የዛሬው የፍረዱኝ እንግዳችን አቶ በቀለ ገብረህይወት ይባላሉ፡፡በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ስሙ ወረዳ 25 ቀበሌ 05 በአሁኑ መጠሪያው ወረዳ 10 የቤት ቁጥር 081 ባለይዞታና ነዋሪ ናቸው፡፡
አቶ በቀለ ለዝግጅት ክፍላቸው ይዘውት በመጡት ቅሬታ፣በማን አለብኝነትና ህግን ባልጠበቀ አካሄድ በህጋዊ መንገድ በሚያስተዳድሩት የይዞታ ቤታቸው ላይ ድርብ ካርታ እንደወጣባቸውና ካርታውም በፍርድ ቤትና በከተማው ከንቲባ ቢሮ ትዕዛዝ እንዲመክን መደረጉን ያስረዳሉ፡፡
ይሑንና በአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማና በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 የሚገኙ ህግ አስፈጻሚዎች የፍርድ ቤቱንና የከንቲባ ቢሮውን ትዕዛዝ ወደ ጎን በመተው ትዕዛዙን ሊፈፅሙ እንዳልቻሉና በዚህም ምክንያት ለእንግልት መዳረጋቸውን ይገልፃሉ፡፡ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማና ወረዳ 10 የህግ አስፈጻሚ አካላት የፈጸሙብኝን በደል ‹‹ህዝብ አይቶ ይፍረደኝ!››ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ይላሉ፡፡
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አመራሮች፣ግለሰቦችና የሰነዶችን በመመርመር ያገኘውን ውጤት ለህዝብ መፍረድ እንዲያስችል ጉዳዩን እነሆ ብሏል፡- አቶ በቀለ ገብረ ሕይወት በኮልፌ ለምለም የህብረት ስራ ማህበር በ1997 ዓ.ም ከ500 ሰዎች በላይ በወቅቱ በነበረው መንግሥት በመደራጀት ቦታው ተከፋፍሎ ሁሉም የማህበሩ አባላት በራሳቸው ፕላን መሰረት ቪላ ቤት በመስራት መኖር እንደጀመሩም ይገልጻሉ፡፡
‹‹ከወይዘሮ ታየች አጎናፍር በ1986 ዓ.ም 340 ካሬ ሜትር ይዞታ ገዝቼ በካርታ ቁጥር ኮ/ቀ/የማ/ ን/መ/122/17448/00 በ23/9/1997ዓ.ም በስሜ የተመዘገበ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቶኛል፣እኔም ዲዛይን በማሰራት ቤት ሰርቼ እየኖርኩኝ ባለበት ሁኔታ የእኔ አጎራባች የነበረው አቶ ሳሙኤል ጣሰው የተባለ ግለሰብ አጣና ሲሸጥበት የነበረውን ሙሉ በሙሉ በመንገድ ልማት ምክንያት የተነሳ ሲሆን ከእኔም ሁለት ሜትር በመንገዱ ምክንያት ተነስቷል፣ ይሑንና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ባሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የመሬት የይዞታ ኃላፊዎች በሙስና በመመሳጠር በይዞታ ካርታዬ ላይ ደርበው ለአቶ ሳሙኤል ካርታ ሰጥተዋል›› ይላሉ፡፡ ግለሰቡ‹‹በግድግዳዬ ላይ በአጣና፣ ብረት፣በብሎኬት በመስራትና እንዲሁም ሸራና ላስቲክ በመወጠር በአካባቢው የማይታወቁ ሰዎችን በማከራየት ታይዋን በሚል ስም የተለያዩ የንግድ ሥራ እየሠራ በወቅቱ በ2006 ዓ.ም መጋቢት 1 ቀን እየተጠቀመው ይገኛል››ይላሉ፡፡
ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ግንባታና ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት፣ለግለሰቡ በ7/8/2006 ዓ.ም በቁጥር 1230/2006 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤም የተሰጠ እድሳት ፈቃድን እንዲመክን መወሰኑን ዋቢ ያደርጋሉ፡፡
ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ግንባታና ፈቃድ አሠጣጥና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ኃላፊው ገረመው ንጉሴ የተፈረመ ደብዳቤ፣‹‹አቶ ሳሙኤል ጣሰው የተባሉት ግለሰብ በወረዳ 10 ቀበሌ 05 የቤት ቁጥር 434 የሆነውን ቤት እድሳት ፈቃድ መውሰዳቸውን ይታወቃል፣ይሑንና የወሰዱት የእድሳት ፈቃድ በአጎራባች በኩል የድንበር ክርክር ስለተነሳ የተሰጠው የእድሳት ፈቃድ ይዞታነቱ የእርሶ መሆኑ ተረጋግጦና አሁን ባለው ይዞታ መሰረት ካርታው ተስተክክሎ እስኪቀርብልን ድረስ የተሰጠው የእድሳት ፈቃድ እንደማያገለግል እናሳውቃለን››ብሏል፡፡
