሰላም አለ። ስለዚህ የአንቺን ሃሳብ ጭንቅላቴ ውስጥ አምጥቼ ግብ ግብ ፈጥሬ ራሴ ላይ ችግር አልፈጥርም። ግን ደግሞ በሃሳቡ ላይ መወያየትና መከራከር ይቻላል።
አሁን ያለንበትን አገራዊ ችግር ምንአልባት የግለሰቦች ሰላም እጦት ነው ብለን ብቻ ልናሳንሰው አይቻል ይሆናል። ግን ደግሞ ከአንድ ግለሰብ ሰላም በላይ ከፍ ያለ ነገር ሊሆን ይችላል።
ሰላም እንዳይኖር ያደረጉት ሰዎች ሃሳብ ምንድን ነው? የሚለውን ነገር ፖለቲካዊ እይታ ሊፈልግ ይችላል። አንድ አገር ሰላም እንዲያገኝ ተቻችሎ መኖርና መታሳሰብ መኖሩ ወሳኝ ነው። እኔ ለምሳሌ ሰላም ቢኖረኝና ጎረቤቴ ግን ሰላም ባይኖረው አለኝ የምለው ሰላም ሊበጠበጥ ይችላል። በአገር ደረጃም ስናየው በአንድ ወገን ብቻ ሰላም መፈለግ ትክክለኛ ሊሆን አይችልም። ከሁሉም ወገን ሰላምን መሻት ይጠይቃል። አንዱ ተንኳሽ ከሆነ ሌላኛው ሰላም ፈላጊ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ተገደሽ ራስሽን ለሰላም ስትይ የምታስገዢበት ሁኔታ አለ።
በታሪካችን እንደምናውቀው የውጭ ወራሪዎች ሲመጡብን ያሉብንን ግላዊ ችግሮች ወደኋላ ትተን በጋራ አንድ ሆነን የምንቆምበት ተሞክሮ አለን። ይህም የሚያሳየው የአገር ሰላም ከግል ችግርም በላይ መሆኑን ነው። ስለዚህ ከግለሰብ የአዕምሮ ልማትም በላይ በየአቅጣጫቸው ነገሮችን ማገናዘብ የሚፈልግ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ለዘመናት የኖረው የህዝቡ ተቻችሎ የመኖር እሴት እየተመናመነ በመጣበት፤ አብዛኛው ሰው በሁሉ ነገር ሆድ የሚብሰውና ለጠብ ዝግጁ ሆኖ የሚታይበትና ለልዩነት ድንበር አበጅቶ ከሚኖርበት ሁኔታ እንዴት ማላቀቅ ይቻላል?
አቶ ዳንኤል፡– ያነሳሽው ነገር በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው። ድሮ የነበሩ የምንላቸው የመቻቻል፤ ሌላውን እንደራስ የማየትና የመከባበር ባህላችን አሁን ላይ ብዙ አናየውም።
እርግጥ ልዩነታችን እንጠቀምበት ካልን ውበትም ጭምር ነው። ግን ደግሞ ያንን ልዩነት የመለያያና የፀብ ምክንያት ከማድረግ ይልቅ የአንድነት መንገድ ማድረግ ትቺያለሽ። ለምሳሌ ሁላችንም መልካችን አንድአይነት ቢሆን ኖሮ እንሰለቻች ነበር። ስለዚህ ህብረተሰባችን መረዳት የሚገባው ጉዳይ ያ ልዩነታችን የህይወት ማጣፈጫ ቅመም አድርጎ ነው። ያለንን ልዩነት እርሾ አድርገው ለጠብ የሚጠቀሙበትን አካላት ከጥፋት መመለስ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው ሊሆን የሚገባው። ለዚህ ደግሞ የቀደመውን እሴቶቻችንን መልሰን ማምጣት መቻል አለብን።
ወደ መፈቃቀርና ወደ አንድነት መምጣት መቻል አለብን። ምክንያቱም እነዚህ አመለካከቶች ናቸው ተጠራቅመው የአንድ አገር ባህል የሚሆኑት። ስለዚህ በእያንዳንዱ ግለሰብ አዕምሮ ውስጥ እንዲህ አይነት ሃሳቦችን ማስረፅ መቻል አለብን። በእኛም ትምህርት እያንዳንዱ ሰው ልዩ እንደሆነ ነው የምናስተምረው። ይህም ማለት እገሌ እኔን መምሰል አለበት ማለት አንችልም። ምክንያቱም ያደግንበት ማህበረሰብ፤ አካባቢ፤ ሁኔታ ይለያያል።
ስለዚህ ከሌላ ሰው ጋር ስኖር ባህሉንም ሆነ አመላከከቱን አክብሬ መሆን ያለበት። ልዩነታችን ግን ለመከፋፈላችን ምክንያት መሆን መቻል የለበትም። ለምሳሌ በአንድ ቤት ውስጥ ያሉ የቤተሰብ አባላት በፆታ ስለተለያዩ ብቻ መለያየት አለብን ብለው እንደማይከፋፈሉ ሁሉ በአገርም ደረጃ የአመላከከት ልዩነት ስላለን ብቻ ልንለያይ አይገባም። የዚህ ትውልድ ጭንቅላት ከተመረዘም ሆነ በመልካም ነገር ከተሞላ የሚቀጥሉት 40 እና 50 ዓመታት የዚህች አገር እጣፈንታ ነው የሚሆነው። ስለዚህ የ50 ዓመት እድላችንን ነው አሁን ላይ ቅርፅ እያስያዝን ያለነው። ስለዚህ ከእኛ በተቃራኒ በሆነ መንገድ ካለው ወገናችን ልንጠቀም የምንችለው መልካም ነገር ይኖራል በሚል ሃሳቡን አክብረን እና ተቻችለን ልንኖር ነው የሚገባው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ ከትውልዱ ላይ እየጠፋ ያለውን የአገር ፍቅር ስሜትና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን እንዴት መመለስ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
