አዲስ አበባ:- መንገዶች ባለቤት የላቸውም የሚል ቁጭት አዘል ሽሙጥ መስማት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚኖር ሰው ብርቅ አይደለም። አባባሉ «ቁጭት የወለደው» መሆኑን በልባችን ይዘን «ግን ስለእውነት ባለቤቱ ማነው?» ብለን ስንጠይቅ አንድ ራሱን የቻለ ግዙፍ መንግሥታዊ ተቋምን እናገኛለን፤ «የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን»ን። ይህ ተቋም የከተማዋ መንገዶች ሁሉ ይመ ለከቱታል።
ከእግረኛ እስከ ተሽከርካሪ፣ ከኮብል ስቶን እስከአስፋልት፣ ከግንባታ እስከ ጥገና፣ ድልድዮች ወዘተ ያሉትን ሁሉ የሚያዝባቸው እሱው ነው። ከፈለገ ያፈርሳቸዋል፤ ወይም ያለማቸዋል። ባጭሩ የከተማዋ የመንገድ ጉዳይን በተመለከተ ሙሉ ለሙሉ የሱው ተግባርና ኃላፊነት ነው። በመሆኑም በከተማዋ ውስጥ ለሚታዩት ጥሩም ሆኑ የተበላሹ የመንገድ ገፅታዎች ተመስ ጋኙም ሆነ ተወቃሹ እሱው ብቻ ነው። ባለድርሻ አካላት ካሉም ተከትለውት ሊሰለፉ እንጂ ቀድ መውት ይገኙ ዘንድ መብቱ የላቸውም። የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንም ከሳም ንት በፊት የተቋሙን የ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻፀም አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ 95 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ገልፆ ነበር።
ይህ ከሌሎች ተቋማት የእቅድ አፈፃፀም (በተለይ የእቅዳቸውን 50 በመቶ እንኳን ማሳካት ካልቻሉት ጋር ሲነፃፀር) ያስመሰግነዋል፤ አርአያም ያደርገዋል። አነጋጋሪው ጉዳይ ግን የ95 በመቶ አፈፃፀም ካለ በከተማው ውስጥ ለሚሰሙ ቅሬታዎች ችግሩና መንስኤው ምንድ ነው? የሚለው ነው። እኛም ጋዜጣዊ መግለጫውን ተከትሎም በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች መንገዶች ከተገነቡ በኋላ በሌላ አካል መልሰው ለምን ይፈርሳሉ፤ ይህስ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ለምን አቃተው የሚል ጥያቄ አነሳንላቸው፡፡
በዚህ ዙሪያ ኃላፊዎቹ በሰጡን ምላሽ መንገዶች እየተቆፋፈሩ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ወደነበሩበት ሳይመለሱ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን ባለስልጣኑም ያውቀዋል። ሆኖም ባለስልጣኑ ወዲያውኑ ወደ ጥገና የማይገባው ከቆፈረው አካል ጋር በተገባው ውል መሰረት ተገቢው ርክክብ ስለማይፈፀም ነው። ምንም እንኳን ቆፋሪው አካል ከመቆፈሩ በፊት ለሚቆፈረው ቦታ መልሶ ማስጠገኛ ለመንገዶች ባለስልጣን ገንዘብ የሚከፍል ቢሆንም መልሶ ለመጠገን ሥራውን ካጠናቀቀው አካል ስለማጠናቀቁ በአግባቡ መረካከብን ግድ ይላል። አሁን ያለው ችግር ይህ ነው፤ እሱም «ተቀናጅቶ የመስራት ችግር» በሚል «ሙያዊ»መጠሪያው ይታወቃል።
በዘርፉ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ችግር አለ ማለት ነው። እንደዋና ዳይሬክተሩና የዘርፉ ኃላፊዎች ማብራሪያ ይህ ችግር ለረጅም ጊዜ የቆየ ችግር ነው፤ ይሁን እንጂ አሁን የሚመለከታቸውን ተቋ ማት አቀናጅቶ የሚመራ ራሱን የቻለ ጽሕፈት ቤት ስለተቋቋመና የጋራ እቅድ ወጥቶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ስለሆነ እነዚህ ችግሮች አይቀጥሉም፤ በቅርቡም ሁሉም መፍትሄ ያገኛሉ። ሌላውና ለሌላ ዘርፍ ልማት «ከሚታረዱት» መንገዶች በተጨማሪ ችግሮች የሚታዩበት ዘርፍ ቢኖር የትላልቅ አስፋልት መንገዶች ግንባታ ነው። ይህ ዘርፍ «የአዲስ አበባ መንገዶች ባለቤት የላቸውም እንዴ?» ከሚያስብሉት መካከል አንዱ ሲሆን «ተሰርተው አልቀዋል» በሚባሉበት ደረጃ ከደረሱ በኋላ ወደ ሥራ ሳይገቡ ለረጅም ጊዜያት የሚቆዩበት፤ ከችግር ያወጣሉ ተብለው ሲጠበቁ ሌላ ችግር የሚፈጥሩበት ሁኔታ መኖሩ ነው። ቃሊቲ መስመር ገነት መናፈሻ አካባቢ ያለውን መንገድ ለዚህ እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
