ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ነን። ቀጥሎ ስለምናቀርበው የሙዚቃ አይነት ብዙም አልተባለም። ይህም ስለውጭው ዓለም እንጂ ስለራሳችን እንደማናጠና እና እንደማናውቅ አንድ ማሳያ ነው።
ዓለም የሚያንቆለጳጵሳቸው እነ ሞዛርትና ቤትሆቨንን ነው። እነዚህ የሙዚቃ ተምሳሌቶች በ18ኛውና 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቅ ያሉ ናቸው። ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ግን ከእነርሱ ሺህ ዓመታት በፊት ዜማን ፈጥሯል፤ በዓለም በኢትዮጵያም የሙዚቃ ፈጣሪ እየተባሉ የሚጠሩ የውጭዎቹ ናቸው። የውጭዎቹ ለመተዋወቃቸው ምክንያቱ ምንም ሳይሆን ጠንክረው የሰሩባቸውና ያስተዋወቁዋቸው መሆኑ ላይ ነው፡፡
አንድ የታወቀ ነገር ካለ በዚያው ላይ ብቻ መረባረብ ነው የተለመደው። ያልተወቁትን ለማስተዋወቅ አይሰራም፤ ጥናት አይካሄድባቸውም፤ ለዚህም ነው የሙዚቃ ቅኝቶቻችን ስንት እንደሆኑ አንድ ወጥ እይታ የሌለን። አንዳንዶቹ አምስት ናቸው ይላሉ፤ አብዛኞቹ ደግሞ አራት ናቸው ይላሉ። አንዳንዶቹም ከአራትም ከአምስትም በላይ ናቸው ይላሉ።
ለዛሬው በሚገባ ባልተዋወቀው ፊላና ሌሎች የሙዚቃ ቅኝቶች ላይ ቆይታ እናረጋለን። ዋቢ ያደረግነው በፍሬው ተስፋዬ የተጻፈውን ‹‹ፊላና ሌሎች ሙዚቃዊ ጥበባት በጋርዱላ ዲራሼ›› መጽሐፍን ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የተሰሩ ጥናቶችና ምርምሮች የአካታችነት ችግር እንዳለባቸው ፀሐፊው ጠቅሰዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በጥናትና ምርምሮቹ መሰረት የሙዚቃ ቅኝቶች በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በወሎ አካባቢ ብቻ የተወሰኑ ናቸው። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያሉትን የአገሪቱን የሙዚቃ ቅኝቶችና ስልቶች አላጠኑም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የጋምቤላና የደቡብ ኢትዮጵያ ሙዚቃዎች እየተጠኑ ነው።
በጋሞ ከፍታ ቦታዎች የሚገኙ ዶኮዎችና የጋርዱላ ዲራሼዎች የሚጫወቷቸው ሙዚቃዎች ‹‹ሆሞፎኒክ›› ምድብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በተለይም የፊላ ሙዚቃ በኢትዮጵያ ብቸኛ ባለሰባት ኖታ የሙዚቃ መሳሪያ ነው።
ፊላ ምንድነው? የሚለውን እንመልከት፡፡
ፊላ ሦስት ትርጓሜዎች አሉት። ፊላ ሙዚቃ ነው፤ ፊላ ውዝዋዜ (ዳንስ) ነው፤ ፊላ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። ፊላ እንደ ሙዚቃ መሳሪያ ሲታይ ከአንድ ሜትር እስከ አምስት ሜትር ርዝመት ያለው የትንፋሽ መሳሪያ ሲሆን፣ የሚዘጋጀው ከቀርቀሃና ከሸንበቆ መሆኑ በመጽሀፉ ላይ ተመልክቷል። እነዚህ ከሸንበቆና ከቀርቀሃ የሚዘጋጁ የሙዚቃ መሳሪያዎች በአንድ በኩል ክፍት፤ በሌላኛው በኩል ድፍን ናቸው። የፊላ የሙዚቃ መሳሪያ እንደ ዋሽንት አንድ (ነጠላ) ብቻውን አይሆንም፤ በስብስብ ነው፤ ስብስቡ ዝቅተኛው 24 ሲሆን እስከ 32 እና 48 ይደርሳል።
