ነገርን በወቀሳ በደልን በካሳ ይባላል። የበደለ ካሳ መክፈል አለበት ለማለት ነው። በተቃራኒው የተበደለ ካሳውን ካለመቀበል አልፎ ራሱ በዳይን በገዛ ፍቃዱ ይቅር ለማለት ሲሰናዳ ያስገርማል። ይህኛው አካሔድ ላይ በመጠኑም ቢሆን ከተለመደው ወጣ ያለ ምክንያት ወይም ደግሞ የተበዳይ የተለየ አስተሳሰብ ሊቀርብ ይችላል። ለየት ሲል ደግሞ የተለየ የፖለቲካ ትርጉም ይኖረዋል። እንደእኔ አይነት ይቅርታ እንደሚያንቀው እልኸኛ ሰው፤ ተበዳይ እንደበዳይ የይቅርታን መንገድ ሲይዝ በስሜት መንዘርዘር የግድ ይሆናል።
ይህ አይነቱ አካሄድ በአንድም ይሁን በሌላ የይቅርታን መንገድ መቃወምን ማስከተሉ የማይቀር ነው። ምንም ያህል እልኸኛ ብሆንም ተበዳይ ይቅር ማለቱ ቢቆረቁረኝም፤ በሙሉ አፌ ‹‹ለምን ይቅር ተባለ?›› ለማለት አልደፈርኩም። ምክንያቱም በልቤ ተበዳይ ይቅር ያለበት የራሱ ተጨባጭ አሳማኝ ምክንያት አለው ብዬ አምኛለሁ።
‹‹ምንም በደል ሳይኖራት ሰው አማሽ ብለው ሰደቧት›› እንደሚባለው ዓይነት ትልቅ የማይገፋ ተራራ ከፊት ለፊት የተደነቀረ ይመስላል። ምንም በደል ሳይሰራ ተበዳይ በዳይን ይቅር በማለቱ፤ በአንዳንዶቻችን ዘንድ ይቅር ባይ ተበዳይ እንደበጥባጭ ተቆጥሯል። አገር አመሰ ተብሏል። ያው መቼም የገደለን ይቅር ያለ፤ የተቃወመን እና ያወገዘን ምንም አይልም በሚል አይነት ሊሆን ቢችልም እዚያም እዚያም ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ ከመወያየት እና ሃሳብ ከመለዋወጥ አልፎ መሰዳደብ ላይ የደረሰም አይጠፋም። ነገር ግን አሁን ጊዜው የውይይት ነው።
አገራዊ ውይይት በማካሔድ የጋራ መግባባት ለመፍጠር መሰነዳዳት ተይዟል። የይቅርታው መንፈስ ከአገራዊ ምክክር እና ከብሔራዊ መግባባት ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ብዬ መንግስትን አምኜ ተበዳይ ይቅር ቢልም መከፋቴን ፍቄዋለሁ። ቀድሞስ ቢሆን መንግስት የሕዝብ ልጅ ነው። ያው ወላጅ እንደሚቆጣው ሕዝብ ሲከፋ መንግስትን ይቆጣል። በሁለቱ መካከል እውነተኛ የወላጅ እና የልጅ ግንኙነት ካለ አንዱ ሌላው ላይ ቢከፋ ቢቆጣ የተለመደ ነው። ብዙ የሚያስጨንቅ አይደለም። ነገር ግን ማንም በማንም ሊያዝን አይገባም።
ዋናው ጉዳይ ልጅ ‹‹ወላጅን ያስቆጣው ምክንያት ምንድን ነው?›› ብሎ ማሰብ፣ ማሰላሰል እና መረዳት አለፍ ሲልም የራሱን ተጨባጭ ምክንያት ለወላጅ መግለፅ እና ማብራራት ይጠበቅበታል። ወላጅ በበኩሉ የልጅን ጥፋት ማየት ማኩረፍ እና መቅጣት ብቻ ሳይሆን ወላጅ እንደጥፋት የቆጠረው ምክንያት በእርግጥ ጥፋት መሆን አለመሆኑን በማሰብ ለልጅ እንዲናገር ዕድል መስጠት ተገቢ ነው። በዚህ ዘመን ሁሉንም ነገር በልኩ ለመመዘን እና ለመረዳት ለማዳመጥ ካልተሞከረ ያው ዓለምን ቀርቶ አገርን አልፎ ተርፎ ቤተሰብን መምራት እና አብሮ መኖርም አዳጋች ነው።
በእርግጥ ሁለት ሶስት አልፎ ተርፎ አራት እና አምስት እንደውም ቡድንን እስከነ አካቴው አገርን የበደለ አካል ይቅር ሲባል ይቅር ባዩ ማን እና በምን መልኩ ይቅር አለ? የሚለው ሊያጠያይቀን ይችላል። መቼም አገር የበደለ ቡድን ይቅር ሲባል አነጋጋሪ መሆኑ ሊያጠያይቅ አይችልም። ምክንያቱም ተበዳይ አንድ አካል ሳይሆን ብዙ ወገኖች ናቸው። አገር ሳይቀር ከእስር በተፈቱት ሰዎች ትልቅ በደል ተፈፅሞባታል። ስለዚህ ይቅር መባሉ ሊያስከፋ ይችላል። ነገር ግን ለአገር ሲባል የማይተው አይኖርም።