ባለስልጣኑ እንደሚለው ከሆነ ይህም ከእሱ ያልተሰወረና የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ አንድ መንገድ በተለያዩ የርክክብ ደረጃዎች ውስጥ ስለሚያልፍ ይህ መንገድም በዛ ሂደት ውስጥ ነው ያለው። ተቋራጩ ማሟላት ያለበትን ጉድለቶች እንዲያሟላ ተነግሮት እየተጠበቀ ነው የሚገኘው። ባለስልጣኑ ይህን ይበል እንጂ ምክንያቱ ብዙዎችን ሲያሳምን አይታይም። ይህንኑ ያልተጠ ናቀቀ መንገድ በቀን ሁለት ጊዜ ሳይጎበኙት የማይውሉት አንድ ታዛቢ እንደሚሉት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ባካባቢው አይታይም። መንገ ዱን እስከነመፈጠሩም እንኳን የሚያውቀው አካል አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከአጠቃላይ አገራዊ የመንገድ ልማት አፈፃጸም አንፃር ሲመዘን 433 ኪሎ ሜትር ለመገንባት አቅዶ 413 ኪሎ ሜትር አከናውኗል። ይሁን እንጂ በተለይ በጥገናው ዘርፍ ከጥራት ጀምሮ የክትትልና ቁጥጥር ክፍተቶች እዚህም እዚያም ይታያሉ። ተቀናጅቶ የመስራት ጉዳይ ሲነሳ ደግሞ ጣት የመጠቋቆሙ ነገር ልብ ያቆስላል። እዚህም እዚያም በተገነቡ ባጭር ጊዜ ውስጥ ተፈነቃቅለው ከመታየት ባለፈ ለመፈነካከቻ የተዘጋጁ የሚመስሉ የኮብል ስቶን ጥርብ ድንጋዮችን በየሰፈሩ ማየት የተለመደ ነው። ለሌላ ዘርፍ ልማት የተቆፈሩ፤ ግን ደግሞ ተመልሰው ያልተጠገኑ መንገዶች በከተማዋ ሞልተዋል። ወደ መነን እና አካባቢው ብቅ ቢሉ ይህንን ይመለከታሉ።
ተጀምረው የቆሙ መንገዶች (በተለይም የእግረኛ መንገዶች) ጥቂት አይደሉም። ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ሲኬድ ራስ መኮንን ድልድይ ጋር የቆመው ግንባታ ለዚህ ማሳያ ነው። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነዋሪውን የልማቱ ተጠቃሚ ካለማድረግ ባሻገር የከተማውን ፅዳትና ውበት ከመፈታተን አኳያ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ። የጥራት ጉዳይም ሌላው የታዘብነውና ብዙ እያነጋገረ ያለ ችግር ነው። ለዚህም ባለስልጣኑ እቅዴን 95 በመቶ አጠናቅቄያለሁ ባለበት ዋዜማ በኮተቤ አካባቢ የተደረመሰውና በሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው የድልድይ ግንባታም ከዚሁ ጋር ሊጠቀስ የግድ ነው። በመንገድ ግንባታ ምክንያት በተቆፋፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ ገብተው ህይወታቸው ያለፈ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይ ደለም፤ «በፕሮጀክቶች መዘግየት መንግሥት ለ43 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ተዳርጓል» ከሚለው «በአዲስ አበባ በኮንስትራክሽን ጥንቃቄ ጉድለት 3ሺህ 200 ሰዎች ሞተዋል» እስከሚለው ድረስ ያለው ዜና እንደገና ቁጥሩን ጨምሮ፤ ሌላ ዜና ሆኖ ሊመጣና ልናነበው አይገባም። በመሆኑም ባለስልጣኑ እንዳለው፤ አዲስ የተቋቋመውና በቅንጅት የመስራቱን ሂደት በማቀናጀት ይሰራል ተብሎ የሚጠበቀው መስሪያ ቤት ችግሩን ሊፈታ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
በግርማ መንግሥቴ