አቶ ዳንኤል፡- ራሴ ተሞክሮ ስነሳ ወላጅ አባቴ ፖሊስ በመሆኑ አስተዳደጌ ኢትዮጵያዊነትን ከልጅነቴ ጀምሮ አስርፆብኝ እንዳድግ ምክንያት ሆኖኛል ብዬ አምናለሁ። እንዳልሽው ኢትዮጵያ ስሟ ገና ሲነሳ የተለየ ስሜት ነበር የሚሰማን። በአካባቢያችንም ያደግነው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ቢሆንም አንድምቀን ስለዘሩ ወይም ቋንቋው አስበን አናውቅም። አብረን መኖራችን ሁላችንም ኢትዮጵያዊነታችን ነበር ጎልቶ የሚወጣው። የምንኖርበት አካባቢም የሁላችንም ነው ብለን እንድናድግ የተደረግነው። ሲጀመርም ስለ ልዩነታችን በጥያቄ መልክ አይነሳም።
ሴ ተሞክሮ ስነሳ ወላጅ አባቴ ፖሊስ በመሆኑ አስተዳደጌ ኢትዮጵያዊነትን ከልጅነቴ ጀምሮ አስርፆብኝ እንዳድግ ምክንያት ሆኖኛል ብዬ አምናለሁ። እንዳልሽው ኢትዮጵያ ስሟ ገና ሲነሳ የተለየ ስሜት ነበር የሚሰማን። በአካባቢያችንም ያደግነው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ቢሆንም አንድምቀን ስለዘሩ ወይም ቋንቋው አስበን አናውቅም። አብረን መኖራችን ሁላችንም ኢትዮጵያዊነታችን ነበር ጎልቶ የሚወጣው። የምንኖርበት አካባቢም የሁላችንም ነው ብለን እንድናድግ የተደረግነው። ሲጀመርም ስለ ልዩነታችን በጥያቄ መልክ አይነሳም።
ባንዲራችን ሲታይ የሚሰማን የተለየ ስሜት አለ። ይህ የኢትዮጵያዊነታችን እሴት አሁንም በአግባቡ ልንጠብቀውና ከትውልድ ትውልድ ልናስተላልፈው የሚገባ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ከፍ እንድትል ከተፈለገ ምንም አይነት ልዩነት ቢኖረንም እንኳን ያቺን ኢትዮጵያዊነታችንን መጠበቅ በጣም መሰረታዊ ነገር ነው። አሁን ላይ ያ እሴታችን በብዙ መልኩ ተሸርሽሮ ይታያል። ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ ጥረት መደረግ አለበት።
ሰፋ ያለ ስራ ይጠይቃል። ምንአልባት የፖለቲካ መፍትሄ ሊፈልግ ይችላል፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ ልጆቹ ላይ መስራት ይፈልግ ይሆናል። ብዙ ጊዜ እንደምንለውም ለአንድ ችግር አንድ መፍትሄ ሳይሆን በርከት ያለ መፍትሄ ነው መሻት ያለብን። አንቺ ያነሳሽው ችግርም በአንድ መንገድ የሚፈታ አይደለም። በየትምህርት ቤቱ፣ በየአካባቢው፣ በመንፈሳዊ ቤቱ ድሮ የነበሩ እሴቶቻችንን መመለስ መቻል አለብን። አሜሪካን የፈጠሯት የተለያዩ ሃገሮች ተዳምረው ነው። እኛም አንድ ላይ መኖር የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም።
አብዛኞቹ ምዕራባውያን ሃገራቸውን በጣም ይወዳሉ፤ ሃገራቸውን መውደዳቸውን የሚያሳዩበት መገለጫቸው ደግሞ ስራ ነው። ስለዚህ እኛም ሃገራችን መውደዳችን የሚረጋገጠው በስራችን ልንለውጣትና ልናሳድጋት ስንችል ነው።ሳትሰሪ አገሬን እወዳለሁ ብትይ ምንም ዋጋ የለውም። ያ አገር መውደዳችን ደግሞ በስራ የሚገለፁትን መንገድ መፈለግ መቻል አለብን። በእጃችን ያለውን ነገር ሁሉ ተጠቅመን አገሪቱን የችግር ሁሉ መጠሪያ ከመሆን ልንታደጋት ይገባል። በነገራችን ላይ በአንድ ላይ ሰርተን ጥሩ ውጤት ማምጣት ከቻልን በራሱ አንድነታችን ይጠናከራል።
አዲስ ዘመን፡- ጦርነቱ ካደረሰው የቁስና የኢኮኖሚ ጉዳት ባሻገር የስነ ልቦና ቀውሱን ለማከም ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ዳንኤል፡- አሁን ያነሳሽው ጥያቄ በጣም አሳማኝ ሃሳብ ነው። ምክንያቱም የምናልፋባቸው ችግሮች ጥለው የሚያልፉት ዘላቂ ጉዳት አሉ። በተለይም አሁን እንደተከሰተው አገራዊ ችግር አይነት ሲፈጠር አካላችን እንደሚቆስለው ሁሉ አዕምሮም ይቆስላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ዜጎች ተስፋ ይቆርጣሉ፤ አንዳንድ ጊዜም ራስን እስከማጥፋ ሊደርስ ይችላል። ከደረሰው ጥፋት አኳያ በጦርነት ውስጥ ያለፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ የስነልቦና ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