ለችግሮቻችን ዋነኛ መላው መመካከር ነው። አንዱ ሌላው ላይ ከሚቆጣ፤ ወላጅ ልጅን ልጅም ወላጅን ለመቅጣት ከሚዳዳ አንዱ የሌላውን ምክንያት ማወቅ እና መደማመጥ ሲኖር ሁሉም ነገር ቦታ ይይዛል። ያለበለዚያ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ክፍተት መሥጠት ጣልቃ ለመግባት ለሚዳዱት የውጭ ኃይሎች መንገድ መሥጠት ይሆናል። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በምንም መልኩ እጅ አንሰጥም። እጅ ሰጥተንም አናውቅም። እጅ የማንሰጠው በጦርነትም ሆነ በተለያየ መልኩ በተንኮልም ጭምር ለሚመጣ የውጭ ኃይል ጭምር ነው ።
እጅ አለመሥጠት ብቻ አይደለም፤ አሁን ላይ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ የሚፈፀመውን በደል ዋጥ ቻል አድርገን እርስ በራሳችን እንመካከራለን። አንዱ ሌላው ቢበድለውም ይቅር ይላል። ምክንያቱም የእዚህ ትውልድ ትልቅ አደራ አገርን በሰላም ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን አገርን በተሻለ መልኩ አበልፅጎ ማሻገርን የያዘ ነው።
ኢትዮጵያ እንዳትበለፅግ የሚፈልጉ ብዙ በመሆናቸው ፈተናው አይሏል። ጭራሽ መወጣት የማይቻል ይመስላል። ነገር ግን ወላጅም ሆነ ልጅ መታገስ እና መደማመጥ ከቻሉ መታለፍ ይችላል። ችግሩ ሁለቱም እንቻቻል ያሉ ቀን ሁሉ ነገር ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ ሆኖ የአገር ፍፃሜ ደጃፍ ላይ ይደነቀራል።
ይህ ቀን እንዳይመጣ ከሁሉም ወገን ትዕግስት፣ አርቆ አሳቢነት እና አስተዋይነት ይጠበቃል። በማስተዋል የሚደረግ ጉዞ ጊዜ ቢፈጅም ፍሬውን ማግኘቱ አይቀርም። ያለበለዚያ የዛሬውም ዕድል ይመክናል። የዛሬው ዕድል እንዳይመክን ማሰብ እና መጨነቅ ፈሪነት አይደለም። ይልቁኑም አስተዋይነት ነው። በተለያየ መልኩ ፈታኝ ጋሬጣዎች ከፊት ለፊት ይደቀናሉ። ጦርነቱ እና የውጭ ጫና ሲባል፤ በሌላ በኩል እንደተቀደደ ከረጢት የውስጥ ችግር ፈንድቶ አገር አምሶ የባሰ ሕዝብን ሌላ ጭንቀት ውስጥ ይከታል።
በዚህ ጊዜ ለሁሉም የሚበጀው መረጋጋት ነው። ያው መቼም ችግር ለምን ተፈጠረ ብሎ መንጨርጨር ምንም ውጤት አያመጣም። እርግጥ የሚመለከተው አካል የችግሩን ምንጭ ማጣራት አስፈላጊ ከሆነ ችግር እያመነጨ ያለውን አካል የብዙዎች ጉሮሮ ሳይደፈን ራሱን መድፈን ያስፈልጋል። ከዛ ውጭ ወጣ ገባ እያሉ እርስ በእርስ መቧደን ምንም ትርፍ አይኖረውም።
ስለአገራዊ ምክክር እና ስለብሔራዊ መግባባት ሲነሳ ከፊታችን ሌሎችም ትልልቅ ፈተናዎች በተለያየ መልኩ ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ፈተናዎች ለምን መጡ ማለት ተራ የዋህነት ነው። ዋናው ነገር ቀድሞ ፈተናዎች እንዳይመጡ መሥራት፤ ፈተናዎች ከተፈጠሩም በጊዜ ከሥር ከሥር እያሉ ችግሮችን መፍታት ነው።
ለአገር ሲባል በዳይ ተፈቷል። ያው ለምጣዱ ሲባል… እንደሚባለው ማለት ነው። ከዚህም በኋላ ለአገር ሲባል ብዙ ይፈፀማል፤ ከወላጅ ደግሞ ልጅ የፈፀመውን አይቶ መጨነቅ፣ መበሳጨት እና ሌላ ቤትን የሚያፈርስ እልህ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ምክንያትን ለማዳመጥ ራስን ማዘጋጀት እና ደጋግሞ ልጅን ይቅር ማለት ይገባል። ሰላም!
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም