አሸባሪው ሕወሓት ከአማራና አፋር ክልሎች በፀጥታ ሃይሎች ጥምረት ተደምስሶ ቢወጣም ዛሬም ትንኮሳው አላቆመም። በተለይ በአፋር በኩል የሚያደርገውን ትንኮሳ አሁንም ቀጥሎበታል።
ለመሆኑ ይህ ትንኮሳ የሚያሳየው ምንድ ነው? ለዚህ ትንኮሳ የፀጥታ ሃይሉ ዝግጅትስ ምንድነው? አሸባሪው ሕወሓት ጭልጥ ያለ ከሃዲ መሆኑን ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከከፈተበት ውድቅት ሌሊት ይጀምራል።
በትግራይ ክልል ከህዝቡ ጋር ሆኖ ሰብል በመሰብሰብ የሚረዳውን፣ የአንበጣ መንጋ በተከሰተበት ወቅት የትግራይ ህዝብ ሕዝቤ ነው ብሎ በመከላከል ስራ ተሰማርቶ ሲያግዝ በነበረው የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ከበባ በማድረግ፣ በትሕነግ ጁንታ ለእኩይ ዓላማ የሰለጠነው የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የከፈተው ጦርነት በእናት ጡት ነካሽነት የተፈጸመ ታላቅ የክህደት ወንጀል ነው።
አሸባሪው ሕወሓት የደፈረው የገደለው የሀገሩ ጠባቂና መኩሪያ የሆነውን የሰሜን ዕዝን ሠራዊት አባላት ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያንን በመሆኑም ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ነበር። በከሃዲዎቹ ዓማካኝነት በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ የደረሰ የመጀመሪያው ዘግናኝና በታሪክ ጸያፍ ሆኖ የሚነሳ ነውር ፈፅመዋል። የሰሜን ዕዝ በተጠቃበት ወቅት ጄኔራል ባጫ ደበሌ አካባቢውን ቃኝተው ለመገናኛ ብዙሀን የተናገሩትን ማስተዋስ ተገቢ ነው።
‹‹የታፈኑ አመራርና ወታደሮችን ጁንታው ልብሳቸውን አወላልቆ ራቁታቸውን ወደ ሻዕቢያ ሂዱ ብሎ ሰዷቸዋል፤ የባዕድ ጦር ልብስ ነው ያለበሳቸው፤ በመከላከያ ውስጥ ያሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች የጁንታው ኔትዎርኮች ናቸው ጥቃቱን ያቀናጁት።
የተረሸኑ የመከላከያ አባላት ዘረኛው ጁንታ የሟቾችን አልባሳት አውልቆ ፀሃይ ላይ ለቀናት በማስጣት እንዲፈነዳዳ አድርጓል፤ የሌሎቹን አስከሬንም እንዳይቀበሩ በማድረግ ብዙዎች በጅብ ተበልተዋል›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
እንግዲህ አሸባሪው ሕወሓት ዓይን ያወጣ ክህደቱንና የማሸበር ስራውን በዚህ ደረጃ ከጀመረ ወዲህ የሀገር መከላከያ አጸፋውን በመውሰድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን ማስከበሩ ጠላትን አንገት ያስደፋ የወገንን ሞራል በእጅጉ ከፍ ያደረገ ክስተት ነበር።
አሸባሪው ሕወሓት በቀየሰው ሳይሆን በተቀየሰለት ወጥመድ ውስጥ በመግባት ክፉኛ ተቀጥቅጧል። ከሃዲዎችና ባንዳዎች እንደ አመድ ቡን ብለው እንደ ቦና ቅጠል ተደቁሰው ዋጋቸውን ማግኘታቸውም ሃቅ ነው። ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጻሚዎች በሀገር መከላከያና እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ተደምስሰው ድል መበሰሩ ይታወሳል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የነበረው አዛዥ እና ታዛዡ በሚገባ የጠቀናጀ እና ድል የጠማው አንደነበርም ታሪክ የሚመሰክረው እና በወጉ የሚሰንደው ይሆናል። በወቅቱ በነበረው ጦርነት የአሸባሪው ሕወሓት መሳሪያ ማከማቻ ዴፖ ሙሉ በሙሉ ያወደመው አየር ኃይላችን እስከ ቅርብ ቀን ድረስ በተመረጠ ዒላማ ላይ የተሳካ ድብደባ በማድረግ ኢትዮጵያን መታደግ ችለዋል።
እጅ አልሰጥም ያለውን እስከ መጨረሻው በመደምሰስ ጀብድ ተፈጽሟል። ለጆሮ የሚከብዱ ዘግናኝ ወንጀሎችን የፈፀመውን የትሕነግ ስግብግብ ጁንታ ቡድን ከተደበቀበት የቀበሮ ጉድጓድ ማንቁርቱን ይዞ ሕግ ፊት ለማቅረብ፤ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ደማቅ ታሪክ ፅፏል። ታዲያ በእዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች መካከል የትግራይ ክልል መቶ በመቶ መቆጣጠር ከተቻለ በኋላ ነገሮችን በእርጋታ ለማየትና ለህዝቡም ጽሞና ጊዜ ለመስጠት በማሰብ የሀገር መከላከያ