ተስፋ መቁረጥና ተናዳጅ ሊያደርግ ይችላል። በወቅቱ የደረሰብን ነገር ሁሉ በአዕምሯችን የተመላለሰ ህመምተኛ ሊያደርገን ይችላል። ስለዚህ በጣም ብዙ የስነልቦና እና የስሜት ጉዳቶች ያስከትላል። ያ ሁኔታ እየበዛ ሲሄድ ዘላቂ የሆነ አገራዊ ችግር መፍጠሩ አይቀርም። ከዚህ አኳያ ብዙዎቻችን የምንረባረበው ማብላትና ማጠጣቱ ላይ ነው። ግን ደግሞ ከዚያ ባልተናነሰ በተለይ የጦርነቱ ዋነኛ ሰለባ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የስነልቦና ጉዳታቸውን ማከም ይገባናል።
እርግጥ ነው እንዲህ አይነት ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ ባሙያዎች እጥረት ሌላው ችግር ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ግን በተመሳሳይ ዘርፍ ተምረው ሥራ ያጡ መኖራቸው ይታወቃል።
ከዚህ አኳያ በዘርፉ የምናሰለጥናቸው ተማሪዎች መሬት ላይ ላለ ችግር መፍትሔ የሚሆኑ አድርገን ስላልቀረፅናቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ይህንን ክፍተት መሙላት ይጠበቅብናል። ስለዚህ የምግብና የገንዘብ ድጋፍ እንደምናደርገው ሁሉ አሁን ያሉንን ባለሙያዎች በተጨባጭ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሰረታዊ ጉዳይ ይመስለኛል። ይህ ስራ የመንግስት ሃላፊነት ብቻ ሊሆን አይገባም፤ አቅሙ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በግሎት መንግስት በአሁኑ ወቅት እያራመደ ያለውን የምክክርና የብሔራዊ እርቅ መንገድ እንዴት ይመለከቱታል? ለአገር ያለውስ ፋይዳ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ዳንኤል፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ መረጃ ባይኖረኝም እንደአጠቃላይ በሰዋዊ ልማት ዘርፍም የምናስተምረው ማንኛውም ሰው ለውጥ ለማምጣት ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ ይቅርታ ነው። ስለዚህ እርቅና ይቅርታ ማድረግ ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም ጋር ሊሆን ነው የሚገባው። ከአካቢዎችና ከክስተቶች ጋርም ልንጣላ እንችላለን። እናም ሙሉ አቅምሽን ተጠቅመሽ ወደፊት መሄድ ስትፈልጊ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ይቅር ማለት ያስፈልጋል።
የትላንትናውን ስህተቴን በዛሬው ብስለቴ አይቼ ራሴን ከወቀስኩኝ አደጋ ነው። አንድ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር ከዚህ ቀደም ያጠፋሁት ጥፋት በወቅቱ ከነበረኝ ጥፋት አኳያ ነው ብሎ ተንደርድሮ መሄድ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል። ሰዎችም ሲያጠፉ በተመሳሳይ መንገድ ይቅር ማለት ይገባናል። ሆኖም ፖለቲካው ከዚህ የተለየ አካሄድ ሊፈልግ ይችላል። ግን ደግሞ አገሪቱን አንድ ማድረግ ከተፈለገ የእርቅና ምክክሩ አስፈላጊነት ጥርጥር የለውም።
አብረን መኖር ካለብን የተቀያየምነው ነገር ወደ ጎን አስቀምጠን ወደፊት መራመድ መቻል አለብን። እንዴት ነው እርቁ የሚፈፀመው የሚለው ነገር ወደፊት መታየት ያለበት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ዳንኤል፡- እኔም ሃሳቤን እንድገልፅ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014