ከዚህ በኋላም ደረጃ በደረጃ እስከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ድረስ አቤቱታ ማቅረባቸውና ከንቲባውም በአስቸካይ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋማቸውን የሚያስታውሱት አቶ በቀለ፣ከተቋቋመው ኮሚቴ መካከልም የወቅቱ የቅሬታ ሰሚ ኃላፊ ወይዘሮ ሃይማኖት ወልደ ገብርኤልና የመሃንዲስ ኃላፊው አቶ ጌቱ ዘውዴ የተባሉ ግለሰብ ይገኙበት እንደነበር ዋቢ ያደርጋሉ፡፡
በወቅቱም እነዚህም ኮሜቴዎችም ቦታው ድረስ በመሄድ ግራ ቀኙን በማጣራት ለከንቲባው በካርታዬ ላይ ድርብ ካርታ እንደሆነ ሪፖርት አቅርበዋል፣በዚህ መስረት በ24/4/2009 ዓ.ም በነበረው ነባር ካርታዬ መሰረት እንዲስተካከልና በይዞታዬ ላይ ያለ ማንኛውም ግንባታ በማንሳት በ 5 ቀን ውስጥ ፈፅማችሁ ሪፖርት እንድታደርጉ የሚል የፅሁፍ ትእዛዝ ከከንቲባው ፅህፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተማ መሰጠቱንም ይገልፃሉ፡፡
ይሑንና ትእዛዙ የተሰጣቸው አካላት ከግለሰቡ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት ጉዳዩን ለመፈፀም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል››ይላሉ፡፡ አቶ በቀለ እንደሚገልጹትም፣የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ግንባታና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ ፀረ ሙስናና
ሥነ ምግባር ኮሚሽን ጥቆማ ሰጥቷል፡፡ ኮሚሽኑም በቀረበለት ጥቆማ መሰረት ቦታው ድረስ በመሄድ ጉዳዩን መርምሮ አጥርቷል፡፡ ከዚህ በኋላም ከእርሳቸው ካርታ ላይ የተደረበ ካርታ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የግለሰቡ ድርብ ካርታ መሆኑን በማረጋገጥ ከክፍለ ከተማው ስራ አስፈፃሚ ጋር በመሆን የተደረበው የግለሰቡ ካርታ እንዲመክን ተደርጓል፡፡ አቶ በቀለ ‹‹ይሕን ወንጀል የፈፀሙ ካርታውን የፈቀዱ ኃላፊ እና መሃንዲሶችም በፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ ተመስርቶባቸው በክስ መዝገብ ቁጥር 178369ና በክስ መዝገብ 181900 በ2 ክስ መዝገብ ተከሰው 9 ወር በእስር ተቀጥተዋልም›› ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የአቶ ሳሙኤል ጣሰው ካርታ ማምከኑን የሚያሳውቅ ደብዳቤንም ዋቢ ያደርጋሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ለአቶ ሳሙኤል ጣሰው በ6/11/2008 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ “በእጅዎ የሚገኘው በካርታ ቁጥር 10/46/1/1056 የተዘገበው ካርታ የመከነ መሆኑን ማሳወቅን ይመለከታል” ይላል፡፡
የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ ቦጋለ ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤም ከላይ በአድራሻ ለተጠቀሰው ይዞታ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን በሚወስዱበት ጊዜ በህጋዊ ወኪል አማካኝነት የድንበር ክርክር ወይም ቦታው ለእኔ ይገባኛል የሚል ክርክር የሚነሳበት ከሆነ ካርታውን ለመመለስ ግዴታ የገቡ በመሆኑና በአሁን በይካተትልኝ ጥያቄ አገልግሎት ተካቶ በተሰጠዎት ይዞታ ላይ የይግባኝ ወይም የድንበር ክርክር የተነሳበት በመሆኑ በይዞታ አስተዳደሩ መመሪያ ቁጥር 12/2004 አንቀፅ 16 ንኡስ አንቀጽ 16/4 መሰረት የባለ ይዞታ ካርታው እንዲመክን በክፍለ ከተማው የይዞታ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ማኔጅመንት ኮሚቴ ታይቶ በመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ በ01/11/2008 ዓ.