ሰራዊት አካባቢውን ለቆ ወጥቷል። ነገር ግን በዚህ ወቅት ቀሪ የሕወሓት ርዝራዞች ህዝቡን ለዕኩይ ዓላማ ማነሳሳት ጀመሩ። ቆላ ተንቤን ተደብቀው የነበሩ በጣት የሚቆጠሩ የአሸባሪው ሕወሓት አመራሮችም ዳግም ነፍስ እየዘሩ ወደሚዲያ ብቅ ማለት ጀመሩ። ከሞት አፋፍ የተመለሱት የአሸባሪው ጀሌዎችና አመራሮች ዳግም ሥልጣን እያማራቸው፤ ዳግም በኢትዮጵያ ላይ ግፍና በደል መፈጸም እየዳዳቸው መጡ። ከሞት አፋፍ ተመልሰው እንደገና ሌላ የሞት ሞት እያማራቸው ከሠላም ይልቅ ጦርነትን መናፈቅ ጀመሩ።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሚገባው ተቀጥቅጦ እና የሚመካበትን ዋና አመራሮችን ወደመጨረሻው ሞት ከሸኘ በኋላ ዳግም የባሩድ ሽታ ናፍቆት የማሸበር ስራውን መቀጠሉ ይታወሳል።
በዚህም በአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርገውን ትንኮሳ አጠናክሮ ቀጠለ። አሸባሪው ትህነግ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚያደርገውን ትንኮሳ ተከትሎ የዜጎች መፈናቀል ችግር እየተባባሰ የሄደ ሲሆን በቢሊዮን የሚገመት ንብረትም ውድመት ደረሰ። በለስ የቀናው የመሰለው አሸባሪው ቡድን መንግሥት የወሰነውን የተኩስ አቁም ውሳኔውን እንደመልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ሞከረ።
ይሄም ብቻ ሳይሆን ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ በፍጥነት ለተጎጂዎች እንዲደርስ መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ቢሆንም አሸባሪው ቡድን አሁንም ሀሰተኛ መረጃዎችን በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ በማስተላለፍ ሰዎችን በማደናገር ሥራ መጠመዱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
አሸባሪው ቡድን በአፋር በኩል ጥቃት እየፈጸመም በሌላ ጎን ደግሞ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተላለፊያ ዘግቷል በማለት ቡድኑ ሌላ ተጨማሪ መተላለፊያ መስመር እንዲከፈት በተለይም ደግሞ የሱዳን ኮሪደር ክፍት እንዲሆን ሲወተውት ነበር።
ለአሸባሪው ሕወሓት በሰብዓዊ ድጋፍ ውጪ መሳሪያና ሌሎች ድጋፍ እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉ አፈቀላጤዎችና ድጋፍ ሰጪዎችም ሌላ መስመር እንዲከፈት ግፊት ሲያደርጉ መቆታቸው ይታወሳል። በተለይም በሱዳን ኮሪደርን በማስከፈት የጦር መሳሪያ ለማስገባትና በሰመራ ጭፍጨፋ ፈጽመው ወደ ሱዳን የተሻገሩ 30ሺ የሚሆኑ ሳምሪ የተባለ ቡድን አባላት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ቋምጠው ነበር።
ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ የነበራቸው ጀነራል አበባው ታደሰ እንዳሉት፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን አሁንም ትንኮሳውን አላቋረጠም። ሆኖም አሸባሪውን ቡድን ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት የተገኘው ድል ሕዝባዊ ድል እንደሆነና የጠላትን የማድረግ አቅም ያዳከመ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የንብረት ኪሳራ ያደረሰ ነበር።
አሸባሪው ሕወሓት ከፍተኛ ድል አደረግሁ ብሎ ሰፊ እቅድ ነድፎ ቢንቀሳቀስም በጋሸና፣ ሚሌ እና በመሀል ግንባሮች ፈታኝ ውጊያዎች ተደርጎ የኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች ጥምረት ጠላትን እምሽክ ማድረጉን አብራርተዋል። በእነዚህ ግንባሮች ሠራዊቱ ከፍተኛ ጀብዱ የሰራባቸው ሲሆን ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሠራዊቱን ዝግጁነት አቅም ያሳደገ መሆኑንም መናገራቸው ይታወሳል።
አሸባሪ ሕወሓት እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ ዘልቆ ለአዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትሮች ቅርበት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም አከርካሪው ከተሰበረ በኋላ እንደ እብድ ውሻ እየፈረጠጠ ወደ ትግራይ መሽጓል። ይሁንና አሸባሪው አሁንም በተለያዩ የአማራ እና አፋር አጎራባች ወረዳዎች ትንኮሳውን አላቆመም።
የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ሰሞኑን ከመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአደረጃጃትም ሆነ ተልዕኮውን የመፈፀም ብቃቱ ከወትሮ እጅግ ዝግጁና በአስተማማኝ ቁመና ላይ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን አስፈሪ የሀገር ዘብ ስለመሆኑም መስክረዋል። ከለውጡ በፊት ቀደም ብሎ በነበረው የሰራዊት አደረጃጀት ደረጃ ላይ ሳይሆን ቴክኖሎጂን የታጠቀና ኢትዮጵያን ተክለ ቁመና የሚመጥን መሆኑን አመልክተዋል።
