የአከርካሪ አጥንት ጤና ችግር ከግዜ ወደ ግዜ እየከፋ መጥቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ 1 ቢሊዮን ያህል ሰዎች በአከርካሪ አጥንት ችግር እንደሚጠቁና ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 67 ከመቶ ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም ቢሆን የአከርካሪ አጥንት ችግር አሳሳቢ እየሆኑ ከመጡ የጤና እክሎች ውስጥ አንዱ ነው።
ዛሬ ላይ “ወገቤን፣ አንገቴንና ጀርባዬን” አመመኝ የሚል ሰው መስማት እየተለመደ መጥቷል። ‹‹ካይሮፕራክቲክ›› የአጥንት፣ የነርቭ ፣ ጡንቻና በተለይ ደግሞ የአከርካሪ አጥንት ላይ የሚያተኩር የህክምና መንገድ መሆኑን በዚህ ዘርፍ ያሉ የህክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ።
ይሁንና ይህ የህክምና ዘርፍ በኢትዮጵያ ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ ትምህርቱ በኮሌጁ አልያም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሲሰጥ አይታይም። በአፍሪካም ቢሆን ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በሌሎች ሀገራት አይሰጥም።
ከዚህ በመነሳት ታዲያ አንድ የአገር ባለውለታ በአገራቸው ያዩትን የአከርካሪ አጥንት ጤና ችግር በዝምታ ለማለፍ አልፈቀዱም። ይልቁንም በአሜሪካን አገር ለአስራ ሁለት ዓመታት ሲሰሩበት የቆዩትን “የአከርካሪ አጥንት ህክምና ሙያ” ይዘው ከሃያ አንድ ዓመት በፊት ወደ አገራቸው በመመለስ የመጀመሪያውን የአከርካሪ አጥንት ህክምና ማእከል አቋቁመዋል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የሆኑት የአከርካሪ አጥንት ሀኪም የተለያዩ በጎና አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግም ይታወቃሉ።
በህክምና ሳይንስ ውስጥ በተቻለ መጠን አብዛኛው ህክምና የአከርካሪ አጥንትን በማስተካከል ቢጀመር የተሻለ ነው የሚል እሳቤም አላቸው። በኢትዮጵያ የአከርካሪ አጥንት ህክምና ማዕከል ለማቋቋም የተነሱበት አላማም ይኸው ነው።
በተለይ ደግሞ ‹‹አስር ለጤና›› በሚለው መርሀግብራቸው ሰዎች ከባድ ስራ ከመስራታቸው በፊት ሰውነታቸውን እንዲያሟሙቁ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና ከውስጣቸው እንዲተነፍሱ በማድረግ ውጤታማና ጤነኛ ሰራተኛ እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
በትምህርት ቤቶችም ‹‹ቀጥ በልጅነት›› የሚለውን መርሃግብር ተግባራዊ በማድረግ ልጆች የአከርካሪ አጥንታቸው ተስተካክሎ እንዲያድግ በሰውነት ማጎልመሻ መምህራን በኩል በርካታ ስራዎችን ያከናውናሉ።
ሰዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ለአስር ደቂቃ ያህል ከስራ ሰዓታቸው ላይ ውስደው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መንግስት በይፋ እንዲፈቅድ ግፊት እያደረጉም ነውበአከርካሪ አጥንት ህክምና ሙያ ከሰላሳ ዓመት በላይ የቆዩት “የፈርስት ስፓይን ሴንተር” መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሰላም አክሊሉ ናቸው። ዶክተር ሰላም እድገትና ውልደታቸው በድሬዳዋ ነው።
ለቤተሰባቸው ስምንተኛና የመጨረሻ ልጅ ናቸው። በእናትና አባታቸው፣ በታላላቅ እህትና ወንድሞቻቸው ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው ነው ያደጉት። ገና የአስራ ሰባት ዓመት ታዳጊ እያሉ ነው ወደ አሜሪካን አገር ያቀኑት።
በአሜሪካን አገር ቆይታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኬሚካል ቴክኖሎጂ ኬሚስትሪ ሜጀር ከካሊፎርኒያ ትሬድ ቴክኒካል ኮሌጅ አግኝተዋል። በካይሮፕራክቲክ ህክምና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከክሊቭላንድ ካይሮፕራክቲክ ሴንተር ተቀብለዋል።