ም የፀደቀ በመሆኑ የስሪ ቁጥር 045220 በካርታ ቁጥር 10/46/1/1056 የተመዘገበው ካርታ የመከነ / የተሰረዘ/ መሆኑን እየገለፅን በግልባጭ የተመዘገበላቸውም አካላትም ካርታው ህጋዊ ያለመሆኑን በመገንዘብ አስፈልጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጭምር እናሳውቃለን››ይላል፡፡
በ23/2/2009ዓ.ም ከህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ፅህፈት ቤት የተላከው ደብዳቤ፣‹‹አቤቱታ አቅራቢ በተለያየ ጊዜ ለመሬት ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫቸው ድርርቦሽ ተፈጥሮ ለሌላ ግለሰብ ካርታ የተሰጠበት አግባብ ትክክል አይደለም በሚል አቤቱታቸውን እየገለፁ ቆይተዋል፣ በህገ ወጥ መንገድ ከግንባታ ፈቃድ ውጭ አዲስ ግንባታ እየተገነባ ነው የሚል ጥቆማ እያሳወቁ ቆይተዋል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ለአቶ ሳሙኤል ጣሠው የይካተትልኝ ጥያቄ አቅርቦ የተስተናገደበት አግባብ ትክክል አለመሆኑን ገልፆ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያሳወቀ ሲሆን ነገር ግን ስህተቱ እስከ አሁን ድረስ ሳይታረም ቆይቷል››ይላል፡፡
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ዴስክ የአቤት ባይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከ 2006 ዓም ወዲህ 2 ጊዜ የተቀያየረ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ድርርቦሹ መኖሩን ቢያምንም የትኛው አካል የገፋ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ አለመቻሉን አሳውቀዋል፡፡ ሆኖም ይህ አባባል ህግን ያልተከተለ፣ ሙያዊ ክህሎት ያልተላበሰ፣ አግባብ ያልሆነ ምላሽ ነው ይላሉ፡ ፡ ምክንያቱም ከስህተት የፀዳ እና ለክርክር የማይዳርግ
የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመስጠት ኃላፊነት ያለበት አካል በመሆኑና የድንበር ክርክር ሲያጋጥም አጣርቶ የመፍታት ስራና ኃላፊነት ለዚህ ተቋም የተሰጠ በመሆኑ ነው፡፡
ይሕ በእንዲህ እንዳለ የከፍለ ከተማው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት ድርርቦሽ ያለበትን ካርታ መነሻ በማድረግ የእድሳት ፈቃድ ለአቶ ሳሙኤል ጣሠው የሰጠ መሆኑን፣በዚህ ሰበብ እድሳት ሳይሆን አዲስ የሼድ ግንባታ የጀመሩ መሆናቸው ሲረጋገጥ የእድሳት ፈቃዱ እንዲመክን የተደረገ መሆኑና በህገ ወጥ የተሰራው አዲስ ግንባታ እንዲፈርስ ውሳኔ የተላለፈ ቢሆንም ግንባታው በከፊል ፈርሶ በከፊል የሚጠቀሙበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በመሆኑም የክፍለ ከተማው የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፐሮጀክት ፅሕፈት ቤት የካርታ መለዋወጥ የተደረገበትና የይዘት ለውጡ ለድርርቦሽ መንስኤ ስለሆነ ይሕ የተሰራበት በአግባቡ ታይቶ የተፈጠረው ድርርቦሽ እንዲስተካከል ሆኖ አቤት ባይ ቀድሞ የተፈቀደላቸው የይዞታ ማረጋገጫ ባለቤትነት ተከብሮ ያለአግባብ ሳይፈቀድ ተስፋፍቶ ለተያዘው በመመሪያ ቁጥር 18/2006 መሰረት መስተናግዶ መስጠት ሲገባው የቀድሞ ይዞታን በመቀነስ ሰጥቶ የተስፋፋውን በሊዝ እንዲካተት የተደረገበት አግባብ ትክክል ስላልሆነ እንዲታረም›› ብሏል፡፡
‹‹አቤት ባይ የነበራቸው የይዞታ ማረጋገጫ መነሻ ተደርጎ የተፈጠረው ድርርቦሽ የእርማት ስራ ሲሰራ የአቶ ሳሙኤል ጣሠው በመንግድ ተወስዶ የሚቀረው ቦታ በዋናው መንገድ ላይ ስለሚገኝ ራሱን ችሎ ይለማል ወይስ አይለማም፤ እንዲሁም ሙሉ ተነሽ ይሆናሉ ወይስ በከፊል ተነሽ የሚለው በተመሳሳይ መልኩ በከተማው በልማት ተነሺ ለሆኑት አካላት በተስተናገዱበት አግባብ ውሳኔ ቢሰጥበትም የሚል የውሳኔ ሃሳብ አቅርበናልም››ይላል፡ ፡በዚህ ደብዳቤም አቶ ጌቱ ዘውዴ፣ኢሳያስ ግርማ፣ ሃይማኖት ወልደ ገብርኤል፣መኮንን መሸሻ የተባሉ የኮሚቴ አባላት ስምና ፊርማ ሰፍሮበታል፡፡
በ19/4/2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የከንቲባ ፅህፈት ቤት የህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ተክሌ ዱዱ ተፈርሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሬትና ልማት ማኔጅመንት ቢሮ የተፃፈ ደብዳቤም፣የአቶ በቀለ ገብረ ህይወት ለከብር ከንቲባ ያቀረቡት አቤቱታ በፅህፈት ቤታቸው አማካኝነት ኮሚቴ ተዋቅሮ አጣርተው እንዲያቀርቡ በተመራው መሰረት የተቋቋመው ኮሚቴ አጣርቶ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በክቡር ከንቲባው የጸደቀ ስለሆነ ውሳኔ በቢሮ ተፈፅሞ ሪፖርት እንዲደረግላቸው›› ይላል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት፣ ለይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት በ24/04/2009 ዓ.ም የአቶ በቀለ ገብረሕይወትን ይዞታ አስመልክቶ በከንቲባ ፅህፈት ቤት የተሰጠውን ውሳኔ እንዲተገበር ስለመላክ በሚል ደብዳቤ ልኳል፡፡
አቶ በቀለ ገብረ ሕይወት በክቡር ከንቲባ ያቀረቡትን አቤቱታ አስመልክቶ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ያቀረበውን ውሳኔ ሃሳብ በክቡር ከንቲባው የፀደቀ ስለሆነ ውሳኔው በቢሮው ተፈፅሞ ሪፖርት እንዲደረግ በማለት የከንቲባ ፅህፈት ቤት አአ/ከአ/08/77/118 በ 19/04/2009 ዓ.ም ለቢሮው የፃፈውን ደብዳቤ ተከትሎ ውሳኔውን በ5 ቀን ውስጥ ተፈፅሞ ሪፖርት እንዲቀርብ ከቢሮው ተመርቷል፡፡
በመሆኑም በክቡር ከንቲባው በፀደቀው ውሳኔ መሰረት ተፈጻሚ አድርጋችሁ ይህ ደብዳቤ በደረሳችሁ በ5 የስራ ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንድታደርጉልን እያሳሰብን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ለቢሮው የተላከውን ደብዳቤ 1 ገፅና የኮሚቴውን ውሳኔ የያዘ ሰነድ 5 ገፅ በድምሩ 6 ገፅ ከደብዳቤ ጋር አባሪ አድርጎ ልኳል፡፡
ይሑንና ግለሰቡ ማለትም /አቶ ሳሙኤል ጣሰው/ ልደታ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት ሁከት ይወገደልኝ በሚል አመልክቶ የእግድ ትእዛዝ በማውጣት ወደ ክርክር መግባቱንም የሚያስታውሱት አቶ በቀለ፣‹‹በወቅቱም የችሎት ዳኛው ሁላችንም ባለንበት በቦታው በመገኘት ከተመለከቱ በኋላ የከሳሽን ክስ ውድቅ በማድረግ እግዱን በማንሳት የከሳሽ ካርታ የመከነው በአግባብ ነው ሲል ወስነዋልም››ይላሉ፡፡
ይሕ ሲሆንም ከሳሽ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እያለ እስከ ሰበር ችሎት ጉዳዩ የደረሰ ሲሆን ሰበር ችሎቱም ይሕ ጉዳይ ቀደም ሲል በክቡር ከንቲባው የተወሰነ ስለመሆኑ አሁንም በዛው በመስተዳድሩ በኩል ለምን አያልቅም በሚል አስተያየት መሰጠቱንም ያስታውሳሉ፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት ፣የመሬት ይዞታ አስተዳደር ፅህፈት ቤት በ20/ 6 /2012 በቁጥር 3/84 በተፃፈና በፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ታደለ ከበደ በተፈረመ ደብዳቤ‹‹ጉዳዩ በከንቲባ ፅህፈት ቤት ደረጃ ታይቶ አቅጣጫ የተሰጠበትና የተፈፀመ ሲሆን በፍርድ ቤትም ይሕንን የሚሽር ነገር ያልቀረበ በመሆኑ ሁለቱም አሁን ከያዙት የይዞታ ማረጋገጫቸው ውጪ አንዱን በመከልከል ለአንዱ በመጨመር መስተንግዶ መስጠት የማንችል መሆኑን እየገለፅን በአካል ግን ወርደን እንዳየነው የአቶ ሳሙኤል ጣሰው ይዞታ በሼድ የተከፋፈለና ያለው ግንባታ በአቶ በቀለ ገብረ ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ለማስተዋል ችለናል ››ይላል፡፡
በዚሁ ሁሉ ሂደት ውሳኔ እንዳላገኙ የሚናገሩት አቶ በቀለ በኋላም፣ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ በመሄድ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም በአድራሻ ለክብርት ከንቲባ ማመልከታቸውንም ይገልፃሉ፡፡
በዚህ መነሻ መሰረት ጉዳዩ ወደ ህዝብ ቅሬታ አቤቱታ ማስተናገድ ፅህፈት ቤት ተላልፎ የፅህፈት ቤቱ ሁሉም ኃላፊዎች ቦታው ድረስ በመሄድ ማረጋገጣቸውንም ያመላክታሉ፡፡ ከዚህ በኋላም ‹‹ከመጀመሪያ ጀምሮ የተወሰነልኝ ሁሉ ከ1 እስከ 10 ተራ ቁጥር ድረስ በመዘርዘር አንድ ግለሰብ በራሱ ንብረት ለ7 ዓመት ፍትህ በማጣት መጉላላት ተገቢ ባለመሆኑ በክፍለ ከተማው የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ በወቅቱ ምክትል ከንቲባ ለነበሩት ለወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቅሬታ ኮሚቴ ኃላፊ ወይዘሮ አስራት ንጉሴና ወልደ ሚካኤል አማካኝነት የውሳኔ ሃሳብ ቀርቧልም››ይላሉ፡፡
በሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስራት ንጉሴ ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤም፣በፅህፈት ቤቱ ተጣርቶ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ስር፣‹‹አቤቱታ አቅራቢ አቶ በቀለ ገብረሕይወት በግል ነባር ይዞታቸው ላይ ከአጎራባች አቶ ሳሙኤል ጣሠው ህገወጥ ግንባታ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውና በዚህም ምክንያት በእንግልት ላይ የቆዩ ሲሆን ክብርት ከንቲባም፣ ከዚህ በላይ በዝርዝር የጠቀስናቸውን ውሳኔዎችና የሰነድ ማስረጃዎች 36 ገፅ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አያይዘን ያቀረብን በመሆኑ በክፍለ ከተማው ይዞታ አስተዳደር የፅህፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ላይ አስተማሪ የሆነ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ በአቤቱታ አቅራቢ ይዞታ ላይ የደረሰው ጉዳት እንዲታረም መመሪያ እንዲሰጥ በማክበር አቅርበናል››ይላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ፣ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት በ2/7/13 በቁጥር 2282/13 የተፃፈውና የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሚልኬሳ ጃጋማ ፊርማ ባረፈበት ደብዳቤ፣ ቀደም ሲል በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ቅሬታና አቤቱታ አፈታት ዳይሬክቶሬት ተጣርቶ በቀረበው የሰነድ ማስረጃ መሰረትና ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ከዚህ ቀደም በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ቅሬታ የቀረበበት ቦታ በአካል በመሄድና ችግሩን በማጥራት በአቤቱታ አቅራቢው ይዞታ ጋር በመገናኘት የተገነቡት ህገ ወጥ ግንባታዎች ከግለሰቡ ይዞታ ላይ እንዲነሱ ተደርጎ ተገቢው የሆነና የማዳግም ውሳኔ እንዲሰጣቸው እያሳሰብን አቤቱታ አቅራቢውም በማጉላላት ለሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ክፍለ ከተማው ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን እየገለፅን በአፋጣኝ ውሳኔ ተሰጥቶ ለቢሮ ሪፖርት እንዲደረግ እናሳስባለን››ሲል ፅፏል፡፡