የመሳሪያዎቹ ብዛት ያስፈለገበት ምክንያት የተለያየ ድምጽ ለማውጣት ነው። አጨዋወቱ የራሱ ምትና ስልት አለው። ከትንሿ ቀጠን ያለች ድምጽ ይጀምርና እስከ 24ኛው ወፍራም ድምጽ ድረስ ይዘጋጃል። ለአቀማመጥ እንዲያመች በታችኛው በኩል የክር ማስገቢያ ቀዳዳ ይኖረዋል። ሁሉንም ፊላዎች በአንድ ክር በማስተሳሰር በጥንቃቄ ግድግዳ ላይ ማስቀመጥ ይቻላል።
እነዚህ 24 የፊላ የሙዚቃ ድምጾች በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች (በባለሙያዎች ቋንቋ ቤዞች) ይመደባሉ። ይሄውም ካሳንታ (ወፍራም ድምጽ) ፣ ኦታንትያ (መካከለኛ ድምጽ) እና ፍት ፍታ (ቀጫጭን ድምጽ) በመባል ይመደባሉ። መሳሪያዎቹም በዚህ መልክ የተዘጋጁ ናቸው። በጨዋታ ጊዜ እያንዳንዱ መሳሪያ የሚያወጣው ድምጽ ቀዳሚና ተከታይ በመሆን ነው። መካከለኛና ወፍራም ድምጽ የሚያወጡት ከቀርቀሃ የሚዘጋጁት ፊላዎች ናቸው። ቀጭን ድምጽ የሚያወጡት ደግሞ ከሸምበቆ የሚዘጋጁት ናቸው። ፊላ ሙዚቃ በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ ስለሆነ ከጃዝ ጋር እንደሚመሳሰል የአፍሪካ ጃዝ አባት የሚባሉት ሙላቱ አስታጥቄ መናገራቸውም በመጽሐፉ ተመልክቷል።
ፊላ ውዝዋዜ (ዳንስ) ነው። የፊላ ውዝዋዜ ለየት የሚያደርገው ነገር ተወዛዋዡ ራሱ የመሳሪያው ተጫዋች ነው። ተወዛዋዥ ለብቻው አያስፈልገውም። ውዝዋዜውን የሚመሩት በፊላ ጨዋታ ውስጥ የሚገኙ ሦስት መሪዎች ናቸው። እነዚህ መሪዎች ራሳቸው ፊላ እየነፉ ከመሀል አቋርጠው በመውጣት ውዝዋዜውን ይመሩና እንደገና ፊላ ወደመንፋቱ ይመለሳሉ። ለፊላ ጨዋታ አዲስ የሆነ ሰው የአጨዋወት ስልታቸው ግራ ያጋባዋል፡፡
የፊላ ጨዋታ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይታያል። ከ1998 እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በአርባ ምንጭ ይታይ በነበረው ‹‹ሺ ኮከቦች›› የሙዚቃ ፌስቲቫል፣ በብሄር ብሄረሰቦች ቀን እና የዓድዋ ድል በዓላት በሚከበሩባቸው ጊዜያት በአገር አቀፍ ደረጃ ይታያል፤ ሙዚቃዎቹም በቴሌቭዥን ጣቢያዎች ይታያሉ፡፡
የሙዚቃ መሳሪያዎቹ የተለያየ አይነት አላቸው። የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎች ሎላት፣ ማይራ፣ ኩሉታት፣ ታርባ፣ ሐናት፣ ሉላ፣ ካሳ፣ ካልጋ እና ሀምቡፓ የሚባሉት ናቸው።
ሎላት የሚባለው ከሳላ ቀንድ ወይም ከአጋም እንጨት ይዘጋጃል። ከተዘጋጀ በኋላ በቅቤ ታሽቶ ጭስ ባለበት ይቀመጣል፤ ይህ የሚደረገው እንዲወዛ ነው። ከፍየል ጺም አካባቢ በሚገኝ ቆዳና ፀጉር ይዋባል። ቁመቱ እስከ 40 ሴንቲ ሜትር ይሆናል። ይህ መሳሪያ በሁለቱም ጫፍ ቀዳዳ ያለው ሲሆን አንደኛው ሰፊና ሌላኛው ቀጭን ነው። አነፋፉ በሰፊው በኩል ሲሆን በቀጭኑ በኩል ደግሞ በጣት ያዝ ለቀቅ በማድረግ የተለያየ ድምጽ እንዲያወጣ ይደረጋል፡፡
ሎላት ለዲራሼ ማህበረሰብ የሙዚቃ መሳሪያ ብቻ አይደለም። መግባቢያም ነው። እያንዳንዱ ቤተሰብና መንደር የየራሱን ሎላት ያውቃል። ለሆነ ጉዳይ የሚጠራሩት በሎላት ነው። ማታ ከሥራ ሲገቡም መጥተናልና ተዘጋጁ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉት በሎላት ነው። አነፋፉም እንደየ መልዕክቶቹ ይለያያል። አንድ ጊዜ ሲሆን ምን እንደሆነ፣ ሁለት ጊዜም ሦስት ጊዜም… ከሆነ መልዕክቱን የአካባቢው ማህበረሰብ ያውቀዋል፡፡
ሌላው የትንፋሽ መሳሪያ ማይራ የሚባለው ነው። ከቀጫጭን ሸምበቆ ይዘጋጃል። እነዚህ ቀጫጭን ሸንበቆዎች ስድስት ሲሆኑ ከላይ ክፍት ከታች ድፍን ናቸው። ቁመታቸው የተለያየ ሲሆን ከትልቅ ወደ ትንሽ ይደረደራሉ። በቃጫ ገመድ ከታሰሩ በኋላ በቁልቋል ወይም በቅንጭብ ደም ይጣበቃሉ። ከቁልቋልና ቅንጭብ የሚወጣ ደም የማሟጨጭ ባህሪ ያለው ነው። የማይራ አደራደር በድምጹ አወራረድ መሰረት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ወይም ከከፍተኛ ወደ ዝቅተኛ ነው።
ማይራን የሚጫወቱት ወንዶች ሲሆኑ በጃንሜዳው ጥምቀት ላይ ከምናየው ሀርሞኒካ ጋር ይመሳሰላል። አጨዋወቱም ልክ እንደ ሀርሞኒካ ከንፈር ላይ በማድረግ ከግራ ወደ ቀኝ ወይም ከቀኝ ወደ ግራ በማመላለስ የሚጫወቱት የትንፋሽ መሳሪያ ነው። የማይራ ጨዋታ ለወጣቶች የፍቅር መገለጫ ሲሆን አዋቂዎችም ጀግንነትንና ማንነትን ለመግለጽ ይጫወቱታል።
ይሄኛው የትንፋሽ መሳሪያ ደግሞ ከዋሽንት ጋር ይመሳሰላል፤ ዲራሼዎች ኩሉታት ይሉታል። ኩሉታት የሚዘጋጀው አንድ ወጥ ከሆነ ሸምበቆ ወይም ቀርቀሃ ነው። ቁመቱ እስከ 50 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ሲሆን በሁለቱም ጫፍ ክፍት ነው (እንደ ዋሽንት ማለት ነው)። በእኩል ርቀት የተበሱ አራት ቀዳዳዎች ይኖሩታል። አጨዋወቱም ልክ እንደ ዋሽንት በሁለት እጅ ተይዞ ቀዳዳዎችን በጣት በመያዝና በመልቀቅ ነው። ይህን ጨዋታ የሚጫወቱት በብዛት ሴቶች ናቸው። በነገራችን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተረው ዋሽንት ሴቶች ሲጫወቱት አይስተዋልም።
ከዘመናዊው ሳክስፎን ጋር የሚመሳሰለው የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ ታርባ ይባላል። የሚሰራው የቀርቀሃ አንጓዎችን አንዱን በአንዱ ላይ በመሰካት ነው። ጥንት የነበረው አገልግሎት አደጋ መከሰቱን ለማሳወቅና ትልቅ ሰው ሲሞት ለማርዳት ነው። በሁሉም እጅ ላይ አይገኝም፤ ኃላፊነት በተሰጣቸው ሰዎች ዘንድ እጅ ላይ ብቻ ነው ያለው። አሁን ላይ ግን ይህ መሳሪያ እምብዛም አይታይም።
ሐናት የሚባለው የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ ከረጅም የሳላ ቀንድ የሚዘጋጅ ነው። በአፉ በኩል የሚነፋ ሲሆን ዋና አገልግሎቱም ከለቅሶ ሥርዓት ጋር ይያያዛል። ሐናት ሲነፋ ከተሰማ በአካባቢው ሰው እንደ ሞተ ይታወቃል። የለቅሶ ስነ ሥርዓቱና መጠናቀቁም በሐናት ይደረጋል። ይህን መሳሪያ አሁን ላይ ለማዘጋጀት ስለሚያስቸግር ያለውን የሳላ ቀንድ በጥንቃቄ መያዝ ይገባል፡፡
ሌላው የመጥፋት ደረጃ ላይ የደረሰው መሳሪያ ሉላ የሚባለው ነው። የሚዘጋጀውም ከድኩላ ቀንድ ነው። እርሻ የሚውሉ አርሶ አደሮችና እረኞች ወደቤት ሲገቡ ይጠራሩበታል።
የዲራሼ ማህበረሰብ ከሚጠቀማቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች ለየት ያለው ደግሞ ሀምቡፓ የሚባለው ሲሆን፣ የሚሰራው ከዛፍ ፍሬ ነው። ፍሬው የሚገኘው ማህበረሰቡ ሺጫራ ብሎ ከሚጠራው ሐረግ መሰል እሾሃማ ተክል ነው። የፍሬውን ጠንካራ ቅርፊት በመተው በውስጡ የሚገኙ ትንንሽ ፍሬዎችን በማጽዳት ሦስትና ከዚያ በላይ ቀዳዳዎች እንዲኖሩት ይደረጋል። አንደኛው ቀዳዳ የሚነፋበት ሲሆን የቀሩት በጣት እየተሸፈኑና እየተለቀቁ ድምጽ እንዲያወጡ ይደረጋል፡፡
የጋርዱላ ማህበረሰብ የክር የሙዚቃ መሳሪያዎችም አሉት። አንደኛው ሾንቃ ይባላል፤ ከክራር ጋር ይመሳሰላል። ቀደም ሲል ከእንጨት፣ ከቃጫ ገመድ፣ ከቆዳና ከጅማት የሚዘጋጅ ቢሆንም አሁን ግን ከሲባጎና ሌሎች ዘመናዊ ክሮች እየተዘጋጀ ነው። ትምባ የሚባለው የምት የሙዚቃ መሳሪያ ደግሞ በአማርኛ ከበሮ ከሚባለው ጋር ይመሳሰላል። አሰራሩም ሆነ አገልግሎቱም ከከበሮ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሉሌት የሚባል የሙዚቃ መሳሪያም አለ። ይሄኛው የሙዚቃ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የእግር ጌጥም ነው። ከመዳብ የሚዘጋጁ ትንንሽ ቃጭሎች ናቸው። በቀጭን ጠንካራ ክር ከተሳሰሩ በኋላ የሴቶች እግር ቁርጭምጭሚት ላይ ይታሰራሉ። ይህ ቁርጭምጭሚታቸው ላይ የታሰረ ቃጭል በተንቀሳቀሱ ቁጥር እያቃጨለ ሙዚቃ ይፈጥራል። ድምጹም እንደ አረማመዳቸው ይሆናል፤ በዚህም ማን እንደሆነች ለመለየት ያስችላል።
እንግዲህ በእነዚህ የሙዚቃ መሳሪያዎች (የትንፋሽ፣ የክር፣ የምት፣ ቃጭል) የሚጫወቱት ጨዋታ የተለያየ መልዕክት ያለው ነው። ለሀዘን፣ ለደስታ፣ ለፉከራ የሚውሉ ናቸው። አንዳንዶቹ መሳሪያዎችም የማህበረሰቡ መግባቢያና መጠራሪያ ናቸው። ጨዋታዎችም እንደየወቅቱ ይከናወናሉ። በዝናብ ወቅት፣ በበጋ ወቅት፣ በሰርግ ወቅት ይጫወቷቸዋል። ጨዋታዎችም የየራሳቸው መጠሪያዎች አሏቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ባህልና ሚዲያ ጥናት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ እና የመጽሐፉ ደራሲ ፍሬው ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፤ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፊላና ሌሎች የሙዚቃ ጥበባትን የሚያጠና ተመራማሪ ተመድቧል። ፌስቲቫሉን በተባበሩት መንግሥታት የባህል፣ የትምህርትና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በክልሉ ባህልና ቱሪዝምና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተሰራ ነው።
እንደ አቶ ፍሬው ገለጻ፤ የፊላና ሌሎች የደቡብ አካባቢ ሙዚቃዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ግብዓት የሚሆን ክምችት ያለባቸው ናቸው። ግን በሥርዓት አልተጠኑም፤ አልተዋወቁም። እንኳን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ በኢትዮጵያ ራሱ በሚገባ አልተዋወቁም።
አፍሪካ የሰው ዘር ብቻ ሳይሆን የሙዚቃ ጥበባት መገኛም መሆኗን የሚያሳይ ነው፤ የጃዝ መነሻ ነው። በመሆኑም በቀጣይ መተዋወቅና መጠናት ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 19/2014