በሰፈሩ አንድ እጅግ ተወዳጅ ሰው ነበሩ። አንድ ቀን መጥፎ ቀን ገጠማቸው። ከሰፈራቸው ተውበው የወጡት ሰው አመላለሳቸው እያነከሱና ልብሳቸው አይሆኑ ሆኖ ገርጥተው ሆነ። ሁኔታቸውን የተመለከቱ የሰፈሩ ሰዎች አባት ምን ሆኑ? ሲወጡ ደህና ነበሩ፤ ምን ነካዎት? ሲሉ ጠየቋቸው።
እሳቸውም ለተሰበሰቡ ወዳጆቻቸው ቀና ብለው መልስ ሰጡ። አንድ ሰው በድብደባ ጉዳት እንዳደረሰባቸው በደከመ ድምፅ ተናገሩ። በመሀል አንዱ የቅርብ ጓደኛቸው ጥያቄ ያነሳል። ማን ነው እሱ? በምንድነው እንዲህ የጎዳዎ? ይላቸዋል።
ሰውየውም በቁጭትና በተከፋ ስሜት “በሽመል ነው የቀጠቀጠኝ” ብለው ይመልሳሉ። ይሄኔ “ጠዋት እርሶም ከቤት ሲወጡ ሽመል ይዘው ነበር፤ ሽመል ይዘው እንዴት ይህን ያህል ጉዳት ደረሰብዎት” ሲል ሌላ ሰው ይጠይቃቸዋል።
“እኔም መመታቴ አይደለም ያሳመመኝ፤ ሽመሌን በዘዴ ወስዶ በገዛ ሽመሌ የደበደበኝ መሆኑ ነው ያንገበገበኝ፤ እሱ ነው ከህመሙ በላይ ያንገበገበኝ። አምጣው ልደገፍበት ብሎ ወስዶ እኔኑ ስላጠቃበት ነው የነደደኝ” ብለው በቁጭት ተናገሩ። እኚ ሰው መጨረሻ ላይ የሰጡት ማብራሪያ ነው የእኔ ትኩረት።
አሸባሪው ሕወሓት ከፈጸመብን በደል ሁሉ እጅጉን የሚከፋው ከእኛ በዘረፈው ገንዘብና መሳሪያ በደል የፈጸመው መሆኑ ነው። በሥልጣን ዘመኑ ያለ ከልካይ እንዳሻው አሟጦ በሰበሰበው የኢትዮጵያ ሀብት ነው የወጋን።
አገራችንን ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባት ያደረገበትና ህዝባችንን ለሞት፣ለስደትና ለስቃይ የዳረገበት መሳሪያና ለአጫፋሪዎቹ ፣ ለአግባቢዎቹ ሲበትን የነበረው ገንዘብ የእኛ መሆኑ ነው። ይህ ከሀዲ ራሱ በማሰው ጉድጓድ እንዲገባ ሁላችንም እንፈልጋለን።
የሁላችንም ምኞት ይህ ከሀዲ ቡድን እንዲጠፋ ተባባሪዎቹ እጃቸውን እንዲሰብስቡ ማድረግ ነውና ይህን ማድረጋችን ትክክል ነው። መንግሥት ይህን ከሀዲ ለመደምሰስ ያደረገውን ጥሪ በመቀበል ኢትዮጵያውያን ተቆጥተው ዳር አስከ ዳር ተነቃንቀው መስዋእትነት በመክፈል ድል ጨብጠዋል።
በዚህም ቡድኑን በወረራ ይዟቸው ከነበሩ የአማራና አፋር ክልል አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲደርስበት በማድረግ የተራረፈው ሀይሉም ብን ብሎ እንዲጠፋ ማድረግ ተችሏል።
ኢትጵያውያን ይህን ድላቸውን በተለያዩ መልኩ እያጣጣሙትም ይገኛሉ። ቡድኑ ክፉኛ ቢመታም፣ አሁንም የአልሞት ባይ ተጋዳይ ተግባር እያከናወነ ይገኛል። በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አሁንም ትንኮሳ እያደረገ ይገኛል።
ይህም ቡድኑ ተሸንፏል ብለን እንዳንቀመጥ ጨርሶ አስከሚደመሰስ ድረስ ሁሌም ዝግጁ መሆን እንዳለብን ያመለክተናል፡፡ የእስከ አሁኑ ድልም ሆነ ይህ እርምጃ ግን በቂ አይደለም፤ የምንፈልገው ዘላቂ ሰላም ነውና።
የተጎናጸፍነውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ብዙ መሰራት ይኖርብናል። ለእዚህ ደግሞ ወታደራዊ አማራጭ ብቻውን ብዙ ርቀት አይወስድንም። ጠላትን ማሸነፍ የሚቻለው በአንድ መንገድ ብቻ አይደለም።
ሌሎች የተለያዩ መንገዶችም አሉ። ጸረ ሰላም ሀይሉ አለሁ ሲል እንዲጠፋ፤ ለመለምኩ ሲል እንዲከስም ማድረጊያ መንገዶችን መጠቀም ያስፈልጋል። እዚህ ላይ በሀይል ሲመጣ ይህን ድፍረቱን እንዳይደግመው የሚያደርግ ከፍ ያለ ሀይል መጠቀም አንዱ መንገድ አይደለም እያልኩኝ እንዳልሆነ ይሰመርበት፡፡
ከሀይል ይልቅ ሌላኛውን መንገድ መጠቀሙ ዘላቂ ድል ሊያስገኝ ይችላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ አገራዊ ሁኔታዎች በተለይም በክስ መቋረጡ ከእስር በተለቀቁት የሕወሓት መሪዎች ምክንያት ብዙ አይነት አስተያየቶች ተንፀባርቀዋል።
እጅጉን በርክቶ የነበረው ግን የዚህ ሁሉ እልቂት ምስቅልቅልና የአገር ጉዳት ጠንሳሽና ዋንኛ መሪ የነበሩት ሰዎች የክስ ሂደት ለምን ይቋረጣል? የሚለው ነበር።
መንግሥት በተለያዩ መድረኮች አማካይነት በጉዳዩ ላይ የሰጣቸው ማብራሪያዎች ይህን ቅሬታ ትንሽ ለዘብ ያደረገው ይመስላል። ይህ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
መንግሥት ግን ስለምን እዚህ እርምጃ ላይ ደረሰ? ለኢትዮጵያ ጠቃሚው መንገድ የትኛው ነው? ለኢትዮጵያ ዘላቂ ድል አድራጊነት የሚያዋጣው መንገድ የትኛው ነው? አገሪቱ ያለችበት ሁኔታስ ምን ይመስላል? በአገሪቱ ለማድረግ ለታሰበው የብሄራዊ መግባባት ውይይት ምን ጠቀሜታ አለው? ዓለማቀፉ፣ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊው አሰላለፍና አጠቃላይ ሁኔታውስ በምን ላይ ይገኛል? የሚሉ ጉዳዮችን በጥልቀት መመርመርን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡
አንዳንዴ እየመረረን የምንውጠው መድሀኒት ነው ፈውስ የሚሰጠን። ሕወሓት መወገዱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰውን በደል የሚክስ ፍርድና እርምጃ እንዲወሰድበት ብሎም ይህ አደገኛ ሽብርተኛ ድርጅት እንዲጠፋ የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ የራሱ አባል ካልሆነ በቀር አይኖርምና በምን መንገድ ማጥፋት ይቀላል የሚለውን ስሌት እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መንግሥት በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርግ ስራ እየሰራ መሆኑን አምናለሁ። ውሳኔዎቹ ላይ ጠንከር ያሉ ቢሆኑም፣ ምን አልባት ውሎ ሲያድር የማየው፣ እየቆየ የሚገባኝ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድል የምታደርግባቸውን መንገዶች እየተከተለ ነው ብዬ አምናለሁ።
በአጠቃላይ ጠላት ከፊት ሲጠብቅ ከኋላ አከርካሪውን መትተን የምንጥልበትን በስሌት የተመራ ፖለቲካዊ አካሄድ እየተከተልን ነው ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ ሁኔታም ይታሰበኛል። እኔ እንደሚገባኝ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በተለይም ምዕራባዊያን ለትህነግ ሲሉ ያን ሁሉ ጫና ሲፈጥሩና አበቃላችሁ ብለው ሲረዱት የነበረበት ሁኔታ እየተቀዛቀዘ የመጣ ይመስለኛል። ይህ ለምን ሆነ ብለን አስቲ እንጠይቅ።
እነዚህ ሀይሎች ከኢትዮጵያ ጋር በዲፕሎማሲው መስክ የሚያደርጉት ግንኙነት እያንሰራራም ይመስለኛል። ይህም እንዴት ሆነ ብለን እንመርምር። እንደ አኔ እንደ እኔ እነዚህ ለውጦች መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤቶች ይመስለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሁድ ምሽት ለመገናኛ ብዙኃንና ለኪነጥበብ ባለሙያዎች በተካሄደ የዕውቅና መስጠት መርሀ ግብር “እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ነገር፤ኢትዮጵያ አሸንፋለች። ዓለም የኢትዮጵያን ማሸነፍ በቃል ሳይሆን በተግባር አረጋግጧል” ሲሉ የተናገሩትም ይህንኑ አባባሌን አረጋግጦልኛል።
በዲፕሎማሲው መስክ የሚታዩት ለውጦችም ይህን ተከትሎ የመጡ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምንም ያህል በአገራችን ብንከፋ ኢትዮጵያዊያን አንድ ነገር እንፈልጋለን።
በመከፋታችን ውስጥም ብንሆን የኢትዮጵያን ማሸነፍዋን እንፈልገዋለን። ያኔ ደስታችን ሙሉ ይሆናል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በመንግሥት በኩል የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ሁሉ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ የተወሰዱ እርምጃዎች መሆናቸውን ይበልጥ እንድረዳ አርጎኛል።
የሚፈለገውን ድል ማምጣት እስከቻለ ድረስ መንግሥት የቱንም እርምጃ ቢወሰድ ችግር የለውም፤ ዋናው ድሉ ነው። ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ የትኛዎቹም እርምጃዎች ጥሩ ናቸው። ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ እርምጃ ግን ያስፈልገናል። ጠብ ሲል ስደፍን አያዋጣንም። ለእዚህ ደግሞ መንግሥት በተጎናጸፍነው ድል ላይ ሆኖ እየሰራ ነው። ለብሄራዊ መግባባት እየተከፈለ ያለውን ዋጋ በእዚህ ልኩ ማየት ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እየሠራ ነው፤ እኛም በየትኛውም መንገድ ይሁን ድል የኢትዮጵያ እንዲሆን ብርቱ ፍላጎት አለንና በጎ በጎውን እየተመኘን አገራችንን በሚጠቅሙ መልካም ተግባራት መሳተፍና አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ህብረት መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅብናል። እኔም የማምነው በዚሁ ነው።
አስፈላጊ በሆነ ጊዜ የምሰማው አልያም ደግሞ እየቆየ የሚገባኝ አንድ እውነት እንዳለ ይሰማኛል። እሱም ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ይበልጥ አሸናፊ የሚያደርጋትን ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ማግኝቷ ነው። ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ስንል ቆይተናል፤ ዛሬ የኢትዮጵያን አሸናፊነት አውጀናል፤ ነገ ደግሞ በዘላቂ ሰላም ውስጥ ሆነን እንዴት እንዳሸነፈች የምንተርክ ይሆናል። አበቃሁ ፤ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014