ከዚህ በኋላም በከንቲባ ፅህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በ8/6/2013 ለመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ጉዳዩን እንዲፈፅሙ እንደተላለፈላቸው ይገልፃሉ፡፡ በዚህም መሰረት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 መስተዳድር ፅህፈት ቤት ፣ ለክፍለ ከተማው ደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት፣ ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ በመፃፍ ትእዛዝ የተሰጠ ቢሆንም ክፍለ ከተማው ትእዛዙን ለመፈፀም ፈቃደኛ አልሆነም›› ይላሉ፡ ፡እስከ ሰበር ደርሶ የነበረው ጉዳይ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት በእኔ ካርታ ላይ ተደርቦ የነበረው ካርታ በማምከን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል›› ይላሉ፡፡
ይሕን ቅሬታቸውን ያስረዱት አቶ በቀለ በመጨረሻም፣፣‹‹አዲስ አበባ አስተዳደር ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን የምጠይቀው ሰብዓዊ መብቴን እንዲከበርልኝና ለ7 ዓመት ሲያጉላሉኝ በነበሩ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎችና ሙያተኞች ላይ አስተማሪ የሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድባቸው በይዞታዬ ላይ ያሉ ሸራ፣ላስቲክና ብሎኬቶች በአጠቃላይ ከግድግዳዬ ጋር የተያያዙ ነገሮች እንዲነሱልኝና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ትእዛዝ እንዲተላለፍላቸው ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት ድሪባ ኩማ በወቅቱ የክፍለ ከተማው የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የካርታ መለዋወጥ የተደረገበትና የይዘት ለውጡ ለድርርቦሽ መንስኤ ስለሆነ ይሕ የተሰራበት በአግባቡ ታይቶ የተፈጠረው ድርርቦሽ እንዲስተካከል ሆኖ አቤት ባይ ቀድሞ በተፈቀደላቸው የይዞታ ማረጋገጫ ባለቤትነት ተከብሮ ያለአግብብ ሳይፈቀድ ተስፋፍቶ የያዘው በመመሪያ ቁጥር 18/2006 መሰረት መስጠት ሲገባው የቀድሞ ይዞታን በመቀነስ ሰጥቶ የተስፋፋውን በሊዝ እንዲካተት የተደረገበትን አግባብ ትክክል ስላልሆነ እንዲታረም በማለት በሰጡት ትእዛዝ መሰረት የባለቤትነት መብቴ እንዲከበርልኝ ካርታዬም እንዲስተካከልኝ በማለትም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም፣የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱአለም ይጥና ታደሰ ጋር በመቅረብ ስለጉዳዩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡አቶ አንዱአለም ለቦታው አዲስ መሆናቸውን በመግለፅ ስለጉዳዩ ለመናገር እንደሚቸገሩና ባለጉዳይ ያላቸውን ቅሬታ ለፅህፈት ቤቱ እንዲያቀርቡ ጠይቀው፣ፅህፈት ቤቱም ቅሬታውን በመፈተሽ አስፈላጊውን መልስ ለመስጠት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014