የጋናው የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ኵዋሚ ንክሩማህ የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት፤ የዛንጊዜው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከ60 ዓመታት በፊት በግንቦት 1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲመሰረት፤ “ዛሬውኑ አንድ ካልሆን እንጠፋለን። የኢኮኖሚ ነጻነታችን የሚረጋገጠው በአንድነታች ነው። …” የሚል ዛሬ ድረስ የሚታወስ ትንቢት አከል ታሪካዊ ንግግር አላቸው።
ለአፍሪካ ቀጣይ ህልውናም ሆነ ብልጽግና አንድነት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል። የፖለቲካ ነጻነትና ሉዓላዊነት በኢኮኖሚው ዘርፍ ካልተደገመ፤ ዛሬም ከምዕራባውያንና ከአሜሪካ ተጽዕኖ መውጣት ካልተቻለ ትርጉም የለውም። ራስን መመገብ ባለመቻሉ ስንዴ የሚሰፈር፤ የእነ የዓለም ባንክንና የአለማቀፍ የገንዘብ ተቋምን (አይ ኤም ኤፍን ) እጅ የሚታይ ከሆነ ሉዓላዊነትና ነጻነት ሙሉኡ አይሆንም።
የአፍሪካ አንድነትና ፓን አፍሪካኒዝም በተነሳ ቁጥር ፋና ወጊ የሆኑት ንክሩማህ፤ “ሉዓላዊነታችንን መስዋዕት በማያደርግ ሁኔታ አንድ መሆን አለብ ። የጋራ መከላከያ፣ የውጭ ጉዳይ፣ ዲፕሎማሲ፣ ዜግነት፣ መገበያያ ገንዘብና ባንክ በመመስረት ፖለቲካዊ አንድነት መፍጠር እንችላለን። ለአህጉራችን የተሟላ ነጻነት ስንል መዋሀድ አለብን። “ ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት በራሱ ሙሉኡ አለመሆኑን በማስገንዘብ፤ የተሟላ አንድነት ሊረጋገጥ የሚችለው አፍሪካውያን አንድ ስንሆን ነው በማለት በአገኙት የአጋጣሚ ሁሉ ይወተውቱ ነበር።
አፄ ኃይለስላሴ፣ ኬኒያታ፣ ሉሙምባ፣ ኔሬሬና ሌሎች መሪዎች ስለአፍሪካ አንድነት አስፈላጊነት የወተወቱ ቢሆንም የዛን ጊዜም ሆነ የዛሬ መሪዎች ይሄን የተቀደሰ አላማ በቁርጠኝነት ወደፊት ሊያራምዱት አልቻሉም። ወይም ፍላጎቱ የላቸውም። ሁሉም ከሚገዙትና ከሚመሩት ሀገር የተሻገረ አፍሪካዊ ህልም የላቸውም ቢባል መቼም ከድፍረት አይቆጠርም። የቀን ተሌት ሕልማቸው የሀገር እንጅ የአህጉር መሪ መሆን አይደለም። እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ መሠሪና ስልጣን አምላኪ አምባገነኖች እንኳንስ ለአፍሪካ አንድነት ሊጨነቁ ይቅርና የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም የዘር ፖለቲካ በማንበር ጭራሽ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ጥለው አልፈዋል።
አሁን ስልጣን ላይ ያሉ መሪዎችም የአፍሪካ አንድነት ጉዳይ እኛንም ይለፈን ያሉ ይመስላል። ለዚህ ነው የአፍሪካን አንድነት ጉዳይ ሁለት ትውልድ አሻግረው ለ2063 እኤአ ዓ.ም አርቀው የቀጠሩት። የሚገርመው የሕብረቱ መሪ ቃል፤”የተባበረና ጠንካራ፤”አፍሪካ ፤ መዝሙሩም “አንድ እንሁን…፤” የሚል ቢሆኑም ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአፍሪካ አንድነት ጉዳይ ለዚህ ትውልድም ሆነ ለመጭው የህልም እንጀራ ሆኗል። እንደ ሳዳክ፣ ኢጋድና ኤኵዋስ ባሉ ቀጣናዊ መድረኮች እንኳ አገራቱን አንድ ማድረግ ሲቸግር እየተስተዋለ ነው። ከእነ ንክሩማህ ከፍታ ዘመን ወርዶ ዛሬ ስለ ሕብረቱ መቀመጫና ስለቀጣዩ ጉባኤ ማካሄጃ ቦታ የሚራኮት ሆኖ አርፎታል።
የአፍሪካ እንደ አህጉር አንድ አለመሆን የ55 ሀገራትን ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አለማቀፋዊ ፣ ዲፕሎማሲና ሌሎች ጥቅሞችን የማስከበር ነገር አዳጋች አድርጎታል። አፍሪካውያን ዛሬም ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነጻ አልወጡም። መሪዎቻቸውን የሚመርጡላቸው ምዕራባውያንና አሜሪካ ናቸው። ቶማስ ሳንካራ፣ ኩዋሚ ንክሩማህ፣ ሮበርት ሙጋቤ ፣ ሙአመር ጋዳፊ አገሬን በማለታቸው የገጠማቸውን ፈተና ይታወሳል። ሱዳን፣ ማሊ ፣ ጊኒ ፣ ቡርኪናፋሶና ሌሎቾ አገራት ፓሪስ ፣ ለንደን ፣ ብራስልስና ዋሽንግተን በሚተላለፍ ውሳኔ ነው የሚመሩት ።
በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መሪ የአይኑ ቀለም አላማረንም ብለው በመፈንቅለ መንግስት ወይም በግድያ ሊያስወግዱት ሁሉ ይችላሉ ።
ይህ አልሆን ካላቸው በዘርፈ ብዙ ማዕቀብ አሳሩን አብዝተው ሕዝብ እንዲነሳበት በማድረግ ገሸሽ ያደርጉታል ። በተፈጥሮ ሀብቱና በማዕድኑ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀም ተደርጎ ይበዘበዛል ። የወርቁ ፣ የአልማዙ፣ የነዳጁ ፣ የጥጥ ፣ የካካዋ ፣ ወዘተረፈ ልማትና ዋጋ የሚወስኑለት እነሱ ናቸው ። ስርዓተ ትምህርቱን ፣ ባህሉና ወጉን የሚበይኑለት ቅኝ ገዥዎቹ ናቸው ።
በአፍሪካ ብቸኛ የራሷ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት ኢትዮጵያ ብቻ ናት ። አይደለም የአገራቱን የሕብረቱን ቋንቋ ብንመለከት እንግሊዘኛ ፣ ፈረንሳይኛ ፣ አረብኛ ፣ ስፓኒሽ ፣ ፖርቹጊዝና ኪሲዋሊ ነው ። ከዚህ በላይ ባህሉና ማንነቱ ተነጥቋል። ተበርዟል ። ተከልሷል። በራሱ እምነት እንዳይኖረውና እንዳይኮራ ለዘመናት ስነ ልቦናው ሲሰለብ ኖሯል። አንድ አለመሆኑ እነዚህንና መሰል ምርኮዎቹን አሳጥቶታል ።
ከሁሉም በላይ የአፍሪካን ጥቅም በአንድነት የሚያስከብር ፤ ድምጹን የሚያሰማ ተቋምና መሪ ስለሌለ አጀንዳ ቀርጾ ወደፊት የሚያመጣ የአመራር ክፍተት ተፈጥሯል ። ይሄን የአመራር ክፍተት የመሙላት ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባት ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። አፄ ኃይለስላሴ የሞኑሮቪያና የካዛብላንካን ጎራ (ብሎክ) በጥበብና በማስተዋል ወደ አፍሪካ አንድነት እንዳመጡት ሁሉ ፤ ዛሬም የአፍሪካን አንድነት በማጠናከር የተከበረና የታፈረ ተቋም አድርጎ እንዲወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኃላፊነት አለባቸው ።
እንደ ከተማ ይፍሩና አክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ በሳልና ጥበበኛ ዲፕሎማቶችም ሊፈጠሩ ይገባል። አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖረው፤ በአለም ባንክ ፣ በአይኤምኤፍና በሌሎች ተቋማት የመደራደር አቅም (ሌቨሬጅ) ከፍ እንዲል እና ጥቅሙ እንዲከበር ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መጫወት ይጠበቅበታል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲያገኝ ያቀረቡትን ጥያቄ የደቡብ አፍሪካው ራማፎዛ ፣ የኡጋንዳው ሙሴቬኒና ሌሎች ተቀላቅለውታል ። ሆኖም ጥያቄው ከተናጠላዊነት ወጥቶ ተቋማዊ ሆኖ በተደራጀ አግባብ በአፍሪካ ሕብረት በኩል በኦፊሴል ሊቀርብ ይገባል ።
የ#በቃ ፣ የ#እንቢ ፣ የ#No More ንቅናቄ በአህጉረ አፍሪካ የአመራር ክፍተት መኖሩን ግሀድ አውጥቶታል። ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ የምዕራባውያንና የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት በበረታበት ወቅት በጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ አቀጣጣይነት የተለኮሰው ለአዲሱ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ (ኒዎኮሎኒያሊዝም) #እምቢ #በቃ #No More ንቅናቃ አፍሪካውያንን ፣ ካሪቢያንን ፣ አፍሪካን አሜሪካንንና ሌሎችን ዳር እስከዳር ያነሳሳው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተጫወቱት የመሪነት ሚና ነው ። የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ፣ መሪዎችና ሀገራት በአጭር ጊዜ ንቅናቄውን ተቀላቀሉ ። ባልተጠበቀና በልተገመተ ሁኔታ በአጭር ጊዜ እንደ ቋያ እሳት ተዛመተ ።
ማሊ ፣ ቡርኪና ፋሶ ፣ ጊኒ ፣ ሌሎች #No More አሉ። የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካውያን ፣ የጥቁር ሕዝቦችና የሰው ልጅ አጀንዳ መሆኑ ምዕራባውያንን አስደንግጧል። አቋማቸውን እንደገና እንዲመረምሩ አስገድዷቸዋል ። ባልተደራጀና ተቋማዊ ባልሆነ ንቅናቄ ይህን ያህል እርቀት መጓዝ ከተቻለ ንቅናቄው በአፍሪካ መሪዎችና ተቋማት ቢታገዝ በአለም አደባባይ የገዘፉ አጀንዳዎችን ማቀንቀን ይቻላል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደነ አፄ ምኒሊክና ኃይለስላሴ አፍሪካን የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል ። ይሄን የመሪነት ሚናም ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ። የእነ አፄ ኃይለስላሴና ምኒሊክ አሻራ ወራሽ ናቸውና ። የአፍሪካን አጀንዳ ይዞ ወደፊት የመምጫው ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ።
የታላቁ የአድዋ ድል የአፄ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱ (በርሀነ ዘኢትዮጵያ) ዝና በመላው አለም እንዲናኝ ከማድረጉ ባሻጋር አገሪቱን በአለማቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ መነጋገሪያ አደረጋት ፡፡ ከአፅናፍ አፅናፍ የአለምን ትኩረት እንድትስብ አደረጋት ፡፡ ድሉ ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉ በማሳየቱ ፤ በቅኝ ግዛት ፣ በጭቆና ለሚገኙ የአለም ሕዝቦች በተለይ ለአሜሪካ ጥቁሮች መነቃቃትን ፈጥሯል ፡፡ ለማርከስ ጋርቬ ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ፣ ለስቲቭ ቢኮ ብላክ ኮንሽየስ ንቅናቄዎች እርሾ በመሆን አገልግሏል ፡፡ ለደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድም ሆነ ለሌሎች ለፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ጉልበት ሆኖ አገልግሏል ፡፡ የአረንጓዴ፣ ቢጫ ፣ ቀይ ባንዲራችን በብዙ የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት ሰንደቅ በተለያየ ቅርፅ የመገኘቱ ሚስጥርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ፡፡
የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ አህጉራዊና አለማቀፋዊ ተቀባይነትም የራሳቸው ጥረት እንዳለ ሆኖ መነሻው አንፀባራቂው የአድዋ ድል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካና የታሪክ ልሂቃን የትላንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ሆነ የዛሬው የአፍሪካ ህብረት (ኤዩ) የምስረታ ሀሳብ የአድዋ መንፈስ የበኩር ልጅ የሆነው የፓን አፍሪካኒዝም የመንፈስ ክፋይ ነው የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ይሄን ታሪካዊ ኃላፊነት ዳር የማድረስ አደራ አለበት። አፍሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአለም አደባባይ የሚመራት ቆራጥ መሪ ትሻለች ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከጥር 25 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ፤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ አፍሪካዊ ወንድማማችነታችንን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር በሚያስፈልገን በዚህ ወሳኝ ወቅት ፤ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መሪዎች ተስማምተው የሕብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመወሰናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ።
ኢትዮጵያ – የአፍሪካዊነትን ጉዳይ እንደ መጀመሪያ አጀንዳዋ እንጂ እንደ ሁለተኛ አድርጋ ወስዳው አታውቅም ። ለአፍሪካ ነጻነት ያላት አቋም አንድም ቀን ቀንሶ አያውቅም። ለፓን አፍሪካዊነት የምትሰጠው ቦታ ሁሌም ጉልህ ነው። ጥንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ናት። በአፍሪካዊነት ላይ አታወላውልም። ይሄን የኢትዮጵያን አቋም ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች እንደተገነዘቡት ሁሉ፣ የዚህ ዘመን መሪዎችም በሚገባ ተገንዝበው አጋርነታቸውን በሚያሳይ መልኩ የሕብረቱን ጉባኤ በአካል እዚህ ለማከናወን ያሳለፉትን ውሳኔ ኢትዮጵያ ታደንቃለች ። ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው በሁሉም መስኮች አሸናፊ ከሆነች ነው።
ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ለአፍሪካ የገባነውን ቃል ጠብቀንና አጽንተን መቀጠላችን ነው። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት ያላት አቋም መቼም ቢሆን አይለወጥም። የገባችውን ቃልም በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ሆና ማክበሯን ትቀጥላለች። ይሄንን አቋሟን ስለተገነዘቡ አፍሪካውያን ወገኖቻችንን በድጋሚ አመሰግናለሁ ብለዋል።
የአፍሪካ አንድነት ይለምልም !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 19/2014