በመቀጠል ደግሞ በዶክተር ኦፍ ሜዲስን ከሶቼካልኮ ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል። በተማሩበት የካይሮፕራክቲክ ህክምና ሙያ የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት ዓመታት በዛው አሜሪካን አገር ካሊፎርኒያ በሚገኝ አንድ የህክምና ማእከል ውስጥ ሰርተውበታል።
ወደዚህ ሙያ የገቡትም በታላቅ እህታቸው አነሳሽነት ነበር። በተለይ ደግሞ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ወደ አሜሪካን አገር ሄደው የካይሮፕራክተር ህክምና ትምህርት ከተከታተሉት የመጀመሪያዎቹ ሀኪሞች ውስጥ አንዱ ከነበሩት ከዶክተር ተስፋ ወሰኔ ጋር መገናኘታቸውና ማውራታቸው
ወደዚህ ሙያ ለመግባት ይበልጥ ገፋፍቷቸዋል።
ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙትም በዛው አሜሪካን አገር ሲሆን ከትዳር አጋራቸው ሁለት ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን አፍርተዋል። በባለቤታቸው ሀሳብ ጠንሳሽነት ልጆቻቸው ወደ አገራቸው ተመልሰው በኢትዮጵያዊ ባህል ማሳደግ ስለፈለጉ ከዛሬ ሃያ አንድ አመት በፊት ኑሯቸውን በአገር ቤት አድርገዋል።
ነገር ግን ወቅቱ ሰው ወደ አገሩ የሚመለስበት ምቹ ግዜ አልነበረም። ሆኖም ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን በህይወታቸው ከወሰኗቸው ትክክለኛ ውሳኔዎች ውስጥ እንደ ዋነኛው ይቆጥሩታል። ከዛሬ ሀያ አንድ ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያዋ ካይሮፕራክቲክ ሀኪም የነበሩት ዶክተር ሰላም፤ በኢትዮጵያ የካይሮፕራክቲክ ህክምና ማእከል በማቋቋምም ቀዳሚ ናቸው።
ፈርስት ስፓይን ሴንተር የተሰኘና በአከርካሪ አጥንት ህክምና ላይ የሚሰራ ማእከል መመስረት ችለዋል። ማእከሉ በአዲስ አበባ ሶስት ክሊኒኮች ያሉት ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ በድሬዳዋና ጅማ ከተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል። ዘጠና ሰባት የጤና ባለሞያዎችንም በውስጡ አቅፏል።
በዋናነትም በአከርካሪ አጥንት ችግር ላይ አተኩሮ ይሰራል። በተጨማሪም የአንገት፣ ወገብ፣ ጀርባ፣ ትከሻ፣ እጅ፣ ዳሌ፣ ጉልበት፣እግር፣መገጣጠሚያ፣ ጡንቻና የነርቭ ህመም ህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በቀዶ ህክምና ሲስተካከል የሚታወቀውን የዲስክ መንሸራተት ከቀዶ ህክምና ጋር በተያያዘ በርካታ አደጋዎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሩን ያለቀዶ ህክምና በተፈጥሯዊ መንገድ ለማስተካከል የፊዚዮቴራፒና የካይሮፕራክቲክ ሞያን ቀላቅሎ የተዛባውን የአከርካሪ አጥንት የማስተካከል ስራ ይሰራል። ይህም ዲስኩ ላይ ያለውን ጫና በማንሳት ነርቩ ላይ ያለውን እክል ማስተካከልን ያካትታል።
ማእከሉ ብዙ ሰዎች የቀዶ ህክምና እንዳያደርጉ በማስቆም የሚታወቅ ሲሆን በተቻለ መጠን ሰዎች ወደ ቀዶ ህክምና እንዳይሄዱ የመከላከልና የበለጠ ደግሞ ቀጣይነት ያለው የአከርካሪ አጥንት ማስተካከል ስራዎችን በማከናወን የተሻለና ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው ጥረት ያደርጋል። በኢትዮጵያ ከአከርካሪ አጥንት ጤና ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች ስለሚስተዋሉና ህመሙም ከባድ በመሆኑ ማእከሉ በዋናነት ችግሩን አስቀድሞ መከላከል ላይ አተኩሮ ይሰራል። ሰዎች ከዚህ የአከርካሪ አጥንት ችግር ጋር በተያያዘ እንዳይጎዱም ያስተምራል። በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች ሁለንተናዊ ጤና እንዲኖራቸው በአኗኗር ዘይቤ ማስተካከል ላይ በርካታ ስራዎችን ያከናውናል። በአሁኑ ግዜ ማእከሉ የመጀመሪያውን ከህመም ማገገሚያ ሆስፒታል እየገነባ ይገኛል።
በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥም የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚሁ ፕሮጀክት ጎን ለጎንም በውጭ አገራት ስራ ሰርተው አቁመው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ሰዎች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡበት ማእከል እያዘጋጀ ይገኛል።
ማእከሉ 150 ሰዎች አብረው ሊኖሩበት የሚችል ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከውጭ አገር የሚመለሱ ዲያስፖራዎች ናቸው። ‹‹የመላው ሰውነት ጤንነት መሰረቱ የአከርካሪ አጥንት አቀማመጥ ትክክል መሆን ነው›› የሚሉት ዶክተር ሰላም ይህ ካልሆነ የሰዎች መላው ሰውነታቸው ጤነኛ ሊሆን እንደማይችል ይገልፃሉ። ከዚህ አንፃር በተለይ በግንባታና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ከባድ ስራዎችን የሚሰሩ ሠዎች ችግሩን እንዲገነዘቡት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ባለሞያውም ጭምር ስለማያውቀው ስለጉዳዩ የማስገንዘብ ስራ እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ። በዚህ መነሻነት ፈርስት ስፓይን ሴንተር ‹‹አስር ለጤና የሚል››አገራዊ ንቅናቄ እንዳስጀመረ ገልፀው፤ ይህም ሰዎች ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ለአስር ደቂቃ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከልባቸውና ከትንፋሻቸው ጋር እንዲሆኑ ብሎም ሠውነታቸውን ለስራ እንዲያዘጋጁ የሚያስችላቸው መሆኑን ያብራራሉ።
ይህ አገራዊ ንቅናቄ ሰዎች የተረጋጋ ማንነትና ለስራ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው በማድረግ በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረጉም በዘለለ አሰሪዎችም ምርታማ የሰው ሃይል እንዲኖራቸውና በዚህም ትርፋማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው እንደሆነም ዶክተር ሰላም ይጠቁማሉ።
ይህ ተደምሮ ሲታይ ጤናማ ህዝብ እንዲኖርና ለአገር ብልፅግናም ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ያስረዳሉ። ‹‹አስር ለጤና›› የተሰኘው ፕሮግራም በሁሉም የግንባታና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን በጤና ሚኒስቴር በኩል እንደፀደቀና በተመሳሳይ በሰራተኛና ማህራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩልም እውቅና እንዳገኘም ይገልፃሉ።
ፕሮግራሙ በሁሉም የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት ቢተገበር ጤናማና የተሻለ ብሎም ምርታማ የሰው ሃይል እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ይጠቁማሉ። የፈርስት ካይሮፕራክቲክ ሴንተር ዋነኛ አላማም ይህንኑ ‹‹አስር ለጤና›› የተሰኘውን ፕሮግራም በሁሉም ተቋማት ውስጥ በስፋት ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይህንኑ ፕሮግራም ተግባራዊ የሚያደርጉ አስር ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን መፍጠር መሆኑንም ዶክተር ሰላም ያብራራሉ።