በፊት በነበረው የብሔር ተኮር የሠራዊት ግንባታ ዋጋ የከፈለው እራሱ ሠራዊቱ በመሆኑም ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ እና በሙያው ብቁ የሆነ ሠራዊት እየተገነባ ስለመሆኑም ተናግረዋል። በቅርቡ የተካሄደው ወታደራዊ የማዕረግ እና የሜዳልያ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ላሉ ዕዞች ማዕረግ የተሰጠበት፣ የሠራዊቱ አመራሮችን የሚመጥን እና የሠራዊቱን ሞራል የገነባ እንደነበር ገልፀዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጠላት የሰው ኃይል ቁጥር እና ትጥቅ ያነሰ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን ስንቁ ያደረገ እንደነበርም በማስታወስ ጦርነቱ ሲጀመር ከ250ሺ በላይ የታጠቀ የአሸባሪው ሕወሓትን ኃይል እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ከተጨማሪ ጀሌዎቹ ይዞ ከ44ሺ ባልበለጠ የኢትዮጵያ ሠራዊት መግጠሙንና ድባቅ መመታቱን ተናግረዋል።
ታዲያ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት አለመጠናቀቁንና ሠራዊቱ ምዕራፍ አንድ ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ የጠላትን ግብዓተ መሬት ሳንፈጽም ወደኋላ ማለት የማያውቁት የአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎችና ዲካሂናዎች (ወጣቶች)፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና ሌሎች አደረጃጀቶች ፈጥኖ ደራሽ በመሆን አሸባሪው ሕወሓት ላይ የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ ድል አስመዝግበዋል።
በዚህም አሸባሪው የያዛቸውን ቦታዎች በማስለቀቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ መረጋጋትን መፍጠር ችለዋል። ለሌላ ግዳጅ ለመሰማራት ሁሌ ዝግጅነታቸውን አረጋግጠዋል።
ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባልና ለህዝባችን ነፃነትም እስከ መጨረሻው እንደሚፋለሙም ደጋግመው አረጋግጠዋል። አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ዳግም ወረራ ሲፈፅም ብዙ ፍላጎቶችን አንግቦ ነበር።
የመጀመሪያ ኢትዮጵውያንን አሸንፎ አሊያም ደግሞ መንበረ መንግስትን መቆናጠጥ ይህም ካልሆነ በጫና ውስጥ በመክተት መንግስትን በግድ ወደ ድርድር ማስገባት ነበር። ይህም ሳይሆን ከቀረ ዓለም አቀፍ የሰላም አስከባሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ መጋበዝ ነበር።
ይህን ለማሳካትም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ ተቋማት፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራትን ጭምር የሕወሓት ቱቦ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል። ሌላኛው የሱዳን ኮሪደር በማስከፈት ሀገሪቱን በሽብር ማመስ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመሆን ሽብራቸውን ማቀጣጠል ነበር። እነርሱ የማይመሯት ኢትዮጵያን አለማየት ወይንም ማፍረስ ጭምር ነበር እቅዳቸው። ግን ሁሉም ህልም ሆኖ ቀርቷል። አሸባሪው ሕወሓት እንኳንስ በምስራቅ አፍሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሥም ያለው አሸባሪ ለመሆን አልታደለም።
ፈጽሞም ሊወጣው የማይችለው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በአማራ እና አፋር ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች የሚስተዋለው ትንኮሳም አለሁ አስታውሱኝ ለማለት ከሞት አፋፍ ላይ የሚደረግ ከንቱ ጩኸት እንጂ ፋይዳ እንደሌለው ራሱም ያውቀዋል።
አሸባሪው ሕወሓት አሁን ያሉት ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው። የመጀመሪው ለትግራይ ህዝብ የሚያስብ ከሆነ በሠላማዊ መንገድ እጅ ሰጥቶ ፀጥ ለጥ ብሎ ማደር። አሊያም ደግሞ እስከ ወዲያኛው ድረስ ማሸለብ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 17/2014