አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የመሬት መቃኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ እና የህዋ ፖሊሲ ለማጽደቅ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ 14ተኛ ዓመታዊ ጉባዔ ባካሄደበት ወቅት ሥራ አስኪያጇ ወይዘሮ ቤዛ ተስፋዬ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከተመሰረተ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም በቅርቡ የመሬት ቅኝት የሚያደርግ ሳተላይት ለማምጠቅ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ለዚህ የሚረዱ ፖሊሲዎችን የማጽደቅ ሥራም ተጀምሯል፡፡ ጉባዔዎች በሚደረጉበት ወቅት ተማሪዎች ስለ ህዋ እንዲያውቁ የሚረዱ ገለፃዎች እንደሚደረጉ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጇ፤ ይሄም ለማህበሩ በጎ ፈቃደኛ አባላትን ለማፍራት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ማየትና መስማት ለተሳናቸውም ስለ ህዋ ምርምር የሚያሳይ ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት ወጣቱ ስለህዋ ያለውን እውቀት ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች በመሰራታቸው በአሁኑ ወቅት በጎ ፈቃድ ሰጪ ወጣቶች መብዛታቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ 24 ቅርንጫ ፎችን ከፍቶ ስለ ህዋ ሳይንስ በትምህርት ቤት በሚገኙ ክበባትና አጋዥ መጽሐፍት አማካኝነት ግንዛቤ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ነገር ግን የአባላት ቁጥር ለመጨመር የተሰሩ ሥራዎች በቂ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በክልሎች የተደራሽነት ችግር መኖሩ፣ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ሥራቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው፣ በጉ ፈቃደኞችን በአግባቡ አለመጠቀምና የሀብት አሰባሰብ ላይ ችግሮች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡ ፡
በተጨማሪም አስፈላጊ እቃዎችን ለመግዛት የገንዘብ እጥረት እንደነበር አመልክተዋል፡፡ በጉባዔው ላይ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከምስረታው ጀምሮ በእውቀትና በገንዘብ እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት ላገለገሉ 22 ሰዎች የክብር አባልነት ምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት2/2011
በመርድ ክፍሉ