‹‹ይህ ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ ውጤት እያመጣም ነው›› የሚሉት ዶክተር ሰላም፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞቻቸው ላይ የጀመሩት ስራ ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። አንድ መስሪያ ቤት ወይም ተቋም ቢያንስ ለአንድ ዓመት ይህን ፕሮግራም ልምድ አድርጎ ሰርቶበት ለስራ ዝግጁ የሆነ የሰው ሃይል ይዞ መስራት ከቻለ የፕሮግራሙ ውጤታማነት እንደሚያረጋገጥም ያስረዳሉ። ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ትምህርት ቤቶችም ጭምር ተማሪዎቻቸው ፕሮግራሙን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማድረግ የማእከሉ ሌላኛው አላማ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በቀጣይም ማእከሉ እያንዳንዱ ሰው ሰውነት ራሱን የማዳን ሃይል እንዳለው ተገንዝቦ የራሱን ጤና እንዲጠብቅ የማብቃት ስራዎች በስልጠናና በልዩ ልዩ መንገዶች ለመስጠት እቅድ እንዳለው ይገልፃሉ። የአኗኗር ዘይቤዎችን ማስተካከል ላይ ማእከሉ በቀጣይ አተኩሮ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ መሆኑንም ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ሃላፊነት ወስደው የራሳቸውን ጤና እንዲጠብቁ የሚያበቁ የጤና ባለሞያዎችን የማሰልጠን ስራም ማእከሉ በቀጣይ እንደሚያከናውን ይገልፃሉ።
በተለይ ደግሞ ማዕከሉ ሰዎች ስራ ከመጀመራቸው በፊት ከስራ ሰዓታቸው ላይ አስር ደቂቃ ተወስዶ ‹‹አስር ለጤና›› የሚለውን ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመንግስት በይፋ እንዲፈቀድ ሰፊ ጥረቶችን እንደሚያደርግም ዶክተር ሰላም ይናገራሉ።
እምብዛም ባልተለመደው አከርካሪ አጥንት ህክምና ሞያ ለሰላሳ ሶስት ዓመታት ያህል የቆዩት ዶክተር ሰላም ከሃያ አንድ ዓመታት በላይ በዚሁ ሞያ አገራቸውን በማገልገላቸው ይህን እንደ አንድ ስኬት ይቆጥሩታል።
ወደ ኢትዮጵያ ሞያውን ይዘው እንደመጡ ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ ህብረተሰቡ ለሞያው የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ እንደነበር ነገር ግን ዛሬ ላይ ይሄ ተለውጦ የካርይሮፕራክቲክ ህክምና ለጤና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ህብረተሰቡ እየተረዳው መምጣቱም ለኔ ተጨማሪ ስኬት ነው ይላሉ። ሆኖም አሁንም በርካቶች በዚህ የአከርካሪ አጥንት ችግር ተጠቂ ከመሆናቸው በፊት መከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በመስራት በሞያቸው ከዚህም በላይ ስኬታማ መሆን እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።
የአከርካሪ አጥንት ጤናን መጠበቅ መሰረታዊ፣ ብዙ ወጪ የማያስወጣና ብዙ መድሃኒት የማያስገዛ የጤና አጠባበቅ ዘይቤ ስለሆነ በተለይ ለአፍሪካ ብቸኛው መልስ ይሆናል ብለው ያስባሉ። ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም እንዲሆን ለማድረግ እንደሚሰሩም ያመለክታሉ።
የአገር መሰረቱ ሰው ነውና የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ጉዳይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጀምሮ የሁሉም ሰው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባም ገልፀው፤ በተለይ ደግሞ የአከርካሪ አጥንት ችግርን አስቀድሞ መከላከል ላይ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
በመንግስት በኩል ያሉ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመውም ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበራቸውን አጭር ቆይታ አጠናቅቀዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014